ዛሬ የተረከብናት ኢትዮጵያ በትውልድ ፈረቃ ታላቅ መስዋዕትነት የተከፈለባት ሀገር ነች። ቅደመ አያቶቻችንና አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከጠላት ወረራ ለመታደግ የከፈሉት የገዘፈ የሕይወት መስዋዕትነት ነው ዛሬ በነጻነት ቆመን እንድንራመድ፣ ነጻ አየር እንድንተነፍስና የራሳችን ነጻ ሀገር እንዲኖረን ያስቻለን። ዓርበኞቻችን ለዚህች ሀገር ክብርና ታላቅነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ሁሌም እንዘክረዋለን። ያለትላንት ዛሬ የለም፤ያለዛሬም ነገ አይኖርም።
ኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲልና ፋና እንድትሆን በተለያዩ ዘመናት በትውልድ መፈራረቅ ከጥንት እስከዛሬ ድረስ በአራቱም ማዕዘናት የከፈሉት የደም ዋጋ ነው ዛሬ ቀና ብለን ደረታችንን ነፍተን በተከበረች ሀገር ውስጥ እንድንኖር ያስቻለን። ይህ ትውልድ የቀደሙ አባቶቹን ታላቅ መስዋዕትነት ደግሞ ደጋግሞ የመዘከር፣ የማስታወስና ተገቢውን ክብር የመስጠት የትውልድም የዜግነትም ግዴታ አለበት።
ትላንት ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር ሲባል በጀግኖች ልጆቿ ለተከፈለው ታላቅ መስዋዕትነት ተገቢውን ክብር ሰጥቶ ማስታወስና በአግባቡ መዘከር የውዴታ ግዴታም ነው። የዓለማችን ሀገራት ተከብረው የኖሩት ከአብራካቸው በተገኙት ጀግኖች ልጆቻቸው መስዋዕትነት ነው።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ለነጻነታቸው ኩሩ፤ ክብራቸውን ወዳድ፤ መደፈርን የማይቀበሉ፤ ከሀገሬ በፊት ልሙት ብለው ወራሪ ጠላታቸውን ግንባር ለግንባር ገጥመው በልበሙሉነት የሚዋጉ እንደ እሳተ ገሞራ የሚንቀለቀል የሀገርና የወገን ፍቅር ያላቸው ሞት ለምኔ ባይ ጀግኖች መፈጠሪያ ምድር ነች። በነጻነት ቀንዲልነታችው በስልጣኔ ቀደምትነታቸው የተደመመው ወራሪው
የኢጣሊያ ኃይል ባሕር አቋርጦ ዘመናዊ፣ ግዙፍ ሠራዊትና ድርጅት (ታንክ፣ መድፍና የጦር አውሮፕላን) ታጥቆ በዓለም በተከለከለ የመርዝ ጋዝ ጭምር በአውሮፕላን የቦምብ ድብደባ ያካሄደው ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት አደርጋለሁ ብሎ ነበር።
የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊትን በታላቅ ጀግንነት ተዋግቶ ድል ያደረገው በእጁ ጎራዴ፣ ጋሻና ጦር እንዲያም ሲል እጅግ ኋላ ቀር የሆኑ ጠብመንጃዎችን ታጥቆ ሀገሬን ለሰው አልሰጥም እያለ የተዋጋው ድል አድራጊው መላው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ሕዝብ ነው። ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የሀገራቸው መወረር እንደ እሬት መሯቸው ቀፎው እንደተነካ ንብ አስገምግመው ተነስተው፤ በባዶ እግራቸው በረሀውንና ቁሩን ተቋቁመው፣ጋራና ሸንተረሩን አቋርጠው ፤ ጃሎ በል እያሉ እየፈከሩ ሄደው ውጊያ ገጥመው ነው የኢጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ድል የነሱት። በዚህም ድንቅ ተጋድሎና ጀግንነት የኢትዮጵያን ታላቅነትና ድል ለዓለም አበሰሩ። አዎን ይህ ትውልድ የእነዛ ጀግኖች የእነሞት አይፈሬ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ሀገሩን ዛሬም ነገም ነቅቶ የመጠበቅ እነርሱን የመዘከር ኃላፊነት አለበት።
በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደር፤ አንገቱንና ደረቱን አሳልፎ የሚሰጥ፤ ለሀገር ሲባል ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ትውልድ ይሆን ዘንድ ግድ ነው። ትላንት አባቶቻችን ሞተው ነጻነቷን አስጠብቀው በታላቅ ክብር ያስረከቡንን ሀገር ዛሬም ተረኛው ትውልድ ጠብቆ ለቀጣዩ ትወልድ በክብር የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራም ግዴታም እንዳለበት ሁሌም በልቦናው ሊያኖረው ይገባል።
ሀገራችን ክብራችን፣ መኩሪያችን፣ መመኪያችን ጓዳና ማእዳችን ናት። ስናኮርፍ መሸሸጊያችን፣ ስንደሰትም የምንቦርቅባት፣ ውበታችን፣ ጌጣችን፣ ስናልፍም መቀበሪያችን ናት። የደስታችን፣ የትዳራችን ወልደን የመሳማችን ምስጢር ሁሉ የሚደምቀው በሀገር ነው። ለዚህ ክብርና ለነጻነታችን መከበር፤እንደልብ ወጥተን ለምንገባበት ፤ለዚህ የተከበረ ፍጹም ማንንት ያበቁንን ሰማዕት አባቶቻችንን ሁልግዜም በታላቅ ሀገራዊ ክብር ልናስታውሳቸው ይገባል።
አንተ ትውልድ ልብ በል የቀደመው ትውልድ ለእግሩ መጫሚያ አልነበረውም። ቁምጣ ሱሪ ለባሽ በእግሩ ተጓዥ፤ስንቁን በአገልግል ይዞ ጋራና ተራራ ሸጥና ሸለቆ አቋርጦ በሀገሩ ላይ የተነሳን ጠላት ለመዋጋት የሚዘምት ተጋዳይ ዓርበኛ የነበረ ነው። በዚህ መልኩ ሚሊዮኖች በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ለኢትዮጵያ ታላቅነትና ክብር ሲሉ በየፈፋው በየሸለቆው በየሸንተረሩ ወድቀው ቀርተዋል።
ዛሬ ይህ ትውልድ በሰላም ወጥቶ የሚገባው በእነዚያ ጀግኖች ደምና አጥንት በተገኘ መስዋዕትነት ነው። የኢትዮጵያ መሬት ከጫፍ እስከ ጫፍ በልጆቿ አጥንትና ደም ዋልታና ማገር ሆኖ የተዋቀረ ነው። ትውልዱ ይህንን ለአፍታ ሊዘነጋው አይገባም። ሀገራት ሁሉ ጀግኖቻቸውን በተለያዩ በዓላትና የመታሰቢያ ቀናት በልዩ ክብር ይዘክራሉ፤ያስታውሳሉ። አንዳንድ ሀገራት ለሳምንት የዘለቀ ተከታታይ ፕሮግራም በማካሄድ በራዲዮ፣በቴሌቪዥን፣በማሕበራዊ ድረገጾች አዲሱ ትውልድ ስለአባቶቹ መስዋዕትነት እንዲያውቅ ይሰራሉ።
ስራዎቻቸው ሁሉ የቀደመው ትውልድ ስለሀገር ሲባል የከፈለውን መስዋእትነት በመዘከር ላይ ያተኮሩ ናቸው። በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር የካቲት 12 ቀን የሰማዕታት ቀን ነው። ግራዚያኒ በአበሻ መሬት ክብርና ገናናነቱን ሊያውጅ የአዲስ አበባን ነዋሪ በያኔው የገነተ ልዑል ቤተመንግሥት በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰብስቦ ዲስኩር ሲያሰማ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሀገራቸው መደፈር አቃጥሎአቸው በቦምብ ሊያጋዩት ወሰኑ። አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም። አምበሶቹ ቦምባቸውን ወረወሩ። ግራዚያኒ ቆሰለ እንጂ አልሞተም። ለአጸፋው የሰጠው ትዕዛዝ « ወንድ ሴት ወጣት አሮጊት ሕጻናት ሳትመርጡ ኢትዮጵያውያንን በያዛችሁት መሳሪያ ሁሉ ጨፍጭፉ» የሚል ነበር። እናም ያን እለት አዲስ አበባ በደም ታጠበች። የአዲስ አበባ ቤቶች በሙሉ በእሳት ጋዩ። 30 ሺህ ዜጎቻችን በግፍ በአረመኔ ፋሽስቶች ተገደሉ። በአካፋና በዶማ ሳይቀር ተጨፈጨፉ።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ነጻነትና ክብር ጉዳይ ማንም ሊያንበረክካቸው እንደማይችል አለማወቃቸው እንጂ በዚህን መሰሉ ጥቃት በበለጠ ሁኔታ ከብረት ጠንክረው እልህና ቁጭት ውስጥ ገብተው ለሀገራቸው ነጻነት እንዲታገሉ፤ እንዲገድሉ፤ እንዲሞቱ አደረጋቸው። « ሰላቶ ገዳይ— ባንዳ ገዳይ— በየፈፋው ላይ- —-ውሀ– ውሀ ሲል– ከአቀበቱ ላይ!» እያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለታላቅ የዓርበኝነት ሥራ ዱር ቤቴ ብለው ሸፈቱ፤ ድልም አደረጉ።
ዛሬ ይህንን የሰማዕታት ቀን ለመዘከር በግፍ የተገደሉትን 30 ሺህ በላይ ዜጎች እያስታወስን ቢሆንም፤ በኃውልቱ ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጦ እየተጣደፉ ወደየጉዳያችን መሄዱ ብቻ ትርጉም የለውም። የእነዚያ ጀግኖች ደም ዛሬም አልደረቀም። የሰሩት አኩሪ ገድል አዳምጡኝ ፤ሀገራችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ ይላል። ለዚህ ነው ዕለቱ ሲታሰብ በታላቅ ብሔራዊ ድምቀትና ፕሮግራም ሊከወን የሚገባው። ለሰማዕታቶቻችን ታላቅ ክብር እንስጥ። ትውልድም ይቀረጽበት። መገናኛ ብዙኃኖቻችን ሁሉ እለቱ ከመድረሱ በፊትም ሆነ በኋላ ሀገር ለማቆየት የተከፈለውን እልህ አስጨራሽና ታላቅ መስዋዕትነት መዘከርን አይርሱ። እኛ ማነን ለሚለው ጥያቄም መልሱ እነርሱ ተሰውተው በእነርሱ ደምና መስዋዕትነት የበቀልን ነን ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2011
ወንድወሰን መኮንን