የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ‹‹ፍረዱኝ›› ዓምድ በመሬት እና መሬት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም ከአርሶ አደር ይዞታዎች ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ከሚኖሩ የተለያዩ ተጎጂ ግለሰቦችን አቤቱታ እና ቅሬታ ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወቃል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ሸማቾች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ (ቀጣና) የመጡ እና መሬታችን በጉልበተኞች እንዲወሰድ መንግሥት የተለያየ ኃላፊነት በሰጣቸው እና ህጋዊ ያልሆኑ ሰዎች ሸፍጥ ተሰርቶብናል፣ ካሳና ምትክ ያላገኘንበትን መሬት በወረዳ ላይ ባሉ ኃላፊዎች ሽፋን ሰጪነት እንዲወረር እና እንዲወሰድ ተደርጎብናል በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሶስት የአርሶ አደር ልጆች(ወ/ሮ አልማዝ በዩ፣ ወ/ሮ ቡሩሴ በዩ እና አቶ በቀለ በዩ)ናቸው።
በወረዳው ሥራ አስፈጻሚ፣ የአርሶ አደር ተወካዮች ፣ በቀጣና አመራሮች እንዲሁም በወረዳ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ባሉ መሃንዲሶች ተፈጸመብን ያሉትን ግፍ በተከታታይ በሁለት እትም የካቲት 10 እና መጋቢት 1ቀን 2013 ዓ.ም ማስነበባችን ይታወቃል።የመጨረሻውን ክፍል እንደሚከተለው አቅርበናል።
እነዚህ ከአንድ ቤተሰብ የመጡ ሦስት የአርሶ አደር ልጆች ወላጅ እናታቸው ከሞቱ በኋላ ሲጠቀሙበት የኖሩትን የእርሻ መሬት እንዲሁም ቤት ያለበት ይዞታ የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ጉልበተኞች እና ህገወጦች እንዲወሩት ሽፋን በመስጠታቸው ህገወጦች ህጋዊ እንዲሆኑ መደረጉን ይጠቅሳሉ። እኛ በፍርድ ቤት እንኳን ተከራክረን መርታት በማንችልበት መልኩ የተለያዩ የሀሰት ሰነዶች፣ ቃለ ጉባኤዎች እንዲደራጁላቸው በማድረግ በኩል በወረዳ ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች እጃቸው አለበት ሲሉ መረጃዎቻቸውን በጽሑፍ እና በፎቶግራፍ አስደግፈው አቅርበዋል።
በመጀመሪያ ለውጡን ተከትሎ ወረራ ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ህገወጦችን በተመለከተ ለመረጃ እንዲሆን በማሰብ ፎቶ ግራፍ በማንሳት እየተካሄደ ያለውን ወረራ እንዲያስቆምና ህጋዊ ከለላ እንዲሰጣቸው እና ይዞታቻውን በህጋዊ መንገድ ካርታ ለማግኘት ወደ ክፍለ ከተማ ሲሄዱ ህገወጦች በጎን ካርታ ለማውጣት የአጥር ማጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለአምስት ጊዜያት ያክል የተገነባውን ህገ ወጥ ግንባታ ፣ማስፈረሳቸውን በእጃቸው ላይ የሚገኙ የሠነድ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ይሁን እንጂ እንደ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ወራሪዎች ከጀርባቸው አይዞህ ባይ አመራሮች ስለነበሩቸው ለስድስተኛ ጊዜ ህገ ወጥ ወረራው በመካሄዱ በምስክር እና በተለያዩ ሰነዶች (የግብር ወረቀት እና የወራሽነት) የአቤቱታ አቅራቢዎች መሆኑ የተረጋገጠውን ይዞታ በምን ምክንያት ድጋሚ ሊታጠር እንደቻለ እንዲጣራ በሥራ አስፈጻሚው በኩል ለቀጣና አመራሮች በመመራቱ በቦታው ድረስ ሲሄዱ ግንባታውን የሰራውን ሰው ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቅሰው መልስ ይሰጣሉ። በዚህም ህገወጥ ወረራው ይዞታው ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ አቤቱታ አቅራቢዎች ሜዳ ላይ ወደቁ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎች ገለጻ፤ በወረዳ ደረጃ መፍትሄ ቢያጡም ተስፋ ባለመቁረጥ እና ፍትህን ከተደበቀችበት ቆፍረው ለማግኘት በየጊዜው ከወረዳው የተሰጣቸውን ምላሾች በማያያዝ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ አቤት ማለት የየዕለት ስራቸው ሆነ። አቶ ፈቃዱም ይዞታው የግለሰቦቹ መሆኑ ከተረጋገጠ በይዞታው ላይ እየተካሄደ ያለው ህገወጥ ወረራ እንዲቆም የሚል ደብዳቤ ለክፍለ ከተማው ይዞታ አስተዳደር እና ለወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ይልካሉ።ሆኖም ደብዳቤዎቹን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የቀጣና አመራሮች እና የወረዳ አመራሮች ቢመራም ህገወጦችን ከመገንባት ሊያስቆሟቸው አልፈለጉም፤ አልቻሉም።
ሆኖም ህገወጥ ወረራው ባለመቆሙ «በተከታታይ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለይተው እስኪያውቁን ድረስ ወደ ቢሮአቸው እየተመላለስን አቤት ብለናል» የሚሉት አቤቱታ አቅራቢ፤ ሁልጊዜም የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን አቤቱታ አቅራቢዎችን በትህትና ይቀበሏቸው እንደነበር ይናገራሉ። ከክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ ቢሮ የማይጠፉት አቤቱታ አቅራቢዎች ከዕለታት በአንድ ቀን አቤት ለማለት በሄዱበት አጋጣሚ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ደብዳቤ ተቀብሎ ማስፈጸም ያልቻለው የወረዳ አስራ ሁለት ሥራ አስፈጻሚ ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸውን ይናገራሉ። በዚህም አጋጣሚ የቦሌ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚው ‹‹ ለነዚህ አዛውንቶች መሬት ባይኖራቸው እንኳን መሬት ፈልጋችሁ ስጧቸው›› የሚል ትእዛዝ አስተላለፉ።አቤቱታ አቅራቢዎችም ‹‹እኛ የሰው መሬት አንፈልግም የራሳችንን መሬት ከወራሪዎች ብቻ አስጥሉልን›› ብለዋቸው እንደነበር ያስረዳሉ።
ሆኖም እንኳንስ መሬታቸው ሊመለስ ይቅርና በየቀኑ በይዞታቸው ላይ ህገወጥ ግንባታ እየተባባሰ በመምጣቱ እና የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት አምስት ጊዜ ያህል እንዳላፈረሰ ሁሉ ቀንን ቀን ሲወልደው ለጩኸታችን ምላሽ ለመስጠት አምስት እርምጃ ወደ ኋላ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እየሄደ ቁርጥ ያለ ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው በሳምንት ሦስት ቀን (ሰኞ፣ረቡዕ፣አርብ) የአቶ ጥላሁንን ቢሮ ደጅ መጥናት ሥራቸው ሆኖ እንደነበር ቅሬታ አቅራቢዎች እንባ እየተናነቃቸው ይናገራሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ ከክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ጋር ገብተን በወጣን አንድ ቀን ማግሥት አቶ አምዴ ተሰማ፣ አቶ ሰቦቃ ለታ እና አቶ ግስላ ዘውዴ ጠርተው ‹‹አቶ ጥላሁን በእናንተ ጉዳይ እጅግ እየወቀሰን ነው።ልናናግራችሁ እንፈልጋለን እና እንድትመጡ›› በማለት እነርሱ በሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ይቀጥሯቸዋል።አቤቱታ አቅራቢዎችም የመሬታቸው ጉዳይ እልባት ሊሰጧቸው እንደሆነ በማሰብ እና ተስፋ ባለመቁረጥ በሌሊት ከአንደኛው የአርሶ አደር ተወካይ (አቶ ሰቦቃ ለታ) ቤት በር ላይ ከጠዋቱ 12፡30 ላይ ተገኙ። ረፋዱ ላይ መሬታቸውን በወረራ እና በጉልበት ወስደውብናል ከሚሏቸው ሰዎች መካከል የአቶ ተሰማ ገመቹ ልጅ የሆነው ንጉሴ ተሰማ የሚባለው ሰው መጣ። አቶ ሰቦቃም እዚህ የጠራናችሁ “ለሽምግልና ነው” አሉ።ንጉሤ ተሰማም ለወሰደብን መሬት እንደካሳ በሽምግልና 300.000.00 ብር (ሦስት መቶ ሺህ ብር) ሊሰጣቸው እንደሚችል እና አቶ ሰቦቃ የተባሉት የአርሶ አደር ኮሚቴም ብሩን ተቀብለን ክስ እንድናቆም በማስጠንቀቅ ይመክሯቸዋል።
ይሁን እንጂ አቤቱታ አቅራቢ አርሶአደሮች ‹‹መሬታችንን ይመልስልን እንጂ ብሩን አንቀበልም›› በማለት የሽማግሌዎችን አማራጭ ሃሳብ ውድቅ ያደርጋሉ።በሌላ ጎኑ እነዚሁ የገበሬ ተወካዮች “መሬቱን ደርግ ለተሰማ ገመቹ በሰፈራ የሰጠው ነው” ብለው የመሰከሩ ሰዎች መሆናቸውን በክፍል አንድ እና ሁለት በወጡት የፍረዱኝ ተመላክቷል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ይህን የተበዳይ አርሶ አደር ልጆች መረጃ በመስማት እና በማየት እነ አቶ ሰቦቃ ዘውዴን ሰዎቹ ብር ተቀብለው ክስ እንዲያቆሙ ሽምግልና ተቀምጣችሁ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ባቀረብንላቸው ሰዓት ሊያስማሟቸው መሞከራቸውን ነገር ግን ሁለቱ እህትማማቾች ወ/ሮ አልማዝ በዩ እና ወ/ሮ ቡሩሴ በዩ በዚህ አንስማማም ብለው መሄዳቸውን አረጋግጠዋል።
አቤቱታ አቅራቢው የአርሶ አደር ቤተሰብ ተስፋ ባለመቁረጥ ተመልሰው ወደ ቦሌ ክፍለከተማ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን መሄዳቸውን እና እርሳቸውም በጊዜው ለነበሩት የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወረዳ ላይ ሄደው መፍትሄ እንዲሰጡ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን ይናገራሉ። አቶ ተስፋዬም ወረራ የተፈጸመበት ቦታ ላይ አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ እንዲጠብቃቸው ቀጠሮ ያስይዛሉ።በቀጠሮው ቀን አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ቀደም ብሎ ቦታው ላይ ይገኛል። እንደተባለውም የክፍለ ከተማው ኃላፊዎች አቶ ተስፋዬ የመሬት ልማት ማኔጅመት ኃላፊ ፣ አቶ ዳንኤል የይዞታ ክፍል ኃላፊ እንዲሁም አቶ ጣሰው የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ቢሮ ኃላፊውን ጨምሮ ሌሎችም ተገኙ። ይሁን እንጂ እነኝህ የህዝብን ኃላፊነት የወሰዱ አካላት ሚዛኑን ያልጠበቀ ፍርድ ማስተላለፋቸውን አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ያስረዳል።
በዚህም ለከፍተኛ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎች፤“ለምን እውነታን ያልያዘ ውሳኔ አስተላለፋችሁብን?” ብለው ከክፍለ ከተማው ለመጡ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች መጠየቃቸውን ያስረዳሉ። እነኝህ ኃላፊዎችም ‹‹ወረዳው መሬቱ በእናንተ ወራሪ የተባሉት ሰዎች ነው ብሎ ከሰጣቸው ክፍለ ከተማው ምንም ማድረግ አይችልም›› የሚል ሌባን የሚያበረታታ እና ተበዳይን ደግሞ ልብ የሚሰበር ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ አቶ ተሰማ ገመቹ በጉልበት የወሰደብንን ቦታ እንዲሁም እሱ ይኖርበት የነበረውንና መንገድ ሲቀረው አስፋፍቶ የያዘውን የራሱን ቦታ ለማሳየት ይሞክራሉ። መንግሥት ለገበሬው ከፈቀደው በላይ መሬት ወርሮ መያዙን ግቢ ገብተው እንዲያዩ አስፋፍቶ የያዘው የመንግስት መሬት አልበቃ ብሎት የአቤቱታ አቅራቢዎችን ቦታ ጨምሮ መቀማቱን በመሃይም አንደበታቸው ለማስረዳት ደፋ ቀና ብለዋል። አስፋፍቶ የያዘውን የመንግስት ቦታ ከክፍለ ከተማው የመጡት የስራ ኃላፊዎች ለማየት ፈቃደኛ አል ነበሩም። እዚያው አጠገባችን አይናቸው እያየ እና ጆሮአቸው እየሰማ መሬታቸውን በጉልበት ቀማን ከሚሉት ተሰማ ገመቹ ልጅ(ንጉሤ ተሰማ) ጋር ተጨዋውተው እና ተሳስቀው ሲያበቁ ወደ ተበዳዮች ዞረው ‹‹እናንተ በፍርድ ቤት መክሰስ ትችላላችሁ›› በማለት በየመኪናቸው ገብተው ተመለሱ።
በመሰረቱ አቶ ተሰማ የገበሬ ልጅ እንጂ ገበሬ አለመሆኑን የቡልቡላ ነዋሪ በተለይም የአካባቢው ሰው በደንብ ያውቃል ይላሉ ተበዳዮቹ። እውነት ነው አባቱ አቶ ተሰማ ገመቹ ገበሬ ነበሩ። ደርግ ከመሬታቸው ላይ አንስቶ በሰፈራ ከአቤቱታ አቅራቢዎች መሬት ላይ እንዳሰፈሯቸው እና ኢህአዴግ ሲመጣ ደግሞ በልማት ምክንያት ከሰፈሩበት ቦታ ላይ አንስቶ ምትክ መሬት እና ገንዘብ ሰጥቶአቸዋል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ሆኖም በኋላ ላይ ባገኙት እና እጃቸው ላይ ባለው መረጃ አቶ ተሰማ ገመቹ ቀደም ይኖርበት የነበረውን እና አስፋፍቶ የያዘውን ቦታ የአባቱ እንደሆነ አድርጎ ‹‹እነ ተሰማ ገመቹ›› በሚል ካርታ ያሰራበት ሲሆን አቤቱታ አቅራቢዎቹ የቀማውን መሬት ደግሞ በሚስቱ እና በሦስት ልጆቹ ስም ካርታ እንዳወጣበት ይናገራሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅሬታ አቅራቢዎች ፍትህን ለመፈለግ አንዴ ወረዳ አንዴ ቀበሌ ሲመለላሱ በነበሩበት ወቅት
የተለካ መንገድ እና ፕላን የወጣበት ቦታ ግን በወራሪዎች የተወሰደ በወረራ የያዙትን መሬቱን ቦታ ቦታ አስያዙት።ለዚህ ደግሞ ተባባሪያቸው ከወረዳው ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማው ድረስ ያሉ መንግሥት ያስቀመጣቸው ኃላፊዎች ናቸው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎች።
ውድ አንባቢያን ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ ዝግጅት ክፍላችን እጅ ውስጥ ካሉት መረጃዎች አንዱ በ2010 ዓ.ም ድጋሚ መሬት ስለሚጠይቁ አርሶ አደሮች ከወረዳ ስለ አርሶ አደሮች ማጣሪያ የተደረገበት ሲሆን ቦታን ደጋግሞ አለአግባብ ስለወሰዱ ሰዎች እና በክፍለ ከተማው መስተናገድ ስለሌለባቸው ሰዎች ለክፍለ ከተማው ሰነድ አልባ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በሸኚ ደብዳቤ የተጻፈ ቃለ ጉባኤ ነው።በዚህ ቃለ ጉባኤ ላይ የአቶ ተሰማ ልጅ አቶ ንጉሴ ተሰማ የአያቱን የአቶ ገመቹ መኩሪያን ቦታ (ኢህአዴግ አስነስቶ ምትክ የሰጣቸውን ቦታ) በድጋሚ ካርታ ሊያወጣበት መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ ፣ አቶ ገመቹ መኩሪያ በኢህአዴግ መንግሥት የተሰጣቸውን ምትክ ቦታ መሸጣቸውን ነባሩንም ቤታቸውን ማፍረሳቸውም እንዲሁም ቀድሞ በሰፈራ የተነሱበትን ቦታ አሁን የልጅ ልጃቸው ንጉሴ ተሰማ እየኖረበት እንደሆነ በመግለጽ በክፍለ ከተማው ሰነድ አልባ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መስተናገድ እንደሌለበት ጭምር ያትታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅሬታ አቅራቢው እንዲህ ይላሉ ‹‹ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ አቶ ጥላሁን ቢሮ ሄድን ሆኖም አቶ ጥላሁን እንደሌላ ጊዜው ሊያስተናግዱን ቢያንስ የተስፋ ቃል ሊነግሩን አልፈለጉም ፡፡ይልቁንም ከዚህ በኋላ ወደ እኔ ቢሮ እንዳትመጡ በሚል መልስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሰናበቱን፡፡” አቤቱታ አቅራቢዎችም ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ የተጻጻፉትን መረጃዎች ይዘው በጊዜው ማዘጋጃ ቤት ወደሚገኘው የሰነድ አልባ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መሄዳቸውን እና በጊዜው ያገኙአቸው አሁን በውል ስማቸውን የማያስታውሷቸው ኃላፊ ለም ሆቴል የሚገኘው ‹‹የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ቢሮ›› እንዲቀበሏቸው ስልክ ደውለው ይልኳቸዋል። እዚያ ያገኟቸው ኃላፊም ቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ ወዳሉት አቶ ዑመር የተባሉ ኃላፊ ጋር እንዲያስተናግዷቸው ይመሯቸዋል። አቶ ዑመርም የአቤቱታ አቅራቢዎችን መረጃዎች ካዩ በኋላ ‹‹ግለሰቦቹ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ መልስ ለምን እንዳልተሰጣቸው ምክንያቱ ተገልጾ እንዲጻፍ›› በማለት አቤቱታ አቅራቢዎችን ከራሳቸው በራሪ ደብዳቤ ጋር አያይዘው ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ጻፉ። ሆኖም መሬታቸውን ወርደው ወረዳ ላይ ያዩት እና ምንም ፍትህ ሳይሰጧቸው የተመለሱት አቶ ተስፋዬ በቃል ‹‹መልስ አልሰጥም›› ብለው እንደመለሱአቸው የተበዳይ ቤተሰቦች ያብራራሉ።
አቶ ዑመር የተሰጣቸው መረጃዎች እንደሚያመ ለክቱት ወረራው ይቁም፣ አጥራቸው መልሶ ይታጠር፣ መልስ ይሰጣቸው፣ ይፈጸምላቸው፣ ይጣራላቸው የሚል ተስፋ ያዘለ መልስ ቢመስልም ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንዲሉ አንድም የመንግስት አካል መፍትሄ እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ።
‹‹በየጊዜው እና በየቦታው አቤት ብንል የሚሰማን የመንግሥት አካል የለም›› ይላሉ ተጎጂዎች።አዲስ ሰው ሲመጣና የአቤቱታ አቅራቢዎችን ጉዳይ ሲሰማ እጅግ ያዝናል።ሆኖም ውሎ ሲያድር ከህገ ወጦች ጋር ያብርና ፊቱን በማዞር አቤቱታቸው ምላሽ ሳያገኝ እስከዛሬ በዘራፊዎች ተወስዶ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ሆኖም ተስፋ ባለመቁረጥ ለተለያዩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ “አቤት አልን” የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህም ከተወረሩት አንዱ ቦታ(ሀብታሙ ፈቃዱ እና በአዲሱ መኮንን የተያዘው ቦታ) ህገ ወጥ አጥሩ ፈርሶ በመሰጠታቸው ደስ እንደተሰኙ ይናገራሉ።አጥሩ ይፍረስ እንጂ ህገወጦች ውስጥ ውስጡን ከወረዳ ፋይል ተደራጅቶላቸው ስለነበር ክፍለ ከተማው በቦታው ላይ ቅሬታ አለመኖሩ ተጣርቶ ይምጣልኝ ብሎ ለወረዳው መሬት ማኔጅመንት ደብዳቤ ላከ።ጉዳዩ በወረዳው ይታወቅ ነበርና አቤቱታ አቅራቢዎች “ይዞታችን ነው” ብለው በየጊዜው ስለቦታው የተጻፈውን ደብዳቤ ያሳያሉ። በሚቀጥለው ጊዜ አቤቱታ አቅራቢዎች ከወረዳው መሬት ማኔጅመንት ቢሮ በሄዱ ጊዜ የቢሮው ኃላፊ ከክፍለ ከተማው የመጣው ደብዳቤ ጠፋ እንዳሏቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ አመላክተዋል።እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ የወረዳው መሬት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ (አቶ ኢብሳ ዳንዳና) በኋላ ለእነዚህ ህገ ወጦች ፋይል እንዲደራጅ ደብዳቤ የጻፈ ሰው ነው።
እንደ አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ገለጻ፤ ወረራው በዚህ አላበቃም ወራሪዎች የወሰዱትን ከተቀራመቱ በኋላ ወደ ቀሪውም ይዞታችን ዘመቱ።በሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ጎረምሶችን በማሰባሰብ አቶ ተሾመ የሚባል ግለሰብ የወ/ሮ አልማዝ ግቢ ገብቶ አጥሩን ማፈራረስ ጀመረ።ወይዘሮ አልማዝ በጊዜው የተወረረባቸውን መሬት ለማስመለስ ወረዳ አቤት እያሉ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጎረቤቶቻቸው አቶ ተሾመ እና ብዛት ያላቸው ጎረምሶች ተሰብስበው አጥራቸውን እያፈረሱ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል።ያልታሰብ መርዶ የሰሙት ወይዘሮ አልማዝ ሮጠው አጥራቸውን ከሚያፈርሱት ሰዎች ላይ ይደርሳሉ።እየተደረገ ያለውን ህገወጥ ተግባር ያዩት ወይዘሮ አልማዝ ለህይወታቸውም በስጋት ከቤታቸው ፊት ለፊት ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ አጥሬን ህገወጦች አፈረሱብኝ ሲሉ ኡኡኡ ይላሉ።ይሁን እንጂ የወይዘሮ አልማዝን ኡኡታ ከምንም ባለመቁጠር ህገወጦችን እያዩ እንዳላዩ ዝም አሉ። ተስፋ ያልቆረጡት ወይዘሮ አልማዝ ወደ መምሪያው በመሄድ ለወረዳው ፖሊስ በማመልከት የወረዳው ፖሊስ ቃላቸውን እንዲቀበል ትእዛዝ ተላለፈላቸው፡፡
አቤቱታ አቅራቢዋ አክለውም እንደገለጹት፤ ጉዳዩን አቃቤ ህግ ይዞት በወንጀል መታየት ጀመረ።አጥሩን በማፍረሱ ወንጀለኛ ነው ተብሎ ውሳኔ በተሰጠበት በዚህ የፍርድ ቤት ሂደት ላይ በግንባር ቀደምነት አጥራቸውን ያፈረሰው አቶ ተሾመ በቀለ የተባለ ግለሰብ በአዋጅ 47/67 ለሚስቴ ለወይዘሮ ኮሬ ተገኝ የተሰጠ ይዞታ ነው (በአዋጁ ለእርሱ ወይም ለባለቤቱ ስለመሰጠቱ መረጃ የለም) የሚል መልስ ለፍርድ ቤት መለሰ።በአርሶ አደር ተወካዮች እንዲሁም በቀጣና አመራሮቹ በእነስንታየሁ ዳንኤል፣ በእነእሸቱ ግርማ እና በእነአድን ሽፈራው የተፈረመ እና ይዞታው የወ/ሮ ኮሬ ተገኝ ነው የሚል ቃለ ጉባኤ በማስረጃነት አቀረበ። ሰዎቹ ባልኖሩበት፣ ቤት እና አጥር በሌለበት ቤት እና አጥር እንዲያድሱ የተፈቀደበት(የወረዳው ግንባታ ጽ/ቤት የማያውቀው) በቀጣና አመራሮቹ አድን ሽፈራው፣ ስንታየሁ ዳንኤል እና በእሸቱ ግርማ የተመራ የአጥር እና ቤት እድሳት ደብዳቤ አቀረበ።ሰንበት ብሎ ካርታም አለኝ በማለት ካርታ አቀረበ።
ከ20 ዓመታት በላይ ለቤቴ ካርታ ለማግኘት ከቀበሌ እስከ ወረዳ ተንከራትቻለሁ የሚሉት የገበሬ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ አልማዝ ለአቶ ተሾመ ግን በአንድ ወር ውስጥ በባዶ መሬት ላይ ካርታ እንዴት እንዳገኙ አልገባኝም ይላሉ።እዚህ ላይ አንባቢያን ለፍርድ ይመቻችሁ ዘንድ አንድ ነገር ልብ ማለት ይገባል።ይህም ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ አልማዝ በዩ በዚሁ ወረዳ ውስጥ የአርሶ አደር ልጅ እና የአርሶ አደር ቦታ ያላቸው ሲሆን በይዞታው ላይ የተሠራና የሚገለገሉበት ቤት አላቸው።
እንደ ወይዘሮ አልማዝ ገለጻ፤ መንግሥት ቤታቸው በአየር ካርታ ላይ የሚገኝ የገበሬ ልጆች ካርታ እንዲያገኙ ባወጣው መመሪያ መሠረት በመመሪያው የተጠየቀውን መስፈርት በመከተል በቀጣና አመራሮች እና በገበሬ ተወካዮች ቤታቸው እና ቦታቸው ታይቶ በመረጋገጡ ካርታ እንዲሰራላቸው ፋይል ተደራጅቶ ተልኮላቸዋል።
በሰነድነት ካቀረቡት መረጃ ለመረዳት እንደቻልነው ቦታው ተለክቶ መንገድ ፕላን ሰርቶ ሰጥቶአቸዋል።“ይዞታ ላይ የተሰራውን አጥር ነው አቶ ተሾመ በቀለ ያፈራረሰብኝ ” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዋ፣ ከአጥሩ መፍረስ ጋር ተያይዞ ከወረዳው ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማው በተበዳይዋ የቀረቡ አቤቱታዎችና የተሰጡ መልሶች (የሰነድ ማስረጃዎች)ተያይዘው ቀርበዋል። ከነዚያ መካከልም የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጥላሁን ፈቃዱ ‹‹ባለ ይዞታዋ አቅመ ደካማ ናቸውና በህገ ወጥ መንገድ ላያቸው ላይ የታጠረው አጥር ይፍረስ›› የሚል ደብዳቤ አለ።ሆኖም ለአቤቱታቸው ምንም ዓይነት ፍትህ ሳያገኙ መቅረታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ፤ ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት ከክፍለ ከተማ አመራሮች ለወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች የሚታላለፉ ትዕዛዞችን አልቀበልም ማለታቸው እንደሆነ አመላክተዋል።
ውድ አንባብያን ፋይል ካደራጁላቸው የወረዳ አመራሮች መካከል አድን ሽፈራው፣ ስንታየው ዳንኤል እና እሸቱ ግርማ ይገኙበታል።እነኝህ አመራሮች በሌላ በኩል ተገልብጠው መሬታቸውን ለህገወጦች እየፈረሙ ለህገወጦች መስጠታቸውን በክፍል አንድ እና በክፍል ሁለት የፍረዱኝ አምዳችን በመረመርናቸው ሰነዶች ማረጋገጣችንን ነግረናችሁ ነበር ።
በህገወጥ መንገድ የፈረሰባቸውን አጥር ጉዳይ በፍርድ ቤት እየተከታተልኩ ሳለ በመሀል ካርታ ለማግኘት የሚያስፈልጉ ሂደቶች ጨርሰው ካርታ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር የሚያስረዱት ወይዘሮ አልማዝ በዩ፤ ካርታ እንዲሰራልኝ ስጠይቅ በወቅቱ ግቢውን የለካው መሃንዲስ ከቦታው ተነስቶ ሌላ መሃንዲስ ተተክታ ስለነበር። አዲሷን መሃንዲስ ካርታ እንድትሰጣቸው በጠየቁ ጊዜ ቦታውን በዓይኔ ካላየሁ ካርታ አልሰጥም በማለት ቀጠሮ እንደሰጠቻቸው ይናገራሉ።
በጊዜው የመሃንዲሷ ኃላፊ የነበረው ግለሰብ “የእናንተ ያለቀ ስለሆነ ከለካው መሀንዲስ (እዚያው ሌላ ቢሮ ስላለ) መረጃ ተቀብላ ካርታ ልትሰጣችሁ ትችላለች” ቢላቸውም ፈቃደኛ ሳትሆን ትቀራለች።በዚህም ወይዘሮ አልማዝ እንደገና ለሚመለከተው አካል አቤት ማለታቸውን ጠቁመው፤ መሃንዲሷም ወር ያህል ቆይታም ቦታውን ለማየት መጣች።ገና ይዞታቸውን ስትመለከት ‹‹አጥር የታለው? አጥር ከሌለው ካርታ አልሰራም›› በማለት ችግራቸውን ሳትፈታ በመመለስ ላይ እያለች ‹‹አጥሬን ጉልበተኞች አፍርሰውት ጉዳዩ በወንጀል ተይዞ በፍርድ ቤት እየታየ ስለሆነ ነው›› ይሏታል።ነገር ግን ልትሰማኝ ፈቃደኛ እንዳልነበረች ወይዘሮ አልማዝ ያስታውሳሉ።
“ ግፍ አይፈራ መሬት እንክርዳድ ያበቅላል” የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ አዲሷ መሃንዲስ ችግሬን አልፈታም ብላ በሄደች በማግስቱ አጥሬን ያፈረሰው ግለሰብ ወጣቶችን አስተባብሮ ቦታዬ ላይ ቤት መስራቱን ያስረዳሉ።ያዩትን ማመን ያቃታቸው ወይዘሮ አልማዝ በዩ ህግ እና መንግሥት ባለበት ሀገር በጠራራ ፀሐይ “የጨረቃ ቤት እንኳን ሌሊት ነው የሚሠራው” በማለት ህገ ወጦች በይዞታቸው ላይ ቤት ሲሰሩ እንዲያስጥሏቸው ወደ ቀበሌ ሲሮጡ ይሄዳሉ።ነገር ግን መሬታቸውን ከወረራ እና የውስጣቸውን ደም ፍላት ሊያስታግስ የሚችል አንድም የወረዳ አመራር ሆነ ደንብ አስከባሪ አለመኖሩን በስሜት ውስጥ ሆነው ይናገራሉ።
‹‹አፈር ፈጭቼ ፣ ቦርቄ ያደጉበት እና ልጅ ወልጄ የሳምኩበትን የይዞታ መሬቴን ፈሪያ እግዚአብሔርን እና ምድራዊ ህግን በረሱ ሰዎች በጠራራ ፀሃይ ሲወሰድብኝ የማደርገው መላቅጡ ሲጠፋብኝ ፖሊስ ይረዳኛል ብዬ በማሰብ ጎረቤቴ ወደሆነው ፖሊስ ጣቢያ ሮጬ ሄጄ የደረሰብኝን በደል አቤት ብልም ምላሽ የሚሰጠን ፖሊስ ማግኘት የአልማዝ ማዕድን ያህል አስቸጋሪ ሆኖብኛል” ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ ይናገራሉ።ለዚህም ዋናው ምክንያት ፖሊስ ‹‹ የመሬት ጉዳይ አያገባንም›› የሚል ነበር መልሱ።ተስፋ ሳይቆርጡ በደካማ ጉልበታቸው አንዴ ፖሊስ ጣቢያ አንዴ ቀበሌ እየሮጡ ለሚሰማቸው ሁሉ የሆነውን ቢያስረዱ፣ ቢያለቅሱ እና ቢጮሁም ማነሽ ምንድነሽ የሚላቸው ሰው እንዳላገኙ የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ በዩ፤ በዚያኑ ቀን ህገወጦቹ ሦስት ክፍል የቆርቆሮ ቤት ሰርተው ጨርሰው መገንባታቸውን አመላክተዋል።
ውድ አንባብያን የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በጊዜው ይህ ሁሉ ነገር ሲፈጸም የነበሩትን የወረዳ አመራሮች ለማናገር ጥረት ያደረገ ሲሆን ከነዚያ መካከል አንዳንዶቹ ከስራ የለቀቁ ሌሎቹ ቦታ የቀየሩ በመሆናቸው አቶ አድን ሽፈራውን እና አቶ እሸቱ ግርማ ጋር በመደወል ለማጣራት መሞከራችን ከዚህ በፊት በወጣው እትም ላይ የተወሰነው መውጣቱ ይታወሳል።ባለፈው እትማችን ለማሳየት እንደሞከርነው አቶ እሸቱ ግርማ ስልካቸውን ቢዘጉም አቶ አድን ሽፈራው ስለተፈጠረው ጉዳይ ስንጠይቃቸው መሬቱ የተበዳዮች ወላጆች ይዞታ መሆኑን ግማሹ በደርግ ግማሹ በኢህአዴግ መንግሥት መወሰዱን የገለጹልን ሲሆን አሁን ባለው ለውጥ ግን ለእያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሰጧቸውም አክለዋል።እንኳን 500 ካሬ ቦታ መስጠት ያላቸውን ህገወጦች እንዲቀራመቱት መተባበራቸውን ተበዳዮች መናገራቸው ልብ ይሏል)።
ቤት እና አጥር ያልነበራቸው ግለሰቦች ቤት እና አጥር እንዳለው ተደርጎ ስለተሰጠው መረጃ እና በባዶ ቦታ ላይ በተለይ ደግሞ ወይዘሮ አልማዝ በዩ በባለሙያ ባስለኩት እና መንገድ ፕላን በወጣበት ቦታ ላይ ስለተሰራው ቤት ስንጠይቃቸው አቶ አድን የተባሉት የቀጣና አመራር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ቤት እና አጥር ያልነበራቸው ግለሰቦቹ ችግረኛና በሽተኛ በመሆናቸው ቦታውን በሃዘኔታ መስጠታቸውን አመላክተዋል።አንባብያን ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ ከላይ እነዚህ የቀጣና አመራሮች እና የገበሬ ተወካዮች ቦታው የወ/ሮ ኮሬ ተገኝ ልጆች ነው በማለት ቃለ ጉባኤ መዘጋጀቱንና ቤት እና አጥር በሌለበት ቤት እና አጥር እድሳት እንዲያደርጉ በቀጣና አመራሮቹ በነአቶ አድን ሽፈራው ፈቃድ መሰጠቱን ልብ ልትሉ ይገባል)።ለተበዳዮች ተሰጣቸው ስለተባለው 500 ካሬ ሜትር ቦታም አቶ አድንን ስንጠይቃቸው ከዚህ በላይ መናገር አልችልም በማለት ስልካቸውን መዝጋታቸውን ከዚህ በፊት አስነብበናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤት እና አጥር እድሳት ፈቃድ የሰጠኝ የወረዳው የግንባታ ክፍል ባልደረባ የሆነውና አቶ ደምሰው አበራ የተባለው መሀንዲስ ለነዚህ ህገወጦች ቤት እና አጥር በሌለበት ቦታ ላይ ካርታ ያገኙ ዘንድ ከወረዳ የተደራጀ ፋይል ላይ እንደፈረሙላቸው የሚያስረዱት ወ/ሮ አልማዝ በዩ፤ በክፍለ ከተማም ደረጃ ካርታ የሰጠቻቸው የይዞታ ክፍል ባልደረባ የሆነችው ወ/ሮ አበባ ለህገወጦች ግቢዬና መውጫዬ ላይ ካርታ ስትሰጣቸው (እነዚህ ግለሰቦች ህጋዊ ቢሆኑ እንኳን) እንደ ይዞታ አስተዳደር ሕግ ከአጎራባች ሰዎች በኩል ፈቃድ አለመጠየቁን አመላክተዋል።ይህ የሚያሳየው ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ በተዘረጋ ሰንሰለት ለህገወጦች ወረራ እንዴት እንደሚመቻች ነው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዋ።
ወይዘሮ አልማዝ እንደገለጹት፤ አንዱ ወንድማችን አቅመ ደካማ በመሆኑ ጉዳዩን የሚከታተሉት ከሌላኛዋ በደል ከተፈጸማት እህታቸው ጋር ነው። ጉዳያቸውን ከዳር ለማድረስ ተስፋ ባለመቁረጥ አሉ የተባሉ እና የሚመለከታቸውን የመንግሥት መዋቅር አዳርሰዋል። ሴትነታቸው እና ደካማነታቸው ሳይበግራቸው እውነትን እና ፍትህን ፍለጋ ያልገቡበት መስሪያ ቤት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይሁን እንጂ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ስነምግባር የሌላቸው ጥቂት ሰዎች እጅ በስፋት በመኖሩ ተስፋቸውን የሚያጨልም ነገር ገጥሟቸዋል።
በደርግ ጊዜም በደርግ ከተወሰደባቸው መሬት ውጭ በነበራቸው መሬት ግብር ይገብሩ እንደነበር መረጃዎች በእጃቸው ላይ ቢኖሩም የጃንሆይን ርስት እንደሚጠይቁ እየተደረገ መረጃ በመጻፍ እንዲሁም የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ርስት ነው የሚጠይቁት እየተባለ የዘር ሀረጋቸውን በማራቅ በፍርድ ቤት እንኳን መርታት በማይችሉበት መንገድ በአቤቱታ አቅራቢዎች እና ጉዳዩ የማይመለከታቸውን የገበሬ ተወካዮች ቃለ ጉባኤ እና ደብዳቤ በመጻፍ የተንሻፈፈ ፍርድ እንዲፈረድባቸው መደረጉን ይናገራሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ የአርሶ አደር ተወካዮች በግል ሲጠይቋቸው ‹‹እኛ የናንተ መሬት በሌሎች ሰዎች እንዲወሰድ አልፈረምንም›› ይላሉ። አቤቱታ አቅራቢዎች እጃቸው ላይ የደረሱት የሰነድ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ሁሉም ላይ ለህገ ወጥ ወራሪዎች ገበሬ ሳይሆኑ ገበሬ ናቸው ብለው በሀሰት ሰነድ ላይ በሀሰት መፈረማቸውን ነው።ለምሳሌ ቤት እና አጥር በሌለበት ቤት እና አጥር እንዲያድሱ ደብዳቤ የተሰጣቸው እንዲሁም እዚያ ላልነበሩ የወ/ሮ ኮሬ ቤተሰቦች ለሦስት እህትማማቾች የአርሶ አደር ልጆች ናቸው በሚል ቃለ ጉባኤ ላይ ፈርመው ካርታ እንዲያገኙ ያደረጉት የአርሶ አደር ያለጎጣቸው መጥተው ሸማቾችን የወከሉ የአርሶአደር ተወካዮች ናቸው።በዚህ ህገወጥ ቃለ ጉባኤ የአቤቱታ አቅራቢዎችን መሬት እንዲነጥቁ ሲያደርጉ ለአቤቱታ አቅራቢዎች አንደኛው ወንድማቸው ደግሞ አርሶ አደር ነው በማለት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ሌላ አካባቢ ላይ እንዲወስድ የሀሰት ሰነድ አዘጋጅተውለታል።የአቤቱታ አቅራቢዎች የወላጅ እናት ቤት የነበረበትን ሰፊ ይዞታ ለአቤቱታ አቅራቢዎች የእህት ልጅ ለሆኑት አቶ ተካ አለሙ ሳይቀር ሰፊ መሬት ጠቅሎ እንዲወስድ በሐሰት አርሶ አደር ነው በማለት ፈርመውለታል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ባገኘው መረጃ መሠረት እነዚህ የገበሬ ተወካዮች ለሦስት እትማማቾች የአርሶ አደር ልጆች ናቸው በማለት ቃለ ጉባኤ ላይ ሲፈርሙ ለአንደኛው ወንድማቸው አርሶ አደር ነው በማለት መፈረማቸውን ለማረጋገጥ ችሏል።
በአጠቃላይ ደርግ በሰፈራ ከወሰደው መሬት በተጨማሪ የኢህአዴግ መንግስት ካሳና ምትክ ሳይሰጣቸው በጊዜው አርሶ አደር የነበሩት ወላጅ እናታቸው በህይወት ስላልነበሩ እና መመሪያው የሚያካትተው አርሶ አደርን እንጂ የአርሶ አደር ልጅን ስለማያካትት የካሳ ክፍያ አላገኘንም የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ በለውጡ መንግስት ከአርሶ አደሮች የተሰወደ መሬት ካለ ምትክ እና ካሳ እንዲከፈላቸው ወይም በኢህአዴግም ሆነ በደርግ ከመወሰድ የተረፈ መሬት ከሆነ ደግሞ የቀረውን ቦታ እንደማንኛውም የአርሶ አደር ልጆች በይዞታቸው እንዲጠቀሙ የሚል መመሪያ መኖሩን ይናገራሉ።ነገር ግን የተረፈውን የይዞታ መሬታችንን ከህገወጥ ወራሪዎች ጋር በመመሳጠር ይዞታቸውን ቀምተው ባዶ እጃቸውን አስቀርተዋቸዋል።ስለተወሰደው መሬት እንደማንኛውም የገበሬ ልጅ ኮንደሚኒየም እንኳን እንዳያገኙ የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ በመግፋት የሰው ልጅ ይፈጽመዋል የማይባል የከፋ ግፍና በደል አድርሰውብናል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ህዝብ እና መንግስት ጉዳዩን በአንክሮ ተመልክቶ ፍትህን እና እውነትን ከተቀበሩበት በማውጣት እንባቸው እንዲታበስላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013