በዓለም ዓቀፍ የፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ግለሰቦች ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳደር ይችላሉ። እንዳውም ገበያውንና አጠቃላይ አቅጣጫውን የሚመሩት በግል ጥረትና በፈጠራ ክህሎታቸው ስኬት ላይ የደረሱ የዘርፉ ቁንጮዎች ነው። መንግስታት ጤናማ ገበያ እንዲኖር፣ የፈጠራ መብቶች እንዲከበሩ እንዲሁም ኢንቨስትመንቱ እንዲበረታታ ምቹ መንገድ ከመፍጠር ያለፈ ሚና አይኖራቸውም። ለዲዛይንና ለፋሽን ሙያ ፍቅሩ ያላቸው ግለሰቦች ደግሞ ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በዘርፉ ፊት መሪ መሆን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በአገራችን ኢትዮጵያም እንደ በርካታ ዘርፎች ሁሉ ዲዛይን፣ ሞዴሊንግ እንዲሁም አጠቃላይ የፋሽኑ ዘርፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃትና እድገት ማሳየት ጀምሯል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ መንግስትም ሆነ ግለሰቦች የራሳቸውን ድርሻ ተጫውተዋል።
ገና በሚገባ ቅርፅ መያዝ ያልጀመረውና ብዙ ስራዎች በሚጠይቀው በዚህ ሙያ ላይ በቀዳሚነት ጉልህ አሻራ በማሳረፍ ላይ የሚገኙት ግለሰቦች ናቸው። የዘርፉን ማነቆዎች ከመፍታት አኳያም የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ድርሻ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ሙያው ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ይጠቁማሉ። በዛሬው የፋሽን አምድ ላይም ከላይ እንዳነሳነው ሁሉ ኢትዮጵያዊ የፋሽን ዘርፍ ባለሙያዎች እያሳረፉ የሚገኙትን አሻራ ለመዳሰስ በምሳሌነት የአፍሪካ ሞዛይክ መስራችና ፋሽን ዲዛይነር አና ጌታነህን ራእይና ስራዎች የሚመለከት ዳሰሳ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የአፍሪካ ሞዛይክ መስራች አና ጌታነህ “የእኔ ራዕይ ጊዜ የማይሽረው፣ አፍሪካዊ ዘመናዊ ንድፎችን የመፍጠር ህልም ነው›› ትላለች። በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገናኝ ድልድዮችን እና ትብብርን፣ እውነተኛ እና ልዩ የአፍሪካ የቅንጦት ምርት ስምና ብራንድ የመገንባት ራእይም አላት።
በዚህም በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የተለያዩ መልክዓ ምድሮችን እና የበለፀገ የአፍሪካ ቅርስን ለማስተዋወቅ እንደምትሰራ ትናገራለች። አና በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ከመጣር ተሻግራ የ“ፓን አፍሪካ”ን እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግም ዓለም አቀፍ ገበያውን ለመቀላቀል ብዙ ርቀት ተጉዛለች።
የአፍሪካ ሞዛይክ
የአፍሪካ ሞዛይክ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አፍሪካዊ ምንጭና ንድፍ እና የተሻሻሉ ምርቶችን እያሳየ በአፍሪካ ተሰጥኦ እና ተነሳሽነት ላይ ትኩረት በማድረግ ስለ አንድ የጋራ ባህል ጽንሰ -ሀሳብ የሚሰራ ኩባንያ ነው። አፍሪካዊ ሞዛይኮችን፣ አልባሳትን፣ ጨርቃ ጨርቆችን፣ መለዋወጫዎችን እና ፋሽኖችን በሚፈልገው ጥራትና ዲዛይን በማምረት ወደ አካባቢያዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ገበያዎች መላክን ዓላማ በማድረግ የሚንቀሳቀስ አፍሪካዊ የፋሽን እና የዲዛይኒንግ ኩባንያ ነው።
አፍሪካ ሞዛይክ በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የአፍሪካን አቅም በመጠቀም የመሪነት ሚና እንዲጫወት ለማድረግ መመስረቱን አና ጌታነህ ትናገራለች። ኩባንያው በአዲስ አበባ ዙሪያ በለገጣፎ አካባቢ ሙሉ በሙሉ የተቀናጀ የዲዛይን እና የማምረቻ ማእከል ገንብቷል። ለራሱ እና ለሌሎች አነስተኛ እና መካከለኛ ዲዛይነሮች አገልግሎት ይሰጣል።
ኩባንያው ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ሰራተኞችን በመመልመል የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል። በዚህም በአብዛኛው ለሴቶች፣ ለበርካታ ወጣት ሰልጣኞች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
አፍሪካ ሞዛይክ የተፈጠረው በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የአፍሪካን እምቅ አቅም በመጠቀም የመሪነት ሚና ለመጫወት ነው። በሀገሪቱ ጥሬ ዕቃዎች እና ተሰጥኦ ያላቸው ዲዛይነሮች እና የእጅ ባለሞያዎች ይገኛሉ። ይህን በመጠቀም እና በሰፊው ያልተዋወቀውን የባህል፣ የታሪክ፣
የቅርስ እና የፈጠራ እሴት በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራ ይገኛል። በዚህም ኩባንያውን ለማሳደግ እና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ መስራቿ ትናገራለች።
ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን የሚገልጹ እና ታሪካችንን የሚናገሩ አካባቢያዊ ወጎችን መጠበቅ እና ማሳደግ እንደሚገባ የምትናገረው አና፣ ኩባንያው የአፍሪካ ሥራ ፈጣሪዎች ሀብታቸውን በማጣመር ዓለም አቀፍ መሪ የፋሽን ብራንድ መረብ በመዘርጋት እንዲሰሩ እድል ለመፍጠርም ጥረት እያደረገ መሆኑን ትገልጻለች።
በመላ አፍሪካ ለሚገኙ ንድፍ አውጪዎች የተቋማት ድጋፍ እጥረት፣ ተገቢ የሥልጠና ተቋማት አለመኖር፣ ንድፍ አውጪዎቹ ጥሬ ዕቃን በዘላቂነትና በሚፈለገው መጠን አለማግኘት እንዲሁም የሸማች ፍላጎቶች አለመለየትና የግንዛቤ እጥረት እንደሚስተዋልባቸው ጠቁማ፣ የአፍሪካ ዲዛይነሮች በዋና ዋና የሸማቾች ገበያዎች ውስጥ የማሰራጨት ችሎታዎችን ለማዳበር ብዙውን ጊዜ የሃብት እጥረት መኖሩም እንደ እንቅፋት እንደሚታይ ትጠቁማለች።
“የአፍሪካን የአልባሳት ኢንዱስትሪ ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት አስፈላጊውን መሠረተ ልማት የገነባው ለእዚህ ነው” የምትለው አና ጌታነህ፣ በለገ ጣፎ አካባቢ ካለው ማእከል በተጨማሪ ከባህላዊ የእጅ ሙያ፣ የፈጠራ ማዕከል እስከ የሰው ኃይል ልማት ማእከል ድረስ ያተኮረ ምርምር እና ልማት የሚካሄድበት ቅርንጫፍ በባህር ዳር
ከተማም አለው።
የኢ-ኮሜርስ ወይም “የኢንተርኔት ግብይትን ለመፍጠር” ለማስተዋወቅ ኩባንያው ሰፊ እቅዶችን አውጥቶ አየሰራ መሆኑንም አና ትጠቁማለች። በዚህም ኢንዱስትሪው ላይ ጉልህ አስተዋፆኦ እያደረገ መሆኑን ትናገራለች። በቅርቡ በተመረጡ የአፍሪካ አገሮች የችርቻሮ ቦታዎች ለመክፈት እንደሚሰራና ለእዚህም “አፍሪካ ሞዛይክ” ትልቅ ራእይ ይዞ መነሳቱን ለመገንዘብ ችለናል።
አሁን ካሉት የዲዛይንና የሞዴሊንግ ስራዎች ማሳያ መድረኮች የአፍሪካ ፋሽን ኢንዱስትሪ ያለበትን ደረጃ የሚመጥኑ ስንቶቹ ናቸው? የሚለው አጠያያቂ ነው። ምን ያህሉ የዓለምን ትኩረት እየሳቡ ነው? የሚለውም እንደዛው።
ዲዛይነሮቹ በተናጠል የሚያደርጉት ጥረት የተቀረውን ዓለም ትኩረት እያገኘ ቢሆንም፣ እንደ አህጉር በተዋቀረ መልኩ ያለው እንቅስቃሴ ብዙ እንደሚቀረው በርካታ ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ። ባለሙያዎቹ ቅድሚያ የሚሰጡት ያሉትን መድረኮች ጠንካራ ለማድረግ ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ አህጉራዊ ትስስርና ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንደሚጎለብትም ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ እንደ አፍሪካን ሞዛይክ አይነት ተሻጋሪ ራእይ ያላቸው ድርጅቶች በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አፍሪካ አገራት ሊፈጠሩ ይገባል እያልን ዳሰሳችንን እዚህ ላይ እናጠናቅቃለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013