አዲስ አበባ፤- በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ የጎዳና ልጆችን ከጎዳና በማንሳት ሕይወታቸውን ለመለወጥ በጀመረው ሥራ ፈቃደኛ የሆኑ 3ሺ147 የጎዳና ተዳዳሪዎች ተነስተው ወደ ማገገሚያ መግባታቸው ተገለጸ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በጎዳና ተዳዳሪነት የሚኖሩ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን፤ እነዚህን ዜጎች ከጎዳና ላይ ለማንሳትና ቀጣይ ሕይወታቸውን ለማስተካከል ከተማ አስተዳደሩ አቅዶ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሥራ እየሰራ ይገኛል።
አቀባበሉን በተመለከተ ስምንት ከሚደርሱ የተለያዩ ክፍለከተሞች 3‚147 የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን በአንድ ቀን በማንሳት ወደ ተለያዩ የማገገሚያ ተቋማት ማስገባቱን ኃላፊዋ ገልጸው፤ በመጀመሪያው ሳምንት ልጆቹን የማረጋጋት፤ ምግብና አልባሳት የማቅረብ፤ እንዲሁም ንፅህናቸውን የመጠበቅና ልብሳቸውን የመቀየር ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ በሁሉም የማገገሚያ ተቋማት ያሉትን ልጆች የመለየት ሥራ ማለትም፤ ከፍተኛ ሱስ ያለባቸውን ከሌሎቹ ጋር አንድ ላይ እንዳይሆኑ በመለየት የምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል። በተለይም ወደቤተሰብ ለመመለስም ሆነ በሚደረግላቸው እገዛ በቀጣይ ከጎዳና ሕይወት ለመውጣት በስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑም እየተሰራ ነው። የቢሮ ኃላፊዋ፤ አብዛኞቹ የጎዳና ልጆች በጣም ሕፃናት፤ 90 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከክልል የመጡ እንደሆኑ ገልጸው፤ ወደቤተሰብ ተቀላቅለው ትምህርታቸውን እንዲማሩ የማሳመንና ፈቃደኝነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው፤ ብለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የመጡበትን ቦታ የመለየትና ቤተሰቦችንም አግኝቶ የማሳመን፤ እንዲሁም ልጆቹን ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፍልሰት ዓለማቀፋዊ ባህሪ ያለው በመሆኑ አሁን በተጀመረው ሥራ ብቻ ሙሉ ለሙሉ የጎዳናን ልጆች በማንሳት ጎዳናን ነፃ ማድረግ አይቻልም። ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ እንዳይቀጥል መከላከሉ ላይ መሰራት አለበት የሚሉት ኃላፊዋ፤ ኅብረተሰቡ የጎዳናን ሕይወት እንደ አማራጭ እንዳይወስድና ወደ ጎዳና እንዳይወጣ የመከላከልና ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ፍሬ ህይወት አወቀ