አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስር የሚሆኑ ሀገር በቀል የባህል መድሃኒቶች በፋብሪካ ደረጃ ሊመረቱ እንደሚችሉ በጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህልና ዘመናዊ መድሃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አሸንፍ ታደለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ኢንስቲትዩቱ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ባደረገው ምርምር አስር የሚደርሱ የባህል መድሃኒቶች በፋብሪካ ደረጃ መመረት ይችላሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የሚገኙ የባህል መድሃኒቶች በፋብሪካ ተመርተው ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ፈዋሽነታቸውንና አስተማማኝነታቸውን በቤተ ሙከራ መፈተሹን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ከዘመናዊ መድሃኒቶች ጋር የሚቀናጁበትን መንገድ የማጥናት፣ ስኬታማ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ለፋብሪካዎች የማስተዋወቅና ለመድሃኒትነት የሚውሉ እጽዋትን የመጠበቅ ተልእኮ ይዞ እየሠራ እንዳለም አመልክተዋል፡፡
ከ100 በላይ የሚሆኑ ዕጽዋቶች በሀገሪቱ ባሉ የባህል መዳኒትነት መፈተሻቸውን የገለጹት አቶ አሸንፍ የትኞቹ ዕጽዋት ለየትኛው በሽታ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ምን እንደሆነ ፣ በውስጣቸው ያለው የኬሚካል ይዘትና የመሳሰሉት ተፈትሸው በመረጃ ቋት እንደተቀመጡ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም ከ10 እስከ 15 በሚደርሱት እጽዋት የቅመማና የደህንነት ጥናቶች ተደርገው በሀገሪቱ የሚገኙ የመድሃኒት ፋብሪካዎች እንዲያመርቷቸው የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ምርምሩ በይበልጥ ትኩረት ያደረገው ሀገሪቱ ቅድሚያ በምትሰጣቸው በሽታዎች ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸንፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በማህበረሰባችን ላይ ችግር እየፈጠሩ የመጡ በመሆናቸው ለደም ግፊት በሽታ፣ ለስኳር በሽታና ለወባ በሽታ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች እንደተገኙ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ለቆዳ በሽታ የሚያገለግል መድሃኒት ከዕጽዋቱ የምርምር ውጤት የተገኘ መሆኑን ለማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
በምርምሩ የቆዳ በሽታ መድሃኒት ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም እንደተገኘ ያስረዱት ዳይሬክተሩ የውጭ ጥገኛ ትሎችን ከእንስሳት ቆዳ ላይ ማስወገድ የሚያስችል የምርመራ ውጤት ከዕጽዋቱ ቅመማ መገኘቱን ይናገራሉ፡፡ ሀገራችን የእንስሳት ቆዳን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝ እንደመሆኑ ከዕጽዋቱ የተገኘው ውጤት የቆዳ ምርታችን ከበሽታ ነጻ ሆኖ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡
በአገራችን የሚገኙ የመድሃኒት ፋብሪካዎች ያላቸው ዝግጁነት ሲታይ እምብዛም መሆኑን በመግለጽ በሙከራ ደረጃ ከአዳሚ ቱሉ ጸረ ተባይ ማምረቻ ፋብሪካ ጋር በተለይ ከእንስሳት ቆዳ በሽታ ጋር በተያያዘ የተደረሰበትን የላብራቶሪ ውጤት በፋብሪካ ደረጃ ለማምረት የሙከራ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በቀጣይ በተለይም በአነስተኛና ጥቃቅን ከተደራጁ አካላት ጋር በመተባበር የማምረቱን ሥራ ለማከናወን ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ኢያሱ መሰለ