– በአዲስ አበባ በኮንስትራክሽን ጥንቃቄ ጉድለት 3ሺ200 ሰዎች ሞተዋል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት 10 ዓመታት በሜጋ ፕሮጀክቶች መዘግየት መንግስት ለ43 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ መዳረጉ ተገለፀ። በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በኮንስትራክሽን ሥፍራዎች ጥንቃቄ ጉድለት በሦስት ዓመታት ውስጥ ከ3ሺ200 ሰዎች በላይ ሞተዋል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አይሻ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መንግስት በሚያስተዳድራቸው አንድ ሺ ፕሮጀክቶች መዘግ የት የተነሳ 43 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አውጥቷል።
ለአብነትም በቅርቡ በተጠናቀቁ ሦስት የስኳር ፕሮጀክቶች የ9ነጥብ6 ቢሊዮን ብር፤ እንዲሁም በመነሻው 700 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለት የነበረው መገጭ ግድብ አምስት ቢሊዮን ብር ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን አስታውሰዋል። እንደ ዶክተር አርጋው ገለፃ፤ የግዥ ሥርዓት አለመዘመን፤ የዲዛይን መቀያየር፣ የፕሮጀክት ክትትልና ሪፖርት አያያዝ ደካማ መሆን፣ ሌብነት፣ አዋጭነት ጥናት በተገቢው መንገድ አለመካሄዱ፣ የአማካሪዎች፣ ተቋራጮች፣ ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶችና አሰሪ ደርጅቶች የተቀናጀ አሠራር አለመከተል መንግስትን ለወጪ መዳረጉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ግንባታዎች ሲከናወኑ 80 በመቶ መስክ ላይ ከፍተኛ ድካም የሚሰራ ሲሆን፤ 20 ከመቶ ብቻ በፋብሪካ ተጠናቆ የሚቀርብ በመሆኑ በፍጥነትና በጥራት ለመስራት ከፍተኛ ጊዜ፣ መዋዕለ ንዋይና ጉልበት ይጠይቃል። ይህም ለብክነቱ አንዱ መንስኤ ነው። በውጭው ዓለም ደግሞ 90 ከመቶ የኮንስትራክሽን ሥራ በፋብሪካ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ 10 ከመቶ በመስክ የሚሠራ ነው። በእኛ ሃገር ግን ይህ ባለመሆኑ ዘርፉ ከበርካታ ችግሮች የፀዳ እንዳይሆን አስችሎታል።
ዶክተር አርጋው እንዳሉት፤ ከፕሮጀክቶች መዘግየት በተጨማሪም በኮንስትራክሽን ስፍራዎች ጥንቃቄ ጉድለት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት በተገኘ መረጃ፤ 3ሺ200 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በአፈር መደርመስ፣ ከጥንቃቄ ጉድለትና ከግንባታ ላይ መውደቅ ዋንኞቹ የአደጋው መንስኤዎች ሲሆኑ፤ መረጃዎች በአግባቡ ቢያዙና አገራዊ አሃዙ በሥርዓት ቢጠናቀር ጉዳቱ ከዚህ በእጅጉ የገዘፈ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። በኮንስትራክሽ ዘርፍ ያለውን ችግር ለማቃለልም ኢንስቲትዩቱ ከአዲግራት፣ አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሐዋሳ ዩኒቨርሲዎች እና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በ38 ርዕሰ ጉዳች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
የባለሙያዎችን ክህሎት ለማሳደግም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 8ሺ500 በላይ ባለሙያዎችን ማሰልጠን ተችሏል። የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በአዋጅ 2289/2005 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው፤ በቀጣይም ችግሮች እንደሚቃለሉም ዶክተር አራጋው አረጋግጠዋል። የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በግንባታ ሥፍራዎች ከሚከሰት የጥንቃቄ ጉድለት በየቀኑ ስድስት ሺህ ሰዎች ሲሞቱ፤ ከፍተኛ የሆነ የሃብት ብክነትም ይስተዋላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር