የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ወሰነ

የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል መወሰኑ ተገልጿል፡፡ ኅብረቱ ማዕቀቡን የጣለው ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ማዕቀቦቹ በሩሲያ የነዳጅ ዘይትና የኢነርጂ ዘርፎች  ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሏል። ማዕቀቦቹ የሩሲያን የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በማውረድ ከጋዝ ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲቀንስ የማድረግ ዓላማ ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል። ኅብረቱ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ሲጥል የአሁኑ ለ18ኛ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ካያ ካላስ ‹‹መልዕክቱ ግልጽ ነው። አውሮፓ ዩክሬንን ከመደገፍ አይቦዝንም። ሩሲያ ጦርነቱን እስከምታቆም ድረስ የአውሮፓ ኅብረት ጫና ማሳደሩን ይቀጥላል›› ብለዋል። እስካሁን በሩሲያ ላይ ከተጣሉት ጠንካራ ማዕቀቦች መካከል አንዱ እንደሆነም ካላስ ተናግረዋል።

አዲስ የተሾሙት የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪዴንኮ፣ የኅብረቱን የማዕቀብ ውሳኔ በደስታ ተቀብለውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ማዕቀቡ በሩሲያ ላይ ጫና እንደሚያበረታባት ጠቁመው፣ ጦርነቱን በማስቆም ሰላም ለማስፈን ከዚህ የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር መነጋገራቸውንና ለማዕቀቡ ውሳኔም ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል። ‹‹የሩሲያ ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት። ፈረንሳይ ከዩክሬን ጎን ናት፤ ሆናም ትቀጥላለች›› ብለዋል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ በበኩላቸው፣ ኅብረቱ በሩሲያ ላይ የሚያደርገውን ጫና አጠናክሮ መቀጠሉ በጎ ርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ማዕቀቦቹ በሩሲያን የባንክ፣ የኢነርጂና ወታደራዊ ዘርፎች ያነጣጠሩ ናቸው። ይህ ደግሞ ሩሲያ ጦርነቱን ለመቀጠል የሚያስፈልጋትን የፋይናንስ ምንጭ ያዳክመዋል›› ሲሉ ተናግረዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ፣ ሩሲያ የምዕራባውያንን ማዕቀብ የምትቋቋምበት አቅም እንደገነባች ገልጸው፣ ማዕቀቦቹ ሕገ ወጥ እንደሆኑና ማዕቀቦቹን በደገፉ ሀገራት ጭምር ላይ አሉታዊ ውጤቶች እንደሚኖሯቸው አስጠንቅቀዋል።

የኅብረቱ የማዕቀብ ውሳኔ የተሰማው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላት የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት የአሜሪካን የጦር መሣሪያዎች ለዩክሬን ለመግዛት እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ነው። ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የአየር መከላከያ ሚሳኢሎችን ለዩክሬን እንደምታቀርብ መናገራቸው ይታወሳል። አውሮፓውያን የኔቶ አጋሮች መሣሪያዎቹን ከአሜሪካ ገዝተው ለኪዬቭ እንዲያስተላልፉ አስተዳደራቸው መወሰኑን አስታውቀው ነበር። ፕሬዚዳንቱ መሣሪያዎቹ ለዩክሬን ስለሚቀርቡበት ሁኔታ ከድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሃውስ ተወያይተዋል።

ትራምፕ ከሩተ ጋር ከተወያዩ በኋላ ‹‹ዩክሬን የምትፈልገውን እንድታደርግ እናመቻቻለን። ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን እንልካለን። ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያወጡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ዩክሬንን ለመደገፍ በአፋጣኝ ወደ ጦር ግንባሮች ይከፋፈላሉ። አውሮፓ ሒሳቡን ይሸፍናል ነው ያሉት።

ትራምፕም ሆኑ ሩተ ለኪዬቭ እንልከዋለን ስላሉት የመሣሪያ ዓይነትና ብዛት ባያብራሩም፤ ሩተ ግን ስምምነቱ ሚሳዔሎችን እና ጥይቶችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል። ‹‹ዛሬ ቭላድሚር ፑቲንን ብሆን ከዩክሬን ጋር የሚኖረኝን ንግግር ጠበቅ አድርጌ ለመያዝ አጤናለሁ›› ብለዋል። ‹‹አክሲዮስ›› (Axios) ሁለት ስማቸው ያልተገለፀ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አሜሪካ ለዩክሬን ከምታቀርባቸው የአየር መከላከያዎች በተጨማሪ ጥቃት ለመሰንዘር የሚውሉ መሣሪያዎችም ይገኙበታል።

ከጦር መሣሪያው በተጨማሪ ተባብሶ በቀጠለው ደም አፋሳሹ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ደስተኛ ባለመሆናቸው እና ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረጉ ሙከራዎች እስካሁን ውጤት ባለማስገኘታቸው የተበሳጩት ትራምፕ፣ ሩሲያ ግጭቱን እልባት ለመስጠት በ50 ቀናት ስምምነት ላይ ካልደረሰች ማዕቀብ እንደሚጣልባት ዝተዋል።

ሩሲያ በ50 ቀናት ውስጥ ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በቀሪ የንግድ አጋሮቿ ላይ የ100 በመቶ የሁለተኛ ወገን ታሪፍ እንደሚጥሉ ተናግረዋል። ይህም ከሩሲያ ጋር የሚነግዱ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ ታክስ ይጣልባቸዋል ማለት ነው።

ለአብነት ያህል ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቷን ከቀጠለች፤ ከሕንድ ምርት የሚሸምቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች እቃዎቹ የአሜሪካን ምድር ሲረግጡ 100 በመቶ የአስመጪ ታክስ ወይም ታሪፍ ይከፍላሉ። ይህም የምርቶቹን ዋጋ ውድ ስለሚያደርግ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ምርቶቹን ከሌላ ሀገራት በርካሽ እንዲገዙ ይገፋፋል፤ ይህም ሕንድ ገቢ እንድታጣ ያደርጋል።

የታሪፍ ሃሳቡ በሩሲያ ምጣኔ-ሀብት ላይ እክል  እንደሚጥል ይታመናል። በሃሳብ ደረጃ ሞስኮ ነዳጇን ለሌሎች ሀገራት ሸጣ ገንዘብ ካላገኘች በዩክሬን ለምታካሂደው ጦርነት ገንዘብ ያጥራታል። የነዳጅና ጋዝ ምርቶች ለሞስኮ ሦስተኛ ከፍተኛ ገቢ ማግኛ ምርቶች እና ከ60 በመቶ በላይ የወጪ ንግድ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው የ100 በመቶ ታሪፍ ለሀገሪቱ ፋይናንስ ከፍተኛ አደጋ ይሆናል ተብሏል።

የታሪፉም ሆነ የኔቶ የመሣሪያ ስምምነት ዝርዝር ውስን ቢሆንም፤ ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዩክሬን መሣሪያ ለመላክ ቃል ገብተዋል። ባለፈው የካቲት ትራምፕና ዘለንስኪ በዋይት ሃውስ ዱላ ቀረሽ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው የጦር መሣሪያና የደህንነት መረጃ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ መስጠታቸው የሚታወስ ነው። ግን ብዙም ሳይቆዩ ይህን ትዕዛዛቸውን ሽረው ለዩክሬን የሚቀርበው ድጋፍ እንዲቀጥል አድርገዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ከምትሰጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን ማቋረጧን አስታውቃ ነበር። በወቅቱ ውሳኔው የተወሰነው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ መገምገሙን ተከትሎ የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም እንደሆነ ዋይት ሃውስ ገልጿል።

ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክምችት እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን ተዘግቦ ነበር። ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ጋር በዚያው ሰሞን በኔዘርላንድስ በተካሄደው የ‹ኔቶ› ጉባዔ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነበር።

በወቅቱ ትራምፕ አሜሪካ ተጨማሪ የፀረ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን ተጠይቀው ‹‹አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል›› ማለታቸው ይታወሳል። ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት መወሰኑ ዩክሬንንና አጋሮቿን ክፉኛ አስጨንቆ ነበር።

ትራምፕ ይህን በተናገሩ በቀናት ልዩነት ደግሞ ሀገራቸው ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን እንደምትልክ አስታውቀዋል። ለዩክሬን ከሚላኩት መሣሪያዎች ውስጥ ዋናዎቹ የአየር መከላከያ መሣሪያዎች እንደሆኑ ጠቁመው ነበር። ‹‹ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንልካለን። ዩክሬኖች ራሳቸውን መከላከል አለባቸው›› ማለታቸው ይታወሳል። ትራምፕ የአየር መከላከያዎች ለዩክሬን ለማቅረብ መወሰናቸው እና በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል መዛታቸው በቭላድሚር ፑቲን ላይ የሚያሰሙት ተቃውሞ ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ መሆኑን ያሳየ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል ዩናይትድ ኪንግደም ከ20 በላይ በሚሆኑ የሩሲያ የደህንነት ባለሙያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች። ሀገሪቱ ማዕቀብ የጣለችባቸው ሰላዮችና መረጃ መንታፊዎች አውሮፓን በሚበጠብጥ የሳይበር ወንጀል ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው ብላለች።

ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ባለሙያዎች መካከል ከሦስት ዓመታት በፊት በዩክሬን ማሪዩፖል ትያትር ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ያቀነባበሩ እና በ2018 ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ይኖር በነበረው በሩሲያዊው ሰላይ ሰርጊ ስክሪፓልና ሴት ልጁ ላይ በተፈፀመው የኖቪቾክ መርዝ ጥቃት ውስጥ የተሳተፉ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደቪድ ላሚ ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹የሩሲያ ሰላዮች አውሮፓን ሰላም የመንሳት፣ የዬክሬንን ሉዓላዊነት የመድፈር እና የብሪታኒያ ዜጎችን ደህነነት አደጋ ላይ የመጣል ዘመቻዎችን እያካሄዱ ነው›› ብለዋል። ሩሲያ የዩናይትድ ኪንግደም የመገናኛ ብዙኃንን፣ የቴሌኮም አቅራቢዎችን፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ተቋማትን እና የኃይል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ እንዳደረገች ለንደን አስታውቃለች። ሩሲያ ግን የዩናይትድ ኪንግደምን ውንጀላ አስተባብላለች።

‹‹ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ›› ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤ ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል። ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩት ጥረቶች ሁሉ ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘት አልቻሉም። ሁለቱም ሀገራት የሚፈፅሟቸውን ጥቃቶች በየፊናቸው አጠናክረው ቀጥለዋል። ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ባለችው ዝርዝር እቅድ ውስጥ የተካተቱት ቅድመ ሁኔታዎቿም በዩክሬንና በምዕራባውያን አጋሮቿ ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ አይታሰብም። ምዕራባውያንም የማዕቀብ በረዷቸውን በሩሲያ ላይ እያዘነቡና ዩክሬንን እያስታጠቁ ቀጥለዋል። ሩሲያም ‹‹ማዕቀቡን ለምጀዋለሁ፤ ዩክሬንን ማስታጠቃችሁንም ጦርነቱን ከማባባስ ውጭ ምንም ለውጥ አያመጣም›› ብላ ጦርነቱን ቀጥላለች። ብዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞችም ‹‹ሩሲያና ዩክሬን የመስማማት ተስፋ አላቸው? ዘላቂ የተኩስ አቁም ብሎም የሰላም ስምምነትስ ይፈራረሙ ይሆን…?›› ብለው አበክረው ይጠይቃሉ።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You