አዲስ አበባ፡- የወጪ ንግዱ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ። የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ የአምራች ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ልክ አለመንቀሳቀሱ፣ ከግብርና እና ማዕድን ዘርፍ የተጠበቀውን ያህል ገቢ ማግኘት አለመቻሉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
ከወርቅ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በ2006 ዓ.ም ከነበረበት 430 ሚሊዮን ዶላር ባለፈው ዓመት ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር መውረዱ ለአብነት የጠቀሱት ዶክተር ይናገር፣ የዓለም ገበያ አለመረጋጋትም ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ በጥቅል ውጤቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አስከትሏል ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ በአሁን ወቅት ከፍተኛ የዕዳ ጫና እንዳለባት የገለጹት ዶክተር ይናገር፣ መከፈል የነበረበትን ብድር ለማቃለል ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መቀነሱ እክል መፍጠሩንና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መምጣት በኋላ በተደረገ ጥረት የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘምና የወለድ መጠን እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
85 በመቶ የሚሆነው የውጭ ብድር ከቻይና የተወሰደና አሁን ላይ መከፈል መጀመሩንም ተናግረዋል። የብድር ጫና እስኪቃለል ድረስ ከዚህ በኋላ አነስተኛ መጠን ወለድ ያለውና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ካልሆነ በስተቀር ሀገሪቱ ብድር ውስጥ እንደማትገባም ጠቅሰዋል፡፡ በሀገሪቱ እየተስተዋለ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት በተመለከተም ዶክተር ይናገር እንደገለጹት፣ የዋጋ ግሽበቱ ምጣኔ ሀብታዊ የሆኑና ያልሆኑ ምክንያቶች ድምር ውጤት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ከነበረው 16 በመቶ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ጥር ወር ላይ ወደ 10.9 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
የባንኩ ገዢ እንደተናገሩት ብሔራዊ ባንክ ጥናት በማድረግ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በሀገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ብድር ለሚፈልጉ ዜጎች ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና በማስያዝ ብድር በማቅረብ የፋይናንስ ችግራቸውን መቅረፍ እንዲችሉ የሚያስችላቸው መመሪያ ተዘጋጅቶ ለማፅደቅ በሂደት ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎችም የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደተግባር ማስገባት እንዲችሉ የሚያስችል ብድር የሚያገኙበት አሰራር ለመዘርጋት ታቅዷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
የትናየት ፈሩ