ከምሽቱ 4፡30 ነው። ለወትሮው በሞቃታማ አየር ፀባይዋ የምትታወቀው የአዳማ ከተማ የሐምሌው ጭጋግ አጨፍግጓት ቀዝቃዛ አየር ትተነፍሳለች ። ከተማዋ የቀን ገጽታዋ ተቀይሮ ሌላ ድባብ ይታይባታል ። ከሰዓታት በፊት ከወዲህ ወዲያ ሲከንፉ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ጋብ ብለዋል። ከጥቂት ሆቴሎች በስተቀር አብዛኛዎቹ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል ። በጎዳናዎች ግራና ቀኝ ሲተረማመሱ የነበሩ እግረኞችና አላፊ አግዳሚውን እያስቆሙ ምጽዋት ሲጠይቁ የነበሩ ሰዎች ቦታውን ለሌሎች አስረክበው ወደየማደሪያቸው ገብተዋል። አሁን ተራው ከአንድ መጠጥ ቤት ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ ለሚዝናኑ ጥቂት ጠጪዎችና በየጥጋጥጉ እልፍ እልፍ ብለው ለሚቆሙ ሴተኛ አዳሪዎች የተተወ ነው።
እኔና የስራ ባልደረቦቼ ካረፍንበት ሆቴል ሰገነት ላይ ሆነን በከተማዋ አውራ ጎዳና ላይ ያለውን ትዕይንት እየታዘብን ነው። ከርቀት አስፋልት ዳር ካለው ዛፍ ስር ሻጭና ገዢዎች ሲገበያዩ ይታያል ። የካሜራ ባለሙያው ሀዱሽ አብርሃ እና የበከልቾ ጋዜጣ ሪፖርተር አዲሱ አዶላ የውድቅቱ ግብይት ለጋዜጣችን ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ሀሳብ አፍልቀው ካረፍንበት ህንጻ ወርደን ወደ ስፍራው አቀናን። ሀሳባቸው ትክክል ነበር፤ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ውርጭ ላይ ቁጭ ብለው ሲሸቅጡ የሚያድሩ ባልና ሚስት አገኘን ።
ኢብራሂም አክመልና ፌሩዛ አህመድ ይባላሉ። ኢብራሂም የአዳማ ከተማ ተወላጅ ሲሆን ፌሩዛ የሐረር ተወላጅ ነች። የስራ ድርሻችንን አሳውቀናቸው የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው ።
ኢብራሂም ጣቱን ወደ ባለቤቱ ፌሩዛ እየጠቆመ ‹‹ከእኔ ይልቅ እርሷ ብዙ ታሪክ ያላት ሰው ነች። እርሷን ጠይቋት፤ በደንብ ትነግራችኋለች›› አለን። ፌሩዛ የህይወት ታሪኳን ለመናገር አላቅማማችም ። ከሐረር ተሰዳ አዳማ ከመጣች በኋላ ከጎዳና ህይወት እስከ ሴተኛ አዳሪነት ያሳለፈችውን እና አሁን ያለችበትን ህይወት ዝክዝክ አድርጋ ነገረችን ። ከምትሰጠን መረጃ ባሻገር የሐረር ሰውን ግልጽነት ያየንበት አጋጣሚም ነበር ። አሳዛኝ፣ አስገራሚና፣ አስደሳች ህይወቷን ልናጋራችሁ ወደናል ። መልካም ንባብ።
ፊሩዛ አህመድ ተወልዳ ያደገችው ምስራቅ ሀረርጌ ገለምሶ በሚባል ወረዳ ነው ። ወላጅ እናቷንና አባቷን እንደ ህልም ከማስታወስ በዘለለ በደንብ አታውቃቸውም። ሁለት ታላላቅ ወንድሞችና ሁለት እህቶች የነበሯት ሲሆን እርሷ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነበረች። በ1985 ዓ.ም ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለች በወቅቱ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ወላጆቿን በኦነግ ስም ፈርጆ እያሰረ ክፉኛ ይደበድባቸው እንደነበር ትናገራለች። አባቷ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት ይሞታሉ ። እናቷም ድንገት ተሰውረው በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ሳይታወቅ ይቀራሉ ። እንደአባትና እንደእናት ሆኖ ታናናሾቹን ሊያስተዳድራቸው የሞከረው ታላቅ ወንድሟ ነበር። እርሱም የመንግሥት ታጣቂዎች ክትትል እያደረጉበት ቁምስቅሉን ሲያሳዩት ወንድምና እህቶቹን ከፊሉን ዘመድ ቤት ከፊሉን ጎረቤት በታትኖ አካባቢውን ለቆ ይጠፋል ።
ፌሩዛ ያኔ የ7 ዓመት ልጅ ነበረች ። ወንድሟ በአደራ ያስቀመጣት ቤት ሆኗ ቤተሰቦቿን እያስታወሰች ታለቅስ ነበር ። አስቀምጧት ሲሄድ በአጭር ጊዜ እንደሚመለስ ነግሯት ስለነበር ነጋ ጠባ መጥቶ የሚወስዳት እየመሰላት መንገድ መንገዱን ስታይ እንደምትውል ትናገራለች። ቤተሰቦቿን በድንገት ያጣችው ታዳጊ ሁሌም እነርሱን በማሰብ ትሰቃይ እንደነበር ትገልጻለች።
swiss Classic Shop – Pizza Coupons,Online Pizza Coupons from 1PizzaCoupons.com online for cheap sale.ተመልሼ እወስድሻለሁ ያላት ወንድሟ የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀርባትና የእህት ወንድሞቿ ናፍቆት ሲያንገበግባት ሁለት ዓመት በአደራ ከተቀመጠችበት ቤት ትጠፋለች። ፌሩዛ ትኖርበት ከነበረው ቤት ስትጠፋ ለመሳፈሪያ እንዲሆናት ሰላሳ ሶስት ብር ሰርቃ መሰወሯን ትናገራለች። አስፋልት ዳር ቆማ በያዘችው ብር ተሳፍራ ወደ አዳማ ትመጣለች። አዳማ የምታውቀውም የሚቀበላትም ሰው አልነበረም። ብቻ አዳማ እንደደረሰች እንደእርሷው ከተለያየ ቦታ መጥተው አስፋልት ዳር ከሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ትቀላቀላለች ።
ጥቂት ቀናትን በጎዳና ካሳለፈች በኋላ እድለኛ ሆና ጎል ኢትዮጵያ በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ታቅፋ በካምፕ ውስጥ እየኖረች ከአንደኛ ክፍል ጀምራ ትምህርቷን መማር ትጀምራለች ። ትምህርቷን እየተማረች ጎን ለጎን ድርጅቱ በሚያሰለጥነው የሰርከስ ቡድን ውስጥ ገብታ ጅምናስቲክ መለማመዷን ትቀጥላለች ። ፌሩዛ የጅምናስቲክ ስፖርት ተወዳዳሪ በመሆን ድርጅቱን በመወከል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄድ ትጀምራለች ። በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ከተሞች በተደረገው ውድድርም ተሳታፊ በመሆን ለራሷ ሜዳሊያ ለድርጅቷም የዋንጫ ሽልማት ታስገኛለች።
ፌሩዛ በጎል ኢትዮጵያ ድርጅት እየታገዘች ትምህርቷን እየተማረችና የሰርከስ ችሎታዋን እያሳደገች ባለችበት ወቅት መንግሥት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲዘጉ ሕግ ማውጣቱን ተከትሎ ጎል ኢትዮጵያም የሚረዳቸውን ልጆች ለመበተን ይገደዳል ።
ፌሩዛ ጥሩ የህይወት ተስፋ አግኝታ መኖር በጀመረችበት ሰዓት ሌላ ፈተና ይገጥማታል ። መውደቂያ የሌላት ታዳጊ ድርጅቱ የሠጣትን 10 ሺ ብር እና አንድ ማውንቴን ብስክሌት ይዛ ቤት ተከራይታ መኖር ትሞክራለች። ያኔ 13 ዓመት ይሆናታል ። የብስክሌቱ ኪራይ የወር ወጪዋን መሸፈን ያቅተዋል። ፌሩዛ ትቸገራለች። ቤት ተከራይታ መኖር ያልቻለችው ታዳጊ ዳግም ጎዳና ለመውጣት ትገደዳለች። በጎዳና ህይወቷ መከራና ስቃይ ማሳለፏን ትናገራለች። ፌሩዛ ጎዳና ላይ ሸራ ወጥረው ከሚኖሩ መሰሎቿ ጋር ተቀላቅላ መኖር እንደጀመረች ለአንድ ዓመት ያህል መፋቂያና ሶፍት እየሸጠች እራሷን ከተለያዩ ጥቃቶች እየተከላከለች ኖራለች። ራሷን የመጠበቁ ጉዳይ ግን ብዙ መዝለቅ አልቻለም። ፌሩዛ በአንድ ወቅት የመደፈር አደጋ ያጋጥማታል፤ እርሱን ተከትሎ ታረግዛለች። እስከ ተወሰኑ ወራት ድረስ እዚያው ጎዳና ላይ እየሰራችና እያደረች ህይወቷን ትገፋለች ። የመውለጃዋ ጊዜ ሲቃረብ አስፋልት ዳር ስትኖር የሚያውቋት የትራፊክ ፖሊሶች ፈቅደውላት በእነርሱ ማረፊያ ቤት ውስጥ ትወልዳለች። ፌሩዛ በሰዎች አስተባባሪነት እየተረዳች ለሶስት ወራት ያህል ከታረሰች በኋላ አሁንም ልጇን ይዛ ወደ ጎዳና ትወጣለች። ብዙም ሳትቆይ እንደገና ትደፈርና የአንድ ዓመት ልጇን እንደታቀፈች ሌላ ታረግዛለች። እንደተለመደው የመውለጃ ጊዜዋ ሲደርስ ሰዎች ቤት ተከራይተውላት መንታ ልጆችን ትገላገላለች ። ፌሩዛ በጎዳና ላይ ህይወት የሶስት ልጆች እናት ትሆናለች። ለተወሰኑ ወራት በጓደኞቿና በሚያውቋት ሰዎች እየተረዳች ትቆያለች። አሁን ሶስት ልጆችን ይዛ ጎዳና ለመውጣት አልመቻት ይላል።
ፌሩዛ አብረዋት ያሳለፉ ሴት የጎዳና ተዳዳሪዎች በሰጧት ምክር መሰረት የተከራየችበትን ቤት ሳትለቅ ልጆቿን ለሰው አደራ እየሠጠች፣ በሴተኛ አዳሪ ስራ ላይ ተሰማርታ ውጭ እያደረች በምታመጣው ገንዘብ መተዳደር ትጀምራለች። ከጊዜ በኋላ እንደውም ለልጆቿ ጠባቂ የምትሆን ሰራተኛ ቀጥራ እርሷ ማታ እየወጣች ጠዋት በመምጣት በምታገኘው ገንዘብ ህይወቷን መምራት ቀጠለች። ‹‹በወቅቱ ልጆቼን ለማሳደግ ከልመና ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረኝም›› የምትለው ፌሩዛ የሴተኛ አዳሪነቱን ስራ ወዳ የገባችበት እንዳልሆነ ትናገራለች።
ፌሩዛ ማታ በሴተኛ አዳሪነት ስራ ቀን ቀን ደግሞ መፋቂያ፣ ጀብሎና ሶፍት እየሸጠች በምትኖር ሰዓት በአጋጣሚ ከዛሬው ባለቤቷ ጋር ትተዋወቃለች። ቅርርባቸው ጠንክሮ ትዳር እስከ መመስረት ይደርሳሉ።
ኢብራሂምና ፌሩዛ ትዳር መስርተው መኖር ከጀመሩ በኋላ ቀንና ሌሊት በጎዳና ላይ እየነገዱ መኖር ይጀምራሉ። በሴተኛ አዳሪነቷ ሳይጠየፋትና የሶስት ልጆች እናት መሆኗ ሳይከብደው አብሯት እየኖረ ያለው ባለቤቷ ትልቅ ባለውለታዋ እንደሆነ ትናገራለች ። ሲተዋወቁ እርሱ የጋራዥ ሰራተኛ ነበር። አብረው መኖር ከጀመሩ አሁን 12 ዓመታትን አሳልፈዋል። ሶስት ተጨማሪ ልጆችን አፍርተው በጎዳና ላይ ንግድ ስድስት ልጆችን ያስተዳድራሉ።
ኢብራሂምና ፌሩዛ ምንግዜም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት ድረስ ከአዩ ሆቴል አቅራቢያ አስፋልት ዳር ባለች ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲሸጡ ያድራሉ ። ከማለዳው አንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ እነርሱ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ልጆቻቸው እየተፈራረቁ ያግዟቸዋል ።
ጭር ባለው ሌሊት ወደ ጂቡቲ ለሚመላለሱ የከባድ መኪና ሾፌሮችና ጭፈራ ቤት ለሚያመሹ የከተማዋ ወጣቶች እንዲሁም እግር ጥሏቸው ለሚመጡ ሰዎች የእነፌሩዛ የሌሊት ንግድ መፍትሄ የሰጠ ነው ። እንደ ሻይ፣ ቡና፣ ዳቦ፣ የተቀቀለ እንቁላልና ድንች፣ ውሃ፣ የሞባይል ካርድ፣ ብስኩት፣ ሲጋራ፣ ሻማ፣ ካልሲ፣ ቁምጣ ፣ ወዘተ ከሚሸጧቸው ውስጥ ናቸው ። በሌሊቱ ንግድ እቃዎች ቀን በሚሸጡበት ዋጋ አይሸጡም ። በሁሉም እቃዎች ላይ ያልተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ይስተዋላል። ለምን? ብለን ስንጠይቅ የሰጠችን መልስ አለ። ‹‹በውድቅት እየሰሩ በመደበኛ ዋጋ መሸጥ አዋጭነት የለውም ። አንድ ሰው እንቅልፍ አጥቶ፣ ብርድ እያቆራመደው የሚቀመጠው ለማግኘት ነው ። ተገልጋዩ የሚፈልገውን ነገር በዚያ ሰዓት ማግኘቱ በራሱ አንድ ነገር ነው ። ስለዚህ እኛንም ተጠቃሚውንም በማይጎዳ መልኩ ነው የምንሸጠው›› ትላለች።
ፌሩዛና ኢብራሂም የሌሊት ንግዱን የጀመሩበት አጋጣሚ እንዲህ ነው። መጀመሪያ የሚሰሩት ቀን ቀን ነበር። ደንብ አስከባሪዎችና ታጣቂዎች ሕገወጥ ንግድ አትሰሩም እያሉ ሲያባርሯቸው ከነሱ ለመደበቅ ሲሉ ልክ የሚቆጣጠሯቸው አካላት ወደ ቤት እንደገቡ እነርሱ እየወጡ መስራት ይጀምራሉ። ሶስት ሰዓት ስራ ይጀምሩና እስከ አምስትና ስድስት ሰዓት ከሸጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ይገባሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ እስከ ሰባት እስከ ስምንት ሰዓት መስራትን እየተለማመዱ የሌሊት ንግዱም እየተመቻቸው ሲመጣ እያደሩ ለመስራት ይበቃሉ ።
አሁን በሚያገኙት ገቢ ወጪያቸውን ሸፍነው አራት ልጆችን እያስተማሩ ናቸው። የመጀመሪያ ልጇ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆናለች ። ቀን ቀን የትምህርት ሰዓቷ እስኪደርስ ወይም ከትምህርት ቤት ከመጣች በኋላ ከወንድሞቿ ጋር እየተፈራረቀች እነፌሩዛን ታግዛለች ። ሁለቱ ልጆች ለትምህርት ያልደረሱ ናቸው ። ፌሩዛ ከጎዳና ህይወት ወጥታ፤ ትዳር መስርታ፤ ቤት ተከራይታ ልጆቿን እያስተማረች መኖሯን ስታስብ ማመን ያቅታታል ።
በተለይ ህይወቷን እንድትቀይር የረዳት ስራ በጀመረች ጥቂት ዓመታት በሴፍቲኔት ስር ታቅፋ በቁጠባ ያጠራቀመችውን 17 ሺ ብር በመውሰድ የተለያዩ ሸቀጦችን ገዝታ ስራዋን ማስፋፋቷ እንደሆነ ትናገራለች ።
ፌሩዛ ማጅራቷ ላይ እባጭ ወጥቶባት እየሰራች ባጠራቀመችው ብር መታከም እንደቻለች ትናገራለች። ይህም ለእርሷ ትልቅ መሻሻል ነው ። ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ሰዎች ተቸግረው ማየት አትፈልግም ። በአንድ ወቅት የእርሷው የቅርብ ሰው የሆነች የማህጸን እጢ ታማ ያቅሟን እረድታት እንዳሳከመቻት ትናገራለች ።
ፌሩዛ በርትታ በመስራት የራሷ የሆነ መኖሪያ ቤት እንዲኖራት ትፈልጋለች። ልጆቿን አስተምራ ለቁምነገር ማድረስና አቅሟን አሳድጋ ስራዋን መቀየርም ትመኛለች። ዛሬ በአንድ እግሯ መቆም ባትችልም ተስፋዋን ከርቀት እያየች ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች ። ለጊዜው ከሴተኛ አዳሪነት ህይወትና የሰው እጅ እያዩ ከመኖር ወጥታ ቤተሰቦቿን እያስተዳደረች መኖሯ ለእርሷ ትልቅ ዓለም እንደሆነ ትናገራለች ። ወንድሞቿንን እና እህቶቿን አላህ በሰላም በጤና አቆይቷቸው በአይነ-ስጋ ልታያቸው ጓጉታለች። እኛም አላህ ሃሳቧን እንዲያሳካላት ተመኘን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013