አራተኛው የኢትዮ-ኤርትራ የሚኒስትሮች የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡ መድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ በተገኙበት በትናንትናው ዕለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው የተካሄደው።
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል ከወራቶች በፊት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ወደ ስራ ለማስገባት ተለይተው በተቀመጡ አጀንዳዎች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
በዋናነትም በታህሳ ወር 2011 ዓ.ም በአስመራ በተካሄደው 3ኛው ዙር የምክክር መድረክ ወቅት መግባባት ላይ የተደረሰባችው ጉዳዮች ያሉበትን የአፈፃፀም ደረጃ ገምግመዋል።
ከዚህ ባለፈም በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች መተላለፉቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ህጋዊ ማዕቀፍ ለማበጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል።
የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ለመመስረት የሚያስችል የሰነድ ልውውጥም በወቅቱ ተደርጓል።
የወደብ አጠቃቀም፣ የንግድና ትራንስፖርት እንዲሁም ከድንበር ንግድና ከጉምሩክ አሰራር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው በሚቻልበት ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።
የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተላከ መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አድርሰዋል ሲል ፋና ብሮድ ካስት ዘግቧል።