በመንግሥት የሚከናወኑ የልማት ተግባራት መሰረታቸው የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ማንኛውም በመንግሥት ወይም በሌሎች አካላት የሚታቀዱና የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ዜጎችን የሚያፈናቅሉ ከሆኑ የሰዎቹ የኑሮ ሁኔታ ሊሻሻል እና ካሳ ሊሰጣቸው ይገባል።
አካባቢው ሲለማ ሰዎች ተፈናቅለው የመተዳደሪያ ዋስትናቸውን ከማጣት ይልቅ፤ እነርሱም የመልማት መብት አላቸው። በዚህ መነሻ ማንኛውም ልማት ከህብረተሰብ ተጠቃሚነት ውጭ ሊሆን እንደማይገባ ይታወቃል። የህብረተሰብን ተጠቃሚነት፣ ተሳትፎና ፈቃድ ያላገኘ የትኛውም ልማት ስኬታማ እና ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። በከሰም ግድብ ግንባታ ላይ ከልማት ተነሺዎች ጋር ተያይዞ አወዛጋቢ ጉዳይ መኖሩን ፤ በአካባቢው ከልማቱ ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ እና ካሳ ያልተከፈላቸው ሰዎች መኖራቸውን አስመልክቶ መረጃ ያገኘነው ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ነው።
ከረዥም ዘመናት በፊት በእርሻ ስራና በከብት እርባታ ይተዳደሩ እንደነበር የሚነገርላቸው የበርታ ብሄረሰብ አባላት፤ ከቤንሻጉል ጉምዝ ክልል ተነስተው በሰፈራ ፕሮግራም ወደ አፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ ሰፈሩ። እነዚህ ዜጎች ሳቡሬ ላይ ሲኖሩ በድጋሚ ማህበራዊ ትስስራቸውን እና በተገኙበት አካባቢ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመኖር መብታቸው የሚነካ ጉዳይ ያጋጥመናል ብለው አልገመቱም ነበር። ሆኖም እነኚህ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት በሚኖሩበት አካባቢ ደግሞ ሌላ እንዲነሱ የሚያስገድድ አፈናቃይ ዱብዳ ወረደባቸው።
የከሰም ግድብ ፕሮጀክት መታቀዱን ሰሙ። መስማት ብቻ አይደለም፤ ግድቡ እንደሚገነባ ተገልፆ፤ ግድቡ በተሰራበት ቦታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ካሳ እንደሚከፈላቸው ተነገራቸው። በአርሶ አደሮች እንደታመነው ግድቡ በተሰራበት ቦታ ለነበራቸው ይዞታ ብቻ ለ31 አርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሏል። ነገር ግን ውሃ ለተኛበት የእርሻ ቦታ ለእነኚህኞቹ ማለትም ለ31ዱም አርሶ አደሮች ምንም አይነት ካሳ እንዳልተከፈላቸው፤ ከእነርሱም በተጨማሪ ውሃው በተኛበት አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በአጠቃላይ 210 አባወራዎች ተገቢውን ካሳ እንዳላገኙ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የተፈፀመውን በሚመለከት የነገሩን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መርማሪ ሃይሌ ተፈራ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ እነአቶ ቫንዳም እንድሪስ እና መሃመድ አደም በከሰም ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ካሳ የማግኘት መብታቸው በኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተጣሰ መሆኑን ለተቋሙ አመልክተዋል።
‹‹አርሶ አደሮቹ ምትክ ቦታ ሳይሰጠን ተነስተናል።›› ማለታቸውን ተከትሎ፤ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቦታው ድረስ በመሔድ የተነሱ አርሶ አደሮች ከካሳ አከፋፈል፣ ከመልሶ ማቋቋም፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ ከልማት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ መካሄዱን ገልፀውልናል።
የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ
ከግድቡ ጋር በተገናኘ የእርሻ መሬታቸው በውሃ መዋጡን እና የተለያዩ ጉዳቶች መድረሳቸውን፤ እንዲሁም የአንዳንዶቹ አርሶ አደሮች ቦታ ለልማት መዋሉንም በህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ ለማረጋገጥ ተችሏል።
በእርግጥ ምርመራው ሲካሔድ በወቅቱ ካሳ የተከፈላቸው መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል። ነገር ግን ለሁሉም የልማት ተነሺዎች ካሳ አለመከፈሉም ተረጋግጦ። አጠቃላይ በግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺዎች ቁጥር ብዛት 210 (ሁለት መቶ አስር) ነው። የብዙዎቹ አርሶ አደሮች መኖሪያ ቤት ከእርሻ ቦታቸው አቅራቢያ የነበረ በመሆኑ፤ ምንም እንኳ የግድቡ ግንባታ ባይነካቸውም በግድቡ ውሃ መሙላት ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ታውቋል።
እነዚህ አርሶ አደሮች ካሳና ምትክ ቤት መስሪያ ቦታ አልተሰጣቸውም የሚሉት መርማሪ ሃይሌ፤ በዚሁ ሳቡሬ ቀበሌ የግድብ ግንባታን ለማከናወን የግንባታ ግብዓቶችን ለማጓጓዝ እንዲያስችል በሚል ታስቦ የተሰራው ጥርጊያ መንገድ አካባቢ የልማት ተነሺዎቹ ላስቲክና ሸራ ወጥረው በመኖር ላይ እንደሚገኙ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባካሔደው ምርመራ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
እንደመርማሪ ሃይሌ ገለፃ፤ እነዚህ በግድብ ግንባታ አካባቢ የሰፈሩት እና ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ ያቀረቡ ሰዎች የግድቡ አካል የሆነውና ውሃ የተኛበት ቦታ ላይ የቀድሞ ባለይዞታዎች እንደነበሩ በምርመራው ለማወቅ ተችሏል። አቤቱታውን ተከትሎ ተቋሙ ቦታው ድረስ በመሔድ ባካሔደው ምርመራ በወረዳው የተደራጀ መረጃ ያላቸው መሆኑን እና በግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ እና ምንም አይነት ካሳ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው አርሶ አደሮች ብዛት አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ከአርሶ አደሮቹም ሆነ ከወረዳው እንዲሁም ከኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተሰባሰበው መረጃ እንደሚያስረዳው ለሰላሳ አንድ አርሶ አደሮች ብቻ የካሳ ክፍያ የተከፈለ መሆኑን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ግኝት ያመለክታል።
ተቋሙ ምርመራውን ሲያካሂድ የልማት ተነሺዎቹ አርሶ አደሮች የሚኖሩበት አካባቢ መንገዱ የፈራረሰና ለመኪናም ሆነ ለአርሶ አደሮቹ ኑሮ አመቼ አለመሆኑን አይቷል።
የከሰም ግድብ ፕሮጀክትን ቀድሞ የባለቤትነትና የማስተዳደር ስልጣን የነበረው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ባለስልጣን በመሆኑ፤ ለአርሶ አደሮቹ የመልሶ ማቋቋም ስራ አለመሰራቱ፤ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የስራ ዕድል አለመፈጠሩ እና ግድቡ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት በግድብ ግንባታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት ዙሪያ ከአርሶ አደሮቹ ጋር በቂ ውይይት አለመደረጉን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራውን ባካሔደበት ወቅት ያገኘው መረጃ ያመለከተ መሆኑንም መርማሪ ሃይሌ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በቅድሚያ ካሳ ሳይከፈላቸው መሬታቸውን እንዲለቁ መገደዳቸውን እና የወረዳው አስተዳደር ከውሃ መስኖና ኢነርጂም ሆነ ከሌሎች ፌደራል መስሪያ ቤቶች ጋር በአርሶ አደሮቹ የካሳም ሆነ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን የሚያስረዱ ደጋፊ ማስረጃዎች አለመቅረቡን ይህንንም የህዝብ ዕንባ ጠባቂ መርማሪ ሃይሌ ተጠቁሟል።
ስለዚህ ምትክ የእርሻ እና መኖሪያ ቤት የመስሪያ ቦታ እንዲሁም ካሳ እንዲሰጣቸው አቋም በመያዝ ለሚመለከታቸው ተቋማት ምርመራው ላይ በመመርኮዝ የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረባቸውን መርማሪ ሃይሌ ተናግረዋል።
ለአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ የተሰጠው ጥያቄ እና ሃሳብ
እንደመርማሪ ሃይሌ ገለፃ፤ ምርመራው ላይ በመመስረት የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 አንቀጽ 7(2) መሰረት የመፍትሄ ሀሳቡን ለወረዳው አስቀምጧል። ለአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ችግሩን እንዲፈታ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀረበው ቦታው ድረስ በመሔድ በ2011 ዓ.ም ላይ ነበር። የልማት ተነሺ አርሶ አደሮቹ መተዳደሪያቸው ከነበረ ይዞታቸው የተነሱ እና ካሳ ያልተከፈላቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግር ስለተጋለጡ መሰረታዊ ፍላጎታቸው የሚሟላበትን ሁኔታ በመፍጠር የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው የሚል ሃሳብ ተሰጥቷቸዋል።
ለህዝብ ጥቅም በሚል አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ሲነሱ የአርሶ አደሮቹን ሙሉ ዝርዝር መረጃ የመሬት ይዞታቸውን መጠን፣ በመሬቱ ላይ የሰፈረውን ንብረት እና የመሬት አጠቃቀማቸውን እንዲሁም የአካባቢው ዋና ዋና ምርቶች ምርታማነት መጠንና የምርቶቹ የአካባቢው የገበያ ዋጋ በየዓመቱ ወቅታዊ መረጃ በሚገባ ተደራጅቶ ሊያዝ ይገባ እንደነበር በማስታወስ፤ ወረዳው ይህንን መረጃ እንዲያዘጋጅ ተቋሙ ጠይቋል።
አያይዞም የልማት ተነሺ አርሶ አደሮቹን ባለይዞታነታቸውን በማረጋገጥ በካሳ ገማች ኮሚቴ ካሳ ስሌት በመወሰን ካሳ ክፍያ ለሚፈጽመው አካል ለኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃውን አደራጅቶ በመላክ ካሳው እንዲከፈል እንዲያደርግ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለወረዳው አሳስቧል።
የልማት ተነሺ አርሶ አደሮቹ በፕሮጀክቱ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው በመሆኑ፤ የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በግድብ ግንባታ ምክንያት ለተነሱ አርሶ አደሮች በህግ አግባብ ምትክ የእርሻ መሬት ሊሰጣቸው ይገባል። የወረዳው አስተዳደር ምትክ የእርሻ መሬት ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ሲልም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሔ ሃሳብ ሰጥቷል።
የፈንታሌ ወረዳ ምላሽ
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና ለ210ሩም አርሶ አደሮች ባሉበት ሲል ምላሹን በፅሁፍ የገለፀው የፈንታሌ ወረዳ፤ ወረዳው ስር የሚገኘው የከሰም ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ የሆኑት አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ በተመለከተ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በነሐሴ 2011 ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል።
በጽሁፍ በተሰጠው ምላሽ ላይ እንደተገለፀው፤ ስራው የተካሄደው በ1996ዓ.ም ሲሆን፤ አርሶ አደሮቹ ቅሬታ ያቀረቡት ግን በ2010ዓ.ም በመሆኑ ወረዳው በዛን ጊዜ በቦታ የነበሩ አካላትን በሚመለከት ምንም አይነት መረጃ ማግኘት አልቻለም።
ወረዳው ለክልል እና ለዞን በደብዳቤ ቢጠይቁም ምንም መረጃ ካለማግኘት በተጨማሪ፤ ለክልሉ በደብዳቤ ባለሙያ በመላክ ወረዳው ጉዳዩን አስመልክቶ እንዲታገዝ ቢያሳውቁም የተሰራ ስራ አለመኖሩን አመልክቷል።
ወረዳው የህብረተሰቡ ቅሬታ በማገናዘብ በቦታው ድረስ በመሄድ የመስክ ምልከታ ቢያደርግም መሬት የነበረው አካባቢ ሙሉ በሙሉ በውሀ የተሸፈነ በመሆኑ የአርሶ አደሩን ይዞታ እና የእርሻ መሬት የሆነውን እና ያልሆነውን መለየት አልቻለም።
ስራ ከተሰራ ከአሥር ዓመት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ፤ ተጨባጭ መረጃን ባለማግኘታቸው የካሳ ክፍያ ስራ መስራት እንዳልቻሉ ጠቅሰው፤ የካሳ ክፍያ ስራ ለመስራት ከፈንታሌ ወረዳ አቅም በላይ እንደሆነባቸው አመልክተዋል።
በመጨረሻም ከወረዳው ምላሽ በኋላ የፈንታሌ ወረዳን በማነጋገር የመሬት ጉዳይ ወረዳውን የሚመለከት በመሆኑ ለተነሺዎቹ ቦታ መሰጠት እንዳለባቸው መተማመን ላይ መድረሳቸውን መርማሪው ሃይሌ ጠቁመዋል።
ወረዳውም የእርሻ መሬታቸውን ለመተካት የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ከ 2012 በጀት ዓመት የአርሶ አደር ምትክ የእርሻ መሬት እንዲያገኙ ኮሚቴ ተዋቅሮ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ መግለፃቸውን መርማሪው አመልክተዋል።
የቤት መስሪያ ቦታውን በተመለከተ የፈንታሌ ወረዳን በተመሳሳይ መልኩ በማነጋገር ቦታው እንዲሰጣቸው ተብሎ፤ ወረዳው የተሰጠውን ሃሳብ ተቀብሎ በፅሁፍ ምላሽ መስጠቱንም ተናግረዋል።
እንደመርማሪ ሃይሌ ገለፃ፤ ሆኖም ግን ወረዳው የሚሰጠውን የእርሻ መሬት ምትክ ቦታ ለይቶ ለሥራ ምቹ ለማድረግ መንገድ እና አካባቢው ለእርሻ በሚያመች መልኩ በግሬደር መጥረግ ከጀመረ በኋላ የበጀት እጥረት አጋጠመኝ ብሏል። በዚህ ምክንያት ለአርሶ አደሮቹ እስከ አሁንም ድረስ ቦታውን እንዳላስረከቧቸው ማወቅ ተችሏል። ቤት መስሪያ ቦታ ጭራሽ ያልተሰጣቸው ሲሆን፤ የእርሻ መሬት ለመስጠት በግሬደር በመቆፈር ለእርሻ ምቹ ለማድረግ በ2012 መስራት ቢጀምሩም ቦታው ሳይሰጥ ሥራው መቆሙን አቤት ባዮቹ ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጠቁመዋል።
ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተሰጠ የመፍትሄ ሀሳብ
ምርመራውን መሰረት አደርጎ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሄ ሀሳብ ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጠቁሟል። የግድብ ግንባታውን በባለቤትነት ያስገነባውና ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባም ሲያስተዳድር በመቆየቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲገነባ እና በአማካሪነት ሲሰራ ከነበረው አካላት ጋር በመነጋገር እና የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ፤ ለወረዳው አስተዳደር የቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በመመስረት ስንት ሄክታር መሬት በልማቱ ምክንያት እንደተወሰደባቸው የሚጠቅሱ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ብዛት በመለየት፤ ከኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በህጉ መሰረት ለአርሶ አደሮቹ በቅንጅት በመስራት በቀረበው የካሳ ጥያቄ ላይ ተመስርቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ሲል የመፍትሔ ሃሳብ ሰጥቷል።
ፕሮጀክቱ በባለቤትነት ለኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ከመተላለፉ በፊት ለ 31 አርሶ አደሮች የቀድሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግድብ ግንባታ ለተሰራበት የእርሻ ቦታ ብቻ ካሳ ክፍያ የፈጸመ መሆኑን በማስታወስ፤ ውሃ ለተኛበት አካባቢ የእርሻ ቦታቸው በውሃ ለተዋጠባቸው ለሰላሳ አንዱ አርሶ አደሮች በተጨማሪ ምንም ካሳ ላልተከፈላቸው ለቀሪዎቹ ለአንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ አርሶ አደሮች፤ በአጠቃላይ ለሁለት መቶ አስር የልማት ተነሺ አርሶአደሮች የካሳ ጥያቄን በሚመለከት ከኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመወያየት ለዜጎች በህገመንግስቱና በሌሎች የህግ ማዕቀፎች መሰረት ካሳ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ ሲል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመልክተዋል።
ለኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የተሰጠ የመፍትሔ ሃሳብ
ምርመራውን መሰረት አደርጎ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሄ ሀሳብ የሰጠው ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ለኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንም ጭምር ነው። የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የከሰም ግድብ ፕሮጀክት ባለቤትነቱንም ሆነ የማስተዳደር ስልጣን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጅ የተሰጠው በመሆኑ፤ የልማት ተነሺዎቹን የካሳ ይከፈልን ጥያቄን ተቀብሎ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በህግ አግባብ በሚቀርበው መረጃ መሰረት የካሳ ክፍያው ተፈጻሚ እንዲሆን ተብሏል።
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ለኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በነሐሴ 2011 ዓ.ም የመፍትሔ ሃሳቡን ሲልክ፤ የከሰም ቀበና ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ 01 ተነሺ አርሶ ኣደሮችን በሚመለከት በከሰም ቀበና ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ አለመፈጸምን በሚመለከት የተደረገው የምርመራ ውጤት ተያይዞ ለተቋማቱ ተሰጥቷል። በተጨማሪ የፕሮጀክቱን ዘላቂነት ለማሳካት ያስችል ዘንድ ተቋማቱ በቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ መሰረት ተገቢውን የእርምትና ማስተካከያ እርምጃ በአስቸኳይ ሊወሰዱ እንደሚገባ እና ውጤቱን በሚመለከት ምላሻቸውን በ 45 ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲያሳውቁም ተብለዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምላሽ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢፌዴሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምላሽ ሰጥቷል። በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ 01 ቀበሌ በከሰም ቀበና ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን አስመልክቶ ነሐሴ 3 ቀን 2011 በቁጥር እንባ/ዘ-አበ/15714 ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ መፃፉን አስታውሰው፤ ተቋሙ የደረሰውን የካሳ ክፍያ አለመፈጸም ጥቆማን መነሻ በማድረግ ምርመራ አካሂዶ ዘጠኝ ገጽ የውጤትና የመፍትሄ ሃሳብ በማያያዝ በመፍትሄ ሃሳቡ መሰረት በመፈፀም ውጤቱን በ 45 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ መግለፁን አስታውሰዋል።
በዚህም መሰረት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ደብዳቤ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ስድስት አባላትን የያዘ ኮሚቴ በማቋቋም በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ያሰባሰበውን መረጃ መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ያለውን ሃሳብ አቅርቧል።
ከከሰም መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የልማት ተነሺዎችን የካሳ ጥያቄዎችን ያስተናግድ የነበረው ከአካባቢው የወረዳ አስተዳደር እና የቀበሌ አመራር ጋር ነበር። በወቅቱ የማማከር ስራ ይሰራ የነበረው የፌዴራል የግንባታ ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የምርት ካሳ የሚገባቸው ባለይዞታዎች የይዞታ ካርታ እና መጠን በሄክታር የምርት ግመታ እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ሲቀርቡና ክፍያውም ይፈጽም የነበረው በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ውክልና አማካኝነት ነበር። በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በወቅቱ የማማከር ስራ ይሰራ ከነበረው ከፌዴራል የግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን በደብዳቤ ስለጉዳዩ መረጃ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል።
በተፃፈው ደብዳቤ መሰረት ኮርፖሬሽኑ በመስክ ቢሮ ባለሞያዎቹ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው ካሳ የተከፈላቸው በውሃ መተኛ ቦታ (Reservoir Area ) ውስጥ ይኖሩ የነበሩት፤ የበርታ ብሔረሰብ አባላት በቁጥር ሰላሳ አንድ ብቻ እንደነበሩ እና በተወሰደው ልኬት የቦታው ስፋት 21 ነጥብ 08 ሄክታር መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተሠጠው ውክልና የካሳ ክፍያውን ይፈጽም ለነበረው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ስለጉዳዩ መረጃ እንዲሰጥ በደብዳቤ ጠይቋል። በጥያቄው መሰረት ቢሮው የካሳ ክፍያ ይፈጽም የነበረው የምርት ካሳ ክፍያ ለመክፈል የሚያስችልና በልማት ተነሺ ስለመሆናቸው የሚገልጽ ከአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር እና ከፌዴራል የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን የይዞታ ካርታና ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎች ለክልሉ የካሳ ኮሚቴ ሲቀርቡለት እንደነበር በመግለጽ፤ በዚህ መሰረት
ማስረጃዎች ተሟልተው ክፍያ የተፈጸመላቸው ሰለሳ አንድ የበርታ ማህበረሰብ አባላት መሆናቸውን ጠቅሷል። የምርት ካሳ አልተከፈላቸውም በሚል ለቀረቡት አርሶ አደሮች በወቅቱ የይዞታ ካርታም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎች አለመቅረባቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ መግለፁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አብራርቷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ላይ በራሱ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረትም ስለጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተሰባሰበው መረጃ መሰረት ቀደም ሲልም ሆነ በአሁኑ ወቅት የካሳ ይገባኛል ጥያቄ ላቀረቡት ሁለት መቶ አስር አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ እንዲከናወን ሊያደርግ የሚያስችል ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት እንደሌለ ማረጋገጡን ጠቅሶ፤ ሙሉ የማጣራት ሂደቱን ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ልኳል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምላሽ
ኮርፕሬሽኑ ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የከሰም ቀበና ግድብና ግንባታ ፕሮጀክት ተነሽ አርሶደሮች ጉዳይን በሚመለከት ነሐሴ 03 ቀን 2011 ዓ.ም ለተጻፈ ደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል። ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ 01 ቀበሌ በከሰም ቀበና ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ አለመፈጸምን በተመለከተ የተካሄደው የምርመራ ውጤት እንደደረሳቸው ጠቅሰው፤ በተቋሙ የቀረበውን የምርመራ ውጤትና የመፍትሄ ሃሳብ በዝርዝር ማየታቸውን አመልክተዋል።
ተቋሙ የሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ኮርፖሬሽኑ የግድቡን ባለቤትነትም ሆነ የማስተዳደር ስልጣን በ2008 ዓ.ም በአዋጅ የተሰጣችሁ በመሆኑ የልማት ተነሺዎቹን የካሳ ይከፈለን ጥያቄም ተቀብላችሁ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በህግ አግባብ በሚቀርብለት መረጃ መሰረት የካሳ ክፍያ ተፈጻሚ እንዲሆን እንድታደርጉ የሚል መሆኑን መገንዘባቸውን አብራርተዋል።
ጉዳዩን በሚመለከት ማብራሪያ ሲሰጡ፤ በኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 366/2008 አንቀጽ 5(3) በግልጽ ተደንግጎ እንደሚገኘው ኮርፖሬሽኑ ግድቦችን በባለቤትነት ተረክቦ የሚያስተዳድረው መጀመሪያ በፌዴራል መንግስት በጀት ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው የካሳ ክፍያ ጉዳዮችን ጨምሮ ማንኛውም ለግንባታ የሚያስፈልገውን ወጭ የሚመድበው ኮርፖሬሽኑ ሳይሆን የሚመለከተው ባለ በጀት የመንግሥት መስሪያ ቤት ሆኖ ግንባታው ሲጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ ተረክቦ የማስተዳደር ሥራውን ያከናውናል ማለት ነው። ስለሆነም የካሳ ክፍያ ጥያቄ ለኮርፖሬሽኑ ሊቀርብ የሚችልበት የሕግ አግባብ የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በከሰም ቀበና ግድብና ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት የተነሱት የአፋር ክልል የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ 01 ቀበሌ ነዋሪዎችን በሚመለከት፤ ወረዳው የጀመረውን ሥራ ያቆመበትን ምክንያት በመጠየቅ እና ክልሉም ሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የደረሱበትን ውሳኔ ጠይቀን በቀጣይ ምላሻቸውን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013