አንዳንዴ እስከ አሥር ቀን የረዘመ የህፃናት እንቅልፍ ማጣት አጋጠመን የሚሉ እናቶች ይደመጣሉ። ህፃናቱ በእንቅልፍ እጦት የተነሳ ሲነጫነጩ ብሎም አምርረው ሲያለቅሱ መመልከት ለወላጆችም እጅግ ፈታኝ ነገር ነው፤ የጨቅላ ህፃናት የእንቅልፍ ማጣት ችግር ከምን ይመጣል? ስንል የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የልጅ በእድሉ አይደግ መፅሀፍ ደራሲን ዶክተር ሄኖክ ዘውዱን አነጋግረናል። መልካም ንባብ፡፡
ለህፃናት ጤና በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የተስተካከለ የእንቅልፍ ሰዓት ነው፡፡ አንድ የተወለደ ጨቅላ ህፃን በቀን ከ14 እስከ 19 ሰዓታትን በእንቅልፍ ሊያሳልፍ ይችላል። ወደ ሁለት ዓመት እድሜ ገደማ ያሉ ህፃናት ደግሞ ከ10 እስከ 14 ሰዓታትን በእንቅልፍ ያሳልፋሉ። ይህ ቁጥር እድሜ ከፍ እያለ ሲሄድ እየቀነሰ ሲመጣ የአምስት ዓመት ልጅ ከ9 እስከ 13 ሰዓታትን በእንቅልፍ ያሳልፋሉ፡፡ እድሜያቸው በጣም ዝቅ ያሉ ልጆች ከፍ ያለ የእንቅልፍ ሰዓት እንደሚያስፈልጋቸው ወላጆች በመረዳት በአግባቡና ያልተቆራረጠ እንቅልፍ ልጆቻቸው እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው፡፡
የመጀመሪያ ልጅ የወለዱ ወላጆች በጣም ብዙ ጊዜ ጨቅላ ልጃቸውን ለማስተኛት ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፤ በተለይ ደሞ የመጀመሪያ ወር ላይ ከባድ ነው:: ይህ ጭንቀት ከ 2 እስከ 3 ወር በኋላ የእንቅልፍ ሰዓታቸው ተስተካክሎ ሌሊት ላይ ለረጅም ሰዓት መተኛት ይጀምራሉ::
ለዛሬ ጨቅላ ህፃናት አልተኛም ብለው ሲያስቸግሩ በጨርቅ ወይም በፎጣ በደንብ መጠቅለል፤ ይህም ልክ እናታቸው ማህፀን ውስጥ እንዳሉ አድርገው እንዲሰማቸው እና በምቾት እንዲተኙ ይረዳቸዋል:: በቂ የሆነ ሙቀት መስጠት ይህም ልብስ በደንብ በማልበስ ወይም ከእናት ጋር ገላለገላ ንክኪ በማድረግ (ካንጋሮ አያያዝ) ሊሆን ይችላል ከአቅማቸው በላይ ልብስ ደራርበንባቸው ከፍተኛ ሙቀት እንዳይሰማቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
የምናለብሳቸው ልብሶች ከጥጥ የተሰሩ ማድረግ፤ ዳይፐር (ሽንት ጨርቅን) ጡት ከመጥባታቸው በፊት መቀየር፤ ምክንያቱም ከጠቡ በኋላ ወዲያው እንዲተኙ ማንኛውንም ንክኪ መቀነስ እና በሰላም እንዲተኙ ማድረግ ያስፈልጋል:: ጡት ከጠባ በኋላ ከሕፃኑ ጋር ዓይን ለዓይን አለመተያየት (ዓይን ለዓይን መተያየት እንዲነቁ እንጂ እንዲተኙ አያግዝም)።
ከማስተኛታችን በፊት በበቂ ሁኔታ ማጥባት፣ ካጠባን በኋላ ማስገሳት፣ ስናስተኛ ሁሌም በጀርባ ማስተኛት የምናስተኛበት አልጋ ቀጥ ያለ እና የማይሰረጉድ መሆን አለበት፡፡ ቀን ላይ ረጅም የእንቅልፍ ጊዜ (ከ3 ሰዓት በላይ) እንዳይኖራቸው መቀስቀስ እና ማጥባት ማጫወት ማናገር ማንቀሳቀስ ተገቢ ነው። ሆኖም ግን ቀን ላይ በጣም ማድከም አይመከርም ቀን ቀን ብርሃናማ ቦታ ማስተኛት ማታ ደግሞ ጨለማ እና ፀጥ ያለ ቦታ ማስተኛት ይሄም የቀን እና የማታን ልዩነት እንዲያውቁ እና የእራሳቸውን የተፈጥሮ ሰዓት (Circadian rythm) እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል::
ማታ ማታ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ አለማጫወት፤ ይህም ሰዓቱ የእንቅልፍ ሰዓት እንደሆነ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል:: በሚተኙበት ጊዜ ህጻናቱን አለመነካካት፣ ማባበል፣ ለስለስ ያለ ዜማ ያለው መዝሙር መዘመር ወይም እሹሹ ማለት፣ አንዳንዴም የእንጀራ እናት (pacifier) መጠቀም ለማስተኛት ይረዳል። ሆኖም ሙሉ ጡጦ እንዲተኙ አፋቸው ላይ ማድረግ ለድንገተኛ ትንታ እና መታፈን ሊያመጣ ስለሚችል አይመከርም።
እናት እና ልጅ አንድ አልጋ ላይ መተኛት ያለባቸው እስከ መቼ ነው? የራሳቸው አልጋስ መቼ ነው የሚያስፈልጋቸው? ለሚል ጥያቄ ዶክተር እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የአሜሪካ የህፃናት ሐኪሞች አካዳሚ ህፃናት ከእናታቸው ጋር አንድ አልጋ ላይ እንዲተኙ አይመክርም::
ህፃናት ሲተኙስ በጀርባ ነው ወይስ በጎን ነው መተኛት ያለባቸው? ለሚለው ደግሞ ህፃናት ሲተኙ ሁሌም በጀርባቸው ቢሆን ይመከራል። ያ ማለት ግን ጭንቅላታቸውን ዞር ዞር ማድረግ አይቻልም ማለት አይደለም።
ልጅን ወልዶ እስከሚያድግ በአግባቡ መጠበቅ የወላጅ ግዴታው ነውና ልጆቻችሁን በተገቢው መንገድ ተንከባከቡ በሚል መልእክት ከዶክተር ሄኖክ ጋር ያለንን ቆይታ አጠናቀናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013