የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በፍፃሜው ዋዜማ ከሚጠብቃቸው አጓጊ ውድድሮች አንዱ በሆነው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍፃሜ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያ በአትሌት ለተሰንበት ግደይ አማካይነት አስመዝግባለች። ከወር በፊት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን አርባ ስምንት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተነጣጠቁት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበትና ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን እንደተጠበቀው ለኦሊምፒክ ክብር ተፋልመዋል።
ለተሰንበት የርቀቱን ክብረወሰን ሁለት ቀን ሳይሞላው ከሲፈን እጅ የወሰደች አትሌት እንደመሆኗ የኦሊምፒክ የአሸናፊነቱ ግምትም ወደእሷ አመዝኖ ነበር። ያም ሆኖ በውድድሩ ከሁለቱ አትሌቶች በተጨማሪ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የባህሬን አትሌት ቃልኪዳን ገዛኸኝ ያልተጠበቀች የሜዳሊያ ተፎካካሪ ሆና ታይታለች።
ለተሰንበት በርቀቱ የክብረወሰን ባለቤት ከመሆኗ በተጨማሪ በሌሎች ርቀቶች ኦሊምፒኩ ላይ ሣትወዳደር ጉልበት ቆጥባ መቆየቷና ያላት ትልቅ አቅም ለድል ያበቃታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ በውድድሩ የተሣተፉት ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንድም እገዛ ሣያደርጉላት በመቅረታቸውና ለተሰንበት ከሃያ አምስቱ ዙሮች አስራ ስምንቱን ለብቻዋ በመምራት ጉልበት በመጨረሷ ወርቁን ሣታጠልቅ ብትቀርም ለሀገሯ እንደ ወርቅ የሚቆጠር የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብላ የተጠበቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ ገና በሁለተኛው ዙር ውድድሯን አቋርጣ የወጣችበት ያልታሰበ አጋጣሚ እንዲሁም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፀሐይ ገመቹ ገና ከመጀመሪያው ወደ ኋላ መቅረት ለተሰንበትን ውድድሩን ካከረሩት ኬንያውያን ጋር በጊዜ ወደ ፊት እንድትወጣ አስገድዷታል።
ከአምስተኛው ዙር ጀምሮ እስከ መጨረሻ በመምራትና ዙሮችን በማክረር ለተሰንበት ጠንካራዎቹን ኬንያውያን ከውድድር ውጪ ማድረግ ብትችልም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ሲፈንና ቃልኪዳንን መቁረጥ አላስቻላትም። እንዲያውም ጉልበቷን ከመጨረስ በተጨማሪ ለሁለቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስራ ያቀለለ ነበር። ይህም መጨረሻ ላይ ዋጋ አስከፍሏት ማጥለቅ የምትችለውን ወርቅ ለሲፈን አሣልፋ እንድትሰጥ አስገድዷታል።
የ5 ሺህ ሜትርን ወርቅ ያጠለቀችው ሲፈን በ1500 ሜትርም ነሐስ ያጠለቀች ሲሆን፣ የለተሰንበትን ክፍተትና የራሷን የአጨራረስ ድንቅ ብቃት ተጠቅማ 29:55:32 በሆነ ሰዓት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ትልቅ ታሪክ ሠርታለች።
የምትችለውን ሁሉ ጥረት አድርጋ ወርቁን ለመውሰድ ትልቅ ተጋድሎ ያደረገችው ለተሰንበት ወርቁ ከእጇ እንደወጣ ለብር ሜዳሊያው ያደረገችው ጥረትም በቂ አልነበረም። በዚህም ቃልኪዳን ገዛኸኝ 29:56:18 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያውን ለባህሬን ማስመዝገብ ችላለች። ለተሰንበት ያ ሁሉ ጥረቷ የሚያስመሠግናት ቢሆንም 30:01:72 በሆነ ሰዓት ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ባዶ እጇን አልተመለሠችም። በኦሊምፒክ መድረክ ለራሷ የመጀመሪያ የነሐስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛውን የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።
ለተሰንበት በርቀቱ ትልቅ አቅም ያላት አትሌት እንደመሆኗ በውድድሩ ላይ የተጠቀመችው ታክቲክ ከድል አርቋታል። ባለፈው የ2019 ዶሃ የዓለም ቻምፒዮናም ለተሰንበት በርቀቱ ከሲፈን ጋር ተመሣሣይ ታክቲክ ተጠቅማ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ስትችል ብር ማጥለቋ ይታወሣል።
በትናንቱ ውድድርም ለተሰንበት ገና ከጅምሩ ዙሩን በማክረር ባትጠመድና ጉልበት ለመቆጠብ ብትጥር ወርቁን ማጥለቅ የምትችልበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር። በርካታ ዙሮችን መምራቷ ካልቀረም በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ያዳበረችው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ያላትን ሲፈንን ውድድሩ አራት መቶ ሜትሮች እስኪቀሩት ድረስ ማስከተሏ ዋጋ አስከፍሏታል።
ምናልባትም ውድድሩ ስምንት መቶ ሜትሮች ሲቀሩት ለተሰንበት መውጣት ብትችል ድሉን የግሏ የምታደርግበት ዕድል ይኖር ነበረ። ይህም ባለመሆኑ አቅሙ እያላት ወርቁን ባለማጥለቋ ለተሰንበት ሥሜቷ ተነክቶ ከውድድሩ በኋላ ታይታለች። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ በተለያዩ ርቀቶች ያሰበቻቸው ሜዳሊያዎችን ማሣካት ባልቻለችበት ሁኔታ የለተሰንበት የነሐስ ሜዳሊያ ወጣትና ነገ ሌላ ድሎችን የምታስመዘግብ ተሥፋ ያላት አትሌት እንደመሆኗ ያስመሰግናታል ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ በርካታ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ የሚችሉ በርካታ ድንቅ…ድንቅ አቋም ያላቸው አትሌቶችን ማሣተፍ ብትችልም በተለያዩ ስህተቶች ማሣካት ሣትችል ቀርታለች። በዚህም ሰለሞን ባረጋ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ መሠናክል የብር፣ ጉዳፍ ፀጋይ በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ እንዲሁም ለተሰንበት ያስመዘገበችው የ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ ኢትዮጵያ የቶኪዮ ቆይታዋን እያገባደደች ትገኛለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013