የተወለደው በሰሜን ሸዋ ዞን ሳሳት በምትባል አካባቢ ነው። ያደገውም እዚያው ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሳሲት አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ደብረ ብርሀን በሚገኘው ኃይለማርያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው።
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን በእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ተቀብሏል። ሁቱትሲ (የትርጉም ሥራ)፣ የጾም ጣእምና ብእረኛው የሞጃ ልጅ የተሰኙ መጻህፍትን አሳትሟል። በአሁኑ ወቅት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ ክፍል መምህርና ተመራማሪ ነው። ደራሲ፣ ተርጓሚና መምህር መዘምር ግርማ።
ክህሎት
መዘምር ለህብረተሰብ ጠቃሚ ሚና ያላቸውን የበጎ ፈቃድ ስራዎችን መስራት ያስደስተዋል። አዲስ ነገር መሞከርም ልዩ ተሰጥኦው ነው።
ራስ አበበ አረጋይ ቤተ መጻህፍት
ለስድስት ዓመታት ለደብረብርሃን ከተማ ህብረተሰብ በነጻ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መስራችና ባለቤት የሆነው መዘምር፤ ቤተመጻሕፍቱ ሊመሰርት የቻለው ሁቱትሲ የተባለችውን የትርጉም ስራውን ካሳተመና ካሰራጨ በኋላ ነው። ቀጥተኛ ምክንያቱም የተማሩ ጓደኞቹ ሳይቀሩ በህይወታቸው አንብበው የጨረሱት የእርሱን መጽሐፍ ብቻ መሆኑን ስለነገሩትና፤ በማስተማር ልምድም ከሚታዘበው፤ ንባብ ላይ ያስተዋለው የኋላ ቀርነት አባዜ ስለገባው ነው።
“በኪራይ ቤት፣ በአንድ መምህር ደመወዝ፣ የግል ቤተመጻሕፍት በማይታወቅበትና በፖሊሲም በማይደገፍበት አገር ይህን ስራ የሰራሁት በብዙ ውጣ ውረድ ሲሆን፣ ተግባሩ በመላ አገሪቱ ሊስፋፋ የሚገባው ነው” ሲል ይናገራል።
ከደራሲው ሥራዎች የትርጉም ሥራ የሆነውን ሁቱትሲን እንመልከት። መዘምር ሁቱትሲን ለመተርጎም የወሰነው በአገራችን ያለው የከረረ የዘር ፖለቲካ ሩዋንዳ ከ1994ቱ የዘር ጭፍጨፋ በፊት ከነበረችበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነገር በማየቱ መሆኑን ይገልጻል፤ ይህን ማድረጉም ለጥንቃቄ ይረዳል የሚል እምነት አለው። ህብረተሰቡ በሚገባ የተቀበለው ይህ የትርጉም ሥራው ለውጥ ማምጣቱንም ያምናል። አንባቢያን ዘረኝነታቸውን ለመተው መወሰናቸውን ጭምር እንደጻፉለትም ነው የሚያስታውሰው። መጽሐፉን ወደ አፋን ኦሮሞ አስተርጉሞም አሳትሟል። ሁለቱንም ትርጉሞች በነጻ በሶፍት ኮፒ ለህብረተሰቡ ለቅቋል።
ባህር ማዶ
ከውጪ ሰዎችና ጉዳዮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን፤ አሜሪካውያን በጎ ፈቃደኞችን ወይም የሠላም ጓዶቹን ማወቁና አብሯቸው በበጎ ፈቃደኝነት መስራቱ ለውጪ ጉዳዮች በር ከፍቶለታል። በበይነመረብ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም እንዲሁ። በመጀመሪያ ከ2014 እ.ኤ.አ ጀምሮ በበጎ ፈቃድ በሰራበት በደቡብ አፍሪካው የርቀት ትምህርት ተቋም ግብዣ እ.ኤ.አ በ2017 ወደ ጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ በሕጻናትና ልጆች ሥነጽሑፍ ላይ በተካሄደ የድረገጽ አጠቃቀም ሥልጠናና ተያያዥ ጉዳዮችን የያዘ ምክክር ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
በዚህ ድርጅት ውስጥ በልጆች ንባብ ላይ በሚሰራው በአፍሪካን ስቶሪቡክ ኢኒሼቲቭ ውስጥ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ነው። በድረገጽ ኢትዮጵያን ጨምሮ የድፍን አፍሪካን ሕጻናትና ልጆችን በየቋንቋቸው ያስነብባሉ።
ሌላው የጋናው ጉዞው ሲሆን፤ አክራ ሊሄድ የቻለው በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበር የአብያተመጻሕፍት ምዝገባ የኢትዮጵያ በጎፈቃደኛ አስተባባሪ በመሆኑ ነው።
የአክራው ስብሰባ የቤተመጻሕፍት መረጃ ስብሰባው የደረሰበትን ለመገምገም ነበር። እርሱ እንደሚለው፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ አፈጻጸም ዝቅ ያለ ቢሆንም፤ እያደር ባደረጉት ጥረትና በበጎፈቃደኛ የአብያተ መጻሕፍት ሰራተኞች ትጋት የኢትዮጵያ አብያተ መጻሕፍት በድረገጽ ላይ እንዲታዩ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
ወደ ፊት
መዘምርን ለስኬት ያበቃው የተሰማራበት የማህበረሰባዊ ለውጥ አራማጅነትና የጽሑፍ ስራ ነው። ይህም የሆነው ለዓመታት ሳይሰለች አዳዲስ ነገሮችን ስለሞከረ ነው።
ለወደፊቱ በዚሁ ጅምር ሃዲድ መሄድና አእምሮው ያመለከተውን ስራ በመስራት ይቀጥላል። የስራዎቹን ጥራትና ስፋት መጨመር እንዳለበትም ያምናል። የህይወት ሚዛን (ላይፍ ባላንስ የሚባለው) ማስተካከል ላይ መስራት አለብኝ ይላል። እስካሁን በሰራባቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ወደግል ህይወቱም በመመለስ ሰርቶ አገርን የበለጠ መጥቀም ምኞቱ ነው።
የእረፍት ቀን ውሎ
ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የእረፍት ቀን የለኝም የሚለው መዘምር፤ እሁድን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት በማስነበብ እንደሚያሳልፍ ይገልጻል። ምክንያቱ ደግሞ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ እረፍት እሁድ ስለሆነ ነው። ምናልባት እሁድ ባለችው ጥቂት የእረፍት ጊዜ ምሽት ከ12፡00 በኋላ ቤተመጻሕፍት ከሚመጡ አንባቢያንና መምህራን ጓደኞቹ ጋር ማውራት፣ በእግር መዘዋወርና በሆቴል ኢንተርኔት መጠቀም እንደሚያዝናኑት ጠቅሷል። አልፎ አልፎ ጉዞ ሊሄድና አዝማሪ ቤት ጎራ በማለት ሊዝናና እንደሚችልም ተናግሯል።
“አሁን አሁን እየቀረሁ መጣሁ እንጂ ጓደኞቼን እየያዝኩ የአዝማሪ ቤቶች ተወዳጅ ደንበኛ ለመሆን ችዬ ነበር። ” ይላል። አዝማሪ ቤት የሚያዘወትረው ባህላዊ ነገሩና ጨዋታው ስለሚያስደስተው እንዲሁም አንደ ሌሎች ዘመናዊ የምሽት ቤቶች ፀብና ረብሻ እንዲሁም ሞንታርቦም ስለሌለበት ነው።
የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶችን እንደ አቀባበል፣ ሽኝት፣ ልደት፣ ሰርግ የመሳሰሉትን የማስተባበርና ጓደኞቹን የማስተሳሰር ስራ ይሰራል። በተለይ እነዚህ ሁነቶች በእረፍት ቀን ላይ ከገጠሙ ሁነኛ መዝናኛ ተገኘለት ማለት ነው። ችግሩ ደግሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት አልበላም ማለት ስለጀመረ ወዳጆቹ ይሳቀቁበታል። ለወደፊቱ ግን በቀን አንዴ የሚመገበውን በዚያ ማህበራዊ ክስተቱ በሚደረግበት ሰዓት በማድረግ ለማካካስ አስቧል።
መልዕክት
“እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ወይም ማህበራዊ ሁኔታ በፍጥነት መለዋወጥ ቢሆን አንድ ስራ ፈጣሪና አዲስ ነገር የሚሞክር ሰው በቀላሉ ተስፋ ቆርጦ ሊቀመጥ የሚችልበት ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ታይቷል። ስለስራ ብታወራ ወገን እያለቀ፣ አገር እየተሸበረ ሊፈርስ ነው ትባላለህ። ይህም ስሜትን የሚጎዳ ነው። አገር ችግር ውስጥ ብትሆንም ስራና ህይወት አይቆምም። ወቅታዊ ሁኔታው በሰላም ተፈትቶ ሁሉም ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለስ ተስፋ አደርጋለሁ። “ሲል መዘምር በአሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያለውን ሀሳብ ሰጥቷል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013