የተለያዩ ሀገራት በወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ ሲፈተኑ ኢትዮጵያ ግን ከሁለተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየወጣች ነበር። የእፎይታ ገዜ አግኝታ ነበር። ነገር ግን ሦስተኛው የኮቪድ ዝርያ ለመታየቱ፤ በየዕለቱም የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረና ከሦስት እጥፍ በላይ እያደገ መምጣቱን ሦስተኛው ማእበል ስለመነሳቱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ በኢትዮዽያ ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከሰቱ ማሳያ መሆኑን የኢትዮዽያ የህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በተለለያዩ ጊዜያት የተከሰቱት የቫይረሱ ወረርሸኞች ወጎኖቻቸንን አሳጥቶን አልፏል፤ አሁንም ያልተገባ ዋጋ እንዳያስከፍለን ከወዲሁ ልንከላከለው ይገባል በማለትም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የሦስተኛው ዝርያ ወረርሽኝ ተከስቷል የሚል ማረጋገጫ መጠበቅ አይገባም፤ ከዚህ በፊት ሌሎች የአለማችን ሀገሮች ቀድመው እኛ ተከትለናል። ዝርያው በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከታየ ድረስ በኢትዮጵያም የማይገባበት ምክንያት አይኖርም። ስለሆነም ሕብረተሰቡ ከመቼውም በላይ ጥንቃቄ ማድረጉን እንዲቀጥል፤ በማስገደድ ሳይሆን ሰው ከዚህ ቀደም ያየውን እውነት ወደ ህይወቱ እንዳይመጣ ለማድረግ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ አለበት። እያንዳንዱ ወረርሽኝ ሲከሰት የጉዳት መጠኑን በሀይል ጨምሮ የሚከሰት መሆኑን ከዚህ ቀደም የተከሰቱት ወረርሽኞች ማሳያ ናቸው የሚሉት ዶክተር ተግባር ባለፉት ሁለት ወራት ናሙና ከሰጡ 100 ግለሰቦች ከ1 እስከ 2 ግለሰቦች የመያዝ ምጣኔ የነበረ ሲሆን፤ ካለፉት ሦሰት ሳምንታት በኋላ ግን በቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ ጨምሮ ከ7 እስከ 9 ግለሰቦች የመያዝ ምጣኔ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል።
በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ህሙማን ከሦስት ሳምንት በፊት በአማካይ 124 ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን በእጥፍ በመጨመር ወደ 300 ከማደጉም በላይ በየእለቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ወደ ስምንት ሰው እየሆነ ነው፤ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ካበቃ በኋላ በተወሰነ መልኩ በማህበረሰቡ መዘናጋቶች እንዲሁም የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ሦስተኛው ዙር ሊከሰት መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እንዲከበሩና ማስክ ማድረግ፣ የእጅ ንፅህና መጠበቅ እና ርቀትን በመጠበቅ፤ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባትን በመከተብ ቫይረሱን መከላከል ይገባዋል።
ሦስተኛው ወረርሽኝ ለመከሰቱ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ፅኑ ህሙማን ክፍል በኮቪድ19 ታማሚዎች በመሙላቱ የተነሳ ወደ መቶ የሚሆኑ ኦክስጂን የሚፈልጉ ተካሚዎች በሆስፒታል ውስጥ መተኛታቸውንና ከእነዚህ መካከል 25 የሚሆኑት ደግሞ በከፍተኛ ክትትል ሥር መሆናቸው ማሳያ ነው።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው እንደተናገሩት አንድ አራተኛ የሚሆነው የፅኑ ህሙማን ክፍል በማሽን የሚተነፍሱ ታካሚዎች አሉበት። ሆስፒታሉ ካለው የማከም አቅም በኦክስጂን እርዳታ መተንፈስ የሚያስፈልጋቸውን መቀበል ቢችልም የጽኑ ህሙማን ክፍሉ ግን ሞልቷል። ዶክተር ያሬድ ሆስፒታሉ እንዳሉት ሆስፒታሉ ከ600 በላይ አልጋዎች አሉት። ካለፈው ሦስት ሳምንታት ጀምሮ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ የፅኑ ህመም ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎችን አለመቀበል መቻል ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ተናግረዋል።
ሰኔና ግንቦት ላይ የመቀነሰ ሁኔታ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለያዩ ሀገራት እየተከሰተ ያለው በዴልታ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣውን ሦስተኛ ወረርሽኝ እየተጠባበቅን የነበርንበት በዚህ ወቅት የታካሚዎች ቁጥር መጨመሩ የማእበሉን የመከሰት ማሳያ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ቀድሞ የሚያውቀውን ኮቪድን እንዴት መከላከል እንዳለበት በተግባር በመግለፅ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ጉዳት ራሱን መጠበቅ አለበት በማለትም ዶክተር ያሬድ አሳስበዋል።
የዴልታ ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አቅሙም ሆነ በገዳይነቱ ከከዚህ ቀደሞቹ የላቀ እንደሆነ የሚናገሩት የጤና ባለሙያዎቹ ማህበረሰቡ መዘናጋቱን ወደ ጎን በመተው ራሱን ከዚህ ገዳይ ቫይረስ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
ኮሮና ቫይረስ ሀገራችን ከገባ ሁለት ዓመታትን ከማስቆጠሩም በላይ በሁለት የወረርሽኝ ማዕበሎች መትቶን በርካቶችን የህይወት መስዋዕትነት ያሰከፈለ ሲሆን፤ አሁን ሦሰተኛው መጥቶ ሣይጨርሰን ተገቢውን ጥንቃቄ እናድርግ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም