ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ናቸው።የዶክተራል ዲግሪያቸውን ከሜኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉ ሲሆን የጁሪስ ዶክተር/J.D/ ማዕረጋቸውን ደግሞ ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።በአሜሪካ ሕገ መንግሥት፣ በሰብአዊ መብት ሕጎች፣ በሕገ ሥነሥርዓት፣ በአፍሪካ ፖለቲካ፣ በአሜሪካና ካሊፎርኒያ መንግሥታት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ምሁራዊ አገልግሎት ይሰጣሉ።በወንጀል መከላከልና የፍትሐ ብሔር ክርክሮችም ልምድ አላቸው።በአሜሪካ ከእነዚሁ ጉዳዮችም ጋር የተያያዙ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል።በኢትዮጵያ ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት ከፍተኛ አርታዒ ሆነውም ሠርተዋል።
ፕሮፌሰር አለማየሁ በአፍሪካና በኢትዮጵያ የፖለቲካና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያዎች የሚጽፉ፣ የሚያብራሩና የአድቮኬሲ ሥራዎችን የሚሠሩ ምሁር ናቸው።አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የለውጥ ሂደት በመደገፍም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ /EDTF/ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።እኛም በዛሬው የወቅታዊ አምድ ዝግጅታችን ከዘመን መፅሄት በወቅታዊ የአገራችንን ጉዳይ ዙሪያ በኢሜል ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፤መልካም ንባብ።
ዘመን፡- ኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች ከምን የመነጩ ናቸው?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- ኢትዮጵያ በትግራይ በምታካሂደው ሕግ የማስከብር እርምጃ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካና በአውሮፓ ህብረት ሀፍረተ ቢስና የማይጠበቅ ጫና እየገጠማት ነው።የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ላለፉት ስምንት ወራት አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት ከዚሁ ቡድን ጋር “እንዲነጋገር” እና “እንዲደራደር” ጉልበታቸውን ሲያሳዩ ፤ ሲያስፈራሩና እጁን ለመጠምዘዝ ሲጥሩ ነበር።አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ለአሸባሪው ህወሓት /ትህነግ/ እየሰጡ ያሉት ጭፍን ድጋፍ ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን በእብደት የተሞላ የውጪ ፖሊሲ ነው።
አሜሪካን እና አውሮፓ ህብረት በትህነግ የሽብር ቡድን ስም ኢትዮጵያ ላይ ግፊት የሚያደርጉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።በመጀመሪያ ደረጃ የአሜሪካን መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው የውጭ ፖሊሲ በባይደን የአገር ውስጥ ፖሊሲዎች አማካሪ ሱዛን ራይዝ ተጠልፏል።አሜሪካን በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የውጪ ፖሊሲ ለማለት እቸገራለሁ፣ ሱዛን ራይዝ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ነው።ራይዝ ከ1990ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ከትህነግ ጋር ረጅምና ጥላ የጠለባት የቀደመ ግንኙነት አላት።አሁን በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ኮቪድ ምላሽና የጤና ደህንነት አስተባባሪ ከሆኑት ጋይል ስሚዝ ጋር በመሆን በአሜሪካ መንግስት ውስጥ የትህነግ ወኪሎች ነበሩ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን በኦባማ አስተዳደር ውስጥ ለሩዝ ሰርተዋል።ያልተቀደሰ ጥምርት ያላቸው እነዚህ ሶስት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን በመተግበር፣ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መድረክ በማግለል ተነጥላ እንድትቀር በማድረግ እና በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የሀሰት ዘመቻ የኢትዮጵያን ስም በማበላሸት አሸባሪውን ህወሓት ወደ ስልጣን መመለስ እንችላለን ብለው ያምናሉ።
ሁለተኛ አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ቻይና አፍሪካን በመቆጣጠር ረገድ የወሰደችብንን የበላይነት ለማቆምና ለመቀልበስ ያለን የተሻለ ዕድል ኢትዮጵያን የቻይና መቃብር ማድረግ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።የኢትዮጵያ መንግስትን በመጫን ቻይናውያንን እንዲያባርር ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እና ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንሱ ማድረግ ከቻሉ ቻይና ከአፍሪካ እንድትወጣ ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ።አሁን ያለው መንግስት ለእንዲህ አይነቱ ጫና አይንበረከክም።የባይደን አስተዳደር ይህንን ለማሳካት እንዲዘል ሲጠየቅ በምን ያህል ከፍታ ብሎ የሚጠይቅ ታዛዥ አገዛዝ ይፈልጋል።ትህነግ የኦባማ እና የባይደን (ኦባማ ሁለተኛ) ቆሻሻ ስራን የሚያስፈጽም ተላላኪ ነው።
ሦስተኛ አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ከፍተኛ ብሔራዊ ስሜት ያለው በመሆኑ በአፍሪካ ለሚተገብሩት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አይገዛም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።እምቢተኛ ፣ በራሷ የምትተማመን እና ነጻ የሆነች ኢትዮጵያ ለተቀረው አፍሪካ መጥፎ አርአያ ትሆናለች።የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲ ወዘተ ጫና የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት እና መንፈስ ለመስበር እና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በተያዘች አገር ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ ታስቦ የሚደረግ ነው፡፡
አራተኛ በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና ጠንከር ያለ የነጭ የበላይነትን የማረጋገጥ ፍላጎት አለው።የአሜሪካን እና የአውሮፓ ህብረት የሚያወጧቸውን መግለጫዎች እና ፖሊሲ አውጪዎቻቸው ትዊተር ላይ የሚጽፉትን ስትመለከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ክብር ምን ያህል እንደሚንቁ አይተህ ትገረማለህ።በሚሰጧቸው መግለጫዎች የሚይዟቸው የማዕቀብ ማስፈራሪያ፣ የእርዳታ ማቋረጥ፣ “ገደብ የለሽ የሰብአዊ አቅርቦት” ፣ “የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ” ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አስተሳሰባቸውን በግልጽ ያሳያሉ፡፡
እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡት እነሱ ማን ናቸው ? በእውነቱ አስቂኝ የሆነው ነገር የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን እየጠየቀ ያለውን አይነት ጥያቄ የትኛውንም የአሜሪካ ስቴት መጠየቅ አይችልም።ለምሳሌ የባይደን አስተዳደር የአሜሪካ ስቴቶች ኮቪድ 19ን ለመከላከል የፊት ጭንብል እንዲደረግ የሚያስገድድ ህግ እንዲያወጡ ማዘዝ አይችልም።ምክንያቱም ግዛቶቹ ሉዓላዊ ስልጣን እንዳላቸው ስቴት የጤና እና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ህግ የማውጣት ስልጣን አላቸው፡፡
ሆኖም የባይደን አስተዳደር በአስር ሺህ ማይሎች ርቀት ላይ ያለች ሉዓላዊት ሀገር ስራዋን እንዴት እንደምታከናውን፣ ምርጫዋን እንዴት እንደምታካሂድ፣ የራሷን ህጎች እንዴት እንደምትፈጽም እና የውጭ ፖሊሲዋን እንዴት እንደምትመራ የማዘዝ ድፍረት አለው።ይህ ነው የሱዛን ራይዝ፣ ብሊንከንና ሱሊቫን በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ድፍረትና እብሪት።
ዘመን፡- አሜሪካ በኢትዮጵያ በስም ባልተጠቀሱ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ ከማድረጓ በፊት እርስዎ ያቀረቡት መላምትን ሙሉ በሙሉ ተግብረዋለች።ከዚህ በኋላስ የአሜሪካ ቀጣይ ሂደት ምን መልክ ሊኖረው ይችላል?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡– የባይደን አስተዳደር በዝርዝር ባልታወቁ እና ስማቸው ባልተጠቀሰ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ማዕቀብ ጥሏል።ስማቸውን በምስጢር ለመጠበቅ ወስነዋል።ስማቸውን በይፋ መጥቀስና ማሳፈር ይችሉ ነበር።ነገር ግን ይህን ላለማድረግ መርጠዋል።ይህ በባይደን አስተዳደር በኩል መጥፎ እምነት መኖሩን ያሳያል።የማዕቀቡ አጠቃላይ ዓላማ ግፍ በመፈጸም እና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተሳተፉ ሰዎችን ማጋለጥ ነው።እኔ አጥፍተዋል በሚል የሚቀርቡባቸውን ክሶች የሚደግፉ ተጨባጭ ማስረጃዎች አነስተኛ በመሆናቸው ወይም ባለመኖራቸው ምክንያት አሜሪካ ስሞቹን በሚስጥር ይዛለች ብዬ እከራከራለሁ።ሆኖም የባይደን አስተዳደር እንደዘበት የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን መናፍስት እና ስም የለሽ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች በሕግ እንዲከስ አጥብቆ ይጠይቃል።ስለዚህ አሜሪካ በሰብአዊ መብቶች ላይ ወይም የሰብዓዊ መብት
ጥሰት ፈጻሚዎችን ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ፍላጎት የላትም።አሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ክሶችን ኢትዮጵያን ለማሳጣት እና ዓለም አቀፋዊ ገጽታዋን ለማጠልሸት መሳሪያ አድርጋ መጠቀም ትፈልጋለች።
የቪዛ ማዕቀቦቹ ህዝባዊ አስተያየቶችን ለመፈተሽ በጊዜያዊነት የተጣሉ ናቸው።የማዕቀቡ ሙሉ ገጽታ ወደፊት ይፋ ይደረጋል።የባይደን አስተዳደር የጣለው ማዕቀብ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚያገኝ ማየት ይፈልጋል።የኢትዮጵያ ህዝብ ይደግፈዋል? አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ፍርሃት ይገባቸዋል? የአሜሪካንን የማዕቀብ ቁጣ በመፍራት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አሉታዊ ምላሽ ይሰጣል ?
የቪዛ ማዕቀቦቹ እንደ ተነፈሰ ፊኛ መሬት ወድቀዋል።ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል፣ እምቢተኛ እንዲሆኑ እና አንድነት እንዲኖራቸው አድርጓል። የቪዛ ማዕቀብ የጉዞ እገዳው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊያዊ አዕምሮ ውስጥ የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው የሚል ድምዳሜ እንዲኖር አድርጓል።
የባይደን አስተዳደር ሁሉንም ዓይነቶች የኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ማዕቀቦች በመጠቀም አስፈራርቷል።የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ብድር እና ዕርዳታ እንዳይሰጡ በአሜሪካ ጫና እንደተደረገባቸው በቅርቡ ይፋ ተደርጓል።አሜሪካ የአውሮፓ የገንዘብ ተቋማት ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ተናባ እየሰራች ነው።አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ በ 2001 ዓ.ም እንዳደረገው በትግራይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ለማድረግ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ ጋር በቅንጅት ለመስራት ሞክራለች።ቻይና ፣ ሩሲያ ፣ ህንድ እና ሌሎችም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ማዕቀብ የመጣል ሀሳቡ ላይ ተሳልቀዋል፤ ምክንያቱም የትግራይ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይም ለዓለም አቀፍ ሰላም ምንም ሥጋትነት ስለሌለው ማለት ነው።አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ሰኔ 14 ቀን ለተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ትክክለኛነት እውቅና ላለመሰጠት አሲረዋል።የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያቀደውን 107 ሚሊዮን ዶላር “የበጀት ድጋፍ” ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆን የራሱን ማዕቀብ ጥሏል።አሜሪካም ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፀጥታ እና “የልማት ዕርዳታ” ከልክላለች፡፡
አሜሪካ መሳሪያ በምታደርገው ማዕቀብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ ማኅበረሰባዊ እና የፖለቲካ ሂደት በማተራመስ አከርካሪዋን ለመስበር እና ጉልበቷ ስር ለማንበርከክ ሁሉንም ነገር ትጠቀማለች።አሜሪካ ከአውሮፖ ህብረት ጋር በመሆን በጉልበቷ እንደ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ ብድሮችን እንዲከለክሉ፣ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዳያራዝሙ ወዘተ እና ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ስምምነቶችን እንዳያድሱ ለመከልከል ተባብራ እየሰራች ነው ብዬ አስባለሁ።
በኢትዮጵያ የግል የንግድ ፋይናንስን እና ኢንቨስትመንትን ለማገድ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። አሜሪካ በቅርብ በተካሄደው በቮዳፎን የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃድ ስምምነት ላይ ይህንን ማድረግ ጀምራለች። በዓለም አቀፍ ትራንስፖርት፣ በግል ጉዞ እና በግንኙነት ላይ ገደቦችን ይጥላሉ።ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ገበያዎች፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና የባንክ ሥርዓቶች የመጠቀም ዕድል እንዳታገኝ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ብዬ እጠብቀለሁ።በንግድማስተዋወቂያ ተግባራት ላይ እቀባ ያደርጋሉ እንዲሁም ታሪፎችን ይጥላሉ።መሰረታቸውን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት ያደረጉ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ተደራሽ እንዳይሆኑ እንቅፋት በመሆን የኢትዮጵያ መንግስት እና ድርጅቶች ብድር እንዳያገኙ በማድረግ እጥረት ለመፍጠር ይሰራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።በአሜሪካ የሚገኙ የማናቸውንም የኢትዮጵያ ድርጅቶች እና ባለስልጣን ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋሉ።ለወጪ ንግድ ድጎማዎች ፣ ለንግድ ድርጅቶች የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎችን ፣ ዝቅተኛ ወለድ ያላቸው ብድሮች ፣ ድጎማ ለተደረገባቸው የብድር ዋስትናዎች ወይም ከወጪና ገቢ ንግድ ባንክ የሚገኝ መድህን፣ ከባህር ማዶ የግል ኢንቨስትመንት ማህበራት እና ለእቃ ብድር የገንዘብ ድጋፎችን ለመከልከል እርምጃዎችን ይወስዳሉ።የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ግፊት ያደርጋሉ፡፡
በአጭሩ አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጦርነት ያውጃሉ ብዬ እጠብቃለሁ።ትህትናን ተሞልቼ እኔ የጠቀስኳቸው ትክክለኛ ትንበያዎች የመፈጸም ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ መሆኑን እናገራለሁ፤ እናም እነዚህ ትንበያዎች አንድ በአንድ ቅርብ በሆነ ጊዜ ሲወጡ ታያለህ፡፡
ሌላ ትንበያም ደግሞ ላድርግ።ልክ ነገ ፀሐይ እንደምትወጣ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሴሩት ሴራ አይሳካም።በኢትዮጵያ ላይ የሚያነሷቸው ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሰይፎች የራሳቸውን ልብ ይወጋሉ፡፡
ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ዲፕሎማሲውን በሚገባ እየተወጣ በመሆኑ የኤምባሲዎቻችንን ቁጥር ስለምንቀንስ ዲያስፖራውም ለዚህ ራሱን ያዘጋጅ ብለዋል።ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ለፓርላማው እንደተናገሩት አገሪቱ በመላው ዓለም ያሏትን ከአምስት ደርዘን በላይ ቁጥር ያላቸውን ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችን ለማስቀጠል አቅም የላትም ወይም አትፈልግም።እኔ ይሄን ንግግር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ተለዋዋጭ እና ስልታዊ የሪፎርም ሂደት አካል አድርጌ ነው የምመለከተው።ውሳኔው የአፈጻጸም፣ ውጤታማነት እና ይህን የመሰለ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስብስብን መያዝ ያለው የገንዘብ አዋጭነት ላይ በጥንቃቄ በተደረገ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ ነው ብዬ አምናለሁ።ውሳኔው ወጪን ለመቀነስ ተሰልቶ የተላለፈ ነው ማለት እችላለሁ።በጣም ብዙ ኤምባሲዎች እና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በመኖራቸው ምክንያት የሚገኙትን ጥቅሞች እና አጸፋዎች በመመልከት ቁጥራቸውን በመቀነስ አጠቃላይ ወጪን መቀነስ ላይ ትኩረት አድርገዋል።እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ፈጣን ምላሽ እየሰጡ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአገሬው የአነጋገር ፈሊጥ የሚናገሩ፣ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያላቸው ዲፕሎማቶች ያስፈልጋታል ብዬ አምናለሁ።ያ ማለት ውጤታማና ነገሮችን ቀድመው የሚያከናውኑ እና ዝም ብለው ጠብቀው ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ምላሽ የማይሰጡ ዲፕሎማቶች ማለት ነው።ኢትዮጵያ በተለመደው ዲፕሎማሲ የሚሳተፉ ብቻ ሳይሆን የተወከሉበትን አገር ህዝብ በመድረስ እና የኢትዮጵያን ዲያስፖራዎችን በማሰባሰብ ረገድ ብቁ እና ከጊዜው ጋር አብረው የሚሄዱ ዲፕሎማቶች ያስፈልጓታል፡፡
እውነቱን ለመናገር፣ ብዙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የአሸባሪው የወያኔ ጁንታ የመጨረሻ ምሽግ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ያሉት የህወሓት ጮሌዎች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚያስንቁ እና ዲያስፖራዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት ናቸው ብለው ያምናሉ።ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን ግንዛቤ እውነታ ነው፤ እናም አብዛኛው ዲያስፖራ ስለኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እንዲህ ነው የሚሰማው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ኃላፊነታቸውን ለመቀበል እና አዲስ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመከተል ዝግጁ የሆኑ የሰለጠኑ የውጭ አገልግሎት መኮንኖች እንዳሏት ተናግረዋል።አዲሲቷ ኢትዮጵያ ንቁ ፣ አተኳሪ ፣ በራስ መተማማን የተሞላ ፣ አኩሪ እና ፈጠራ የታከለበት እንዲሁም በማያቋርጥ ሁኔታ ራሱን በአዳዲስ መረጃዎች እያጎለበተ ከጊዜው ጋር የሚጓዝ እና ለማናቸውም አይነት ተግዳሮቶች እና ዕድሎች በብርታት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ አዲስ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋታል።
እንደነዚህ ያሉ ሠራተኞችን በፍጥነት ማግኘት ተግዳሮቶች እንደሚኖሩት እገነዘባለሁ።ነገር ግን አገሪቱ ከተጋፈጠቻቸው ሌሎች የሪፎርም ችግሮች የተለየ አይደለም።እኔ “መሄድ አስቸጋሪ ሲሆን አስቸጋሪው ነገር እየሄደ ነው” እላለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን እንዲያግዝ ጥሪ አድርገዋል።በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ስል በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን በተሻለ ሁኔታ ለመወከል በኢትዮጵያ መንግስት እና በዲያስፖራዎች መካከል የጋራ ጥረት መኖር እንዳለበት ለመጠቆም ነው።ዲያስፖራዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተመረጡ አገራት በሕዝብ አስተያየት በተለይም በኤሊቶች የሕዝብ አስተያየት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ተቋማዊ አሠራሮችን መፍጠር አስፈላጊ ነው።እንዲህ ዓይነቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ብዙ መልኮች ሊኖሩት ይችላል።ነገር ግን የዚህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዋና ተግባር የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲዎችን ለውጭ አገር ህዝብ ለማብራራት እና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ለማሻሻል እንዲሁም ዜጎቻቸውን በመጠቀም የውጭ መንግስታት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ነው።መሰረታዊ ማህበረሰብ-ተኮር እንቅስቃሴዎች ወይም እንደ ማግባባት ያሉ የተደራጁ ጥረቶች ሊሆን ይችላል።በአዲሶቹ ተተኪ ዲፕሎማቶች የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ትኩረት ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በዚህ ረገድ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን አልተሳካልንም ስል አዝናለሁ።ወያኔዎች ከሚሰሩት በውሸት፣ በተራቀቁ ውሸቶች እና በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጋር ስናስተያየው ውድቀታችን ፍንትው ብሎ ይታያል።ለነገሩ በህወሓት ውስጥ ያለው ሃይል ማለት የውሸት ፋብሪካ ነው።ሮይተርስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ ፣ ኒውዮርክ ታይምስም ሆኑ ሌሎች የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች በየቀኑ የትህነግ አሸባሪዎችን የድል ዜናዎችን ያስተጋባሉ ወይም የኢትዮጵያን መንግሥት በ “ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም”፣ “በጭካኔዎች” እና “በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” ወዘተ ይኮንናሉ።በምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ መንግስት ስላከናወነው ሰፊ የህይወት አድን ጥረት የሚቀርቡት መረጃዎች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው (70 በመቶው ሰብአዊ እርዳታ የሚቀርበው በመንግስት እንጂ በሚጮኹት የምዕራባውያን መንግስታት ወይም ዴሞክራሲን የማጎልበት ጥረት አይደለም፡፡) የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ከወደቀበት ሊነሳ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በተናጥል እና በህዝብ ዲፕሎማሲ ውስጥ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፡፡
በሕዝብ ዲፕሎማሲ ጥረት ውስጥ አጀንዳ ተኮርነትን መግለጽና ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው።በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ውስጥ “የኢትዮጵያ ፀረ-ስም ማጥፋት ማህበር” መፍጠር አለብን።የማህበሩ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ላይ ተንኮል-አዘል ስም ማጥፋት እና የሐሰት መረጃዎችን ለሚያሰራጩ ማናቸውም ግለሰቦች ወይም ተቋማት ምላሽ መስጠት ይሆናል።ለምሳሌ ከማህበሩ የመጀመሪያ ተግባራት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፉ ሚዲያዎችን መዘርዘር ፣ መተንተን እና በሕዝብ ዲፕሎማሲ ውስጥ በመጠቀም የሐሰት ዜናዎችን ማጋለጥ ሊሆን ይችላል፡፡
በመረጃ ጦርነቶች በመርህ ላይ የተመሠረተ፣ እውነታን መሰረት ያደረገ፣ የማጥቃት እና የመከላከል ዘመቻ ለማካሄድ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን መረጃና ትንታኔ የሚያገኙበት መንገድና ድረ ገጽ መፍጠር አለብን።በፖሊሲዎች ፣ እርምጃዎች እና እንቅስቃሴዎች ላይ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ከኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት ጋር መተባበር አለብን።ባሉበት ቦታ በህይወት እስካሉ ድረስ ሁሉንም ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያንን ለማካተት መሠረታዊ የንቅናቄ ሥራ ማከናወን ያስፈልገናል።ኤሊቶች ብቻ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ በሚለው ሀሳብ አላምንም፡፡
ዘመን፡- ለኢትዮጵያ መንግስት «ተደራደሩ እና እገሌ የሚባል አካባቢን ለቃችሁ ውጡ» በሚል ፊት ለፊት ከሚቀርበው ጥያቄ ውጪ ከጀርባ የሚቀርቡለት ጥያቄዎች እንዳሉ በመግለጽ ምዕራባውያኑ ለእነዚህ ጥያቄዎቻቸው መልስ እስካላገኙ ድረስ የሚያደርጉት ጫና ይቀጥላል የሚሉ ወገኖች አሉ።ሀሳቡን የሚጋሩ ከሆነ ከጀርባ የሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡– የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት የሚያንኳስስ ምንም ዓይነት አስተያየት አልቀበልም። አለቀ።አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ሁሉን አቀፍ ውይይት የሚሉት ነገር አሸባሪውን ህወሓት ወደ ሥልጣን ለመመለስ እና እንደተለመደው ዓይነት አካሄድ ለማስቀጠል ይችሉ ዘንድ ለጁንታው በር ለመክፈት የተቀመጠ ደባ ነው።አሜሪካና አውሮፓ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያውያን እና የመንግሥታቸው አዛዥ እስከመሆን ድረስ ጥላቻ ውስጥ የገቡት አንድም ለቡድኑ ተገን እየሆኑ ነው፤ አሊያም በስሕተት እየተመሩ ነው።አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት እነርሱ በአንድ ወቅት አሸባሪ ብለውት ከነበረ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ካለው ኃይል ጋር እንዲደራደር ጫና እያሳደሩ ነው፡፡
ምንም እንኳን አሁን በጦርነቱ በአብዛኛው የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች ቢያዙና ቢገደሉም፣ አሜሪካ ግን ህወሓትን ከአሸባሪነት ዝርዝር ያወጣችው እኮ! በሰኔ 2014 /እ.አ.አ/ ነበር። ታዲያ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲደራደር የሚጠብቁት ከሞተው ህወሓት ጋር ነው ወይስ የእነሱ ማሽን ሆነው ዛሬ በውጪ ሀገር ከቀሩ ተላላኪዎቻቸው ጋር? በአሜሪካና በአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያን ጭራቅ አድርጎ ለመሳልና ጫና ለመፍጠር የተያዘው ጨዋታ ሁሉ ዓላማው ይሄ ነው።
ሀቁ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት አማራጭ ተላላኪ ኃይል የማጣታቸው ነገር ነው።በኢትዮጵያ ላይ የትኛውንም ጫና ተግባራዊ ቢያደርጉ የሚፈልጉትን ውጤት ማለትም ህወሓትን ወደ ሥልጣን የመመለስ ነገር ሊሰካላቸው አይችልም።የተለየ ውጤት ሊያገኙ እንደሚችሉ ስለሚያስቡ ግን ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መጣራቸው አይቀርም።ይህ ግን ዕብደት ነው።ይህንን በኢራን ላይ ላለፉት አርባ ዓመታት አድርገውታል።በቬንዝዌላ ላይ ለአሥራ አምስት ዓመታት አድርገውታል።እንዳስተዋልኩት ከሆነ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት የሚፈልጉትን ሁሉ ሊያደርጉ ይችላሉ።ኢትዮጵያውያን ግን በአንድነት መቆም አለባቸው።የትኛውንም ጠንካራ ጫና መቋቋም አለባቸው።ለእነርሱ እጅ በመስጠት በኔዎ ኮሎኒያል ባርነት ሥር ራስን ለማኖር መወሰን ይሆናል።
እኔ በዚህ አልጨነቅም።አውሮፓውያን በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ሲቀራመቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛ ነጻነቷን ያስከበረች ሀገር ነበረች።በ1896 የጣልያን ኃያል ቅኝ ገዢ ሠራዊት፣ በ1942 የፋሺስት ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ጀግንነት በተሸነፉ ጊዜ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች መቀበሪያ መሆኗ ታይቷል።ኢትዮጵያ አሁንም የ21ኛው የአሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ኔዎኮሎኒያሊዝም መቀበሪያ እንደምትሆን አስባለሁ፡፡
ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ምንጭ ሆና እስካሁን ምንም ሳትጠቀምበት ብትቆይም አሁን ላይ የጋራ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርጋ የህዳሴ ግድብን በመገንባቷ ሌሎች አገራት በተለይም ውሃው የማይመለከታቸው አገራት ጣልቃ መግባት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- የግብጻውያን በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያነሱት የአስመሳይነት ውዝግብ ብዙ ገጽታ ያለው ነው።የመጀመሪያው አልሲሲ በዚህ ምክንያት በግብጻውያን ዘንድ እንዲኖረው የሚፈልገውን ተቀባይነት እና ዝና ለመጨመር በመፈለጉ ነው።በግድቡ ጉዳይ ተጻራሪ አቋም ይዞ መጓዙ የግብጻውያንን አንድነት ለመጨመር፣ ለእርሱም ሊያገኝ የሚፈልገውን ድጋፍ ሊያመንጭበትና እንደ ዘመናዊው ገማል አብድል ናስር ሆኖ የመታየት ጥማት ነው።ከልኩ በላይ ሚና ለመጫወት ሞክሯል።አሁን ግን ተጨናግፎበት በራሱ ፕሮፓጋንዳ በፍጥነት የተጠለፈና የተቸገረ ሆኖ እናየዋለን፡፡
ሁለተኛው ነገር አልሲሲ የአሜሪካንን የውጪ እርዳታ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማንበርከክ መፈለጉ ነው።አሜሪካ ለግብጽ የብዙ ሚሊዮን ዶላር ጦር መሣሪያ ትሸጣለች፣ ትገዛለች እንዲሁም የኢኮኖሚ ድጋፍ ትሰጣለች።አሜሪካ ደካማና ያልተረጋጋች ግብጽ በመካከለኛው ምሥራቅ እንድትኖርና ያንንም በመጠቀም አካባቢውን መቆጣጠር ትፈልጋለች፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ጉዳት ላይ እንዲሆን አይፈልጉም ነበር።ስለዚህ ከግብጽና ከኢትዮጵያ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ሲሆንባቸው አሜሪካ ግብጽን መምረጥ ቀላል ሆኖ ታያት።በግብጽ እና በትራምፕ አስተዳደር በህዳር 2020/እ.አ.አ/ ተወጥኖ የነበረው የዋሽንግተን ውይይት የዚህ ሴራ መታያ ነበር።ግብጽና አሜሪካ ጽፈውት የነበረው ስምምነት ረቂቅ በቀጥታ ኢትዮጵያን የሚደፍቅ/አሳልፎ የሚሰጥ/ ነበር።ምንም እንኳን ትራምፕ ግብጽ ግድቡን እንድትመታ የጋረጠው አደጋ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከአቋሟ ሳትዛነፍ በመገኘቷ ምንም ሳያገኙበት ቀሩ፡፡
ሦስተኛው ነጥብ አሜሪካ አሁን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና እንድትቀጥል አትፈልግም።ምክንያቱም ጠንካራና ኃያል የሆነች ኢትዮጵያ ግብጽን እንደምትጋርዳትና ለሌላው ጥቁር አፍሪካ ሁሉ የነጻነት ምሳሌ ሆና እንደምትወጣ አያጠራጥርም። በሌላ አነጋጋር በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጠንካራ የሆነች ኢትዮጵያ የምዕራቡን ኔዎኮሎኒያሊዝም የምትገዳደር እና ለሌሎች /ነጻነት ፈላጊዎች/ ከለላ የምትሆን ሀገር ትሆናለች።አፍሪካውያን ደግሞ ኢትዮጵያን በሁለት እግሮቿ ራሷን ችላ ቆማ ሲያዩ ለማኝ ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት አይኖራቸውም።ይህ ደግሞ የአፍሪካ እውነተኛው ነጻነት ከስድሰት ዐሠርት ዓመታት በኋላ ‹‹ነጻነት›› ተብሎ ከነበረው አጉል ነገር ነጻ ይሆናሉ፡፡
አሜሪካ ግብጽና ሱዳን የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ሁሉ የሚጠቅም ግድብ መሆኑን ያውቃሉ።ነገር ግን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ኢትዮጵያን በቀጠናው በርካታ ፖለቲካዊ አቅምም ይሰጣታል።ግብጽ ሱዳንና አሜሪካ ያሉበት አጣብቂኝ ይሄ ነው።እርግጠኛ ነኝ ግድቡ ይጠናቀቃል፤ ለኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ይሆናል።እነዚህ ሦስት ሀገራት ግን ለሰከንድም ቢሆን ኢትዮጵያን ከመጉዳት አያርፉም፡፡
ዘመን ፡- ኢትዮጵያ በምዕራባውያኑ አንዳንድ አገራት የሚደረግባት ጫና ተጠናክሮ እየከረረ የሚቀጥል ከሆነ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ቻይና እና ሩሲያን ወደ መሰሉ አገራት ለማዞር ልትገደድ ትችላለች? ውጤቱስ ምን ይሆናል ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ ፡- ምናልባትም ዶግማ ያህል ሆኖ የሚታመን ሌላው ቀርቶ በተማሩ ወገኖች እንኳን ሳይቀር የሚታሰብ የኢትዮጵያ ህልውና፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ልማት ቀጣይነት በአሜሪካ ርግማን ወይም ቡራኬ ላይ የተንጠለጠለ አድርጎ የማሰብ ነገር አለ።ይህ ንግግር /ሐሳብ/ ስሜት የማይሰጥ ነው።ከትራምፕ አስተዳደር በኋላ ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል።ዓለም የአሜሪካንን መንግሥት ባዶነት አይቷል።ትራምፕ የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመግታት የሚሰጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ባለመተግበርና በግትርነት በመቃወም ምክንያት ከ600 ሺህ የሚበልጡ አሜሪካውያን ሞተዋል። ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚል የውጪ ፖሊሲን በመተግበሩ የአሜሪካንን ትስስርና ዓለም አቀፍ የበላይነት በጣጥሷል።ስለዚህ አሜሪካ ከዚያ በኋላ የምትታመን የምትከበር ሀገር አልሆነችም።የአሜሪካ መንግሥት ዴሞክራሲን ሰብአዊ መብትን ነጻነትን በአሜሪካ ውስጥ ማስከበር አይችልም።ታዲያ በኢትዮጵያና በቀረው ዓለምስ ሊያስከብሩ የሚችሉት እንዴት ነው!
የጥር ስድስቱ በኮንግረሱ ላይ የተፈጸመ ጥቃት፣ ከአፍጋኒስተን ያፈገፈጉበት አሳፋሪ እርምጃ፣ በአሜሪካ ማህበረሰብ ዘንድ የተፈጠረው ጥልቅ መከፋፈል፣ በየቀኑ በአሜሪካ የሚፈጸሙ ዜጎችን በጅምላ የመግደል ጥቃት፣ በማህበራዊ ሚዲያ እየተስፋፋ ያለው ክርክር፣ ብሊንከን፣ ሱሳን ራይዝ ፣ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪን ጨምሮ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ኃላፊነት የሚመሩ ግልብ ግለሰቦች መሆናቸው፣ የአሜሪካ በዓለም መድረክ ያላት መሪነት በፍጥነት እየወረደ መምጣቱን ለዓለም ያረጋገጡ ናቸው፡፡
ሀቁ የባይደን አስተዳዳር ጥርስ ከሌለው ማእቀቡ ጋር በዓለም ላይ ሁለት ጎራ ወዳለው ሥርዓት ለመግባት እየተገደደ ነው።በአንድ በኩል አሜሪካ ምዕራብ አውሮፓ ያሉበት ወገን በሌላ ወገን ያሉትን ቻይና፣ራሺያ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ቬንዝዌላ ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራትን በአቋም ወደ መገዳደር የገባ የዓለም የግንኙነት ሥርዓት ለመፍጠር እየተገደደ ነው።አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማግለልና ለማጥፋት በገባበት በዚህ የዕብድት ዘመቻ የሚቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያ ሌላ ጠንካራ አጋር መፈለጓ አያጠራጥርም።
ኢትዮጵያ ቻይናና ራሺያን አጋር የማድረግ ግዴታ ውስጥ አትገባም፤ ነገር ግን የጋራ ጠላት በመጋፈጥ ምክንያት የሚመጣ ተፈጥሯዊ አጋርነት ነው። ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው።ለማንኛውም እንቅስቃሴ አቻ የሆነ ተቃራኒ ምላሽ አለ።ጠንካራ የሆነ የኢትዮጵያ ቻይናና ራሺያ ትብብር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው።በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ስኬታማ በሆነ መንገድ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በውስጥ ጣልቃ ገብነት የሚፈጥሩትን ተጽእኖ መገዳዳር ትችላለች።ከአሁን በፊትም በተደጋጋሚ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዳየነው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለማስጣል ያደረገችው ጥረት ከሽፏል።በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ከአሜሪካና አውሮፓ ጫና ነጻ ሆና የራሷ የሆነውን ነገር በነጻነት ለማድረግ ትችላለች።ሌላው ደግሞ ጠንካራ ሆና የምትገነባ ኢትዮጵያ የጋራ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እስከጠቀመች ድረስ በሦስቱ ሀገራት መካከል/ቻይና ኢትዮጵያና ራሺያ/ የሚኖር ትብብር ኢትዮጵያ በቀጠናው የሚኖራትን ሚና ያሳድጋል፡፡
ዘመን፡- ለምዕራባውያን ጩኸት ጆሮ ያልሰጡ ቻይና እና መሰል የኢሲያ አገራት የሚደርሱባቸውን ጫናዎች ሁሉ ዋጋ ከፍለው በመቋቋም በራሳቸው እግር ቆመው ለሌሎች ለመትረፍ ችለዋል።ኢትዮጵያ ለዚህ ዝግጁ ናት ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- በርካታ አገራት ባላቸው ክብር እና ኩራት ላይ በመመርኮዝ የምዕራባውያኑን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እየተቋቋሙ ተጉዘዋል።አሜሪካንም ከመሰረቱ አባቶች ውስጥ ፓትሪካ ሄነሪ አንዱ ነው።ፓትሪካ ‹‹ነጻነቴን ስጠኝ፤ አሊያም ሞቴን›› ሲል በወቅቱ እንግሊዝ ትገዛው በነበረው የሰሜን አሜሪካ እና ማንነትን መሰረት ያደረገውን ጠንካራ የአሜሪካውያን ትግል መነሻ ምክንያት ነበር።
በታሪኳ፤ ትልቁ ሀቅ አሜሪካ በዓለም አቀፉ አይን ወርዳ የተገኘችበት ጊዜ ቢኖር በቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን የሆነው ነው።ይህም አሜሪካ በወታደራዊም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ የተገደበ አቅም እንዲኖራት አድርጓል።ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ውስጥ አሜሪካ ለመገናኛ ብዙሃኑ ያስተላለፈችው መልዕክት ነበር።ይህም ዓለም ባንክም ሆነ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ብድርም ሆነ ድጋፍ እንዳይሰጡ የሚል ነበር።በእኔ እይታ ይህ ለኢትዮጵያ መልካም እድል ነው እላለሁ።
እአአ ሚያዝያ 2021 ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የ700 ሚሊየን ዶላር ብድር እና 200 ሚሊየን ዶላር ድጋፉን ከልክሏል ።አሜሪካ ይህን ከመነሻው ታቆማለች ብዬ እርግጠኛ አይደለሁም።ይህ ይሁን እንጂ የዓለም ባንክም ሆነ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር እና ድጋፍ ከእዳ ወጥመድ ያለፉ አይደሉም።በየካቲት 2021 የዓለም የገንዘብ ድርጅት የኮረና ቫይረስ ተፅዕኖ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ኢትዮጵያ በ2020/21 ሁለት በመቶ ታድጋለች፤ ነገር ግን በ2021/22 የዓለም ኢኮኖሚ ያገግማል ከሚለው እሳቤ አንጻር አገሪቱ ስምንት ነጥብ ሰባት በመቶ እንደምታድግ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተወሰነ ጫና መፍጠሩ አይቀርም።ነገር ግን ኢትዮጵያን ከጥንካሬዋና ከጉዞዋ አያስቀራትም።አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቡን በከፍተኛ ደረጃ ቢቀጥሉበት ኢትዮጵያ የበለጠ እየጠነከረች የምትሄድበት እድል ይፈጠራል።የእጅ አዙር የቅኝ ግዛቱ ጠላት ነው፤ ደግሞም የምታሸንፈው ነው።ሰን ቲዙ ‹‹ The Art of War›› በሚለው መፅሀፉ ‹‹ጠላትህንና ራስህን ካወቅከው፤ መቶ የሚሆኑ ጦርነቶችን አትፈራም።ራስህን አውቀህ ነገር ግን ጠላትህን ካላወክ፤ በምታገኘው ድል ልክ በሽንፈትም ትሰቃያለህ።ራስህንም ጠላትህንም የማታውቅ ከሆነ በየውጊያው ሜዳ እጅ ትሰጣለህ›› ሲል ምክረ ሀሳቡን አስቀምጧል፡፡
እኔ ለሰን ቲዙ የምመልስለት ምላሽ ይህ ነው።‹‹በጠብ ወቅት ውጤቱን የሚወስነው ወሳኙ ጉዳይ የሚጣሉት ውሾች መጠን አይደለም፤ በውሾቹ መካከል የሚደረገው የጠብ መጠን እንጂ›› በምዕራባውያኑ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ጦርነት ኢትዮጵያ ትንሿ ተቀናቃኝ ናት።በቅኝ ግዛት ጦርነት ውስጥ ድል የሚገኘው ኢትዮጵያ የጠላቷን ጥንካሬ ስታውቅ፤ ጠላቷን የምትረታው ደግሞ በራሷ የውስጥ አንድነት ነው።ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችው ‹‹የኢትዮጵያ አንድነት አይሸነፍም›› በሚለው መርሆ ነው።ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው እና ሉዓላዊነታቸው ማንኛውንም ዋጋ ይከፍላሉ እንጂ አይሸነፉም የሚል እምነት አለኝ ፡፡
ዘመን፡- ህወሓት ዓለም አቀፉን ማኅብረሰብ ማደናበር የቻለበትን አቅም ያገኘው ከኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ አቅም ውስንነት ነው ወይስ ህወሓት ካለው መዋቅር ብልጫ፣ መንግሥትስ አቅሙን ከማሻሻል አንጻር ሊወስዳቸው የሚገቡ የአጭርና የረጅም ጊዜ እርምጃዎች ምን መሆን አለባቸው?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- የትህነግ የዲያስፖራ ርዝራዦች ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በመቃወም ውጤታማ ዘመቻ አድርገዋል።እነዚህ አካላት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚተውኑ ባለስልጣናትን የሚያግባቡ /ሎቢስቶችን/ እና የህዝብ ግንኙነት ስራን የሚሰሩላቸውን በመቅጠር ‹‹ተጎድቻለሁና ጫና ደረሰብኝ›› ትርክት አሰራጭተዋል።የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን እንደ እነ ቢቢሲ፣ሲ ኤን ኤን እና ኒው ዮርክ ታይምስ የትህነግን የሀሰት መልዕክት በመቀበል አስተጋብተዋል፤ በዚህም ድርጊታቸው ኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡
እነዚህ የመገናኛ ብዙሃኑ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ምግብን እንደ አንድ የጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው›› ሲሉ አስተጋብተዋል።ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ሌሎች የተለያዩ አስፈሪ ታሪኮችን ፈጥረዋል።በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ይህ ሁሉ ድራማና ድርጊት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ያሉት ነጮች በአገሪቱ ላይ ጫና እና መገለል እንዲደርስ በማቀድ ነው።
እውነታው ግን በአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና አውሮፓ ያሉት ነጮች በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ያመጡትም ሆነ የፈየዱት ተግባር የለም፤ በአፍሪካም ተመሳሳይ ነው።በሌላ ደረጃ ደግሞ የትህነግ ዲያስፖራ ርዝራዦች የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎቹ /ነጮች/ ኢትዮጵያ ላይ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጫና በመፍጠር ያተርፉናል በሚል ምኞት እየተንቀሳቀሱ ነው።ትህነግ የነጮችን የበላይነት አምኖ የተቀበለ ቡድን ነው።ኢትዮጵያውያን ደግሞ የነጮች የበላይነትን አይቀበሉም፤ እምነቱም የላቸውም፡፡
ለእኔ የትህነግ ርዝራዥ ዲያስፖራ በሚከፍላቸው ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚያደርገው ዘመቻ በምን ተጠናቀቀ? ብዬ ስጠይቅ ያገኘሁት ምላሽ ይህ ነው። በአሜሪካ በኩል የቪዛ እገዳ አግኝተዋል፤ በባይደን አስተዳደር ደግሞ የልማት እና ለደህንነት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ እንዲከለከል አድርገዋል።በባይደንአስተዳደር ጥያቄ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ብድር እና ድጋፍ እንዲያቋርጥ አድርገዋል።በአሜሪካን ሴኔትም ጥርስ የሌለው ህግ እስከ ማስወጣት ደርሰዋል።ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያን ለማሳጣት ለአንዳንድ የአሜሪካ ምክር ቤት ሴናተሮች እና ተወካዮች ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ።እነዚህን ሁሉ ውጤት ያገኙት በጣም ብዙ ሚሊየን ዶላር ከፍለው ነው። በእኔ እይታ ግን ‹ብዙ የውሻ ጩኸት ነገር ግን አነስተኛ ንክሻ ነው› ብዬ እወሰደዋለሁ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የትህነግ ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እየተፋለመ ያለው በወቅቱ በሚያቀርበው ፋክት ቼክ፣ በሚሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችና ማብራሪያ ነው።እዚህ ላይ እውነት መነገር አለበት።ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በተለይ የምዕራቡን ዓለም ማህበረሰብ እውነተኛ መረጃ በማቅረብ ጫና መፍጠርና በምዕራቡ ዓለም ያለውን ኢትዮጵያዊ ማስተባበር የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኃላፊነት ነው።የኢትዮጵያ መንግስት ይህን መሰሉን ተግባር ሊፈፅሙ የሚችሉ የዲያስፖራ ማህበረሰብን አላደራጀም፡፡
ለአብነት ኢትዮ-አሜሪካውያኑ ለኮንግረስ አባላቶቻቸው ቅርበት አላቸው።በዚህም ከታች ጀምረው ህግና ፖሊሲ አውጪዎች ላይ ጫና መፍጠር ይችላሉ።ከዚህ በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ ትህነግ ከፍሎ የሚያሰራጨው የተሳሳተ መረጃ ሀሰት ለመሆኑ መልሶ ለማስተካከል እና ለማጥፋት ይህ ማህበረሰብ በጣም የቀረበ ነው።ስለዚህ በቦታው ያሉ የማህበረሰብ መሪዎችን በማስተባበር ፖሊሲ አውጪዎች ላይ ጫና መፍጠር እንችላለን፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ግን በዚህ ልክ ተደራጅቶ ነው ያለው ማለት አይቻልም።የተማረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በራሱ የሚተማመን አይደለም።በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህን ኃላፊነት በመውሰድ በቁርጠኝነት ሳያቋርጥ ሚናውን መወጣት መቻል ላይ እጥረት አለበት።ይህን ሰፊ ማህበረሰብ ጥቂት የትህነግ የዲያስፖራ ርዝራዥ ከሚያከናውኑት ተግባር ጋር አነፃፅረው እስኪ፤ የሚሰሩት ካላቸው ብዛት እና አቅም በላይ ነው።ብዛት የላቸውም፣ የተደራጁ ሆነው ዓለም አቀፍ ጫናውን ለመፍጠር ለበርካታ አስርት ዓመታት ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፉትን ገንዘብ እየተጠቀሙ ነው።የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ከትህነግ ርዝራዥ ዲያስፖራ ልንማር ይገባል።መሰረቱን ማጠንከርና ማፅናት፣ መደራጀትና አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው፡፡
ዘመን ፡- ከህወሓት ጎን የቆሙ ምዕራባውያን ሀገሮች ከ100 ሚሊየን በላይ ቁጥር ካለው ሕዝብ ፍላጎት ይልቅ ለህወሓት አሸባሪ ቡድን ድጋፍ ለመስጠት ያሳዩት አቋም ከምን የመነጨ ነው? ከኢትዮጵያስ የሚፈልጉት፣ኢትዮጵያ ልታቀርብ ያልቻለችው ፍላጎታቸው ምንድነው?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- ምዕራባውያኑ ከአሸባሪው ህወሓት ጎን በመሆን የኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆኑበት ምክንያቶች በርካታ ናቸው።የመጀመሪያው፤ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለእርሷ ታዛዥ የሆነ መንግስት እንዲኖር ከመፈለግ የተነሳ ነው።በዚህ መልክ የሚፈጠር መንግስት ደግሞ ‹‹ዝለል›› ሲባል ‹‹ምን ያህል ልዝለል?›› የሚል መንግስት እንጂ ራሱን ችሎ የሚቆም መንግስት እንዲኖር አይፈልጉም።ለበርካታ አስር ዓመታት ህወሓት ታማኝ የምዕራባውያኑ የውክልና ጦርነታቸው አገልጋይ በመሆን አፍሪካን ጭምር ሲጎዳት ቆይቷል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ህወሓት ኢትዮጵያን በመከፋፈል ደካማ እንድትሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ መሳሪያቸው ነበር።አሜሪካውያኑ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያደገች እና እየበለፀገች መምጣቷን እጅጉን አይፈልጉም።ሶስተኛው ምክንያት ህወሓት ኢትዮጵያን በአባይ ግርጌ ለመሸጥ አይኑን የማያሽ ሀይል ብቻ ነው።ግብፅና አሜሪካ የህወሓትን ወደ ስልጣን መምጣት በጣም ይፈልጋሉ።ምክንያቱም የሁለቱንም አገራት ጥቅም የሚያስከብሩ የውል መስመሮችን በማስመር ግድቡን እንዲጠቀሙበት ያደርጋቸዋል፡፡
አራተኛው ምክንያት በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ቀጠናዊ አቅም መፍጠር ለምዕራባውያኑ ትልቅ ስጋት ነው።ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ጎረቤት አገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ቢፈጥሩ ለምዕራባውያኑ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በተቃርኖ በመቆም ‹የማይደፈር አለት› ይሆኑብናል የሚል ስሜት አላቸው፡፡
ዘመን ፡- አሁን የመንግሥት ኃይል ከትግራይ ክልል ለቆ ደጀን ወደሚለው አካባቢ ማፈግፈጉን እንዴት ይገመግሙታል፤ የሚፈለገውን ውጤት ስያመጣል ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ ፡- የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ከታወጀ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ ወጥቷል።እንደ ወታደራዊ ታሪክና ስትራቴጂ ተማሪነቴ፣ ሠራዊቱ ትግራይን ለቆ መውጣቱ ተገቢና ትክክለኛ ነው።ከወታደራዊ ስትራቴጂ ባገኘሁት እውቀት መሠረት ስኬታማ ውጊያ መሠረታዊ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት መስጠትን ይሻል።ወታደራዊ ዘመቻ ግልጽና ተጨባጭ ዓላማ ሊኖረው ይገባል።የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በነበረው ሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የመሩ የእዝ መሪዎችን ለመያዝ የህግ ማስከበር ዘመቻ አካሂዷል፤ የህግ ማስከበር ዘመቻው በትግራይ ወይም በትግራይ ህዝብ ላይ የተከፈተ ውጊያ አልነበረም። ዘመቻው በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የተገባበት ነበር። በዚህ ዘመቻ ከአብዛኞቹ የህወሓት ቁንጮ ባለስልጣናት መካከል የተወሰኑት ሲያዙ ሌሎች ደግሞ ሞተዋል።በዚህም ትልቁ የህግ ማስከበር ዘመቻው ዓላማ ግብ መቷል፡፡
ሁለተኛ፣ በጦርነት ሜዳ ጠላትን ድል ለመንሳት የትኛውንም ምቹ አጋጣሚ መጠቀምና ጀብዱ መፈጸም የግድ ይላል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም በተዋጋባቸው የጦርነት ሜዳዎች ሁሉ ህወሓትን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ የድሮን ቴክኖሎጂን ጨምሮ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀሙ ጦርነቱን ድል ለማድረግ በቅቷል።
ሦስተኛ፣ ሠራዊቱ ወደ ጦርነት የገባበትን ዓላማ ካሳካ በኋላ እንደ ወራሪ ኃይል ትግራይን ተቆጣጥሮ የመቆየት ዓላማ አልነበረውም። አራተኛ፣ የመከላከያ ተገቢ በሆነ ሁኔታ ትግራይን ለቆ ሲወጣ በእኔ እይታ፣ አሸባሪው የህወሓት ኃይል መልሶ ግዛቱን ለማስፋፋት በሚሞክርበት ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ እርምጃ ለመውሰድ ራሱን ዝግጁ አድርጎ ነው።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአላማጣና በራያ ቆቦ የሆነውም ይኸው ነው፡፡
በእርግጥ ህወሓት በአሸባሪነት ተግባሩ ቀጥሏል፤ በምኞት ማሸነፉን እያወጀ ነው።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ህወሓት በአሸባሪነት ተግባሩ እንዳይቀጥል አቅሙን እያዳከመና ጨርሶ ለማጥፋት እያጠቃ ይገኛል፤ ይህ ትግል እንደቀጠለ ነው።በሚያሳዝን ሁኔታ ግን አሸባሪው ህወሓት በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት እየተደገፈ ነው።
ዘመን ፡- በህወሓት አሸባሪ ቡድን ፕሮፓጋንዳ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡– የትግራይ ህዝብ ለአስርት ዓመታት በሁለት ለመምረጥ ከባድ በሆኑ አጣብቂኝ መካከል ቆይቷል። ህወሓት በስልጣን በቆየበት ጊዜ ሕጻናትን በየቀኑ መድፍ ሲቀልብ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ህጻናትን በግዳጅ ወደ ውትድርና በማስገባት የአሸባሪነት ተግባሩ መጠቀሚያ አድርጓቸዋል።ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ነው የታገልኩት ይላል እንጂ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ የመጠጥ ውሃ እንኳ አላገኘም። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹን ላይ እምነት እንዳይኖረውና እንደተነጠለ እንዲያስብ “ሊገድሏችሁ ነው ሊያጠፏችሁ ነው” በሚል ስብከት በህዝቡ መካከል የጥላቻና የአፍራሻ አስተሳሰብ እንዲቀረጽ አድርጓል፡፡
ህወሓት ለትግራይ ህዘብ አልቃይዳ ለአረብ ሀገራት እንደሆነው ነው እየሆነ ያለው፤ አልቃይዳ ደም የተጠማ አሸባሪ ድርጅት እንጂ በምንም ሁኔታ አረቦችን ሊወክል አይችልም።ህወሓትም በየትኛውም አግባብ የትግራይ ህዝብን አይወክልም፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላም ቢሆን፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር የመኖርና ያለመኖር እድሉን ራሱ የትግራይ ህዝብ ነው።የትግራይ ህዝብ በህወሓት አስተዳደር እንደየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ ተጎድቷል።የትግራይን ህዝብ ከዚህ የግፍ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የትግራይ ምሁራንና መሪዎች ለእነኚህ መሪዎች በጋራ በመቆም ህወሓት እውነታውን እንዲረዳ ማድረግ አለባቸው።ታሪክ እንደሚነግረን ቡድንተኝነት ፍጻሜው ራስን ማጥፋት ነው።ለህወሓት ቡድን ነጻነት መስጠት ደግሞ ለትግራይ ህዝብ ጥፋት ነው።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያውን የትግራይ ህዝብና ህወሓትን አንድ ለማስመሰል የሚደረገውን የሀሰት ንጽጽር መቀበል የለባቸውም።እንደ መርህም የትኛውንም ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚገባውን ክብር መስጠት እርስ በእርስ መቻቻል እንጂ በማንነቱ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖቱ ወ.ዘ.ተ መመዘን አይገባም።በእርግጥ አንዳንድ በትዕቢት የተሞሉ ግለሰቦች እንዲህ ያለውን ሐሳብ እንደ አላዋቂነት ከዚህም ሲያልፍ፣ እንደ ሞኝነት ሊቆጥሩት ይችላሉ።ትዕቢት ደግሞ የደካማነት ምልክት በመሆኑ ለውድቀት ጋብዟቸዋል።ፍቅር ማሳየትና መቻቻል የድክመት ምልክት ሳይሆኑ፣ ይልቁኑ የጥንካሬ ማሳያዎች ናቸው።ፍቅር በዓለም ላይ ትልቁ ኃይል ነው።ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ብሒል ሊያዳብር ይገባል።ይህ ማለት ለኔ፣ ጎረቤትህን አግዝ፣ ስለ እርሱ እንደሚያገባህ አሳየው፣ በማንነታቸው አታግላቸው ማለት ነው።ይህን ማድረግ ግን፣ ጭፍን ጥላቻና አለመተማመን ባለበት ቀላል አይሆንም።“ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም” እንደሚባለው፣ ህወሓት ለአስርት ዓመታት የገነባውን የብሔር መከፋፈል እና ጥላቻ በአንድ ቀን የሚፈርስ አይደለም።ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጥላቻን ጡብ፣ ጫፍ የወጣን አለመተማመንና የጥላቻን ቤት ያቆመውን ምሰሶ ማፍረስ፣ በህወሓት የተገነባውን አሳፋሪ ነገር ሁሉ ማስወገድና በዚህ ፈንታ የፍቅር ግንብ መገንባት ይኖርበታል፡፡
ዘመን፡- የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ የጎረቤት ሀገር ሕዝብ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ እየተፈጠረ ያለው የግንኙነት ሳንካ ተጽእኖው እስከምን ይደርሳል ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- ህወሓት የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የኤርትራም ህዝብ ጠላት ነው።ህወሓት ጦርነቱን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በኤርትራ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽሟል።የኤርትራ መንግሥት ግን የአጸፋ ምላሽ አልሰጠም።ይህንን የሚያበሳጭ ተግባር ችለው ዝም ብለዋል።ህወሓት ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት የኤርትራን መንግሥት ለመጣልና የራሱን አሻንጉሊቶች ለማስቀመጥ ሞክሯል።በእርግጥ ህወሓት እንዲህ ያለው ቀቢጸ ተስፋ ሊኖረው ይችላል።እውነቱ ግን፣ እንዲህ ያለው ነገር ገፍቶ ከመጣ ኤርትራ ድንበር ጥሶ ለሚመጣ የትኛውም አሸባሪ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ብሔራዊ ደህንነቷን ማስከበር ትችላለች።አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሚያደርገው ድርጊት ሁሉ አሜሪካ ከለላ ትሆነኛለች ብሎ ያስባል። ሊሰመርበት የሚገባው ግን የህወሓት ኃይል የኤርትራ መንግሥት ላይ እጁን ቢያነሳ የማይረሳውን ትምህርት እንደሚወስድ ነው።የትኛውም ሀገር በአሸባሪ ሲጠቃ የህወሓት ኃይል ባለው አቅም ሁሉንም ያደርጋል ኤርትራን ለማስቆጣት፤ ነገር ግን ይህ ሞኝነት ነው። የትኛውም ሀገር ምንም ያህል ሽብርተኞቹን የሚያግዘው ኃይል ትልቅ ቢሆን በሽብርተኞች ሲጠቃ ዝም የሚል የለም።ህወሓት ባለ በሌለ አቅሙ ኤርትራን ለማስቆጣት ቢጥርም ይህ ግን በእጅጉ ከባድ ነው።
ዘመን ፡- የህወሓት አሸባሪነትና የአካባቢው ጠንቅ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ከግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን እጅ ከመጠምዘዝ አካሄድ ጋር ምን ያህል የተቀናጀ ነው ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡– አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ እስካልሆነ ድረስ አጠቃላይ ቀጠናውን የሚያተራምስ፣ የቀውስ ሁሉ ምንጭ ስለሚሆን ለዚህ ነገር ተጋላጭ/ምቹ/ ሆኖ የሚቆይ ኃይል ነው። አሸባሪው ህወሓት ከግብጽ ከሱዳንና ከአሜሪካ ጋር ይሄንን ለማድረግ በስውር እንደሚሠራ አያጠራጥርም። ለጊዜው የጥቅምት 3/2020 /እ.አ.አ/ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የተካሄደው ከአሜሪካ መንግሥት ዕውቀት፣ ድጋፍ፣ ጥቅሻ ውጪ እንዳልሆነ ለማስታወስ እፈልጋለሁ።ህዳር 3/2020/እ.አ.አ/ እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት አሜሪካ በራሷ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ትያዛለች፣ እናም የአሸባሪው ህወሓት የጥቃት ውርጅብኝ አስታዋሽ ሳያገኝ በኋላም ‹‹አንዴ ሆኗል እንግዲህ›› ተብሎ የሚታለፍ እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡
ቴዎድሮስ አድሃኖም ሽብርን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከግብጽ ጋር ሲያሴርና ሲያሰላ እንደነበር ማስረጃ አለ። ያ፣ ግን ፍሬ አልባ አካሄድ ነው።ሱዳን በውድቀት ላይ ያለች ሀገር ነች።የሱዳን መከላከያ እና የደህንነት ኃይሎች አንዳቸው አንዳቸውን የሚውጡ ናቸው።የሃምዶክ የሲቪሊ አስተዳደር በስም ብቻ ያለ ነው። ሱዳን በመሠረቱ የሚሊታሪ ጁንታ ሀገር ሆና እጅግ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ችግሮች ያሉባት ሆናለች።በዳርፉር ያለው ግጭት እየተባባሰ ነው።የእርስ በእርስ ጦርነት ሊጭር የሚችል ነው።በአቢዬ ግዛት ያለው ሁኔታም በዚያው ልክ አደገኛ ነው።ስለዚህ ህወሓት በሱዳን በኩል ጦር መሣሪያና መተላለፊያ አገኛለሁ ብሎ ካሰበ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።ሱዳን ለህወሓት ጦር መሳሪያ አቀበለች ማለት የፈጠረችውን ቀውስ ዓይነት ራሷም ልቅመስ ብላ እንደመወሰን ነው።ለማንኛውም እንቅስቃሴ ሌላ አቻ ተቃራኒ ምላሽ አለውና።በመስተዋት ቤት የሚኖሩ ሰዎች ድንጋይ ውርወራ አይጫወቱም።
በሌላ በኩል አልሲሲ የተቀመጠው ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ በሚችል ሁኔታ ውስጥ ነው።የግብጽ ጦር ዊላያት ሲናይ የሚባለውን እስላማዊ የአካባቢ መንግሥት ለመመሥረት በራሱ ያወጀውንና እቅዱንም ለማሳካት የሚታገለውን ታጣቂ ኃይል ማሸነፍ አልቻለም።አልሲሲ ስድሳ ሺህ ያህል የፖለቲካ እስረኞችን ያከማቸበትን የፖሊስ መንግሥት የፈጠረ መሪ ነው።በእርግጥ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የአልሲሲን መንግሥት ጭፍጨፋና የሰብአዊ መብት ጥሰት የማያዩ፣ የማይሰሙ መስለው ያልፉታል፡፡
እንግዲህ ሊባል የሚችለው መደረግም ያለበት የኔዎኮሎኒያሊስት ውሾች ይጮሃሉ፤ ይናከሳሉም፤ የኢትዮጵያ ግመሎች ግን አንድነትና ብልጽግና በሚባለው መንገድ ላይ በክብር፣ በሞገስ፣ በራስ መተማማን ስሜት ይጓዛሉ፡፡
ዘመን ፡- በጣም እናመሰግናለን፡፡
ፕሮፌሰር አለማየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013