ዘላቂ መቀመጫዋ የነበረውን ብሄራዊ ሙዚየምን ለቅቃ ጊዜያዊ መዳረሻዋ ወደሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ በሰረገላ ታጅባ ስታመራ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ‹‹ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ…እናት አገር ኢትዮጵያ…›› የሚለውን ጥዑም ዜማ ከጎኗ ሆኖ ያስደምጥ ነበር ፡፡ በምክር ቤቱ ቅጥር ግቢ ደግሞ ‹‹የሺ ዓመታት የአፍሪካ ገናና፤ ከብራ የኖረች በዓለም ዙሪያ ገንና፤ ይታየኛል ዳግም እንደገና ኢትዮጵያ የዓለም አውራ ሆና›› የሚለው ዜማ ከፍ ብሎ ተደመጠ፡፡ በመሃል ግን በቅጥር ጊቢው ያለው ሸኚ እናቱ ከገበያ እንደምትመጣ ህፃን መግቢያ በሩን በንቃት ሲመለከት ቆየና በመጨረሻም የሰው ዘር ሁሉ መነሻ የሆነችው ሉሲ በታላቅ ክብር ወደ ውስጥ በመዝለቅ በአሸኛኘት ስነ-ስርዓቱ ከታደሙት ፊት ለፊት ታየች፡፡ ሉሲ፤በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከሰቷ ምስጢር ‹‹ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር›› የሚል መርሃግብር በመቀረፁና የአሸኛኘት ስርዓት በመካሄዱ ነው፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳሁን እንደተናገሩት፤የጉዞው ዓላማ ኢትዮጵያውያን ቀድሞ የነበራቸውን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን መልሶ ለማምጣትና ተፈጥሯቸው ያልሆነውን ዘርኝነትና መከፋፈልን ለማጥፋት በመታሰቡ ነው፡፡ ‹‹ዘረኝነትና አለመግባባት የኢትዮጵያውያንን ጠንከራ አንድነት የሚያላላ ነው፡፡ ይህን ወደ ነበረበት ሊመልስ የሚችለው ገመድ ደግሞ ባህላችንና ቅርሶቻችን እንዲሁም ኃይማኖቶቻችን ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር የተፈበረከው ከዚህ ነው፡፡ በተለይ ኃይማኖታችንና ባህላችን ለሁሉም ነገር ፋብሪካ ናቸው፡፡››የሚሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ከዚህ የምናወጣቸው ምርቶቻችን ደግሞ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅርን የሚያመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን እያቆጠቆጠ ያለውና አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን የሚያቆሽሸው ከነበረንን ከራሳችን ባህልና እምነት ስናፈነግጥ ነው፡፡›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ዶክተር ሒሩት፣ ‹‹ወደራሳችን ማለትም ወደ ባህላችን ወደ እምነታችንና ወደ ቅርሶቻችንና መነሻችን ተመልሰን ወደነበርንበት ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር መምጣት እንችላለን የሚለውን ለማሳየት ተጨባጭ የሆነችውን ሉሲን ይዘን ወደ ህዝቡ ለመሄድ አስበናል፡፡›› በማለት ገልፀዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ለዚህ ጉዞ አስተባባሪው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ የማደራጀት፣ የመምራትና የማስተባበር ስራውን ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይዟል፡፡ ሰላም ሚኒስትር ደግሞ የሰላሙንና የደህንነት ስራውን በመምራት እየተገበሩት ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ ሦስቱም በበጀት በመደጋገፍ ጉዞውን ስኬታማ ያደርጉታል፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት የከበረ፣ የማንነታችን መገለጫ፣ የጀግንነታችን ምልክት ከፍታ እንዲሁም ሁላችንንም የሚያስተ ሳስረን ጠንካራ ሰንሰለት ነው፤ አባቶቻችን ያስረከቡን አብሮነት አንዱ ለአንዱ መድረስ ነው፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አፈ ጉባኤው፣ ‹‹ዓለም አጥንቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሎ ዝምድናችንን እየነገረን ባለንበት ወቅት እኛ ደግሞ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮችን ከለላ እያደረግን አንድነታችንን፣ ፍቅራችንንና አብሮነታችንን ከሚፈታተኑት አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ውስጥ መሆናችን አንገታችንን የሚያስደፋ መሆኑን ተገንዝበን ሰላሟ የተረጋገጠና ብልጽግና የሰፈነባት አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ሁላችንም ድርሻችንን ለአፍታም ሳንዘነጋ መወጣት ይኖርብናል፡፡›› በማለት አሳስበዋል፡፡
‹‹በአንድ ቤተ ከርስትያንና መሲጂድ ውለን፣ በአንድ ትምህርት ቤት እውቀት ሸምተን፣ በአንድ ገበያ ተገበያይተን የኖርንና እየኖርን ያለን ህዝቦች ተለያይተን ላንለያይ ድርና ማግ ሆነን በሚያምር ህብር የተሰራን ነን፡፡›› ሲሉ አስረድተው፤ ‹‹ዛሬ እያቆጠቆጡ ያሉት የዘረኝነት፣ የመለያየትና የአግላይነት አመለካከቶች በታሪካችን ተቀባይነት የላቸውምና የሚበጀንና የሚያምርብን ፍቅርና አብሮነታችን ነው፡፡›› በማለት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔን ወክለው የተናገሩት የጉባዔው ዋና ጸሐፊ መጋቤ ዘሪሁን ደጉ እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ የኃይማኖት አገር ናት፡፡ ይህ በዓለም ላይ የተመሰከረ ትልቅ አኩሪ እሴቷ ነው፡፡ ኃይማኖት ከሰላም ተለይቶ፣ ሰላም ደግሞ በውስጡ የሌለበት ኃይማኖት ሊኖር አይችልም፡፡ ኃይማኖት የሰላም መሰረት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለሺ ዓመታት ያቆማትና በአብሮነት እንድትዘልቅ የሚያደርጋት ይኸው ነው፡፡አንዱ ኃይማኖት ከሌላው ኃይማኖት ጋር በጋራ እንዲቆም እሴት ብቻ ሳይሆን ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለሌላው የዓለም ክፍል በምሳሌነት የምትጠቀስ አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት፡፡
‹‹ጥላቻና መለያየት ከወዴት እንደመጣ ሳይታወቅ በህዝቡ መካከል መከሰቱ ግራ አጋብቶታል፤ ምክንያቱም አገሪቱ የምትታወቀው በሰላሟና በአብሮነቷ በመሆኑ ነው፡፡ ስንሰብክ የነበርነው ሰላምና አንድነትን በመሆኑም ያለመግባባት ችግር ሲመጣ መቋቋም ያቃተን ለዚህ ነው፤ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ለመለያየት፣ ለጥላቻ፣ ለግጭት አንመችምና ወደቀድሞው ሰላማችንና አንድነታችን መመለሱ ነው በአብሮነትና በመከባበር የሚያኖረን፡፡›› ይላሉ፡፡
‹‹ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር›› በሚል መርሃግብር የተዘጋጀው ጉዞ የሚደረገው በአገሪቱ በሚገኙ ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሲሆን፣ በየዋና ከተሞቻቸው እና በከተሞቹ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም የሚከናወን ነው፡፡ ቀዳሚው ጉዞ የሉሲ መገኛ ቦታ ከሆነው ከአፋር ሰመራ የሚጀምር ሲሆን፣ የጉዞው መጨረሻ አዲስ አበባ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሉሲ የአገር ውስጥ ጉዞዋን እንዳጠናቀቀች ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ትጓዛለች፡፡ የአገር ውስጥ ጉዞዋ በሦስት ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ከተማ ለአምስት ቀን ትቆያለች ተብሎ ይታሰባል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ለምን ያህል ጊዜ እንደምትቆይ በቀጣይ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
በሉሲ የአሸኛኘት ስርዓት የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011