ከፍጥረት ልደት እኩል አብሮ የሚጀምር፣ ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሚቆጠር፣ ከራሱ ከሰው ልጅ ዕድሜ የሚስተካከል የረጅም ጥንታዊ ሥልጣኔና አኩሪ ታሪክ ባለቤት ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ከውብ መልክዓ ምድሯ እስከ መንፈሣዊ ሚስጥሯና ጥበባዊ ክብሯ ሁለንተናዋ የዓለምን ዓይኖች ሁሉ የሚስብ መግነጢሳዊ ኃይል ነው፡፡ ይህንን ፀጋ በደንብ ተገንዝቦ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለም ሃገሪቱን የዓለም የቱሪዝም ማዕከል ከማድረግ ባለፈ ተዝቆ የማያልቀውን የመስህብ ሃብት ለግዙፍ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማዋል ይቻላል፡፡ ሆኖም ካለው ታላቅ የመስህብ ሃብት አኳያ ዘርፉ ገና ምንም አልተነካም፤ ኢትዮጵያም እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ዓለም ሃብቷን አልተጠቀመችም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም በርካታ ነገሮችን በምክንያትነት መጥቀስ ይቻላል። ማነቆዎች ከሆኑት መካከል ጥራት ያለው አገልግሎት አለመስጠትና የመስህብ ቦታዎች በተገቢው ሁኔታ ለምተውና ተወዳዳሪ ሆነው አለመገኘት ጎላ ብለው የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
በመሆኑም መስህቦች በተገቢው እንዲጎበኙና የሀብት አመንጪ እንዲሆኑ በየመዳረሻዎቹ ለቱሪስት የሚመጥን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ለኢንዱስትሪው ዘላቂ ዕድገት የሚያገለግሉ ሥልቶችን ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን መንግሥት ይገልጻል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራን የማሣረፍ መርሃ ግብር በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በሥሩ በሚገኘው በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል ችግኝ የተተከለበት የወንጪ ሐይቅና አካባቢው የኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክትም የዚሁ ሥራ አንድ አካል ነው፡፡ በዕለቱ በሥፍራው የተገኙት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን ማልማት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ካለው የላቀ አስተዋፅኦ አኳያ አቅጣጫ ተቀምጦ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተተገበረ ያለው አገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ለማልማት እንደ አንድ ማስፈፀሚያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሌሎች ነባር ቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች እንዳሉ ሆነው በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጭነት ቀጣይ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ተለይተው እየተተገበሩ በሚገኙት ሦስት ሃገር አቀፍ ፕሮጀክቶች በወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ላይ ትኩረት ተደርጎ ችግኞች እየተተከሉና አካባቢዎቹ አረንጓዴ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ በተለይም ተፈጥሮን መንከባከብና አካባቢን መጠበቅና ማልማት ላይ መሠረቱን የሚያደርገው የኢኮ ቱሪዝም ዓይነት ትኩረት እንዲሰጠው በዘርፉ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ አቅጣጫ በተቀመጠው መሠረት ዛፍ በመትከልና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ማልማት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ይህም የመዳረሻ ሥፍራዎችን አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ ቱሪስቱ የመቆያው ጊዜ እንዲራዘም መስህቦች ሀብት አመንጪ እንዲሆኑ በርካታ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ የሆቴልና መሰል አገልግሎቶች መገንባትን ጭምር ያካትታል፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመርና ቆይታውንም ለማርዘም መዳረሻዎችን ማልማትና ማስተዋወቅ ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ብቻ ሣይሆን ባለፉት ዓመታትም ማዕከሉ በወንጪ እና በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በጥናት ላይ ተመሥርቶ በአካባቢዎቹ ችግኝ ከመትከል ባሻገር የተለያዩ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን አረንጓዴ የማልበሱ ሥራ አካባቢዎችን ለጎብኝዎች ምቹ ከማድረግና ገቢ ከማመንጨት ያለፈ መሆኑንም ይጠቅሣሉ፡፡ ለአብነት በወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ችግኝ እየተተከለባቸው የሚገኙ ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱና በከፍተኛ ደረጃ በጎርፍ የመሸርሸር አደጋ ሥጋት ያለባቸው መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የሚተከሉት ዛፎች አካባቢው እንዲያገግምና ወደነበረበት እንዲመለስ በማገዝ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ ያገለግላሉ። ይህም ከተፈጥሮ አልፎ የአካባቢውን ነዋሪ ማህበረሰብ ሕይወትም ከአየር ንብረት መዛባትና ከልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ አደጋ እንዲጠበቅያደርጋል፡፡ ከዚህም በአሻገር በመዳረሻ ሥፍራዎቹ የሚተከሉት ችግኞች በዘፈቀደ ሣይሆን ከአካባቢው ሥነ ምህዳርና ከነዋሪው የልማት ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ በመሆናቸው ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነትና እንደ ሃገር ለሚደረገው ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ጥረት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ብሩክ ታደሰ በበኩላቸው የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል ከተቋቋመ 52 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም መሆኑን በማስታወስ ማዕከሉ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ያበረከተውን አስተዋፅኦ ከተሰጠው ኃላፊነትና ተግባር ተነስተው ሲናገሩ፤ በ1961 ዓ.ም በንጉሡ ዘመን ተቋቁሞ ሥራ የጀመረው የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል ሦስት ዋና ዋና ተግባሮችን እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህም ሥልጠና እና የማማከር አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ጥናትና ምርምር ማድረግ ናቸው፡፡
ሥልጠናን በተመለከተ ማዕከሉ በሆቴልና ቱሪዝም የሙያ መስኮች እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ድረስ በማሠልጠን በዘርፉ በርካታ የሠለጠነ የሰው ኃይል አፍርቷል፤ በማፍራት ላይም ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ በክልል ከተሞችና በማሠልጠኛ ተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች 70 በመቶ በተግባር የተደገፉና 30 በመቶ በንድፈ ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኙ ቤተ ሙከራዎች፣ በትብብር ሥልጠና በሆቴሎችና አስጎብኝ ድርጅቶች ጋር ሂዶ በኢንዱስትሪ ላይ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ፣ በሁለቱም ዘርፍ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች የሚያካትት ቢሆንም በተለይም የቱሪዝም ዘርፍ ሠልጣኞች በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጎበኙ በማድረግ የመስክ የተግባር ሥልጠና ይሰጣል። በዚህም ከማሠልጠን አልፎ በዘርፉ ከተሠማሩ ባለሐብቶችናተቋማት ጋር በመነጋገር ሠልጣኝ ተማሪዎች ለተግባር ሥልጠና ከወጡባቸው ተቋማት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እስከማድረግ የሚደርሱ ሥራዎችን ይሰራል፡፡
የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን በሚመለከትም የማሠልጠኛ ተቋሙ የተለያዩ የጥናት ርዕሰ ጉዳዮችን በመለየት ለዘርፉ ፖሊሲ ዝግጅት ግብዓት የሚሆኑና ተቋሙን ሊቀይሩ የሚችሉ ሀገራዊ የጥናት ሥራዎችን በመሥራት ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት ይፋ ያደርጋል። ለአብነትም በቅርብ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖ በማጥናት ውጤቱንና የደረሰባቸውን ግኝቶች በግብዓትነት እንዲያገለግሉ ለዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ለመንግሥት አቅርቧል፡፡
የማማከር አገልግሎት በመስጠት ረገድም በሀገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ድርጅቶች በዘርፉ ለመሠማራት የሚያስፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ መልካም እድሎች፣ ምቹ ሁኔታዎችንና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማማከር ዓላማ አድርጎ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዚህ ተግባርና ኃላፊነት የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን ለመስጠትና የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የማሠልጠኛ ማዕከሉ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሮች የችግኝ ተከላዎችን በማካሄድ መዳረሻ ሥፍራዎቹ አረንጓዴ እንዲሆኑ የማድረጉ ሥራ ከማዕከሉ ተግባርና ኃላፊነት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ያመላክታሉ፡፡ በመሆኑም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎቹ ቀደም ሲልም በማሠልጠኛ ተቋሙ ሲጎበኙና ለጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሊሰሩ የሚችሉ ጉዳዮች ተለይተው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑባቸው የቆዩ ናቸው፡፡
አሁንም በእቅድ ተይዘው ያሉ የማዕከሉ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል ባለፈው ዓመት በተከናወነው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማዕከሉ ችግኝ የተከለበትና ዘንድሮም ሐምሌ 6 ቀን በ2013 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተካሄደበት የወንጪ ሐይቅ አንዱ ነው። በዚህም ማዕከሉ በወንጪ ሐይቅ አካባቢ በተደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ወደ 2400 ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ በቀጣይነትም በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወደ አምስት ሺህ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በአረንጓዴ አሻራ መጠበቅና መንከባከብ ከተቋሙ ዓላማ ጋር በእጅጉ የተያያዙና ለሚሠራቸው ሥራዎች ወሣኝነት ያላቸው መሆናቸውን የሚገልጹት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው እነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በአግባቡ ከለሙና ከተጠበቁ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎቹ በደን እንዲለሙና አረንጓዴ እንዲሆኑ ከተደረጉ ለገብኝዎች ምቹ ይሆናሉ። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማለትም ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች ወዘተ… ይሥፋፋሉ፣ ቱሪስቶች እነዚህን መስህቦች ለማየት በብዛት ይመጣሉ፡፡ በአጠቃላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ይሠፋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩ ለአካባቢው ወጣቶችና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ከዚህም አልፎ ተቋሙ ለሚያስመርቃቸው ሠልጣኞችም የሥራ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ መንገድ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞችን ልማቱ የራሱ መሆኑን አውቆ የአካባቢው ማህበረሰብ ሊንከባከባቸው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ መንግሥት የመስህብና የቱሪዝም ተያያዥ ዘርፉን ካለበት ተግዳሮት ተላቆ በውጤታማነት እንዲቀጥልና ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ተሸጋግሮ ባላት ዕምቅ ሐብት ልክ ሃገሪቱንና ሕዝቧን መጥቀም እንዲችል ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ከጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ በማካተት የቱሪዝም ዘርፍ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ አድርጋ፣ ፖሊሲ፣ ሥልትና ፕሮግራም አዘጋጅታ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች የምትገኝ አገር ናት፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ያላቸው አረንጓዴ ልማቶችና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ቀዳሚ በሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር ደግሞ በርግጥም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች አካባቢ ችግኝ የመትከሉና አረንጓዴ እንዲሆኑ የማድረጉ ሥራ አንድም የአካባቢ ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳርን በመጠበቅና አረንጓዴ የኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጅን ለሥኬት እንዲበቃ በማድረግ ረገድ ወሣኝ ሚናን ይጫወታል፡፡
ሁለቱም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በማስዋብና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ አቅም ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሣደግ የሚኖራቸው ፋይዳ እጅግ ትልቅ ነው፡፡ እናም በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ላይ ችግኝ መትከልና አረንጓዴ እንዲሆኑና እንዲዋቡ በማድረግ በአቅሙ ልክ ቱሪዝምን ጥቅም ላይ እንዲውልና ለሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያገለግል የማድረግ ውበትን ለዕድገት የመጠቀም እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ፋይዳው የላቀ ነውና ይበል እንላለን፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013