ችግር ሁለት መልክ አለው። አንደኛው የሚፈለገውን ነገር አጥተን የሚፈጠር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሚፈለገው ነገር በእጃችን ኖሮም አጠቃቀሙን ሳናውቅ ቀርተን የሚያጋጥመን ችግር ነው። የእኛ የኢትዮጵያውያንን ታሪክን መለስ ብለን ስንቃኘው የምንረዳው ነገር ቢኖር በችግር ውስጥ የኖርነው የተፈጥሮ ሀብት አጥተን ሳይሆን በተለያየ ምክንያት መጠቀም ተስኖን መሆኑን ነው።
ሰፋፊና ለም የሆኑ ጠፍ የእርሻ መሬቶች፣ ለሃይል ማመንጫና ለመስኖ ሊጠቅሙ የሚችሉ ታላላቅ ወንዞችና ውሃማ አካላት፣ ሰፊ የከርሰና የገጸ ምድር የማዕድን ሀብት፣ ምቹ ዕድል ቢፈጠርለት ከአገሩ አልፎ ለአፍሪካም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያደርግ የሚችል የሰው ኃይል ወዘተ የኢትዮጵያ መገለጫ ከሆኑ ሀብቶቻችን ጥቂቶቹ ናቸው።
እነዚህን ሁሉ ሀብቶች ይዘን ግን አሁንም በየዓመቱ ለእርዳታ እጃችንን ለምጽዋት መዘርጋታችን አልቆመም። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝባችንም የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኑ በዚህ ዘመን ሊኖርበት በማይገባ አኗኗር ህይወትን መግፋት ግድ ሆኖበታል። በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ሃይላችንም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ስደትን አማራጭ አድርጎ ህይወቱን በአደጋ ላይ እየጣለም ጭምር ወደተለያዩ አገሮች መሰደዱን አማራጭ አድርጓል።
በአጠቃላይ ሳናጣ የተቸገርን ህዝቦችና አገር ነን ማለት ይቀላል። የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የትምህርት ሥርዓቱ የጥራት ችግር፣ የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ የመሳሰሉት ችግሮች ከላይ ለዘረዘርናቸው ችግሮች ዳርገውናል ማለት ቢቻልም ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ብለን መደምደም ግን አንችልም። ምከንያቱም አጠቃቀሙን እናውቅበት ብለን በሀብቶቻችን ሌሎች ሲጠቀሙ የበይ ተመልካች የሆንባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉና።
በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አስረኛ ነን ብንልም ስጋንና ወተትን በአግባቡ አቀናብረን መላክ ተስኖን ከዘርፉ አጅግ ዝቅተኛ ገቢ በማግኘት ላይ እንገኛለን። አረንጓዴ ወርቅ የተባለውን የቡና ሀብታችንንም ቆልተን ፣አሽገንና እሴት ጨምረን ለመላክ ባለመቻላችን በእኛ ወርቅ የሚደምቁት ሌሎች ሊሆኑ ችለዋል። ከፍተኛ ዝናና ተቀባይነት ባለው ቡናችን መከራቸውን አይተውና ደክመው ከሚያመርቱት ገበሬዎቻችን ይልቅ ስታርባከስን የመሳሰሉ ሀብታም ኩባንያዎች ብዙም ሳይለፉና ሳይደክሙ ከፍተኛ ሀብት የሚያካብቱበት ሀብት ሆኖ ይገኛል። ለዚህም ነው ከላይ በመግቢያችን ላይ የእኛ የኢትዮጵያውያን ቸግር ምንጩ ሀብት ማጣት ሳይሆን ያለንን መጠቀም ካለመቻላችን የሚመነጭ ነው ያልነው።
በእጃችን ያለወርቅ ሆኖ ያልደመቅንበት ሌላው ሀብት አገር በቀል የህክምና መድሃኒት ነው። ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው አገራችን ለመድሃኒት ግዥ በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮኖች ወጪ ታደርጋለች። በኮንትሮባንድ የሚገቡና ለበርካቶች የጤና እክልና የህይወት መጥፋት መንስዔ የሆኑ መድሀኒቶች ብዛትም የትየሌለ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተነገረ ሀቅ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ የበርካታ አገር በቀል መድሃኒቶች መገናኛ መሆኗ ግን መዘንጋት አይኖርበትም።
ህክምና እንደአሀኑ ገጠር ጭምር ሳይስፋፋ ደዌን ፈውሰውና ሰባራን ጠግነው እፎይታን የሚለግሱ አንቱ የተባሉ የባህል ህክምና ባለሙያዎች እንደነበሩን አሌ አይባልም። ስማቸው የአካባቢ መጠሪያ እስከመሆን የደረሱትን ባህላዊ ሀኪም ማሞ ወርቅነህን ለዚህ ጥሩ ማስረጃ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። በዘመናዊ ህክምና መፍትሄ ያጡ ህመሞችን ሳይቀር ይፈውሱ እንደነበር በብዙዎች የተመሰከረ ሀቅ ነውና።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቀው ከ15 እስከ 20 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ባደረገው ምርምር አስር የሚደርሱ የባህል መድሃኒቶች በፋብሪካ ደረጃ መመረት እንደሚችሉ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ይህ ጉዳይ በመንግሥትም ሆነ በግል ባለሀብቱ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና አስቸኳይ ምላሽን የሚሻ ትልቅ ዕድል ነው ብለን እናምናለን። ምክያቱም የውጭ ምንዛሪን ለማዳን፣ አገር በቀል ዕውቀቶችን ለማበረታታትና በአገር ምርት ለመኩራት ትልቅ ዕድል ይፈጥራልና።
ስለሆነም መንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብቶች ይህንን ትልቅ ሀብት በሥራ ላይ ለማዋልና አገርና ህዝብን ለመጥቀም ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል እንላለን። ይህንንም በማድረግ በራሳችን ወርቅ መድመቅ እንችላለን!
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2011
Your posts always make me feel like I’m not alone in my struggles and insecurities Thank you for sharing your own experiences and making me feel understood
I just like the helpful information you provide in your articles