• አፈናቃይ ሳይሆን አካታች የልማት አቅጣጫን ይከተላል፤
• ፕሮጀክቶች በተጽዕኖ ሚዛናቸው መሰረት እንዲተገበሩ ያደርጋል፤
ጅግጅጋ፡- የቀጣይ አስር ዓመታት የልማት መሪ ፕላን ሁሉም የእኔ ብሎ በሚቀበለው፣አፈናቃይ ሳይሆን አካታች የልማት አቅጣጫን የሚያስቀምጥ፣ በከተሞች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኗቸው ተመዝኖ ወደ ተግባር የሚያስገባ መሆኑም ተገለጸ፡፡በጅግጅጋ እየተካሄደ ባለው ስምንተኛው የከተሞች ፎረም ላይ እአአ ከ2020 እስከ 2030 እንዲተገበር ለሚዘጋጀው የአስር ዓመት መሪ ፕላን ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶች ትናንት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በወቅቱም እንደተገለጻው፤ የልማት ጉዞው የህዝቦችን ይሁኝታ የሚያገኝበት፤ ህዝቦችን በጋራ ተሳስረው በሚለሙበትና በማኑፋክቸሪንግ ልማት ጉዞው የአካባቢ ጥበቃ ስራው በትኩረት የሚሰራበትን አቅጣጫ በመሪ ፕላኑ ይቀመጣል፡፡ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ልማቷን በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ስትመራ ብትቆይም፤ አሁን ላይ የሩቅ ግብ አስቀምጦ መስራት በማስፈልጉ ይሄን የሚያሳይ መሪ ፕላን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ይህ መሪ ፕላን በ2013 ዓ.ም ከሦስተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር አብሮ መተግባር የሚጀምር ሲሆን፤ ለግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችም ተጠናቅቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት መሪ እቅዱ ጥናቶቹን መሰረት በማድረግ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ምን መሆን አለበት? ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውስ በምን መልኩ መተግባር አለበት? ማክሮ ኢኮኖሚው ምን መምሰል አለበት? የቤት ልማት፣ የሃይል፣ የውሃ፣የመሰረተ ልማትና ሌሎችም የልማት ሂደቶች እንዴት መከናወንና የት መድረስ አለባቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሾች ይቀመጡበታል፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡም በምን መልኩ መሆን እንዳለበት ያመላክታል፡፡ ከአገራዊ ልማት ጉዞው ባለፈም 17ቱን የዘላቂ ልማት ግቦች መሰረት አድርገው እንዲሳካ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ፤ መሪ የልማት እቅዱ በ2012 መጀመሪያ ላይ ረቂቁ የሚወጣ ሲሆን፤ በዚህ ላይ ሁሉም ዜጋ ተሳትፎ በማድረግ ግብዓት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም የእኔ ብለው የሚቀበሉት እቅድ ሆኖ ይዘጋጃል፡፡ በዚህ መልኩ የሚወጣው መሪ ፕላንም አንዱን አፈናቅሎ አንዱን የሚያሳድግ ሳይሆን የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ይሄም በከተሞች መካከል ያለውን የልማት ልዩነት የሚሞላ፤ በከተማና ገጠሩ መካከልም ትስስርን የሚፈጥር አካሄድን ይከተላል፡፡ ይህ ሲሆን ሰው የሚያፈናቅል ሳይሆን የሚያካትት የልማት አቅጣጫ ይከተላል፡፡
መሪ ፕላኑ ቀደም ሲል የነበሩ አፈጻጸሞች ላይ የታዩ ችግሮችና ፈታኝ ሁነቶችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ለእቅዱ ተፈጻሚነትም አንድም በጥናት ላይ እንደሚመሰረት ፤ ሁለተኛም ተቋማቱ መፈጸም የሚችሉትን አቅደው እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡ ይህ ሲሆን የተለጠጠ እቅድ ከመያዝ ባለፈ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ አስፈላጊው እርምጃም እየተወሰደ ይኬዳል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከተሞችን የማመጣጠን ስራው አንዱን በማቆምና ሌላውን በመደገፍ ሳይሆን፤ ሁሉም እኩል እድል ኖሯቸው የሚያድጉበትን ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ ክልሎችም መሪ ፕላኑን መነሻ በማድረግ ከተሞቻቸው ምን አይነት ፕላንና የቤት ልማት ሊኖራቸው ይገባል? በእነዚህ ከተሞች ሊፈጠሩ የሚችሉ የሥራ እድሎችና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንዴት መሆን ይኖርባቸዋል? በምን ያህል ስፋትና መጠን ሊያድጉ የሚችሉት? የሚለውን ጭምር ተመልክተው የራሳቸውን እቅድ አዘጋጅተው የሚሰሩበት ይሆናል፡፡
እንደ አቶ ዣንጥራር ገለጻ፤ እቅዱ እንደ አገር ሲዘጋጅ የከተሞች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ሰፋ ያለ ሥራ የሚጠይቅና ትልቅ ትኩረት የሚደረግበት ዘርፍ ሲሆን፤ የዘርፉ ልማትም የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ባደረገ መልኩ ይከናወናል፡፡ ከዚህ አኳያ የትኛውም የልማት ፕሮጀክት በዘፈቀደ የሚተገበር ሳይሆን አካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኗቸው ተገምግሞ ነው ተግባራዊ የሚሆኑት፡፡ ከዚህ አኳያ በትልልቆቹ ከተሞችና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በ2012 በሚጀምሩ 117 ከተሞች የሚሰሩ ልማቶች ባጠቃላይ የአካባቢና የማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ስለሚያስፈልጋቸው፤ ወደ ተግባር የሚገባው ከዚህ ተጽዕኖ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥም ነው ፡፡
ከዚህ ባለፈ የቤት ልማት፣ የከተማ ፕላን ዝግጅት፣ የአረንጓዴ ልማትና የአየር ንብረት ተጽዕኖ መቋቋም፣ ለእነዚህ ሁሉ መሰረት የሆነው የመሬት አቅርቦት እና የከተሞች መሰረተ ልማት በከተሞቹ አቅም ልክ መከናወን የሚገባቸው እንደመሆናቸው የፕላኑ የትኩረት ነጥቦች ናቸው፡፡ በከተሞች የሚደረጉ ልማቶች በሙሉ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚከናወኑ መሆን ስለማይገባቸውም፤ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍና የሚጨምረው እርሾ እንደተጠበቀ ሆኖ የግሉ ዘርፍ በከተሞች አጠቃላይ ልማት ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ እንዲኖረው ይደረጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ወንድወሰን ሽመልስ