በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ለሚሰጡት የትምህርት አገልግሎት የሚያስከፈሉት ክፍያ ወጥነት የሌለው እንደሆነ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለምዝገባ እና ለመደበኛ ክፍያ የሚያስከፍሉት ክፍያ እየጨመረ በመምጣቱ ብዙ ወላጆችን እያሳሰበ ይገኛል። ትምህርት ቤቶቹ በየዓመቱ በምዝገባ እና በመደበኛ ክፍያ የሚያደርጉት ጭማሪ የወላጅ የመክፈል አቅምን ያላገናዘበ በመሆኑ በግል ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆችን በእጅጉ ምሬት ውስጥ እየከተተ ይገኛል።
በተለይ ከ2013 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የትምህርት ቤቶቹ ክፍያ ጭማሪ ከወላጆች የመክፈል አቅም በላይ እየሆነ ይገኛል። ኮቪድ ወረርሽኝ ካመጣው ተፅጽኖ ጋር ተያይዞ ጭማሪው ከወላጆች የመክፈል አቅም ጋር የማይጣጣም በመሆኑ በርካታ ወላጆች ለችግር እየዳረገ ነው።የባሰ አታምጣ እንዲሉት አይነት ሆኖ ዘንድሮው ደግሞ ከዓምናው ባስ ያለ ሆኗል። ዘንድሮም እየናረ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጫና ጋር ተደማምሮ ትምህርት ቤቶቹ እያደረጉት ያለው የምዝገባ እና የመደበኛ ክፍያ ጭማሪ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያ የመክፈል አቅም እየፈተነ ነው።በዚህ የተነሳ በርካታ ወላጆች መቸገራቸው ይታወቃል።
ይህንን ጉዳይ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ስልክ ደውለው ያሳወቁን ወላጆች እንደሚሉት፤ መደበኛ ክፍያ ላይ እስከ 1ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ የጨመረ ትምህርት ቤት ያለ መሆኑን ይናገራሉ።የአንድ ትምህርት ቤት የመመዝገቢያም ሆነ ወርሐዊ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ ያለበት እስከ ስንት ብር ድረስ ነው? ይህንንስ የሚመለከት የተቀመጠ ህግ አለ ወይ ? ይህንን የሚከታተለው አካል ከወላጆች የመክፈል አቅም በላይ የሆነ ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች ለምን መቆጣጠር አቃተው? የሚሉትን ጥያቄዎች ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ ወንደሰን እና አቶ ተካልኝ ገመቹ ናቸው።
ለዝግጅት ክፍላችን ጠይቁልኝ ሲሉ ያደረሱንን ጠያቂዎቻችንን እያመሰገንን፤ ጉዳዩን ይዘን ወደ ሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት እና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለስልጣን አቅርበናል ። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ የሰጡንን አጠር ያለ ምላሽ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ እንደሚሉት፤ ባለስልጣኑ በትምህርት ቤቶች ክፍያ ዙሪያ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቷል።ከዚህ ቀደም በጣም ሲያማርሩ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ለምዝገባ የሚያስከፍሉት ክፍያ ሁለት ሺህ ፣ ሦስት ሺህ እና ከዚያ በላይ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ግን መመዝገቢያ ክፍያ ከወርሐዊ ክፍያ ዋጋ ጭማሪ እስከ 25 በመቶ መሆን እንዳለበት ውሳኔ መወሰኑን ገልጸዋል።መደበኛ ክፍያ ግን በወላጆች እና በትምህርት ቤቱ ስምምነት እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ወላጅና የትምህርት ቤት ስምምነት ከዚህ በፊት እንደነበረው የግብር ይውጣ ሥራ ሳይሆን በደንብ ቁጭ ብለው ተወይያተው ተስማምተው የሚወስኑት ነው።
እርግጥ ነው ወላጆችም ሆኑ ተቋማቱ ጋር ችግር አለ የሚሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ የኑሮ ውድነቱ በጣም ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወላጆች የመክፈል አቅም የላቸውም።ተቋማቱም ቢሆኑ በኮቪድ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ውስጥ ገብተዋል።አምና ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ብዙ ተማሪ አልነበረም፤ እንዲሁም ብዙ ተማሪ አልከፈለም ይላሉ። ስለሆነም ሁለቱንም ሚዛናዊ ያደረገ ጭማሪ እንዲደረግ በማለት ተቋማት እንዲስማሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ በዚህም አንድ ሺ የሚሆኑት ተቋማት ሚዛናዊ ጭማሪን ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን፤ 40 ያህሉ ተቋማት አልተስማሙም ብለዋል።እነዚህ ያልተስማሙት ተቋማት ምዝገባ አልጀመሩም ፤ ምዝገባ እንዳያካሄዱም ታግደዋል። በድጋሚ ጉዳያቸውን እንዲያዩት እየተደረገ ነው ፤ ሆኖም ግን ጉዳዩ እንዳልተቋጭም አመልክተዋል።
በመደበኛ ክፍያ ያልተስማሙ ወላጆችና ተቋማት በእነሱ ደረጃ ጉዳያቸውን መፍታት ካቃታቸው፤ በወረዳ እንዲታይ፣ ከወረዳ የሚያልፍ ከሆነ ክፍለከተማ የሚታይ ሲሆን፤ ከእነዚህ ሁሉ አቅም በላይ ከሆነ ግን ባለስልጣኑ የሁለቱንም አካላት ጉዳይ አይቶ ሊፈታ የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የወላጆች ችግር በጣም ሰፊ ነው፤ የመክፈል አቅም ውስን ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፤ ተቋማት ደግሞ ከመምህራን ደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች እንዳለ ይጠቅሳሉ። ተቋማቱ የሚያነሱት ጉዳይ ለመንግስት ትምህርት ቤት መምህራን የቤት አበል ተጨምሯል፤ ለእነዚህም መምህራን አበል መፈቀድ ወይም ደሞዝ መጨመር መደረግ አለበት የሚሉት ናቸው።ይሁን እንጂ ጭማሪው ይህንን ታሳቢ ያደረገ አይደለም።ጭማሪው ምክንያታዊ ሆኖ የወላጆችን አቅም እና የተቋማቱን ችግር ያገናዘበ እንዲሆን ግን ወላጆችና ተቋማት እንዲመካከሩ ተደርጓል ።
ባለስልጣኑ የሁለቱንም ጉዳይ እያየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማቱም መምህራን ለማቆየት የተሻለ ደመወዝ መክፈል አለባቸው።መምህሩም የተሻለ ደመወዝ እንዲከፈለው ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ፤ ወላጅም ደግሞ የመክፈል አቅሙን በማይነካ መልኩ ተወያይተው የሚወስኑበት ሁኔታ መቀመጥ እንዳለበት ያስረዳሉ ።
ባለስልጣኑ ይህንን በማያደርጉ ተቋማት ላይ ምን አይነት ጫና ማድረግ ይችላል? ብለን የጠየቅናቸው ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጇ ባለስልጣኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 1987 ዓ.ም ባወጣው ደንብ መሠረት የሚሰራ ሲሆን፤ አላስፈላጊ ጫና እንዳይኖር ወላጅና ተቋማቱ እንዲነጋገሩ እና እንዲወያዩ ያደርጋል ። ባይስማሙስ ምን ይደረጋል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ለዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወላጆችና ተቋማት ባይስማሙ ለማስማማት የሚቻልበትን ከወረዳ ጀምሮ እስከ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚደርሰውን የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን አብራርተዋል፡፡
ምክትል ዋና ሥራአስኪያጇ እንደሚሉት አሁንም ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ተወካዮች ጋር መነጋገር አለባቸው። በተለይ ወላጆች ሳይስማሙ የተበተኑባቸው 40 ተቋማት በድጋሚ ጉዳዩ ላይ መነጋገር ይጠበቅባቸዋል። በወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት (ወተመህ) ሚዛናዊ ሆኖ በሁለቱም በኩል ያለውን ችግር ማየት አለባቸው። ወተመህ ለማንም ሳያዳላ በተፈጠረው የአሠራር ሥርዓት መሠረት መጨመር ያለበት፤ በመጨመር መቀነስ ያለበት በመቀነስ ሚዛናዊ ሆኖ ይወስናል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።በዚህ ሁኔታ ከተሰማሙ ጥሩ ነው፤ ካልተስማሙ ደግሞ ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ይህንን ጉዳይ ሊያጣራ የሚችል ኮሚቴ ተዋቅሮ በእነሱ እንዲታይ እንደሚደረግ እና እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በእነሱ ደረጃም የማይፈታ ከሆነ በባለስልጣኑ መስሪያ ቤቱ የተቋቋመ ቡድን ጉዳዩን የሚያየው ይሆናል ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃልለዋል፡፡
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013