በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ፆታ፣ አካል ጉዳተኛነት፣ ጤነኛነት ወዘተ ላይ ልዩነት የማያደርጉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ጉዳዮች ብዙ ናቸው። እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ተግባር ላይ መዋላቸው ተገቢ ነው። ይሁንና በአሉታዊ ጎኑም ዘር፣ ቀለም፣ አካል ጉዳተኛነት፣ ጤነኛነት ….. የማይለዩ ሌሎች ጉዳዮች ያሉ ሲሆን አንዱም ስንፍና እና የእሱ ተቃራኒ የሆነው ጉብዝና ይገኝበታል።
ሰነፍ በየትኛውም ፆታ፣ ሀይማኖት … አባላት ውስጥ አለ። አካል ጉዳተኛ ከሆኑት ጤነኛ ሆነው ስራ ጠል የሆኑት ናቸው ቁጥራቸው የሚበዛው። እያልን ያለነው አካል ጉዳተኛ መስራት አይችልም፤ መስራት የሚችለው ጤነኛው ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ስህተት ነው ነው። የዛሬው እንግዳችን ደግሞ የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በተለይ እጅ እግሩን አስሮ ከያዘው ችግር ቢላቀቅ ደግሞ ከራሱም አልፎ ለሌሎች ቀኝ እጅ እንደሚሆን ከህይወት ተሞክሮዎቹ መረዳት ይቻላል። ደሳለኝ ፈንታን አነጋግረነዋል፤ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶችና ያሉበትን ችግርች እንደሚከተለው ይነግረናል።
ተወልጄ ያደኩት ጎንደር ክፍለ ሀገር ነው። ከተወለድኩ ከ20 አመት እድሜዬ በኋላ ያልታሰበ ህመም አጋጠመኝ። በዚህም ምክንያት ለፀበል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፀበል መፀበል ጀመርኩ። ሽንቁሩ ሚካኤል ብቻ አራት አመት ቆይቻለሁ። እግዚአብሄር ይመስገን ተሽሎኝ ወደ ስራ ገብቻለሁ ሲል ከትውልድ ቦታው የለቀቀበትን፣ ያጋጠመውን የጤና እክልና ጤናውን ለመመለስ የሄደበትን እርቀት፤ እንዲሁም ወደ ስራ አለም የተቀላቀለበትን አጋጣሚ፤ እንዲሁም አሁን ያለበትን ፈተና ይናገራል።
ተሽሎኝ ከፀበል እንደወጣሁ እራሴን ችዬ ወደ መስራት ነው ያቀናሁት። እራሴን በምንም አይነት መንገድ ሰርቶ ከመብላት ውጪ ሌላ ነገር (ለምሳሌ መለመን) ውስጥ መግባት እንደሌለብኝ አሳምኜው ስለነበር ወደ ስራ እንጂ ወደ ልመናና ሌሎች ያልተገቡ አማራጮች አልገባሁም። በመሆኑም መርካቶ አካባቢ ቤት በመከራየት ጧት ጧት ጧፍ መሸጥ ጀመርኩ። በማለት ወደ ስራ አለም የገባበትን አጋጣሚና የቢዝነስ ዘርፉን የሚናገረው ደሳለኝ ወደ አገር ቤት በመመለስ እንደሱ አካል ጉዳተኛ የሆነ ወንድሙን ማምጣቱን፤ ፀበል ማፀበሉንና ተሽሎትም አብረው መስራት መጀመራቸውን ይናገራል።
ደሳለኝ ብዙ መከራዎችን፣ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ተመልሶ ወደ አገር ቤት ሲሄድ ሁሉ እናቱ አርፈው በማግኘቱ እጅግ አዝኖ ነበር። ከሁሉም ከሁሉም ግን የማይረሳና እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ሆኖበት በከፍተኛ ደረጃ ተፈታትኖት የነበረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሲሆን እሱንም ባለ በሌለ አቅምና ትእግስቱ፤ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሄር ሀይል አልፎት እዚህ ለመድረስ እንደበቃ ይናገራል።
ከፀበል እንደተመለስኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የመኖሪያ ቤት የተከራየሁት መርካቶ አካባቢ ነው። ከወንድሜ ጋር እዛ እየኖርን ሳለ ትልቁ ፈተና የነበረው እኛ በጠዋት ወደ ስራ ስንሄድ የአካባቢው ልጆች ልብሳችን ሳይቀር ይዘርፉን ነበር። ይህ ከሚገባው በላይ ስላማረረን ቤት ለመቀየር ተገደድን። በጓደኞቻችን አማካኝነትና ምክር ወደ አራዳ ክፍለ ከተማም መጣን። እዛም ከሶስት መቶ ብር ጀምሮ እስከ 1ሺህ 800 ብር ድረስ የተለያዩ ቤቶችን በመከራየት ኑሮን ስገፋ ቆይቻለሁ በማለት ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ያሳለፈውን አሳዛኝና የአከራዮችን አሳፋሪ ተግባር የሚናገረው ደሳለኝ ህይወቱን ባለትዳርና የሁለት (አንድ ወንድና አንዲት ሴት) ልጆች አባት መሆኑንም ነግሮናል።
ደሳለኝ ቤት ለመከራየት በፈለገበት ወቅት ሁሉ ሲያይ የነበረውን አበሳ ሲናገር በሀዘንና በግርምት ነው። “ለአንተ (ለአካል ጉዳተኛ ማለታቸው ነው) አናከራይም” ከሚሉት አንስቶ ፍጥጥ ባለ መልኩ ልቀቅልን እስከሚሉት ድረስ፤ ቆጣሪ የግላችን ስለሆነ ላንተ መብራት አንሰጥህም ከሚሉት ኩሽና መጠቀም አትችልም (የለንም) እስከሚሉት፤ ለአንተ ከማከራይ ቤቴ እንዲሁ ሳይከራይ ቢቀመጥ ይሻለኛል ከሚል ኢሰብአዊ ምላሽን ከሰጡት እስከ “የፈለጋችሁትን ልጨምር፤ ልጅ ወልጄ ልጄ ካደገበት ቤት አታስወጡኝ” የሚል ተማፅኖውን እስከማይሰሙት (አሁን “መቋሚያ ይዘው ቤተ ክርስቲያን ሳያቸው ይገርመኛል” ይላል ፍቃዱ)፤ ቤት ኪራይ ፈልጌ ነበር ሲባሉ፣ ወይም በደላላ በኩል ሲጠየቁ የተከራዩን አካል ጉዳተኝነትን ሲያዩ “ኪራዩ እኮ አንድ ሺህ አራት መቶ ነው። ሌላውም ጋር እንዲሁ፣ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ነው” (“አንተ አካል ጉዳተኛ ነህ ይህንን ገንዘብ ከየት አምጥተህ ልትከፍል ነው?” በሚል ስሜት) ከሚሉት ሽንት ቤት ትሞላላችሁ፤ ስለዚህ አልፈልግም ውጡ እስከሚሉት ድረስ ደሳለኝና ቤተሰቦቹ፣ እንዲሁም ወንድሙ (ዛሬ እሱም የራሱን ስራ እየሰራ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ፈቃደ ይናገራል) ተፈትነዋል። ይፈተኑ እንጂ በድል ተወጥተውት ዛሬ የሚገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የእነዚህ ተቃራኒ የሆኑ አከራዮች መኖራቸውንም ደሳለኝ ይናገራል። “አንድ የተባረኩ ሰው ጋር በ1ሺህ 800 ብር ኪራይ ቤት አገኘሁ። እንደውም በኋላ የውሀና የመብራት 200 ቀንሼልሀለሁ ብለውኝ 1ሺህ 600 መቶ ብር በመክፈል መኖር ጀመርኩ” የሚለው ደሳለኝ ይህ ቀደም ሲል የነበረው ህይወቱ እንደሆነም ይናገራል።
“አሁንስ የቤት ጉዳይ እንዴት ነው?” በማለት ላቀረብንለት ጥያቄ (የፈቃደ ፊት ከነበረበት የኋላ ትዝታ ድባብ እየወጣ መሆኑ እያስታወቀ) “አሁን በጣም ጥሩ ነው። መንግስት ኮንዶሚኒየም ቤት ሰጥቶኝ በሰላም እየኖርኩ ነው። በጣም ደስተኛ ነኝ። ያ ሁሉ ችግር አልፎ ዛሬ ላይ እዚህ መድረሴን (ከመኖሪያ ቤት አኳያ ማለቱ ነው) ሳስበው በጣም ደስተኛ ነኝ። ቤተሰቦቼም ደስተኞች ናቸው። ደሞ እኔ ብቻም አይደለሁም ወንድሜም የቀበሌ ቤት አግኝቶ፣ ትዳር ይዞና ልጅ አፍርቶ እየኖረ ነው።” ሲል መልስ ሰጥቶናል።
“ወደ ስራህ እንመለስና አሁን የደረስክበት ደረጃ ለመድረስ ያበቃህን ሁኔታ ለአንባቢያን ብትገልፅ?” ብለነውም “እንደነገርኩህ ምንም በማላውቀው ሁኔታ በበሽታ ተያዝኩ፤ ብዙ ተሰቃየሁ፤ ፀበል ቤት ለፀበል ቤት ተመላለስኩ፤ በመጨረሻም ተሽሎኝ (በእግሩ ላይ የደረሰውን ጉዳት አይደለም) ወደ እራሴን መምራት ሁኔታ እንደተመልስኩ ጧፍ፣ መፃህፍትና የመሳሰሉትን ከመሸጥ፣ የተለያዩ ተጓዳኝ ስራዎችን ከመስራት ነው የጀመርኩት። በሂደት እዚህ ደርሻለሁ። ወደ እዚህኛው ስራ የገባሁት ከ1999 አ.ም ጀምሮ ሲጋራ ምናምን በመሸጥ ነው። በሂደት ሲጋራና ምናምኑን ተውኩት። አሁን ይሄ ብቻ (ለገበያ የቀረበውን ማለቱ ነው) ከ15 እስከ 20ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት ነው።
በአጠቃላይ በጣም ጥሩ ህይወት ነው የምኖረው። ልጆቼን አስተምራለሁ። ባለቤቴም ደስተኛ ነች። ሁላችንም ደስተኞች ነን።” በማለት ከስራና የንግድ እንቅስቃሴው አኳያ ያለበትን ይዞታ ይናገራል።
“አሁን ባለህበት ሁኔታ እንደችግር የምታነሳው ነገር አለ?” ላልነውም “አዎ” ካለ በኋላ እስካሁን ባደረገው ጥረት ምንም አይነት የስራ ቦታ ማግኘት እንዳልቻለ፣ በዚህ ምክንያትም መስራት እየቻለ ነገር ግን በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንዳልሆነ፣ እሱና መሰሎቹ በቀን በቀን በደንቦች ሲዋከቡ እንደሚውሉ (ሰሞኑን ከአንድ አይነ ስውር ጓደኛው የአምስት ሺህ ብር ንብረት እንደወረሱበት ጭምር ምሳሌ እየሰጠ)፣ መንግስት እንደው እንደምንም ብሎ ሁለት በሁለት የሆነች ቦታ እንኳን ቢሰጠው ከዚህ በላይ በመስራት እራሱን፣ ቤተሰቡንና ህብረተሰቡን (አገልግሎት ከመስጠት አኳያ) እንደሚጠቅም፣ ልጆቹን ከአሁኑ በተሻለ አስተምሮ ጥሩ ደረጃ ለማድረስ እንደሚፈልግ ….. ይገልፃል። ደሳለኝ ወደ ፊት መንግስት ይህንን እንደሚያደርግለትም (ለጓደኞቹም ጭምር) ተስፋ አለው።
“እግዚያብሄር ይመስገን ሁሉም ነገር ጥሩ ነው፤ ጥሩ እቃ ካቀረብክ ሰዉም ይገዛል።” ገበያውስ እንዴት ነው ላልነው የሰጠን መልስ ሲሆን ይህ ፀሀፊም ደሳለኝን እያነጋገረ ባለበት ወቅት ጥሩ የገበያ እንቅስቃሴና የደንበኞቹ ጉበኝት መኖሩን የተመለከተ ሲሆን ጥፍር መቁረጫ ከ20 እስከ 30 ብር፣ የተለያዩ ስክሪፕቶዎች እስከ 20 ብር ወዘተ ሲሸጡ ተመልክቷል።
ደሳለኝን “በአካል ጉዳተኝነትህ ምን ይሰማሀል? የሚሰማህ ስሜት አለ?” ብለነውም ነበር። “ምንም የሚሰማኝ ስሜት የለም፤ ምንም አይነት። ይኸው አካል ጉዳተኛ ሁሉ እኮ ሰርተው እየበሉ አይደለም እንዴ የኔ ምን ልዩነት አለው። አይነ ስውራን ሰርተው ሲገቡ አታይም? ዋናው ነገር አካል ጉዳተኝነቱ አይደለም። ዋናው ነገር የመስራት ፍላጎቱ ላይ ነው። ችግሩ ያለው እዛ ጋ ነው። ሰው እንዴት እጅ ይዞ በዛ እጁ ይለምናል? እንዴት ሰው ለልመና እጁን ይዘረጋል ሊሰራበት ሲገባ? አላደርገውም።” ነው የሚለው።
ከስራ ባህላችን አኳያ የታዘበው ነገር ካለም አንስተንለት “ለስራ ያለን ፍላጎት ገና ብዙ የሚቀረው ነገር አለ። ይሄ የሚታየው ወጣት ሁሉ ቢሰራ እ……፤ እንደ እኔ አስተያየት ከአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ውጪ ያለው በሙሉ ወደ ስራ በመግባት፣ መስራት ነው ያለበት፤ ሁሉም። በተለይ ወጣቱ ምንድን ነው ብሎ ስራ ሳይንቅ መስራት ነው ያለበት፤ የሚጠበቅበትም ይሄው ነው። እዚህ (ቅድስተ ማሪያም ቤተክርስቲያን) አካባቢ ዛሬ የለም እንጂ ዲግሪ ያለው፣ ግን ደግሞ ተመርቆ ስራ ያላገኘ ልጅ አለ። የቢሮ ስራ ካላገኘሁ ብሎ ቁጭ አላለም። የሊስትሮ እቃውን ይዞ ነው ወደ ስራ የገባው።
በቃ፤ ሁሉም ይህንን ነው ማድረግ ያለበት። እጅ ይዞ እንዴት በእጅ ይለመናል? በእጅ መስራት እየተቻለ በእጅ መለመን ስህተት ነው፤ በእጅ መስራት ነው የሚገባው። ወጣቱም ይህንን ነው መያዝ ያለበትና ወደ ስራ መሰማራት ያለበት። ሱስ መጥፎ ነው። ብዙ ስራ የጀመሩ ወጣቶችን አውቃለሁ። ግን ምን ያደርጋል ሱሱ ይዟቸው ጠፋ። እየከሰሩ ስራቸውን ያቆሙ ብዙ ልጆች አሉ። እናም ከሱስ መላቀቅና ወደ ስራ ላይ ማተኮር ይገባል። ሁሉም መስራት ነው ያለበት።” በማለት ሰፋ እድርጎ አብራርቶልናል።
ሁኔታዎች ቢሟሉልህ ምን ምን መስራት ትፈልጋለህ? ብለነውም “ትክክልኛ ጋዜጠኛ፣ ችግራችንን ለመንግስት የሚያደርስ ጋዜጠኛ ብናገኝ መንግስት እንዲያደርግልን የምንፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። ትንሽ ቦታ እንዲሰጠንና ከደንቦች ተወረስን አልተወረስን ከሚለው የእለት ተእለት ስጋት እንድንድን ነው የምንፈልፈገው።
“እኔ ብዙ አይነት ችሎታና ሙያ አለኝ። መስሪያ ቦታና መሳሪያውን ባገኝ ጧፍ መስራት እችላለሁ፤ ሻማ መስራት እችላለሁ። ሌሎችም እምችላቸው ሙያዎች አሉ። አሁን እዚህ ይሄን ይሄን እችላለሁ ብዬ ልስራ ብል ግን መንግስት አያሰራኝም። ስለዚህ ትንሽ ቦታ ተሰጥቶን መስራት ብንችል ጥሩ ነው። ለማንኛውም ቦታ ባገኝ በምችለው ሁሉ ተሰማርቼ መስራት እፈልጋለሁ። ውጤታማ እንደምሆንም ደግሞ እርግጠኛ ነኝ። ከራሴም አልፌ ለሰው ሁሉ እተርፋለሁ።” ሲል ነግሮናል።
እኛም የእስከዛሬ ጥረትና አርአያነቱን በእጅጉ እያደነቅን ያሰበው ሁሉ ተሳክቶለት ያቀደውን ሁሉ እንዲያሳካ እንመኝለታለን። ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013