በዓለም ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት እየተበራከቱ መምጣታቸውን መረጃዎች ይመላክታሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በበለጽጉትና በታዳጊ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነትና ስደተኞች ያለ ገደብ ድንበር አቋርጠው መግባታቸው እንዲሁም በስደተኞች ላይ ጥላቻን መሰረት ያደረጉ ወንጀሎች በመስፋፋታቸው እና በሌሎችም ምክንያቶች ነው። ከዚህም በተጨማሪ በድህረ ገፆችና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ ወሬዎች ( fake news) በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ መምጣታቸውም በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች የፈጠሩት ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ እየፈጠረ ያለውን ተጽዕኖ በመከላከልና በመቆጣጠር እንኳን ለታዳጊ ሀገራትን ይቅርና የበለፀጉትንም ሀገራት ስጋት ላይ የጣለ እጅግ አዳጋች እየሆነ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያም አሁን ላይ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እየጨመረ መምጣቱ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትሉት ግጭትና ጉዳት ለእኩልነት፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ጠንቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የሚያስችል ህግ ተደንግጓል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55(1) መሰረት ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኝቱ፤ የጥላቻ ንግግርና የሐስተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትሉት ግጭትና ጉዳት ለእኩልነት ፣ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ እና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ጠንቅ በመሆኑ፤ መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን ዓላማ ለማስፈጸም የሚወጡና ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸው በመገንዘብ የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ ወጥቷል፡፡
ባለፈው ዓመት የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዓ.ም ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሄርን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማድረግ፤ መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበር እና መግባባትን ማበረታታትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማጎልበት፤ የጥላቻ ንግግርን፣ የሐሰተኛ መረጃና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የውሸትና አሳሳች መረጃዎችን ስርጭትና መበራከትን ለመቆጣጠርና ለመግታት ያለመ አዋጅ መሆኑን ይገለጻል፡፡
በአዋጁ መሠረት የጥላቻ ንግግር የሚባለው በአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፡ ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።
በተመሳሳይ ሐሰተኛ መረጃ ማለት ውሸት የሆነ እና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሐሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው ይላል።
በአዋጁ የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀል በሚፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊ ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችሉ ቅጣቶች ተደንግገዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአዋጁ አንቀጽ 7 ስር የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀሎች የሚያስቀጡትን ቅጣቶች ተደንግገዋል፡፡ አዋጁን ጥሶ የተገኘ አካል የሚበየንበትን ቅጣት በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡
ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ 4 የተከለከለውን የጥላቻ ንግግርን ወንጀሎች መፈጸም እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከመቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚያስቀጣ፤ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 የተከለከሉት ተግባራት በመፈጸማቸው የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ በአንቀጹ የተከለከሉትን ተግባራት የፈጸመ ሰው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል ሲል በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
በዚሁ አዋጅ መሠረት ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 መሰረት ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከሀምሳ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከተውን የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ አስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ወይም መቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል፡፡
በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተከለከለው ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተግባር በመፈጸሙ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ቅጣቱ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
በተመሳሳይ ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂ የሆነ ሰውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምንና የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል ነው የሚያስቀምጠው።
ከዚህ በተጨማሪ በዚህ አዋጅ የተከለከሉት ተግባራት የተፈጸሙት በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ከሆነ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተካተቱት በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የሚደረጉ ወንጀሎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በአንቀጽ 42 እና አንቀጽ 47 መሠረት ተግባራዊ እንደሚሆኑ አስቀምጧል። ስለዚህ የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ምክንያት በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት በመታገል በጋራ ለመከላከል የሁላችንም ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013