የዛፍ ነገር ሲነሳ በሀገራችን በትልቅነታቸው የሚጠቀሱት የዋርካና የወይራ ዛፎች ናቸው። እነዚህ ዛፎች ከእምነትና ከባህል ጋር በተያያዘ በጣም ጥበቃ ስለሚደረግላቸው የተፈጥሮ አደጋ ደርሶባቸው ካልወደቁ ወይም ካልደረቁ በቀር ዘመናትን ያለምንም ችግር ይዘልቃሉ። በምኒሊክ ጊዜ የተተከሉ የሚባሉ ዛፎች በአዲስ አበባ እንጦጦ አካባቢ እንዳሉም ይነገራል። ከዚህ ወጪ ግን ከሀገራችን ዛፎች ትልቁ ዛፍ ተብሎ የሚተወቅ ዛፍ ያለ አይመስለኝም።
ኦዲቲ ሴንትራል በድረገጹ ሰሞኑን እንዳስነበበው ከሆነ የዓለም ትልቁ ዛፍ የሚገኘው በሜክሲኮ ነው። በሜክሲኮዋ የሳንታ ማሪያ ዴል ቱሌ ከተማ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ የሚገኘው ይህ ዛፍ የ2ሺ ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ነው። ዛፉ ምን ያህል ወፍራም እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ? እንግዲያው ይህ ዛፍ በጣም ከመወፈሩ የተነሳ ሙሉውን ለመክበብ ሠላሳ ሰዎች እጃችውን ታያይዘው መቆም አለባቸው። በመደበኛ ሜትር ሲለካ ደግሞ የዙሪያ ስፋት 42 ሜትር ነው።
ይህ ውፍረት ለዛፍ ፈጽሞ ያልተልመደ ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ይህ የአንድ ዛፍ ውፍረት ሊሆን አይችልም ፤ ምናልባትም ሁለት ዛፎች አንድ ላይ ገጥመው ሊሆን ይችላል ብለው ደምድመው ነበር። ነገር ግን የዘረመል ምርመራ እንዳረጋገጠው ዛፉ ይህን ያህል የወፈረው ከሌላ ዛፍ ጋር ተደባልቆ ሳይሆን በራሱ ነው።
ዛፉ ወፍራም ብቻም አይደለም ፤ ረዥምም እንጂ። ከርዝመቱ የተነሳም ከአጠገቡ ያለውን ግዙፍ ቤተ ክርስቲያን ቁመት በልጦ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኑን አጭር አስመስሎታል። አስገራሚው ነገር ግን የዛፉ ወፍራም እና ረዥም መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ከ2ሺ ዓመት በኋላም አሁንም እድገቱን መቀጠሉ ነው።
በሜክሲኮ ዜጎች ቀን ኤል አራቦ ዴል ቱሌ እየተባለ የሚጠራውን ይህ ዛፍ በአሁኑ ወቅት ከመላው ዓለም ብዙዎች ሊጎበኙት ይጎርፋሉ። ብዙዎች የሮም ስርወ መንግሥት በስልጣን ከነበረበት ዘመን አንስቶ በቦታው ቆሞ ብዙ ታሪክ ያለውን ይህን ዛፍ በአካል ማየት አስደሳች ስሜት ይፈጥርላቸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013