የመድረክ ሥሙ ሚኪ ጎንደርኛ ነው፡፡ የሥሙ መነሻም በሕዝብ ዘንድ ታዋቂ ያደረገው ጎንደርኛ የተሠኘ ሥራው ነው፡፡ እውነተኛ ሥሙ ግን ሚኪያስ ከበደ ነው፡፡ ሚኪ እና ጎንደርኛ የተሠኘ ሙዚቃውን አዋህዶ የሚል ሚኪ ጎንደርኛ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠራው ደግሞ ታዋቂው ዲጄ ኪንግስተን ነው፡፡ በተለይ በወጣቱ ዘንድም በሥራው ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለው ሚኪያስ ከበደ (ሚኪ ጎንደርኛ) የዛሬ የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን ነው፡፡
አርቲስት ሚኪያስ የተወለደው እዚሁ መሀል አዲስ አበባ መገናኛ 24 ቀበሌ የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ ስምንት ልጆች ከወለዱት ቤተሠቦቹ መካከል የመጨረሻው ልጅ ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አብዮት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ ከዚያም ተግባረ እድ ገብቶ የኮሌጅ ትምህርቱን ተከታትሎ በሠርቬይንግ ተመርቋል፡፡
ሚኪ የሙዚቃ ፍቅሩ ከልጅነቱ የጀመረ ቢሆንም ከመድረክ ጋር የተዋወቀው ግን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሣለ ነው፡፡ ገና የሦስተኛ እና አራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ አስተማሪ በማይኖርበት ክፍል ጊዜ ሁሉ የክፍሉን ተማሪ በማዝናናት የሚታወቀው ሚኪ፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገባ ደግሞ በወቅቱ በሚማርበት ትምህርት ቤት በሚዘጋጁ የተማሪ ፌስቲቫሎች ላይ መድረኩን ከሚያደምቁ ወጣቶች መካከል አንዱ ሆነ፡፡
ጥሩ የሚለውን የመድረክ ዕድል ደግሞ ያገኘው ብሪቲሽ ካውንስል ባዘጋጀው ዋፕ የተባለ የወጣቶች የውድድር መድረክ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ለስድስት ወራት በዘለቀ ውድድር ላይ በአማርኛ ራፕ አቅርቦ ሁለተኛ ወጣ፡፡ ከዚያ በኋላ የሙዚቃ ሕይወቱ በይፋ ተጀመረ፡፡
ከውድድሩ በኋላም የሙዚቃ ሥራውን በመግፋት ወደ ስቱዲዮ ጎራ አለ፡፡ ጎንደርኛ የተሰኘ ሙዚቃውንም ሠራ፡፡ ሙዚቃው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፈለት፡፡ ከዚያም አልፎ የሱ የመድረክ ሥም ሆነና ሚኪ ጎንደርኛ ተባለበት፡፡
ይህ ተወዳጅነቱ የሞራል መነቃቃት የፈጠረለት ሚኪ ከዚያም በኋላ ‹‹ፍቅር ይስጠን፣ ነይ እንመቻች፣ ሌባ ነው፣ ገረዶ፣ ሸጌ፣ ኢትዮጵያዬ›› የሚሉና ሌሎች ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡ ‹‹ፐ;›› የተሠኘ አንድ አልበምም እንዲሁ ለአድማጮች አድርሷል፡፡
ከነጠላ ዜማዎቹ መካከል ኢትዮጵያዬ ከያሬድ ነጉ፣ ሌባ ነውን ከሣንቾ ጋር የሠራ ሲሆን፤ ነይ እንመቻች ደግሞ ከኮሜድያን ቶማስ ጋር የሠራው ነው፡፡ ኢትዮጵያዬ እስካሁን ከ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተመልካች በዩ ቲዩብ ያለው ሲሆን፤ ሌባ ነው ከ6 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የዩቲዩብ ተመልካች አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያ ሥራው ጎንደርኛም እንዲሁ በዩቲዩብ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተመልካች አለው፡፡
ኢትዮጵያዬ የተሠኘው ሙዚቃው ከሁለት ዓመት በፊት የተለቀቀ ነው፡፡ ሀገሩን ኢትዮጵያን ርሥቴ ማንነቴ ነሽ የሚል ሲሆን፤ ‹‹እረ ሀገሬ እረ ሀገሬ ስትኖሪ ነው መከበሬ›› በማለት ያሞግሣታል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያን ክልሎች ቤቴ ናቸው በማለት አንድነትን ይሠብካል፡፡ ሽጌ በተሠኘው ሙዘቃው እንዲሁ ከድምጻዊ ያሬድ ነጉ ጋር በመሆን በኦሮምኛ እና በአማርኛ የኢትዮጵያዊት ሴትን ውበት ያደንቃል፡፡ ገረዶ በተሠኘው ሙዚቃ የጉራጊኛ ምትን በዳንሶል ምት በማዋሃድ ውብ አድርጎ ሠርቶታል።። ፍቅር ይሰጠን በተሠኘው ሙዘቃው በሀገራችን ያለው ችግር እንደሚያልፍ እና በጎው ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ ጊልዶ ካሣ ባቀናበረው ሌባ ነው የተሠኘ ሙዚቃው ትግርኛ እና አማርኛን በማዋሀድ የኢትዮጵዊት ሴት ውበትን አሞግሷል፡፡
ሥራዎቼ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ማግኘታቸው ጥሩ ሞራል ፈጥሮልኛል የሚለው ሚኪ ይህ ተወዳጅነት ለአዲስ ሥራ እንደገሚፋፋውም ይናገራል፡፡ “በኢትዮጵያ የመዝናኛ ዘርፉ ገና በደንብ አልተሠራበትም ብዬ አስባለሁ” የሚለው ሚኪ በቀጣይም በሚችለው አቅም አዳዲስ ሥራዎችን በማቅረብ ተሣትፎውን ማሣደግ እንደሚፈልግ ይገልጻል። በሙዚቃው ከሀገር ውስጥ ሁሉንም ክልሎች በኮንሠርት ያዳረሰ ሲሆን፤ ከሀገር ውጭ ደግሞ እሥራኤል እና ኳታርን ጨምሮ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትን በኮንሠርት ጎብኝቷል፡፡
ከወ/ሮ ማህሌት ዲባባ ጋር ትዳር የመሠረተው ሚኪያስ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነው፤ ሚኪ የልጁንም ሥያሜ ገብሬላ ብሏታል፡፡ ሚኪ እና ማህሌት እንዲቀራረቡ ሙዚቃ ድርሻ ነበራት፡፡ ማህሌት የፋሽን ዲዛይነር ስትሆን፤ ሚኪ ከሌላኛው ድምጻዊ እና የልብ ወዳጁ ያሬድ ነጉ ጋር ለአዲስ የሙዚቃ ቪዲዮ ልብስ ለመግዛት ወደ ወ/ሮ ማህሌት ሱቅ ጎራ ባለበት ወቅት ነበር የተያዩት፡፡ በዚያው የተጀመረ ግንኙነት ቀጥሎ ባለፈው ዓመት በኮሮና ወቅት ለሠርጋቸው ያስቀመጡትን ገንዘብ ለኮሮና ተጠቂዎች ድጋፍ በመለገስ ተፈጽሟል፡፡
ሚኪ በትዳሩ ደስተኛ እንደሆነ እና ትዳሩ ለሥራው መሣካት ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራል፡፡ ከባለቤቱ፣ ከእናቱ እና ቤተሠቦቹ ባለፈ በሱ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ብዙ ሰዎች ድርሻ እንዳላቸውም የሚናገረው ሚኪ፣ በሥም ዘርዝሬ ብጠራ የምረሣው ሰው ሊኖር ስለሚችል ማንንም ላለማስቀየም እንዲሁ ብዙ ናቸው ብል ይሻላል ይላል፡፡
በሚኪ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ባለድርሻ የሆኑ ሰዎች ብዙ የመሆናቸውን ያህል የሚያደንቃቸውም የሙዚቃ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከበፊቶቹ ማንን አድንቄ ማንን እተዋለሁ ሁሉም ለኔ ምርጥ ናቸው ይላል፡፡ ነገር ግን ከሱ የአዘፋፈን ሥልት አንጻር ተጽዕኖ የፈጠሩበት ጆኒ ራጋ እና ላፎንቴኖች እንደሆኑ ነግሮናል፡፡
የእረፍት ቀንህን በምን ታሣልፋለህ ብለን ጠየቅነው፡፡ ”የእረፍት ቀኔን የማሣልፈው ብዙውን ጊዜ በሁለት ነገሮች ነው፡፡ አንደኛ ኳስ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ ኳስ በማየት እና በመጫወት አሣልፋለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የእረፍት ቀኔን የማሣልፈው ከቤተሠቦቼ እና ጓደኞቼ ጋር በመሆን ነው፡፡ ከነሱ ጋር ቁጭ ብለን ሥናወራ እና ስለ ብዙ ነገር ስንመካከር ደስ ይለኛል” ብሏል፡፡
የማን ደጋፊ ነህ ብለን ጠየቅነው፤ “ከሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነኝ፤ ከውጭ ደግሞ የአርሴናል ደጋፊ ነኝ” አለን፡፡ እግር ኳስ ከእረፍት ቀን መዝናኛውም ባለፈ ግን ለሙዚቃ ሥራው የሚፈልገውን ትንፋሽ መያዙን የሚያረጋግጥበት መንገድም ነው፡፡
ለአንባቢዎች እና ለአድናቂዎች የሚያስተላልፈው መልዕክት ካለ ጠየቅነው። ”ሁሌም ወደ አዕምሯችን የሚገቡትን ነገሮች መርጠን ማስገባት አለብን፡፡ አዎንታዊ ነገር የሚሰጠንን፣ በጎ ነገር ውስጣችን የሚፈጥረውን ነገር ብቻ መቀበል አለብን፡፡ አጠገባችን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር መደጋገፍ አለብን፡፡ በውስጣችን ደግሞ ራዕይ መያዝ እና ሁለጊዜም ለዚያ መትጋት አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፈጣሪ ጋር በቀና ልብ መገናኘት አለብን ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013