
በሕንድ ምዕራባዊ ግዛት ማሃራሽትራ ግዛት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 110 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። ዝናቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንደሮችን ያጥለቀለቀ ሲሆን፤ ቤቶች በጎርፍ ተወስደዋል፤ ነዋሪዎችም ባሉበት እንቅስቃሴያቸው ተገድቧል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማውጣት እየተረባረቡ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎች ግን ሳይጠፉ እንዳልቀሩ ስጋት አለ። የሕንድ ጦርም በአስቸጋሪ ሁኔታ ተስተጓጉሎ የነበረውን የሰዎችን ሕይወት የመታደግ ጥረት እያገዘ ነው።
ምዕራባዊ ግዛቷ ማሃራሽትራ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ነው የተባለውን የሐምሌ ዝናብ መዝግባለች ። ለጎርፉ አደጋ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ባለሙያዎች ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ሳቢያ የተፈጠረ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ዝናብ ሳያስከትል አይቀርም ብለዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አርብ ዕለት የሕንድ ባለሥልጣናት የአብዛኞቹ ሰዎች ሞት ምክንያት በሁለት ወረዳዎች ያጋጠመው የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ ነው ብለዋል። ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የሕንድ የንግድ ከተማ በሆነችው ሙምባይ ሰሜን ምስራቅ አካባቢ ያለች ትንሽ መንደር በመሬት መንሸራተቱ በመዳፈኗ ቢያንስ 38 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።
የግዛቷ ሚኒስትር ኡድሃቭ ታክሬይ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ እንዲሰጡ ባለሥልጣናትን ጠይቀዋል። ሚኒስትሩ ባለሥልጣናት ሰዎችን ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች እያወጡ መሆናቸውን አክለዋል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአደጋው ሕይወታቸው ባለፉ ሰዎች የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹ ሲሆን፤ በአደጋው ለተጎዱት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። የሕንድ መርከብና የአደጋ ባለሥልጣናት በባህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚከናወነውን የነፍስ አድን ሥራ ለማገዝ ተልከዋል።
በአንድ የባህር ዳርቻ ወረዳ ድልድዮችና የስልክ ማሰራጫ ማማ በመፍረሱ ከሌላው የአገሪቷ ክፍል ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጧል። በጎርፉ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ የሚገኙ ነዋሪዎች በሄሊኮፕተር በሚደረገው የመታደግ ሥራ በቀላሉ እንዲታዩ ጣሪያ ላይ እንዲወጡ ባለሥልጣናት አሳስበዋል።
በሙምባይ ዓርብ እለት የመኖሪያ ሕንጻ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፤ አስር ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የባቡር አገልግሎትም ተቋርጧል። ዝቅተኛ የሆነው የከተማዋ ክፍልም በጎርፍ ተጥለቅልቋል።
የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ቀናትም እየጣለ ያለው ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስጠንቅቀዋል።
በሙምባይ የሚያጋጥመው ከባድ ዝናብ የተለመደ ነው። ከተማዋ በተለይ በዚህ ወቅት በየዓመቱ የጎርፍ አደጋ ያጋጥማታል። ይሁን እንጅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዝናብ መጠኑ እየጨመረ ነው ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ሥራ ለመፈለግ ወደ ከተማዋ ይፈልሳሉ። ይህም በጥድፊያ እና ቁጥጥር ሳይደረግባቸው የሚሰሩ ግንባታዎች በርካታ ሰዎች ጥራት በሌላቸው የመኖሪያ ሕንጻዎች እንዲኖሩ አስገድዷል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013