የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል 1955 (እኤአ) ተመስርቶ እስከ 1996 (እኤአ) ቆይቷል። 3500 የሰው ኃይል 26 መርከቦች ነበሩት። የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አካል ነበር። ከ1955 (እኤአ) እስከ 1990 (እኤአ) ዋና መስሪያ ቤቱ ምጽዋ ነበር። ከ1990 (እኤአ) እስከ 1996 (እኤአ) አዲስ አበባ።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የመጀመሪያው አዛዥ (ከ1955 እስከ 1974 (እኤአ) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነበሩ ሲሆን ከ1958 (እኤአ) እስከ 1974 (እኤአ) ድረስ ምክትል አዛዡ ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ነበሩ። በንጉሱ ዘመን ባሕር ኃይላችን የራሱ የሆኑ የጦር ሄሊኮፕተሮች ነበሩት። ኡኤችአይ ኢሮኩይስ እና ሚ8 ሚ14 የተባሉ።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የተመሰረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1950 (እኤአ) ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ሲወሰን ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ጠረፍና ወደብ በማግኘቷ ነው። በ1955 (እ.ኤ.አ) ባሕር ኃይላችን የመጀመሪያ ጦር ሰፈሩን (ቤዙን) ምጽዋ ላይ አቋቋመ። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ወርክ ሾፓችና የሙሉ ባሕር ኃይል አቅም እንዲኖረው ግንባታቸው በምጽዋ ተጀመረ።
በ1958 (እኤአ) ባሕር ኃይሉ ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ ተቋቋመ። እንደ ምድር ጦርና አየር ኃይል ሁሉ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዞር ሹም ስር ሆነ። የባሕር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ቢሯቸው በአዲስ አበባ ሲሆን የጠረፍ ባሕር ኃይል ሆኖ ቀይ ባሕርን እንዲቃኝ እንዲጠብቅ ነው የተቋቋመው።
ትምህርትና ስልጠናን በተመለከተ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሠራዊት አባላት በዓለማችን እጅግ በጣም ምርጥ ከሚባሉት ባሕር ኃይሎች ውስጥ ነበሩ። ኢትዮጵያ ኤርትራን በፌዴሬሽን ከመቀላቀሏ በፊትም ቢሆን የእንግሊዝ ባሕር ኃይል (ሮያል ኔቪ)
ኢትዮጵያውያንን ምጽዋ በሚገኘው ቤዙ ወስዶ በሚገባ አሰልጥኗል። ተምረዋል።
በ1956 (እኤአ) በአስመራ ከተማ የባሕር ኃይል ኮሌጅ ተመሰረተ። በዚህ ኮሌጅ ኢትዮጵያውያን እጩ መኮንኖች ለ52 ወራት ከፍተኛ የባሕር ኃይል ትምህርት ተምረው በመኮንነት ይመረቃሉ። በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ በአማካይ ከ30 እስከ 40 ተማሪዎች ይማሩ የነበረ ሲሆን ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በናቫል ከሚሽንነትና በባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ይመረቃሉ።
በ1957 (እኤአ) ደግሞ በምጽዋ የባሕር ኃይል በታች ሹሞች ማስልጠኛ ተከፈተ። ከ1950(እኤአ) በኋላ እስከ 1960 (እኤአ) ድረስ የባሕር ጠለቆች (ፍሮግማን ዳይቪንግ) እና የልዩ ኮምንዶ ክፍል፤ እንዲሁም የባሕር ኃይል ወታደሮች (የባሕረኞች) ማሰልጠኛ ተመስርቷል።
ጃንሆይ የኖርዌጅያን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባሕር ኃይል መኮንኖች አዲስ የሚቋቋመውን የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል እንዲረዱና እንዲያደራጁ ሾመዋል። በአብዛኛው ስልጠናና ትምህርቱን የሚሰጡት በአማካሪነት ያገለግሉ የነበሩት ጡረታ የወጡ የእንግሊዝ ባሕር ኃይል(ሮያል ኔቪ) መኮንኖች ነበሩ። ጥቂት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ሊቮርኖ በሚገኘው የኢጣሊያ ባሕር ኃይል አካዳሚ ሌሎች የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ደግሞ በአሜሪካን ባሕር ኃይል አካዳሚ ሜሪላንድ ሚኒያፖሊስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የአሜሪካን ባሕር ኃይል ንብረት የሆነችው ሲ ፕሌን ቴንደር ዩኤስ ኤስ (ኦርካ ኤቪፒ 49 ከሀውተን ዋሽንግተን የካቲት 6 /1944 የተሰራች ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የማስተማርያና የማስልጠኛ መርከብ ሆና ከ1964(እኤአ) እስከ 1993 (እኤአ) አገልግላለች። ትልቋም መርከብ ነበረች። እስከመጨረሻው ድረስ ባሕር ኃይላችን በተለየየ ኃላፊነትና የስራ መደብ ውስጥ የነበሩ በእጅጉ የተማሩ በአለም አቀፍ ደረጃ የባሕረኛ ሰፊ እውቀት በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 3500 ባሕረኞች ነበሩት።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የቅኝት ጀልባዎችንና ቶርፔዶ ጀልባዎችን እንዲሁም የጦር መርከቦችን መጠነኛ ደረጃ ያላቸውን ከውሀ በታች የሚሄዱትን ጭምር ከአሜሪካና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተላልፈውለት የራሱ ንብረት ሆነው ይጠቀምባቸው ነበር። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የመጀመሪያዋ መርከብ የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ፒሲ 1604 መደብ ሰብ መሪን ቼሰር የቀድሞዋ ዩኤስ ኤስ ፒሲ –1616 መርከብ ስትሆን በጥር 2 1957 (እኤአ) ለኢትዮጵያ በብድር ገንዘብ የተላለፈች ነበረች። በኋላም መርከቧ በኢትዮጵያዊው አርበኛ በዘርአይ ደረስ ስም ተሰየመች።
በ1962 (እኤአ) አሜሪካ ሲ ፕሌን ቴንደር ኦርካን የተባለችወን መርከብ ለኢትዮጵያ አስተላለፈች። መርከቧ ኢትዮጵያ ተብላ ተሰየመች። በ31 አመታት አገልግሎቷ ውስጥ የኢትዮጵያ የማሰልጠኛ መርከብና ትልቋም መርከብ ነበረች።
የባሕር ሃይል አየር ኃይል
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አነስተኛ የባሕር ኃይል አየር ኃይል አቋቋመ። 6ስት ዩኤች 1 ኢሮኩይስ ሄሊኮፕተሮች የነበረው ሲሆን የሚንቀሳቀሱት አስመራ ከሚገኘው የባሕር ኃይል አየር ጣቢያ ነበር። ባሕር ኃይላችን አራት የጦር ሰፈሮች ነበሩት። ምጽዋ የባሕር ኃይሉ ዋና መምሪያና የባሕረኞች ማሰልጠኛ፤ የባሕር ኃይሉ አየር ኃይል ጣቢያና የባሕር ኃይል አካዳሚው (ኔቪ አካዳሚ) አስመራ፤ አሰብ የባሕር ኃይሉ ጣቢያና የበታች ሹማምንት ማሰልጠኛ እንዲሁም የጥገና ቦታ፤ በቀይ ባሕር ዳህላክ ደሴቶች የባሕር ኃይሉና የመገናኛ ኮሚኒኬሽን ጣቢያም ይገኝበት ነበር።
ንጉሡ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይሎች ሞዴልና አደረጃጀት መስራቱን ቀጠለ። የተወሰኑ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይል አካዳሚ ሌኒን ግራድና እንዲሁም ባኩ ከተማ የባሕር ኃይል ትምህርት ተከታትለዋል። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ባሕረኞች የባሕር ኃይል ትምህርት የሚወስዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር።
ሶቭየት ሕብረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፏ ከሶማሊያ እንድትወጣ ሲደረግ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አሰብና ዳህላክ ላይ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር አቋቋመች። የሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይል አውሮፕላኖቹን አስመራ አየር ማረፊያ ማከማቸት ጀመረ። የሶቭየት ባሕር ኃይል መኮንኖች በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ የአስልጣኝነት ቦታዎችን ያዙ።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የጦር መሳሪያ እርዳታ በ1977 (እኤአ) ስታቋርጥ ባሕር ኃይላችን የሚታጠቃቸው አዳዲስ መሳሪያዎች በሶቭየት ሕብረት መሳሪያዎች ተተኩ። የቀድሞዎቹ እንዳሉ ሁነው። ሶቭየት ሰራሽ የቅኝት ጀልባዎችና ሚሳኤል የታጠቁ ጀልባዎች የቀድሞዎቹን የአሜሪካና የአውሮፓ መርከቦች መተካት ጀመሩ። በ1991(እኤአ) የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል 2 ፍሪጌቶች (ተዋጊ መርከቦች) ፤8 ሚሳኤል ክራፍቶች(ተዋጊ መርከቦች) ፤ 6 የቶርፔዶ ክራፋቶች(ተዋጊ መርከቦች) ፤ 6 የቅኝት ጀልባዎች ፤ 2 አምፊቢየስ ክራፍቶች እንዲሁም 2 የድጋፍና የማሰልጠኛ ክራፍቶች አብዛኛዎቹ የሶቭየት ስሪት የሆኑ ባለቤት ሆነ።
ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አየር ኃይል(ኔቪ ኤየር ፎርስ) ንብረቶች የነበሩት 6ስቱ ዩኤች 1 የተባሉት ሄሊኮፕተሮች ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዲተላለፉ ተደረገ። ከንጉሱ በኋላም ባሕር ኃይሉ በኔቶ ሪፖርት መሰረት 2 ሶቪየት ሰራሽ የሆኑ ሚሊሚ 14 የተባሉ ሄሊኮፕተሮችን አግኝቷል።
ባሕር ኃይሉ የጠረፍ ጥበቃ ብርጌድ የነበረው ሲሆን ይህም ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ ፒ 15 ተርማይት ወይንም ኤስኤስ 3 በኔቶ አጠራር የጠረፍ ጥበቃ ጸረ መርከብ ክሩስ ሚሳኤል አስወንጫፊዎችን የታጠቀ ነበር። በመንግስት ለውጥ ዋዜማ መርከቦቻችንም ቀን ጥሎአቸው እንደ ሰው ተሰደዋል። ወደ ጅቡቲ የመንና ሳኡዲአረቢያ። የመን የሄዱት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከቦች የመን እንዲወጡ ስላደረገች 16 ያህሉ ጅቡቲ ገብተው ነበር። በኋላ ላይ ጅቡቲ መርከቦቹ የቆሙበት ኪራይ አልተከፈለኝም ሸጬ እወስዳለሁ በሚል መርከቦቹን ለጨረታ አቀረበች።
ኤርትራ አራቱን ስትገዛ ሌሎቹን ጅቡቲ ሸጠች። ለትውልድ የቀረችው ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከብ የቅኝት ጀልባ የነበረችው ጊቢ(GB –21) ተብላ የምትጠራዋ ስትሆን በኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ጣና ሐይቅ ተጭና ተወስዳ ዛሬ ጣና ሐይቅ ላይ ትገኛለች። ከዚያ ሁሉ ጦርነት፤ የመርከቦች ስደትና ሽያጭ ውስጥ ተርፋ ያለች ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሠራዊት መርከብ ነች። (ምንጭ፣ ዊክፒድያ)
ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንደገና እንዲቋቋም በመንግስት ተወስኖ ስራው እየተሰራ ይገኛል። በቅርቡ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የዘመቻና መረጃ መምሪያው ኃላፊ ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለምልልስ ባሕር ኃይሉን የማቋቋሙ ጉዳይ አዛዥና ስታፎች ተመድቦለት እየተሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ዘመናዊ የተደራጀና የታጠቀ የባሕር ኃይል የግድ እንደሚያስፈልጋት ታምኖበታል ወደ ስራም ተገብቶአል ማለታቸው ይታወሳል። ምክንያቱም በጅቡቲ ብቻ ወደ ስምንት ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን መስር ተዋል። ይሄ ደግሞ ከምንም በላይ በቅርበት ያለችውን ኢትዮጵያን የሚመለከት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል- ጀነራል ብርሀኑ ጁላ።
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2011