
አዲስ አበባ፡- በሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየተመሩ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እድሜው እንዲራዘም የሚፈልጉ የሀገር ጠላቶችን መቃወም ይገባል ሲል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አስታወቀ።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለጹት፤ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየተመሩ ከአሸባሪው ህወሓት ጀርባ ሆነው ለቡድኑ ድጋፍ በማድረግ እድሜው እንዲራዘም የሚፈልጉ የሀገር ጠላቶችን መቃወም ይገባል።
ምዕራባውያን እንደዚህ አይነት ችግር በስፋት ይስተዋልባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አሸባሪ ቡድኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑ እየታወቀ በሀሰት ፕሮፓጋንዳው የሚነዛውን መረጃ ተቀብለው የሚያስተጋቡ፣ ፍትሃዊነት የጎደላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትም እንዳሉ ገልጸዋል።
እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በውጭ የሚኖሩ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለዓለም ማህበረሰብ እውነታውን ሊያሳውቁና ሊታገሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የውጭ ጠላቶች ህዋሓትን እያደራጁ ጦርነቱ እንዲራዘም እየታተሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ነገር ግን ሀገራችን ሰላም እንድትሆን እንፈልጋለን፣ በጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ እናውቃለን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደአገር የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ወደ ጦርነት ለመግባት ተገድደናል። የውጭ ሀይሎች ይህን መረዳት ሲገባቸው በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ፍርደ ገምድል ሆነው መታየታቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013