በአገራችን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አስራ አንድ ወራትን አስቆጥሯል፡፡ በነዚህ ወራት በአንድ በኩል በርካታ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ተከናውነዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስጋቶችም ተደቅነዋል፡፡ ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው አሁን አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት ከፊት ለፊት የሚታይ ብርሃን አለ፡፡ ይህ የተስፋ ብርሃን ግን እንክብካቤና የሁሉንም ህዝብ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነትና ርብርብ ይጠይቃል፡፡
ወደኋላ መለስ ብለን ከለውጡ በፊት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት መፃኢ እድላችን ምን ሊሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት የነበረበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ በምስራቃዊው የአገራችን ክፍል የነበረው ሁኔታ አስከፊ እንደበርም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት እና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ በአካባቢው የነበረው ሁኔታ አገሪቱ ወዴት ታመራለች ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ማግኘት እስከሚያዳግት ድረስ የርስ በርስ ግጭቱና አንዱ በሌላው ላይ የፈጸመው በደል አስከፊ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ዜጎች በአገራቸው ላይ ሰርተው ለመኖር ዋስትና ያጡበትና ተስፋ እስከመቁረጥ የደረሱበት ወቅት እንደነበር ብዙዎች በምሬትና በትካዜ ያስታውሱታል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ችግሩን ከመለየት ጀምሮ የአካባቢው ማህበረሰብና መንግስት በተቀናጀ ሁኔታ ባካሄዱት ጥረት ስርነቀል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ በአካባቢው የነበረውን ችግርም ከሞላ ጎደል በማስወገድ አካባቢው ለሁሉም ዜጎች የሰላም መንደር እንዲሆን ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በጅግጅጋ የተካሄደው 8ኛው የከተሞች ፎረም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ፎረም ላይ የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ተጋባዥ እንግዶች በፍቅርና በአንድነት ስለነገ የከተሞች እድገት ተሞክሮዎቻቸውን በሰላም ተለዋውጠው የአካባቢውንም ባህል ተረድተው የተመለሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የነበሩት ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀልም ከለውጡ በፊት በአገራችን ላይ ስጋት ከደቀኑ ክስተቶች አንዱ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በጉጂና ጌዲኦ ዞኖች በተነሱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ለችግር የተዳረጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻጉል ጎምዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችም በተመሳሳይ በዜጎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በአካባቢው ሲንቀሳቀስ በነበረው የኦነግ ታጣቂ ሃይልና በመንግስት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ የሰላም ስጋት የተዳረጉበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ይሁንና እነዚህ አካባቢዎችም በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ወደሰላም እያመሩ ይገኛሉ፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ለተፈጠረው የሰላም መፈጠር ደግሞ የባህላዊ እሴቶቻችን የተጫወቱት ሚና የላቀ ነው፡፡ በተለይ በአባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የተከናወነው የሰላም ጥሪና የእርቅ ተግባር የተጫወተው ሚና ለሌሎችም ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መልኩ የተከናወነ መልካም ተግባር ነው፡፡
በሌላ በኩል አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች ግን እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ አንጻር በተለያዩ አካባቢዎች መልስ ያላገኙት የህዝብ ጥያቄዎች መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ መገንዘብና ለዚህም በጋራ መስራት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከክልልና ዞን እንዲሁም የወረዳ ጥያቄ ጋር የተያያዙት ጥያቄዎች መፍትሄ የሚሹ የቤት ስራዎች ናቸው፡፡
በሌላም በኩል ከመልካም አስተዳደር እና ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችንም ተከታሎ ፈጣን ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ በተለይ በየደረጃው ያለው አመራር ለውጡ የሁሉም መሆኑን በመረዳት በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለውጥ ሲባል ከላይ ያሉት የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ አድርጎ በመውሰድ የለውጡ አካል ከመሆን ይልቅ ለውጡ እነሱ ጋር እንዲደርስ የሚሹ አመራሮችም ቆም ብለው በማሰብ ችግሮችን በየደረጃቸው ለመፍታት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል መላው አገራችን ህዝብም መንግስት በለውጥ ሂደቱ ያስመዘገባቸውን ዘርፈብዙ ጥረቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሌሎች ለውጦችም ተስፋ መኖሩን መገንዘብና ጊዜ በመስጠት መንግስትን መደገፍ አለበት፡፡ አሁን እያየን ያለነው ለውጥ ከአንድ አመት በፊት ፈጽሞ ያልተጠበቀና በዚህ ደረጃ ሊሆን ይችላል ተብሎ ያልተገመተ እንደነበር ማስታወስና በርግጥም የመንግስት ቁርጠኝነት እና የህዝብ ፍላጎት ካለ የምንፈልግበት ቦታ መድረስ እንደምንችል መረዳት ተገቢ ነው፡፡
በዚህ ሂደትም በአገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ እያንዳንዳቸው የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚሰሩ እንጂ በህዝቡ ለመጠቀም አለመሆኑን በመረዳት ከወዲሁ ለህዝብ መስራት መለማመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬን ለሰላም የሚሰራ የፖለቲካ ድርጅት ነገ የህዝቡን ፍላጎት ለመመለስ ችግር እንደማይገጥመው ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊና መደበኛ ሚዲያዎችም ጭምር ህዝብ ከህዝብ ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላት ከዚህ ተግባር በመቆጠብ ህዝብን ለሰላምና ለእድገት የሚያነሳሱ፣ መንግስትም መስራት የሚችላቸውን ጉዳዮች የሚያመላክቱ ስራዎች ላይ ቢረባረቡ ለአገራችን እድገት ጠቃሚ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011