ኢትዮጵያ ብዙ ፈታኝ የሚባሉ ጊዜያትን አልፋለች። ዛሬ ላይ ግን ከአብራኳ ከወጡ ከሃዲ ልጆቿ እና የእርሷን ማደግ ከማይፈልጉ አገራት ጎን በመሰልፍ ሊያንበረክኳት ቢጥሩም በድል እንደምትወጣው አያጠራጥርም። ከሃዲዎቿን የሚያንበረክኩም ብዙ ልጆች አሏት። እንደሚታወቀው አገሪቱን በተለያየ መንገድ ለማሸበር እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሸባሪውን ህወሓትን ለአንድ ጊዜና እስከወዲያኛው ለመቅበር የሕይወትን መስዋትነትን ከመክፈል ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጁትም ብርቱ ሠዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
በአማራ ክልል በወልድያ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶችም ለዚህ ምስክር ናቸው። ወጣቶቹ የአካባቢው ሠላም በዘላቂነት እንዲቀጥል እየሠሩት ያለው ሥራም አስገራሚ ነው። ወጣቶቹ እየሠሩት ባለው ሥራም ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን ጀምሮ በሌሎች ሠዎችም ራሳቸውን ብሎም ከተማቸውን ከአሸባሪው ቡድን ለማዳን እያደረጉ ያሉት ብርቱ ትግል ምስጋና አስችሯቸዋል።
ወጣቶች ተጋድሏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ በቀረበላቸው መሠረትም ከከተማው የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ ሆነው እየሠሩት ባለው ሥራም አሸባሪውን እምቢኝ ብለው ለከተማቸው የሠላም ዘብ ሆነዋል። በቡድን ሆኖ በመደራጀት ከተማቸውንም ከጠላት እጅ እንዳትወድቅ ደከመን ሰለችን ሳይሉ እየተዋደቁ ይገኛሉ። ወልድያን ለመቆጣጠር የቋመጠው አሸባሪው ቡድን እና የዚህ እኩይ ቡድን ተከፋይ ቅጥረኞችም ‹‹ወልድያን በቁጥጥር ሥር አውለናታል›› በማለት የሐሰት ወሬያቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴያቸው ቢነዙም ከተማይቱ ግን ዛሬም ድረስ በድንቅ ልጆቿ እጅ ሥር ትገኛለች።
አገር በተጨነቀችበት በዚህ ሰዓት ለብዙ ወጣቶች አብነት የሚሆኑት የወልድያ ወጣቶች፤ አሸባሪው ቡድን የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ለመከላከል ሲሉ እነርሱ እንቅልፍ እያጡ የከተማው ነዋሪ በሠላም ውሎ እንዲያድር ብዙ ዋጋም በመክፈል ላይ ናቸው። ወጣቶቹ ሥራቸው ብዙ ነው። በህብረት ሆነው ተደራጅተው የከተማዋን መውጫና መግቢያ በር ይጠብቃሉ። የአሸባሪውን ቡድንም ተላላኪዎቻቸውንም ለጸጥታ ኃይሎች አሳልፈው ይሰጣሉ።
የከተማዋ ከንቲባም ‹‹ሰው በላው ወሮ በላና ሽብርተኛ ቡድኑ በእጅጉ ከሚመኛቸው ከተሞች መካከል አንዷ ወልድያ እንደሆነች ይታወቃል።›› በማለት ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል። ከንቲባው ጨምረውም ‹‹የከተማዋ ወጣቶች ከመቼም ጊዜ በላይ ነቅተውና ተደራጅተው ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ከዞን እና ከተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ጋር በጋራ በመሆን አካባቢያቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።›› በማለት ነበር ወጣቶቹ አርአያነት ያለውን ሥራ እየሠሩ መሆኑን ያመላከቱት። በርካታ ወጣቶቿ ዛሬም እንደትናንቱ ከግንባር እስከ መሐል ከተማና የውስጥ ለውስጥ ሰፈሮች በምድብ ምድብ ሆነው ስምሪት ላይ ናቸው።
ወጣቶቹ ከዚህ በተጓዳኝም በከተማዋ ዋና ዋና የመግቢያ ቁልፍ የሚባሉ በሮችን እንዲሁም ለጥቃት ስጋት ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡትን ተራሮች በንቃት በመጠበቅ አሸባሪውን ጉድጓድ ለመቅበር በሚደረገው ጥረት ደማቅ አሻራቸውን እያሳረፉም ነው።
በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ተላላኪና ሰርጎ ገቦችን በመለየት አሳልፈውም ለፀጥታ ኃይሉ ይሰጣሉ። ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት ያልበለጡ ታዳጊዎች ከሽብርተኛው ቡድን ተልከው በአካባቢው ወጣቶች አማካኝነት በቁጥጥር ሥር በማዋል በሕግ ጥላ ሥር እንዲሆኑም ተደርጓል።
ጁንታው እያደረሰ ያለውን ጉዳት እንዲሁም ለማድረስ ያቀደውን ጥቃት ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን ‹‹መክፈል የሚገባውን መስዋእትነት በመክፈል ሀገርን መታደግ አለብን›› ባይ ናቸው። ዛሬም ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። እንዲህ ያሉ ወጣቶች መኖራቸውም ለብዙዎች ተስፋን ይሰጣል። እንዲህ ያለ ወጣት ሲገኝም አሁን ያጋጠመንን ችግር በፍጥነት አሸንፈን ለመውጣት ብርታት ይሆነናል። አሸባሪ ቡድኑን ለመቅበር ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግም እንደዚህ ያሉት ወጣቶች አቅምም፤ ስንቅም ይሆናሉ።
የወልድያ ወጣቶች መስዋዕትነትን በመክፈል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከተማዋን ከጠላት ለመታደግ ቀን ተሌት እየተዋደቁ ይገኛሉ። የወልድያ ወጣቶች በአንድ ድምፅ ‹‹የተጋረጠብንን ወረራ ለመጋፈጥ በቁርጠኝነት እንሠራለን›› ሲሉም ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
የወልድያ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትም ‹‹ከወልድያ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ የምተገኘዋ ሳንቃ ከተማ ተራራዎቿ ማስተላለፍ የሚችለው ለልማት የሚውል መስኖን እንጅ ጠላት አይሸጋገርበትም ብላለች።›› ሲል መረጃውን አስፍሯል።
ወልድያ ዛሬም ሰላም ናት። በጠላት እጅም አልወደቀችም። ወጣቶቹ ሰሜን ወሎ ለሚገኙ እና ግንባር ላይ እየተዋደቁ ላሉት የጀግናውን መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላትን ግንባር ድረስ በመደገፍ እና ሎጂስትኮችን በማቅረብ ከማናቃቃት አኳያ የሠሩት ገድል መቼም ቢሆን የማይረሳ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው አሸባሪው ማሸበሩን ዛሬም ድረስ በቃኝ አላለም። ይባስ ብሎም በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል የተለያዩ አረመኔዊ ጥቃቶችን ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። ቡድኑ በአፋር ክልል ከ100 በላይ ሕፃናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሠዎች ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ እና አረሜኔነት የተሞላበት ጭፍጨፋም እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ዩኒሴፍ) ካሉ የዕርዳታ ድርጅቶች በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከሆኑት መካከልም እንደ አልጀዚራ ያሉት ሰፊ የሚዲያ ሸፋን ሰጥተውታል።
የአፋር ክልል መንግሥትም አሸባሪው የህወሓት ጁንታ በክልሉ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው የነበሩ በንፁሐን አርብቶ አደሮች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ለሦስት ቀናት የኀዘን ቀን እንዲሆን አውጇል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮም አሸባሪው ቡድን በጋሊኮማ በንፁሐን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ እጅግ ዘግናኝ መሆኑን አንስተዋል። ‹‹ታሪክ የማይረሳው 107 ሕፃናትን፣89 ሴቶችን እና 44 አዛውንቶችን ህይወት የቀጠፈውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ያካሄደው የህወሓት ጁንታ ድንገት በከፈተው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ንፁሐን አርብቶ አደሮች መገደላቸውና መቁሰላቸው እንዲሁም በመጋዘን የነበረ የአስቸኳይ ዕርዳታ ሙሉ በሙሉ ማውደሙ ይታወሳል።›› ሲል የክልሉ መንግሥት መረጃውን ይፋ አድርጓል።
ወጣቶቹ እየሠሩት ያለው መልካም ሥራ የአሸባሪውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ውጥን የሚያደናቅፍ ከመሆኑም በሻገር በሐሰት የሚነዛውን ፕሮፖጋንዳም ያመከነ ነው። የወልዲያ ወጣቶች የአሸባሪ ቡድኑን ቀጣፊነት እና ዋሾነት ደርሰውበታል፤ለደቂቃም ጆሮ አይሰጡትም።
መንግሥትም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የክህደት ኃይል ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰዱ አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያን ከአጥፊዎች ለማዳን ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ልክ እንደ ወልዲያ ወጣቶች አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ለሠላም ዘብ መቆም ይኖርበታል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013