የእናት ጡት ማባበያ
የእናት ድብሻ መሸንገያ
የእናት ስሟ መማያ ፤ ማስፈራሪያ
የእናት ፍቅር የመጀመሪያ፤ የማያረጅ የማይረሳ
እስከ ዓለም ፍፃሚ የሚነሳ፤ የሚወሳ
ህፃኑ እናቱ ከዓለም ሁሉ የተለየች እንደሆነች ያምናል:: የማንም ልጅ መሆን አይፈልግም:: ድጋሚ ቢወለድ እንኳ መቼም ቢሆን መወለድ የሚፈልገው አሁን ከወለደችው እናቱ ብቻ ነው:: ምክንያቱም እናቱ ለእርሱ ማድረግ ያለባትን በሙሉ አድርጋለች:: መሆን ያለባትን ሆናለች:: ዘጠኝ ወር አርግዛ በስቃይ መውለድ ብቻ አይደለም፤ አጥብታ፣ አዝላ፣ አባብላ ማስተኛት ብቻ አይደለም፤ በአፏ የአፍንጫውን ቆሻሻ ስባ ንፍጡን ተፍታለች:: ቆሻሻውን አትጠየፍም:: ቢሸናባት የለበሰችውን በሽንት ቢያበሰብስባት ቅር አትሰኝም:: ምክንያቱም ልጇ ነው:: የልጇን ቆሻሻ ማጽዳት ለእርሷ ስቃይ ሳይሆን ተራ ሥራ ነው:: የሚበላ ቢጠፋ አካሏን ስጋዋን ቆርጣ ከመስጠት ወደ ኋላ አትልም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ እናት ናት:: ነገር ግን ሁሉም ልጆቿ እርሷ የምትከፍልላቸውን ዋጋ አይከፍሉም:: አንዳንዶች እንደውም በተቃራኒው የእርሷን ውለታ ከመዘንጋት አልፈው እናትየዋን የሚጠሉበት እና የሚያጥላሉበት ሁኔታም ያጋጥማል::
ታዲያ እናት በአገር ትመሰላለች:: ኢትዮጵያ የእናት ምሳሌ ናት:: አጥፊ ልጅን ጨክና አትገፋም:: ቆሻሻቸውን ሲያራግፉባት የኖሩ ልጆቿን ገፍታ አትጥልም:: አቅፋ ቆሻሻቸውን ታራግፋለች:: የከፉ በተንኮል ቢነሱባትም ደብድበው ሊገድሏት ትንፋሿን ለማስቆም ቢጥሩም እናት ነችና ምንም አትልም:: መልሳ ይቅር ትላለች:: ያው ‹‹ውሃ ቢያንቅ በምን ይዋጣል?›› ይባል አይደል:: መድሃኒቶቼ የአይኔ ማረፊያዎች ብላ የወለደቻቸው ልጆች በስስት ከማየት በቀር ምን ማድረግ ይቻላል?
ታላቅ ነኝ ባይ መካሪ እና ምሳሌ መሆን ሲገባው፤ ታናሹን ሲያሰቃይ ሲበድል ብታይ፤ ምንም እንኳ እናት ሁለቱም ልጆቿ ቢሆኑም ታግሳ ከማለፍ በቀር ቢቻል መሃል ገብታ ከማስታረቅ ውጪ የምታደርገው ምንም ነገር የለም:: ‹‹አንዱ በአንዱ ላይ ለምን እንዲህ ያደርጋል?›› ብላ ብታዝንም አፍ አውጥታ አትናገርም:: በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር እንዲጣሉ እስከ ዓለም ፍፃሜ እንዲራራቁ እንዲለያዩ አትሻም:: ምክንያቱም የሁለቱም እናት ናት::
የትልቁ ተንኮል እና ሴራ እርሷን እስከ ማጥፋት ለመድረስ ጫፍ ላይ ቢገኝም፤ ለትልቁ ወግና ትንሹን ደግፋ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በጥሳ አታቆራርጣቸውም፤ ምክንያቱም እናት ናት:: ትንሹ ልጅ ልጅ ነውና ሁልጊዜም እናቱን ይፈልጋል:: ልቡ የዋህ ነው:: ትልቁ ልጅ እናቱ ስትፈልገው ብትውልም እናቴ ብሎ አይፈልጋትም:: የህውሓት የሽብር ቡድን የትልቁ ልጅ ቢጤ ነው:: የእናት ፍቅር ብሎ ነገር የለውም:: እናቱን የማይወድ ባለጌ ነው:: በእድሜ ያረጁ ትልቅ አባቶች የተሰበሰቡበት ይህ ቡድን በውስጡ በምንም መልኩ እናቱን የሚወድ አልተካተተበትም:: በእርግጥም እንዴት እናቱን የሚወድ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ያብራል? እነርሱ እናታቸውን ከመግደል ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም::
እናታቸውን ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ወግተዋታል:: ለ27 ዓመታት ያላትን ዘርፈው አጥንቷን ግጠው እነርሱ ቢደልቡም በዚህ አልረኩም:: ተበዳይ ታናናሽ ልጆች ‹‹በቃችሁ ዓለም ከደረሰበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ቤቱን ለማስተዳደር አትመጥኑም፤ ነገር ግን ቤታችሁ ነውና ቁጭ ብላችሁ ተከብራችሁ መቀለብ ትችላላችሁ›› ቢሏቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም::
እንደቀድሞ እናታቸውን እየበደሉ ስጋዋን ብቻ ሳይሆን አጥንቷን እየጋጡ መኖርን ሻቱ:: ምክንያቱም እነዚህ ሽማግሌዎች የእናት ፍቅር አይገባቸውም:: ደግሞም አይገባቸውም:: ተግባራቸው ሁሉ እናትን ከመጨረስና ከማስጨረስ ጋር የተያያዘ ነው:: ለእነርሱ ጥቅም ጓደኛ የቅርብ ሰው፣ ህፃን ልጅ፣ ወንድም ፣ እህት ብቻ ሳይሆን እናትም ብትሞትላቸው አይጠሉም:: ‹‹ጥቅማችን ተነካ›› ብለው አሲረው የእናታቸውን ጠባቂ መከላከያን ጥቅምት 24 ለሊት ሲወጉ፣ ስለእናታቸው መጨረሻ እንኳን መጨነቅ ጭራሽ አላሰቡም:: የመከላከያ ሰራዊት መጎዳት ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ እንድትጠቃ መንገድ እንደሚከፍት አስበው አስተውለው ከድርጊታቸው ከመታቀብ ይልቅ፤ እንድትጠቃ መንገድ አመቻችተዋል::
ለትግራይ ህፃናት አላዘኑም፤ ያቺ ልጆቿን አጥብቃ የምትወድ እናት ልጆቿን ተነጥቃለች:: እናትና ልጅን ነጥለው ወደ ጦር አውድማ ያሰማሩ የአሸባሪው ህውሓት አጥፊ ቡድኖች፤ አሁን ደግሞ እናቶች ‹‹ልጆቻችን የት ደረሱ?›› የሚል ጥያቄ እንዳያነሱ እናቶችን ለጦርነት ማሰማራትን ተያይዘውታል::
ሀምሌ 7 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ መንግስት ወቅታዊ መግለጫ ተብሎ በትግራይ ሃውስ እንደተላለፈው ከሐምሌ 5 ጀምሮ በደቡብ ትግራይ የእናቶች ዘመቻ ኦፕሬሽን ተካሂዷል:: በዚህ ዘመቻ ላይ ለጦርነት የወጡ የህፃናቱ እናቶች እንዲሳተፉ ሲደረጉ እንግልታቸው እና ስቃያቸውን ማሰብ በራሱ ያሳቅቃል:: አንዲት የወለደች እና ልጆቿን በስቃይ ስታሳድግ የኖረች እናት፤ ለጦርነት ያልደረሱ ልጆቿን እንድትገብር ከማስገደድ አልፈው እሷን የጥይት እራት ለማድረግ ከፊት እንድትሰለፍና እንድትዋጋ ከማድረግ የበለጠ ምን አረመኔያዊ ተግባር ይኖራል::
በኃይል፣ በዛቻ እና በተለያዩ መንገዶች እናትን ጨምሮ ሁሉንም ለጦርነት የመማገድ የአሸባሪው ቡድን የህውሓት ተግባር እንኳን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በጥንት በቅኝ ግዛት ዘመንም የሚታሰብ አልነበረም:: ‹‹ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጣል›› ይባላል:: ምላጭ ሌሎችን ቆርጦ ከበሽታ ያድናል:: የተቋጠረ ደም እና መግል እንዲፈስ ያደርጋል:: አሁን የብዙ ህመም ማስታገሻ የነበረችው ኢትዮጵያ ታማለች:: ህመሟ አሳብጧታል:: በውስጧ የበሰበሱ እንደምግል ሊታዩ የሚችሉ አጥፊ የህውሓት ቡድን ሽማግሌዎች እየጠዘጠዟት ረፍት ነስተዋታል::
ዓላማቸው እና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም:: ስለወደፊት አብሮ የመኖር ህልም አላቸው ማለት አይቻልም:: ተግባራቸው እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የትግራይ ተወላጅ ሁሉ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚኖርበትን እድል እስከ ዘላለም ለማቋረጥ ያሰቡ ይመስላሉ:: አብሮ የኖረ፤ ከመኖር አልፎ ተጋብቶ የተዋለደ እና ዘር የፈጠረ ህዝብ ሁሉ በሚያሳዝን መልኩ እንዲቆራረጥ እና እንዲጠፋፋ መንገድ እያመቻቹ ነው:: ዓላማቸው ስለ ሰው አይደለም:: ዓላማቸው የእነርሱ ስልጣን ብቻ ነው:: ስልጣናቸውን ስላሰቡ የትግራይ ተወላጅ አንዳንድ የመከላከያ ሰዎችን አባብለው ከማሳመን አልፈው፤ አሰልፈው እስከ ማዋጋት ደርሰዋል:: ወጣት እና ህፃናትን መልምለው እስከ ማሰማራት በመጨረሻም እንደተገለጸው እናቶችን በጦርነት ማሳተፍ ጀምረዋል::
ከልጅነታቸው ጀምሮ አፈና፣ ጦርነት እና አሰቃቂ ድርጊት ልማድ የሆነባቸው የህውሓት የሽብር ቡድኖች በግልጽ ዓላማቸውን ለመናገር ባይደፍሩም ተግባራቸው እናታቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑ አያጠያይቅም:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ከየት ወዴት በሚል በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የተጻፈው የ1986ቱ መጽሃፍ ላይ እንደተገለጸው፤ ‹‹ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ሰዎች እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ አትጠፋም::›› ከመውለድ አልፋ ያሳደገቻቸውን የኢትዮጵያን ጡት ነክሰው ሊያደሟት አናቷን ፈርክሰው ሊቀብሯት ቢሹም እንዳሰቡት አልሆነም፤ ደግሞም አይሆንም::
እናትን መግደል እና ማስገደል፤ ለጦርነት ማሰለፍ መቼም ቢሆን የሥልጣን ባለቤት አያደርግም:: እንኳን ለጦርነት ማሰለፍ የሰዎችን መንፈስ ገድሎ መረረኝ ሰለቸኝ ብለው የሚተነፍሱበትን አፍ ማፈን ስልጣንን በአስተማማኝ መልኩ ለዘለቄታው ማስጠበቅ እንደማያስችል ታይቷል:: ነገር ግን ህውሓት በኢትዮጵያ ለዘመናት ይህንን ሲፈጽም ቆይቷል:: ይህንኑ አሁንም በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ይገኛል:: የእናቶች ዘመቻ ኦፕሬሽን ብሎ የትግራይ እናቶችን ሲያዘምት ሰዎችን ማሰብ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ አስገብቶ በፍራቻ አደንዝዞ በድን ሆነው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ አመቻችቶ ነው:: በዚህ መንገድ ስልጣኑን እንደሚያስጠብቅ እርግጠኛ ሆኗል:: ነገር ግን ስልጣን የዘላለም ርስት አይደለም:: እናት እና ህፃናትን በመማገድ የሚገኝ የድል ውጤት ሊሆን አይችልም::
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በመፅሃፋቸው እንደገለጹት፤ ስልጣንን የሚሹ ቡድኖች ሁሉ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑን በሙሉ ልብ መቀበል አለባቸው:: ህዝብ የፈለገውን ይሾማል የፈለገውን ይሽራል:: ህዝብን በጦር መሳሪያ በፖሊስ ሰንጎ በመያዝ ለጊዜው ጭጭ ማድረግ ቢቻልም አብጦ የፈንዳ ቀን ግፍ ፈንቅሎት ሲነሳ መድረሻ ይጠፋል::
የትግራይ ህዝብ ህፃናት እና እናቶችን የሚያዘምት አሸባሪ ቡድን ላይ መነሳቱ አይቀርም:: የውጪ ሃይሎች እና ቀቢጸ ተስፋ ገፍቶት ግፍ ሳይፈራ በትግራይ ህዝብ ላይ በተግባር እየፈጸመ ያለው ወንጀል ማብቂያው ሩቅ አይሆንም:: በተለይ የሚማልባት፣ የፍቅር መጀመሪያ የሆነች እናት መዝመቷ እና ወደ ጦርነት እንድትሔድ ተገዳ መሰማራቷ ከግፍም በላይ ግፍ ነው:: ግፍ ሞልቶ ሲተርፍ ጎርፍ ሆኖ ገፊዎችን ያጥለቀልቃል:: የዛን ጊዜ ግፍ ፈጻሚዎች መድረሻቸውን ማየት ነው:: ግፍ ሲያጥለቀልቅ ሞትን ቢመኙ አያገኙትም::
በሽማግሌዎች ስልጣኔን ለምን ተነጠቅኩ በሚል እልህ አታካች የሽብር ተግባር ውስጥ ተሰማርቶ ክልሉን ህይወት አልባ ወና ማድረግ ለፈጻሚው ከሞት ጣር የከፋ ሰቆቃ ከማስከተለጁ ባሻገር፤ ራስን ብቻ ሳይሆን የዚህን አጥፊ ቡድን ቤተሰብ እና ወላጅ በታሪክ በመጥፎ እንዲነሳ የሚያደርግ አሰቃቂ ተግባር ነው::
አገርን እሳት የሚነድባት ምድጃ በማድረግ ሥልጣን አይገኝም:: መቼም ቢሆን የተጠበሰ ዓሳ በባህር ገብቶ ነፍስ አይዘራም:: የፈለገውን ይህል ጥረት ቢያደረግ፤ በህዝብ ማዕበልም ሆነ በሌላ ዘዴ በጦርነት ለማሸነፍ ቢያስብ ሃሳቡ ዕውን ሆኖ አገርን መቆጣጠር አይቻልም:: በፍፁም አሸባሪው የህውሃት የጥፋት ቡድን መንግስት ሆኖ አገር እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈቅድም:: በዚህ ተግባሩ አገርን ቀርቶ ክልልን የማስተዳደር ህልሙ መምከኑ አይቀርም ::
በአንድ ወገን እንሞትለታለን የሚሉትን ህዝብ ዕርዳታ እንዳይገባ በመከልከል ፈጅተው እና ጦርነት ላይ በማሰማራት አስፈጅተው የክልሉ መንግስት ሆነን እንቀጥላለን ካሉ፤ ትናንት ታርዳ የተበለተች ዶሮ እንቁላል እንደጣለች የተፈጥሮ ህግን እስከ እንደመጣስ ይቆጠራል:: ቢገባቸው የሥልጣን ዘመናቸው ላይመለስ ተሸኝቷል:: የወለደቻቸው ኢትዮጵያን ከኋላ ከውጪ ጠላት ጋር አድብተው አጥቅተዋታል:: የትግራይን ህዝብ መጠቀሚያ አድርገው በእርሱ ደም ነግሰው የትግራይን እናት ለጦርነት አሰማርተው የግፋቸው ፅዋ ሊሞላ ጫፍ ደርሷል:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጪ ጠላት ጋር አብረው ቆርጠው ቢነሱም፤ ያሰቡት አልሆነም:: አሁንም ያሰቡት አይሆንም::
በጉራጌ ‹‹ከበርቼ ሰላም›› ይባላል:: ግፍ ከመስራት ያድነን ማለት ነው:: ሞትን መሞት ግፍን የመስራት ያህል አይፈራም:: ምክንያቱም ግፍ ሰሪ በቀላሉ አይሞትም:: በእርግጥም የእዚህ ቡድን ግፍ ሰሪዎች ዛሬ ላይ ባያልቁም ጥቂት የማይባሉ የህውሃት የሽብር ቡድን አባላቶች ኢትዮጵያን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ የፈፀሙት ግፍ ፅዋው ሞልቶ በበረሃ ተሰቃይተው ህክምና ሳያገኙ እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል:: አንዳንዶች ፅዋቸው ሞልቶ ለመያዝ በቅተው የእስር ቤት ኑሮን እንደኑሮ ተቀብለው ከሚኖሩት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ቀን መቁጠሩን ተያይዘውታል::
ሌሎች ኢትዮጵያን በገዛንበት ዘመን በቂ ግፍ አልሰራንም ያሉ ፅዋቸው እስኪሞላ ግፍ መስራታቸውን ቀጥለዋል:: ዓላማው ግልፅ ላልሆነ ሊዋደቁለት ለማይገባ ህልም የትግራይ ወጣትን እየማገዱት ይገኛሉ:: ከወጣት አልፎ ጎልማሳ አልፎ ተርፎ ሽማግሌ ሲቀጥል ህፃናት ዛሬ ደግሞ እናቶችን አዝምተዋል:: በእናቶች ዘመቻ በደቡብ ትግራይ የቀጠለው ጦርነት ዘልቆ አዲስ አበባ ደርሶ ኢትዮጵያን ከመቆጣጠር ይልቅ ብዙ በውስጥም በውጪም ያለውን የትግራይ ህዝብ ማስቆጣት አለበት:: በእርግጥም ለእናቶች ያልበጀ እናቶችን የገፋ እና የገደለ ያስገደለ ቡድን ለማንም አይሆንም:: እንደአሸባሪው ቡድን ግፍ ከመስራት ያድነን:: አሜን!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013