
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ አበባ፡- አሸባሪው ህወሓት ቀደም ሲል ለሰው ልጅ ክብር አልነበረውም ። አሁን ደግሞ የህሊናም ክብር ስላጣ ህጻናትን በጦርነት ወደ መማገድ መግባቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ። የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዝምታ እርስ በእርሳችን እንድንባላ ከመፈለግ የመነጨ እንደሆነ አመለከቱ ።
አቶ ኦባንግ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ አሸባሪው ህወሓት በብዙ ነገሮች መሀል የገባ አይጥ ሆኗል፣ ነገ ምን ይመጣብኛልን ሳይሆን ዛሬን እንዴት ላምልጥ በሚል ሀሳብ ተይዟል። በዚህም የዛሬ መሳሪያው ህጻናቱ ሆነዋል።
ቡድኑ ቀደም ሲል ለሰው ልጅ ክብር አይሰጥም። አሁን ደግሞ የህሊናም ክብር ስላጣ ህጻናትን ወደ መማገዱ ገብቷል። እነዚህ ህጻናት ጠመንጃ እንኳን እንዴት እንደሚያዝ አያውቁም፤ ቋንቋና ስልጠናውም የላቸውም። በአልጠነከረ ጉልበታቸው ከአቅማቸውና ከቁመታቸው ልቆ መሳሪያ እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል ብለዋል ።
ከሁሉም የሚከብደው ደግሞ ከሰለጠነው ኃይል ጋር እንዲጋጠሙ መፍቀዱ ነው ያሉት አቶ ኦባንግ ፣ ይህንን ሰብዓዊ ያልሆነ ተግባሩን ለማስቆም አፋጣኝ ሥራ መሰራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል ።
የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዝምታ እርስ በእርሳችን እንድንባላ ከመፈለግ የመነጨ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፤ አሜሪካም ሆነች ሚዲያዎቿ እንዲሁም ሌሎቹ አገራት ከዚህ ቀደም እኛን አባልተው የተጠቀሙት ነገር ስላለ አሁን ያ ስለቀረባቸው በቡድኑ ጫንቃ ላይ ሆነው ስለሚሰሩ ነው። ይህንን ሴራቸውን ደግሞ ራሳቸው ማውጣትና መናገር አይፈልጉም። ስለሆነም የኢትዮጵያ መፍትሄ በኢትዮጵያዊያን እጅ ላይ ያለ በመሆኑ ተረባርቦ ይህንን የሚያደርገውን አካል ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ጉዳዩ አይደለም ሰብዓዊ መብትን እናውቃለን፣ እናስፈጽማለን ፣ጀማሪ ነን የሚሉት ቀርቶ ህጻናቱ በትምህርት የሚያውቁት እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ኦባንግ፣ ከዚህ ቀደም ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በተያያዘም መንግሥትን ሲወነጅሉ ቆይተው አሁን አላየንም አልሰማንም ያሉት ስላላወቁት ወይም ስላልሰሙት አይደለም። ከችግሩ የሚጠቀሙት ስላለ ብቻ ነው ብለዋል ።
ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ባላቸው የቆየ ወዳጅነት የተነሳ በትውልድ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወንጀል ማሰማትም አልፈለጉም። ከዚያ ይልቅ ዋና አጀንዳው ቡድኑ ዳግም ህይወት የሚዘራበትን መንገድ ማመቻቸት ነው ። ኢትዮጵያዊያን ይህንኑ እውነት አውቀው በጋራ ለአገር ደህንነትና ለህጻናቱ ነጻነት መስራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
ህውሓት ለጦርነት ያሰለፋቸው ልጆች የህውሓት ወይም የትግሬ ሳይሆኑ የሰው ልጆች ናቸው፣ የሚደርስባቸው በደል እየታየ ዝም ሊባል አይገባም፤ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል ያሉት አቶ ኦባንግ፣ ህጻናትን በጦርነት መማገድ ከህወሓት የህሊናቢስ ስራ በላይ ተቃውሞ የሚያስፈልገው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው። ሰው በሰውነቱ መከበር የሚጀምረው በአቅሙ ልክ ተለክቶ ነው። ህጻናት አቅማቸው ለእንክብካቤ እንጂ ሌሎችን ለማገዝ የጠነከረ አይደለም። ከአቅማቸው በላይ ህሊና የማይፈቅደው ጫና በአሸባሪው ህወሓት መሸከመቸውን ጠቁመዋል ።
ስለዚህም ህሊና ያለውና ሰው ነኝ የሚል ሁሉ ይህንን ድርጊት ማውገዝ ይኖርበታል።
ህጻናቱ የአንድ ሰው ልጆች ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ህጻናት ናቸው። ከዚህም በላይ የሰው ልጆች ናቸው። ስለሆነም እየተፈጸመባቸው ያለው ነገር ከቃል በላይ ነው ፣አሸባሪውን ህወሓት ከመደገፍና ካለመደገፍ ጋር የሚያያዝ አይደለም ፣ ሰውን ከመርዳትና ካለመርዳት ጋር የሚገናኝ መሆኑን አምኖ ለእነዚህ ህጻነት መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።
ድርጊቱንም መቃወም ለነገ የሚባል ተግባር መሆን የለበትም። ምክንያቱም ቡድኑ ማንም የሚከተለውና አላማውን የሚደግፍለት ስላጣ እነርሱን ከመማገድ ሊያቆም አይችልም። በተሰለፉት ይብቃ ተብሎ ፍጥነት ባለው መልኩ ለህጻናቱ መድረስ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ቡድኑ ውጊያዬ ለትግራይ ህዝብ መብት ነው የሚል ሽፋን እንዳለው የጠቆሙት አቶ ኦባንግ፤ የህጻናትን መብትን እንደ ትግራይ መብት አላየውም። የሰው ልጆች መብትም መስሎ እንዳልተሰማው ጠቁመዋል ። የነገዋን አገር ተረካቢ ልጆችን መቅጠፍና መጨረሻውን ለማሳመር መጣር ላይ በመሆኑ በህጻናት መብት ብቻ ሳይሆን በአገር ተተኪ ማሳጣትም ሊጠየቅ እንደሚገባም አመላክተዋል።
እንደ አቶ ኦባንግ ገለጻ፤ ህጻናቱ የሚዋጉት ከተራ ሰዎች ጋር አይደለም። መከላከያን ከሚያክል የሰለጠነ ሠራዊት ጋር ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ህመም እንደሆነ ይታወቃል ያሉት አቶ ኦባንግ ፣ የውጪው ዓለም ዝም ያለው በእኛ ልጆች ቁማር እየተጫወተ ስለሆነ ነው። አሸባሪው ህወሓት የእነርሱ የጦር መሳሪያ በመሆኑ ነው። በእነርሱ ዘንድ ከእኛ ወይም ከእነኛ የሚል ነገር የለም። ከእነርሱ ለእነርሱ ነው ጨዋታው ብለዋል ። በቡድኑ መሳሪያነት ኢትዮጵያን ማጥፋት የእነርሱ አላማ ነው። በቻሉት ሁሉ የሚደግፉትም ለዚህ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር መሆኗና ራሷን በራሷ ለመምራት መሞከሯ ብዙዎችን አስጨንቋቸዋል። ተቃውሟቸውን ያበዙት በለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱ ሉዓላዊ ብትመስልም በውስጠ ተዋቂነት እያስተዳደሯት ስለቆዩ ነው ። ያንን ዳግም ማምጣት ካልቻሉ የሚቀርባቸው በርካታ ጥቅም አሉ ። ከጫና እስከ መደገፍና እንዲህ አይነት አሰቃቂ ነገሮች ሲኖሩ ደግሞ ተደማጭነት እንዳያገኙ የመሸፋፈን ሥራዎችን ይሰራሉ። አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው ብለዋል።
ማንም እንዳይገባብን ከፈለግን እያንዳንዳችን የተሰጠንን አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለብን። ሳንወጣ ጩሁልን ብንል ማንም አይሰማንም። ማባባሻና የእነርሱን ጥቅም ማግኛ መንገድ ነው የሚከፍቱብን። ስለሆነም በውጪዎች ጫና ሳንጨናነቅ ፤ ለምን አልጮሁልንም ሳንል አሁንም በኃላፊነታችን ልክ ሰርተን ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ለማምጣት እንረባረብ። በብሔር ወገንተኛ መሆናችንን ትተን ለአገራችን መወገንን እንጎልብት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም