በኢትዮጵያ ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አቋምን ማራመድ መብት ቢሆንም፤ ልቀው የወጡት የዜግነትና የብሄር የፖለቲካ አስተሳሰቦች ግን በተቃርኖ የተሞሉ በመሆናቸው፤በተለይ ከዜግነት ይልቅ የብሄር ፖለቲካ የበላይነትን እያገኘ በመምጣቱ የተቃርኗቸው መዳረሻ አሳሳቢ ሆኗል።። በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምርት ቤት ኃላፊ አቶ ደርሶልኝ የኔአባት እንደሚሉት፤ የዜግነት ፖለቲካ በአብዛኛው በሰለጠኑት በምዕራባውያን አገራት የሚቀነቀን ሲሆን፤ በግለሰቦች ነጻነትና በዜጎች እኩልነት ላይ የተመሠረተ ነው።። የሰለጠነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተደርጎም ይወሰዳል።። ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ በየትኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ የሚሆንበት እንዲሁም ከየት መጣ፣ የትኛው ብሄር ነው የሚለውን ግንዛቤ ውስጥ የማያስገባ ነው።። በኢትዮጵያ ይህ አስተሳሰብ እየተዳከመ በመምጣቱ በምትኩ በአሁኑ ወቅት ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ወደ ብሄር ፖለቲካ ያደላ በመሆኑ የአገሪቷ እጣፈንታ አሳሳቢ ሆኗል።። እንደ አቶ ደርሶልኝ ማብራሪያ፤ የብሄር ፖለቲካ ዜጎች ብሄራቸውን እንደመነሻ ከዚህ አልፎም እንደመከታ የሚወስዱበት፤ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውም ሆነ አደረጃጀታቸው ብሄራችን ነው የሚል ማእቀፍ ውስጥ የሚያስገቡበት ሂደት ነው። መብቶቻቸውን በብሄር የሚጠይቁበት፣ የራሳቸው ብሄር ሲጎዳ የበለጠ የሚቆረቆሩበት፣ ሌላው ብሄር ሲጎዳ የማይመለከታቸውና የዜግነት ፖለቲካ አስተሳሰብን በራቀ መንገድ የሚገነዘቡበት ፖለቲካዊ አሰራርን እየተከተሉ ነው።
‹‹የዜግነት ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተከታይ የለውም። አስተሳሰቡ እንዲዳብር ከፍተኛ ስራን የሚጠይቅ ነው። የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመንግስት ጫና እና በራሳቸው የአመራርነት ችግር እየተዳከሙ መጥተዋል። እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተስፋ ሊያሳዩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን የዜግነት ፖለቲካን አስፋፍቶ ብዙ ተከታይ እንዲኖረው ለማስቻል ረጅም ጊዜ ያስፈልገዋል። ይህንን ለማድረግ ህገ መንግስቱ መቀየር ይኖርበታል። መንግስት ራሱ ኢህአዴግ የሚለውን ፓርቲ ከብሄር ተኮር በዘለለ መልኩ በማደራጀት ለሌሎች ፓርቲዎች ምሳሌ መሆን መቻል አለበት። ከዚህ ውጭ አሁን ባለው ተጨባጭ የፖለቲካ ትርክት የዜግነት ፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው ድጋፍ የደከመ ነው።›› በማለት አቶ ደርሶልኝ የሁለቱን ፖለቲካዊ እሳቤዎች አሁናዊ ገጽታ ገልጸዋል።
የዜግነት ፖለቲካ አስተሳሰብ እየወደቀ ነው የሚሉት አቶ ደርሶልኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ሲመዘኑ አደረጃጀታቸውና ህዝባዊ መሠረታቸው ብሔርተኝነት መሆኑ የብሄር የፖለቲካ እሳቤ የበላይነት ጎልቶ እንዲታይ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹በተለይ የብሄር ተኮር አስተሳሰብን መነሻ አድርገው ያልተስማማንባቸውን የታሪክ አስተሳሰቦች በመምዘዝ ድጋፍ ለማግኘት የሚጥሩ አካላትም አሉ›› ይላሉ አቶ ደርሶልኝ።
እነዚህን ሀሳቦች አንድ ላይ ለማስኬድ የሚሰናሰሉበት መንገድ፣ ህጋዊ ማእቀፍ፣ እንዲሁም በዚህ ውስጥ ያሉት ተቋማዊ አደረጃጀቶች እነዚህን አስተሳሰቦች በሚገባ ሊያራምድ የሚችል አይደለም። በመሆኑም ሁለቱም እሳቤዎች በተቃርኖ እንዲቆሙ ተገድደዋል። ይህ አካሄድ ባለበት ሁኔታ የብሄርና የዜግነት ፖለቲካ በአንድ አገር ውስጥ በአንድነት ሊራመዱ እንደማይችሉ አቶ ደርሶልኝ ያብራራሉ።።
አቶ ደርሶልኝ እንደሚሉት፤ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህገ መንግስት ካፀደቀ ጀምሮ ብሄር ተከል አስተሳሰብ ሰፍቷል። ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ አካላት የተመቻቸ ሜዳ ስለነበራቸው በሚገባ ተጫውተውበታል። ይህንን ተከትሎ ከምሁራን ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድረስ ያሉት አስተሳሰቡን እንዲያራምዱ ተደርገዋል። ከውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጭ የዜግነት ፖለቲካን በስፋት ያቀነቀነ የለም። ስለዚህ ምቹ ሁኔታ የነበረው ለብሄር ተኮር ፖለቲካ አራማጆች ነው። አሁን አገሪቷን የሚመራው ፓርቲ ራሱ ህጎችን ያወጣው ይህንን ለመጠቀም በሚያስችለው መልኩ ነው።
አቶ ደርሶልኝ ‹‹በማኅበራዊ ሚዲያዎች አክቲቪስት ነኝ የሚሉ ሰው በሰውነቱ ብቻ ዜጋ በመሆኑ መብቱን ያግኝ ከማለት ይልቅ ለተሰሩበት የማኅበረሰብ አካል አሊያም ብሄር ብቻ የማድላት አስተሳሰብን በስፋት ሲያራምዱ ይታያል። ይህም ምን ያህል የብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ ከፍ እያለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። በዚህ የተቃርኖ እሳቤ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ብለው ያቋቋሙት የድንበር ኮሚሽኑ እንኳ ፈተና እየገጠመው ነው። ለምሳሌ የትግራይ ፖለቲከኞች ህገመንግስቱን ይቃረናል በማለት ከጅምሩ ተቃውመዋል። በተወካዮች ምክር ቤት የወጣን ህግ አንቀበልም በሚል ወደ ውግዘት ሄደዋል። ስለዚህ ይህ ድንጋጌ የእነርሱን ይሁኝታ ካላገኘ ተግባራዊነቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል። በሌላ በኩል የአማራ ፖለቲካ አቀንቃኞችና አክቲቪስቶች የኮሚሽኑን መቋቋም ይጠቅመናል ብለው ካሰቡ በኋላ በተቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ የተሰየሙ ሰዎችን አንቀበልም ማለታቸው በተዘዋዋሪ ኮሚሽኑን አንቀበልም ወደሚለው ሀሳብ እየሄዱ ነው። በዚህም ምክንያት የብሄር ፖለቲካ እየጦዘ ይገኛል።›› በማለት ያብራራሉ።
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ አህመድ በበኩላቸው፤ ‹‹የዜግነት ፖለቲካ እሳቤ አንድን ቡድን ብቻ ይዞ ሲጓዝ ከሌሎች ጋር ተቃርኖ ይኖረዋል። ምክንያቱ ደግሞ ይህን አይነት አስተሳሰብ የሚያራምድ ፓርቲ በምርጫ ወቅት ሲንቀሳቀስ በተወከለው አካባቢ ላይ ብቻ ነው መሠረት የሚኖረው። ስለዚህ በሌላ ቡድን ተቀባይነትን አያገኝም። ከሌሎች ተለይቶ የመታየትን ሳይሆን እንደ አገር እንደ አንድ ህዝብ የመሆን እሳቤ እስካልሰፋ ድረስ ሁለቱን ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች አብሮ ማስኬድ አይቻልም።›› በማለት የብሄርና የዜግነት ፖለቲካ እሳቤዎች ተቃርኖ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚመጣ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሁለቱን የፖለቲካ እሳቤዎች አብሮ ማስኬድ አስቸጋሪ ነው የሚሉት አቶ ኑሩ፤ የፖለቲካ እሳቤው የላቀ ማኅበረሰብ ቢኖር እሳቤዎቹ መሰናሰል እንደሚችሉ፤ በኢትዮጵያ አሁን ባለው የጎሰኝነትና ጎጠኝነት አስተሳሰቦች ምከንያት ግን አብሮ ማስኬድ አስቸጋሪ መሆኑን ፤አገር የሚለው አስተሳሰብ ከንግግር ባለፈ እየተሰራበት አለመሆኑ፣ የብሄር ማንነት ሥር መሰደዱ፣ ለሌሎች ብሄሮችና ማንነቶች የሚሰጠው ቦታና እይታ መጥበቡ የሁለቱን ተቃርኖ እያሰፋ እንደሄደ ያብራራሉ።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ነጋ ሰለሞን በበኩላቸው ከብሄር ፖለቲካ ይልቅ የዜግነት ፖለቲካ እየጎላ መምጣቱን አፅንኦት በመስጠት ከሁለቱ ምሁራን ሀሳብ በተቃርኖ በመቆም ይናገራሉ።። የብሄር ፖለቲካ እሳቤ ከ1960ዎቹ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የብሄር ማንነትን ተንተርሶ የመጣ ሲሆን፤ የዜግነት ፖለቲካ ከ1983ዓ.ም ወዲህ እየጎለበተ የመጣ የፖለቲካ እሳቤ መሆኑን ይናገራሉ።
ዶክተር ነጋ ብሄርን አክብሮ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ወደሚለው መሄድ ችግር እንዳልሆነ፤ የብሄር ፖለቲካን በማክበር የዜግነት ፖለቲካን ማራመድና አገራዊ የጋራ ስሜት ማንጸባረቅና በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሁለቱንም አንድ ላይ ማስኬድ እንደሚቻል፤ ምንም እንኳን የዜግነት ፖለቲካ እሳቤው አንድ ኢትዮጵያ ወደሚል ሀሳብ የሚያመራ ቢሆንም፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ህዝብና ባህል አገር በአንድ አስተሳሰብ አሊያም የዜግነት ፖለቲካን ብቻ ማራመድ እንደሚያስቸግርና የሁለቱ አስተሳሰቦች ተቃርኖ መስፋትም አሉታዊ ተጽእኖ እንደ ሚያሳድር ይገልፃሉ።
ምሁራኑ እንደሚሉት፤ የብሄር ፖለቲካ የበላይነት ሲመጣ የአንዱ ክልል ተወላጅ ሌላ ክልል ሄዶ የመኖር መብቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። መተማመን ይጠፋል። የሁለቱ ተቃርኖ እየሰፋ ከሄደ የፌዴራል መንግስት ሉዓላዊነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል። አገሪቱ ውስጥ ያሉትና በክልል ደረጃ የተዋቀሩት አካላት የብሄረተኝነት አስተሳሰብ የፌዴራል መንግስት ያለውን ህጋዊ የበላይነት እንዲያጣ ያደርጋሉ። የብሄር ፖለቲካ ላይ ያተኮረ እሳቤ ተከባብሮ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አቅም አይኖረውም። አሁን ያለውም ነባራዊ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ አንድ አገር ውስጥ የሚኖር፤ ነገር ግን የማይዋደድና የማይከባበር ማህበረሰብ ከመፈጠር አልፎ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠፋና በመጨረሻም እርስ በእርስ በግጭት የሚፈላለግ ማኅበረሰብ በመፍጠር አገርን እስከ መበተን ያደርሳል፤ የአገሪቷ ሕዝባዊ መሠረትም የላላ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
አዲሱ ገረመው