የሥራ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑ እርግጥ ነው። ይሁን እንጂ ገንዘብ ማግኛ ብቻ ሳይሆን ገንዘብ መቆጠቢያ፤ የጤና መጠበቂያም ነው። ሥራ በመዋልና አለመዋል መካከል ያለው የወጪ መጠን የትና የት ልዩነት እንዳለው ሁሉም የሚያውቀው ሲሆን በተለይ ሁለቱንም (ሥራ መዋልንም አለመዋልንም) የተጋፈጠ የበለጠ ያውቀዋል።
የሥራ ጉዳይ የግለሰብ፣ የማንነት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የሥራ ጉዳይ የትዳር ጉዳይ ነው፤ የሥራ ጉዳይ የጎጆ ጉዳይ ነው፤ የሥራ ጉዳይ የልጆች ጉዳይ ነው፤ የሥራ ጉዳይ የቤተሰብ ጉዳይ ነው። የሥራ ጉዳይ ከዛም ባለፈ የማህበረሰቡ ጉዳይ ነው። የሥራ ጉዳይ የሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ነው። በመሆኑም ሁሉንም ወገን ሰላም፣ እንቅልፍ ይነሳል። “እኔ አገርም ምንም የለኝም” እስከ ማለት የደረሰው የዛሬው እንግዳችንም ይህንኑ ስሜት ነው የሚጋራው፤ የሚያጋራንም።
ሥራ ሁሉንም ነገር ነው፤ ባጭሩ ህይወት ነው ማለት የሚቻል ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ላይ ትኩረታችንን የምናሳርፈው ከመንግሥትም ሆነ ሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት የሥራ እድል መፍጠር አኳያ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ፤ እንዲሁም የዛሬው እንግዳችን አይነት ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚነት ምን እንደሚመስል በገደምዳሜም ቢሆን ማየት ላይ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ እንግዳ ይዘን የቀረብን ሲሆን እሱም ወጣት ጌታቸው ደንድር ይባላል።
ጌታቸው የአዲስ አበባ ልጅ ነው። ተወልዶ ያደገው በቀድሞው (በፈረሰው) አራት ኪሎ ቀበሌ 12 ውስጥ ሲሆን አሁንም ያገኘነው እዚሁ አራት ኪሎ (ቱሪስት ሆቴል አካባቢ) ነው።
ለእንደማንኛውም፣ በሚገባ እንደሚያውቃት ሰው ሁሉ አራት ኪሎ ለጌታቸውም ፍቅር የሆነች አካባቢ ነች። በጉዳዩ ላይ ገፋ አድርገን አልሄድንበትም እንጂ እንደ አንድ የተወለደባት አካባቢ ለእሱ ልዩ ትርጉም እንደምትሰጠው ማወቅ አይከብድም፤ ይህንንም ስንል ከፊቱ ላይ ከመታወቁ በዘለለ ስሟን የሚጠራበትና የሚደጋግምበት ፍጥነትና ቃናው ስለሚያስታውቅ ነው።
ወጣት ጌታቸው እንደምንመለከተው ሳይሆን ከባድ ኃላፊነትን የተሸከመ ወጣት ነው። ይህ ሸክሙም ከባለትዳርነቱና የሁለት ልጆች አባትነቱ የመጣ ሲሆን ከላይ በመግቢያችን ላይ ለማመልከት እንደሞከርነው የሥራ ጉዳይ የልጆች፣ የቤተሰብ ወዘተ ጉዳይ ነውና ይህ ሸክሙ ከብዶት በብዙ ግራ መጋባት ውስጥ የሚገኝ ወጣት ሥራ አጥ ነው።
ጌታቸው እንደነገረን ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ከተስፋ በስተቀር በእጁ ላይ ምንም የለም። ተስፋውም ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች እርቆ የተሰቀለ ዳቦ መስሎ ስለታየው በእርግጠኝነት የተሞላ አይደለም።
ወጣቱ እንደነገረን ከሆነ አራት ኪሎ ተወልዶና አድጎ የአዲስ አበባ ተወላጅ (ነዋሪ) ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰአት ይህንን የሚያረጋግጥለት ምንም አይነት ማስረጃ በእጁ ላይ የለም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአራት ኪሎ መልሶ መልማት ጉዳይና በወቅቱ እሱ በተለያዩ ምክንያቶች እዚህ አራት ኪሎ አለመኖሩ ነው።
“አለመኖርህ ምን ፈጠረ፣ ምንስ አስከተለብህ?” በማለት ላቀረብንለት ጥያቄ “በወቅቱ አልነበርኩም። ከሄድኩበት ስመለስ ሰፈሩ በሙሉ ፈርሶ አካባቢው ባዶ ሆኖ ነው የደረስኩት። ማንም የለም። ምንም አይነት ሰውም ሆነ ቤት የለም። ደነገጥኩ። የእናት አባቴ ቤት ነበር የለም። ምን እንደሆነና ማን እንደወሰደው ሁሉ አላውቅም። አንዴ እህት ወንድሞችህ ወስደዋል ይሉኛል። አንዴ ሌላ ይሉኛል ይሄው እስካሁን ምንም ስለ ቤቴ የማውቀው ነገር የለም። በቃ ከዛ ወዲህ ቤት የለኝ፣ የማድርበት የለኝ፤ ባጭሩ ምንም ነገር የለኝም። አገርም የለኝም። ዝም ብዬ ተባርሬ ነው የምኖረው። የምከፍለው እያጣሁ ቤት ስቀያይር የአሁኑ ወደ ስድስተኛ ጊዜዬ ነው። የምከፍለው እያጣሁ ልቀቅ ሲሉኝ ስለቅ፣ ልቀቅ ሲሉኝ ስለቅ፤ አንዳንዴ ላስቲክ ወጥረን ስንቀመጥ እሱንም ሲያፈርሱት፤ ሌላ ቦታ ደግሞ ሄደን ስንሞክር ከዛም ሲያስነሱን እንደዚህ ነው እየኖርን ያለነው።” በማለት ነው የመለሰልን።
“ከቤቱ ጋር በተያያዘ የሚመለከተውን የመንግሥት አካል አልጠየክም?” ላልነውም ያልጠየቀው አካል እንደሌለ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ፖሊስ ጣቢያ ሁሉ እንደጠየቀ፤ ነገር ግን ምንም አይነት መልስ እንዳላገኘ፤ በዚህ ምክንያትም በአሁኑ ሰዓት መታወቂያ እንኳን የሚሰጠው አካል እንዳጣ ይናገራል።
“መታወቂያ የለህም ማለት ምን ማለት እንደሆነ እስኪ አስበው” የሚለው ጌታቸው “መታወቂያ የለህም ማለት፣ በሥራ አጥነት መመዝገብ አትችልም ማለት ነው፤ መታወቂያ የለህም ማለት፣ ሥራ በሚያስገኙ ዘርፎች ከብጤዎችህ ጋር መደራጀት አትችልም ማለት ነው። መታወቂያ የለህም ማለት የሥራ አጥ መታወቂያ ማውጣት አትችልም ማለት ነው። መታወቂያ የለህም ማለት አገር የለህም ማለት ነው። በመሆኑም ግራ ገብቶኝ ቁጭ ብያለሁ።” ሲልም መረርና ከረር ባለ ድምፀት ውስጡን ይናገራል።
“አሁን ምን አይነት ሁኔታ ላይ ነው ያለኸው?” ላልነውም “ምንም አይነት ሁኔታ ላይ አይደለሁም ያለሁት። ያለሁት ባዶ ሜዳ ላይ ነው። እዚህ ፓርኪንግ (መኪና ማቆምና ስርዓት ማስያዝ ሥራ ላይ) ነው እየሰራሁ ያለሁት። ቦታው በመንግሥት በፓርኪንግ እውቅና የተሰጠው አይደለም። በመሆኑም በግል በማደርገው የማስተናበር ሥራዬ ደስ ያለው ቲፕ ይሰጠኛል በቃ፤ እየኖርኩ ያለሁት በሷ ነው።” ሲል መልሶልናል።
ቦታው ላይ ተደራጅተን ለመስራት ፈልገን ለሚመለከታቸው አመልክተን ነበር። ቦታው ቋሚ አይደለም። ስለዚህ በዚህ፣ ቋሚ ባልሆነው ነገር ከተደራጃችሁ ወደ ፊት በሌላ ዘርፍ ተደራጅታችሁ ለመስራት ትቸገራላችሁ። ስለዚህ አሁን ሥራው እስኪቆም ድረስ ዝም ብላችሁ ሥሩ። ከቆመ በኋላ እንደ አዲስ እኛ ስማችሁን ይዘን እናደራጃችኋለን ተብለናል የሚለው ጌታቸው ደንድር አካባቢው በጣም እየተለወጠ ከመሆኑ፣ እያደገና ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ስለሚጠበቅ ተደራጅተን ለመስራት ሀሳብ አለን ሲልም ይናገራል። ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ግን አንድ ነገር ሲሳካለት ነው – የሥራ አጥ መታወቂያው እጁ ሲገባ።
አሁን ከተወሰኑ ጓደኞቹ ጋር እየሰሩት ያሉትን በተመለከተም እዚህ አካባቢ ያለው ኢሚግሬሽን ቢሮ ከትንሽ ወራት በኋላ የኪራይ ቤቱን ኮንትራት ጨርሶ ወደ ዋና ቢሮው ይመለሳል። እሱ ከሄደ ደግሞ ያንን ያህል መኪና እዚህ አይመጣም። ስለዚህ እዚህ የሚቆም መኪና የለም፤ ያ ማለት ደግሞ ፓርኪንግ የለም ማለት ነውና ከዛ በኋላ እዚህ የሚገኝ ነገር የለም። በመሆኑም ከፊት ያለው ኑሮ ከባድ ነው የሚለው ጌታቸው ደንድር “አሁን የሚመለከተው፣ በተለይ ክፍለ ከተማው የአዲስ አበባ ነዋሪነቴን ቢያረጋግጥልኝና መታወቂያ ቢሰጠኝ ከላይ ያልኳቸውን ችግሮቼን (የሥራ አጥ መታወቂያ የማግኘትና የመደራጀት መብት ማለቱ ነው) በማቃለል እንደ ጓደኞቼ የሥራ እድል ተጠቃሚ እምሆንበት እድል ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ።” ሲልም አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግለት ይጠይቃል።
እኔ ተወልጄ ያደኩት እዚህ ቀበሌ (12) ነው። የሥራ መፈለጊያ የሥራ አጥ ካርድ ላወጣ የምችለውም ከዚህ ከኖርኩበት ቀበሌ ነው። እዚህ ደግሞ ማንም የለም። ቀበሌ ሄጄ ስጠይቅ ፋይላችሁ የለም፤ ቅፅ የላችሁም ልናስተናግዳችሁ አንችልምና የመሳሰሉትን አይነት መልሶች ከመስጠት ውጪ አንድም የሚያስተናግድህ ሰው የለም የሚለው ጌታቸው “አሁን እኔ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ሁሉ ግራ እየገባኝ ነው ያለሁት።” ሲልም ያጋጠመውንና ግራ የገባውን ነገር ክብደት ይገልፃል።
“አሁን እየሰራችሁት ያለው ሥራ ካለቀስ?” ብለነውም “እያለቀ ነው። ከዛ በኋላ ምንም ተስፋ የለንም። ምናልባት መንግሥት አደራጅቶ ሌላ ቦታ ወስዶ ሥራ ከሰጠን በሚል ነው እንጂ የምንፅናናው ሌላ ምንም ይሄ ነው የምንለው ተስፋ የለንም።” የሚል መልስ ሰጥቶናል።
“በየወሩ ነው ቤት የምቀይረው፤ የቤት ክራይ እምከፍለው ሳጣ ‘ውጣ’ እየተባልኩ ከነቤተሰቦቼ ጎዳና ላይ ላስቲክ ቤት ውስጥ ሁሉ ኖሬያለሁ፤ ይህችን አራት ወር ነው፣ አሁን ትንሽ ተረጋግቼ እየኖርኩ ያለሁት። ይህም አሁን እየሰራሁት ባለው ሥራ (ፓርኪንግ) አማካኝነት የተዋወቅሁት አንድ ባለ ሀብት ጉዳዬን አማክሬው ነበር፤” “ስንት ነው የምትከፍለው” አለኝ፤ “ሁለት ሺህ ብር” አልኩት፤ “እኔ እሰጥሀለሁ” አለኝ። “እሺ” ብዬ እየጠበኩት ድንገት ጠፋብኝ። አንድ ቀን ድንገት ሳላስበው ከኋላዬ መጣና ያዝ አድርጎኝ፣ “እንዴት ነህ ጌታቸው፣ ጠፋሁብህ አይደል? ሥራ በዝቶብኝ ነው እኮ” ብሎ 10ሺህ ብር ሰጥቶኝ ሄደ። ከዛ ላይ 8ሺህ ብር በማንሳት የ4 ወር ቅድሚያ የቤት ክራይ በመክፈል አሁን ትንሽ እፎይታ አገኘሁ። ” ሲል ጌታቸው ያለፈበትን የህይወት ውጣ ውረድ ነግሮናል።
“ልጆችህ ይማራሉ?” ላልነውም መልሱ “አዎ” ነበር። ኑሮ በጣም ከባድ ነው። የሁለት ልጆች አባት ነኝ። የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ አለ፣ ቀለብ አለ፣ ልብስ አለ፣ ቤት ኪራይ አለ፤ ይሄ ሁሉ አለ። ሥራ የለም። አንዳንዴ የባሰ ጊዜ ሲመጣ እሷም ወደ ቤተሰቦቿ፣ ወደ ጓደኞቿ ጋር ትሄድና ልመና ብጤ…። እንዲህ እንዲህ እያልን ነው ኑሮን እየገፋን ያለነውና በጣም ከባድ ነው የሚለው ጌታቸው አሁን አንድ ነገር ብቻ እንደሚፈልግ ይናገራል።
“በአሁኑ ሰዓት እኔ እምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። እኔ እምፈልገው ከቀበሌ ሥራ ፈልጌ የምይዝበትን፤ የምደራጅበትን የሥራ አጥ መታወቂያዬን ብቻ ከፋይሌ ውስጥ አውጥተው እንዲሰጡኝ ነው የምፈልገው፤ በቃ። ቀበሌን እንዲተባበረኝና እንዲያደርግልኝ የምፈልገው ይሄንን ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊ መሆኔን፣ ዜጋ መሆኔን የሚገልፅ ጊዜያዊም ቢሆን መታወቂያ፣ እኔነቴን፣ ማንነቴን የሚገልፅ መታወቂያ ብቻ እንዲሰጠኝና የወደቀውን የመስራት፣ የመደራጀት ሞራሌን እንዲያነሳልኝ ነው የምፈልገው። ቀበሌ ይህን ካደረገልኝ እኔ የትም ሄጄ፣ በተገኘው ክፍለ ከተማና በተገኘው የሥራ አይነት ላይ ልሳተፍ ፍቃደኛ ነኝ።” የሚለው ጌታቸው ደንድር ይህ ከተሟላለት ልጆቹን እንደ ማንኛውም ወላጅ በጥሩ ሁኔታ ማስተማርና ሰላማዊ ኑሮን መኖር እንደሚፈልግ ይናገራል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013