“እሽክም” በሚለው ዘፈኗ ትታወቃለች ፤አርቲስት ማዲቱ ማዲቱ ወዳይ። አርቲስቷን ያገኘናት በወሎ ግንባር ለአገር መከላከያ ሰራዊቱ፣ለአማራ ልዩ ኃይል፣ለሚሊሻና ለህዝቡ የሚያነቃቁ የጥበብ ሥራዎቿን ስታቀርብ ነው።
እናቷ በህይወት ከተለዩና እሷም ከእነ ቤተሰቦቿ ከምትኖርበት ወልዲያ ከተማ ከተፈናቀለች ቅርብ ጊዜ ቢሆንም አገርን ለማዳን እየተፋለሙ ለሚገኙ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች አይበልጥም በሚል የጥበብ ሥራዎቿን ለማቅረብ ግንባር ድረስ መምጣቷን ገልጻልናለች። ምክንያቱም ከእናቴ ሞት የበለጠ ህዝብን የሚጎዳ ክፉ ጠላት ነው የመጣው ብላለች።
የጥበብ ሥራዎች ምንጊዜም ለሰራዊቱ ተጨማሪ የሞራል ስንቅ ነው የምትለዋ አርቲስት አወዳይ፤ የጥበብ ሥራዎቿ ለሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ አካሎች ማቅረቧ ደስተኛ መሆኗንና ሰራዊቱም የነበረው መነሳሳት የሚደነቅ መሆኑን ነግራናች።
ከጠላት ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ ወጣቱ ጦር ግንባር በመሰለፍ፤ባለሀብቱ የተለያዩ ዕገዛዎችን በማድረግ፤የስነ ጥበብ ባለሙያው በስነ ጥበብ ሥራዎቹ ሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችን መደገፍ አለባቸው የምትለዋ አርቲስት ማዲቱ ፣እሷም ሆነ የሙያ አጋሮቿ ግንባር ድረስ ተገኝተው አገራዊ አንድነትና የሰራዊቱ ጀግንነትን የሚያወሱ የጥበብ ሥራዎቻቸውን ማቅረባቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላት ገልጻለች።
አርቲስት መብሬ መንግስቱ “መውዜር አማረኝ” የሚለው ዘፈኑ ይታወቃል።እሱና የሙያ አጋሮቹ በወሎ ግንባር በሚገኙ የተለያዩ ሰባት ቦታዎች በመገኘት ለሰራዊቱ፣ለሚሊሻውና ለህዝቡ የሙዚቃ ሥራዎችን አቅርበዋል።
ኪነ ጥበብ አገራዊ አንድነት ለማምጣትና በአወደ ውጊያዎች ሰራዊቱን በማነቃቃትና በማነሳሳት ትልቅ ስፍራ አላት የሚለው አርቲስት መብሬ፤በወሎ ግንባር ተገኝቶ የመከላከያ ሰራዊቱን፣ልዩ ኃይሉን፣ሚሊሻውንና ህዝቡን የማዝናናትና የማነሳሳት ሥራ በመስራቱ ደስተኛ ሆኗል።
አገር አፍራሾች እነሱ ይፈርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም ፤ ኢትዮጵያ ፈርሳም አታውቅም፤ ምክንያቱም በየጊዜው ውድ ህይወታቸውን የሚሰጡላትና የሚጠብቋት ልጆች አሏት የሚለው አርቲስት መብሬ፤ ዛሬም ወጣቱ ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው እንቅስቃሴ ወደ አገር መከላከያ ሰራዊት፣ልዩ ሀይሎች በመቀላቀል አገሩን መጠበቅ ይኖርበታል ብሏል።
አርቲስቱም ሥራውም ኑሮውም ከህዝብ ጋር የተሳሳረ እንደሆነ የሚገልጸው አርቲስት መብሬ፤ በህዝብ ላይ የከፋ በደልና የጭካኔ ተግባር የሚፈጸመውን ጁንታ ለመፋለም በየጦር ግንባሩ የሚፋለመው የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ግንባር ድረስ ሄዶ የማነቃቃትና የማዝናናት ሥራ የሚጠበቅበት መሆኑን ይገልጻል።
እሱና የሥራ ባልደረቦቹ 13 ቀናት በወሎ ግንባር ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በሚገኙባቸው ቦታዎች በመሄድ እነሱ የሚበሉትን እየበሉና የሚያድሩበት ቦታ እያደሩ ሰራዊቱን የሚያነቃቁና የሚቀሰቅሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ማቅረባቸውንና ሰራዊቱም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ድል በድል እንደሚሆን ያለውን እምነት ነግሮናል።
የኪነ ጥበብ ሥራችንን በወሎ ግንባር ድረስ ሄደን ማቅረባችን የአገራዊ ግዴታችን አንዱ አካል ነው የሚለው አርቲስት አስራት ቦሰና ፤የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን በወሎ ግንባር በተለያዩ ቦታዎች በማቅረባቸው ጥልቅ ስሜት እንዳሳደረበት ይገልጻል።
ሰራዊቱ ለእኛ ጥሩ አቀባበል ነበረው፤እኛም በሰራዊቱ መካከል ተገኝተን የጥበብ ሥራዎቻችንን ማቅረባችን ደስተኞች አድርጎናል ሲል የሚገልጸው አርቲስቱ፤ የጥበብ ሰዎች በተለያየ መልኩ ሰራዊቱን ማነቃቃትና መዝናናት አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ያብራራል። ምክንያቱም እኛ በጥበብ ሥራችን የምናወድሳትን አገርና የሚያደንቀንን ህዝብ የሚጠብቀው የአገር መከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ናቸው ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተመሳሳይ መድረኮች ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የምልምል ወታደሮች ማሰልጠኛዎች ተካሂደዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር የኪነጥበብ ልኡክ በጦላይ ምልምል ወታደሮች ማሰልጠኛ በመገኘት ምልምሎቹን አነቃቅቷል። በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ስር የሚገኙት አራት ቲያትር ቤቶችም እንዲሁ በአዋሽ የምልምል ወታደሮች ማሰልጠኛ በመገኘት ተመሳሳይ ተግባር ፈጽሟል።
እነዚህን የሀገር ፍቅር ስሜት አንገብግቧቸው ሳይውሉ ሳያድሩ በየማሰልጠኛው ጣቢያ የገቡትን ኢትዮጵያውያን የተመለከቱት ጀግኖች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የባህል ከዋክብትም ውለው ሳይደሩ በቂ ዝግጅት አድርገው “ ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም፣ በምንም” እያሉ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ደርሰዋል።
በምልምል ወታደሮቹ መሀል ሆነው ልዩ ልዩ ጣእመ ዜማዎች፣ የሰርከስ ትርኢቶችን፣ ኮሜዲዎችን በማቅረብ የሰራዊቱ ደጀን መሆናቸውን እንደተለመደው አረጋግጠዋል። ደማቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ የሰራዊቱን መነሳሳት አጠናክረዋል፤ ንቅናቄ ፈጥረዋል። ልክ እንደ እንጋፋዎቹና ቀደምት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ሰራዊቱ ለሀገሩ ክብር በመቆም ጀግኖች አባቶቹ ያስረከቡትን ሀገር በክብር እንዲያስረክብ ሰፊ የማነቃነቅ ተግባር አከናውነዋል።
በመድረኮቹ ላይ ምልምል ወታደሮቹ በሙሉ ተገኝተው ለጠላትም ለወዳጅም ማንነታቸውን አረጋግጠዋል። አርቲስቶቹ በየመድረኮቹ ባቀረቧቸው ጥበባዊ ትዕይንቶች ምልምል ሰልጣኞቹ በእጅጉ ተመስጠውም ዜማዎቹን አብረው አቀንቅነዋል፤ አብረው ተወዛውዘዋል፤ በአድኖቆት ተመልክተዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርገው በማውለብለብ ለሀገራቸው ዘብ መቆማቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ዝግጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል። በኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ዘንድ የሚታየው መነሳሳትም ይህንኑ ያመለክታል። የሀገር ህልውና ማስከበር ሥራ የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ሚና የሚጠይቅ እንደመሆኑ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ሥራዎቻቸውን ለሰራዊቱ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ጀምረዋል። በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮችን በማዘጋጀት ከሰራዊቱ አጠገብ መሆናቸውን ማሳየታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
አገር ሲኖር ነው የጥበብ ሥራን ማቅረብም ሆነ ወልዶ ማሳደግ የሚቻለው ፤አገር ከሌለች የትም ሆኖ ይሰራል። እናም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ከአፍራሽ ኃይሎች ማዳን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ በየሙያ መስኩም ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ ይገባል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013