ባለፈው ዓመት የተሰራ ጥናት እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ በከተሞች ካለው ስራ ውስጥ አንድ ስድስተኛ የሚሆነው በኢ- መደበኛ ዘርፍ የተያዘ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ከተሞች የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡ ለአብነት ያህል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን ችግር ለመቅረፍ በ2010 ዓ.ም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣውን ኢ-መደበኛ ንግድ ህጋዊ እውቅናና ስርዓት የሚያስይዝ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቆ ነበር፡፡
መደበኛ ስራ ላይ የተሰማሩትን ወደ መደበኛ ለማሸጋገር የመስሪያ ቦታዎችን ለማስተላለፍ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጾ ነበር፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ኢ-መደበኛ የሆኑ የንግድ ዘርፎችን መቆጣጠር እና መከታተል የሚያስችል ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቢሮው ሲከታተል እና ሲመራ የቆየውን መደበኛ ንግድ በተጨማሪ ይህንንም ዘርፍ ለመደገፍ እንዲቻል መዋቅር ተዘርግቶ ራሱን የቻለ ደምብ እና መመሪያ መዘጋጀቱንም ገልጾ ነበር።
ሆኖም ችግሩ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ አሃዞች እንደሚጠቁሙት በዘርፉ የተሰማሩት ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህ የታክስ ስርዓት ውስጥ ያልተካተቱ በመሆናቸው ከተሞች በታክስ መልክ ማግኘት ያለባቸውን ገቢ እንዳያገኙ በማድረግ የከተሞች እድገት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ያሳድራል።
ከዚያ አለፍ ሲልም እንደ አዲስ አበባ ባሉት ከተሞች እግረኛ እና የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ እስከ ማስተጓጎል ደርሷል፡፡ በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት ቁጥር እንዲያሻቅብ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሲኖሩ በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ችግሩ እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል፡፡
ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት መባባስ፣ በመደበኛ ስራ ውስጥ ለመግባት አስፈላጊ የሆነው ብድር እና መሬት በተገቢው መንገድ አለመቅረብ፣ አነስተኛ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ መጫን በርካቶች ወደ ኢ መደበኛ ዘርፍ እንዲሸሹ እያደረጉ ካሉት ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ የኢ መደበኛ ዘርፍ መስፋፋት መንግስትን ከመጉዳቱ ባሻገር በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶችንም ለተለያዩ ችግሮች ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት መደበኛው ጭምር ወደ ኢ መደበኛ እየገባ ነው፡፡ መደበኛ የተባሉት አብዛኞቹ ለተወሰነ ጊዜ እንደ መደበኛ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ይቆዩና ራሳቸውን ቀይረው ኢ-መደበኛ ሆነው ይታያሉ፡፡ ኢ መደበኛው ወደ መደበኛ እንዲመጣ እንዲሁም፤ መደበኛው ወደ ኢ መደበኛ ስርዓት እንዳይሄድ የተለያዩ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ይላሉ፡፡
በኢ-መደበኛ የተሰማሩትን ወደ መደበኛ ዘርፍ ለመመለስ እና በመደበኛ ዘርፍ የተሰማሩት ወደ ኢ- መደበኛ ዘርፍ እንዳይሄዱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ በተለይም በብዛት ወደ ኢ- መደበኛ ዘርፍ እየተቀላቀሉ ያሉ ወጣቶችን ወደ መደበኛው በመመለስ ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ምንም እንኳን ኢ መደበኛ ማጥፋት ባይቻል እንኳ መቀነስ ይቻላል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ፤ በኢ- መደበኛ ዘርፍ የተሰማሩት ወጣቶች ወደ መደበኛ ዘርፍ መምጣት እንዲችሉ በተለይም መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩት ወጣቶች ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ አለበት፡፡ ለዚህም በቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መሸፈን ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ የስራ ቦታ፣ የፋይናንስ እንዲሁም ከታክስ ጋር ተያይዞ ያሉ እንቅፋቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡
እስካሁን ድረስ መንግስት በማህበር ለተደራጁት ብቻ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ምሁሩ፣ በቀጣይ ጊዜያት ግን በግልም አነስተኛ ቢዝነሶችን የሚያንቀሳቅሱ እና ጥሩ አቅም እና ፍላጎት ያላቸው የቢዝነስ ባለቤቶችን በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ከመንግስት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የራሳቸው ቢዝነስ ላይ ትኩረት አድርገው የመስራት ፍላጎት ያላቸው ድጋፍ ሊነፈጋቸው አይገባም፡፡
የኢ- መደበኛ ዘርፍ መስፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለው በከተሞች እንደመሆኑ መጠን፤ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ ትኩረት አድርጎ መስራት ችግሩን ለመቆጣጠር እና ስራ አጥነትን ለመቀነስ ሌላኛው መፍትሄ ነው። በመሆኑም ይህንን ስራ ከክልል ከገጠር ወረዳዎች ቀበሌዎች ጋር በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ፤ በቀጣይ አስር ዓመት የልማት ፕሮግራም ውስጥ መንግስት የገጠር ስራ እድል ፈጠራ እና ለስራ አጦች ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በትኩረት ለመስራት ዝግጁነት እንዳለው እየገለጸ ነው፡፡ ይህ እቅድ በወረቀት ላይ ብቻ እንዳይቀር እና በተግባር መሬት ላይ ወርዶ እንዲተገበር ቁርጠኛ አመራር መስጠት አለበት። ለዚህም በቅርቡ የተቋቋመው የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከፌዴራል እስከ ክልል መዋቅሩን ዘርግቶ መንቀሳቀስ አለበት፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013