ለእርሻ ስራ ውጤታማነት የግብዓት አቅርቦት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዘንድሮ የአርሶ አደሩ ዓመታዊ የግብዓት ፍላጎት በዓይነትም በመጠንም በእጅጉ የጨመረበት ሁኔታ አለ። ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የአፈር ማዳበሪያ የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አሳይቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት በራሱ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ለተያዘው የ2013/14 የመኽር ምርት ዘመን የአቅርቦት ዝግጅት መካሄድ የጀመረው ቀደም ብሎ ነው። አርሶ አደሩም ቀድሞ ግብዓት ስለደረሰው ዘርም ሆነ ማዳበሪያውን ተጠቅሞ የእርሻ ስራውን ለማከናወን አልቸገረውም። ቀደም ባሉት ዓመታት አርሶ አደሩን ከስራው የሚያስተጓጉለውና የሚያዘገየው የግብዓት አቅርቦት ቢሆንም ዘንድሮ ግብርና ሚኒስቴር አስቀድሞ ዝግጅት ያደረገበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ፍላጎቱን እንዳሳወቀ ነው ማሳ ዝግጁት የጀመረው። በብዙዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የእርሻ ማሳዎች ተደጋግመው የታረሱትም ቀደም ብለው ነው። የእርሻ መሬት ዝግጅት በተደጋጋሚ በማረስና በማለስለስ ያጠናቀቁ አርሶ አደሮች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ የሀገራችን የተለያዩ አካባቢ አርሶ አደሮች የ2013/14 የመኸር ምርት ዘመን በአጭሩ ታጥቆና በየአካባቢው ሰብሰብ ብሎ በክላስተር በመደራጀት ጭምር ሲተጋ ተስተውሏል። በተለይ በክላስተር መደራጀቱ ማሳውን ደጋግሞ በማረስና በማለስለስ ያባከነው የነበረውን ድካም ይቀንስለታል። ጉልበቱንም በመቆጠብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርግለታል። በዘር እና በሰብል ስብሰባ ወቅትም ሥራውን ያቀላጥፍለታል። በስራው ወቅት ሊከሰት የሚችል ተባይ ቢኖር በጋራ ለመከላከል አመቺነቱ አያጠያይቅም። በአጠቃላይ የክላስተር እርሻ ቢለመድ ብዙ የሚጠቀምበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ለተያዘው የመኸር ምርትብዙ እገዛ እያደረገለት ይገኛል።
አርሶ አደር ካሳዬ አያሌው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው ጠንክረው በመስራት ድርሻቸውን እየተወጡ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የሚኖሩትና እርሻ ስራቸውን እያከናወኑ ያሉት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት ጁነሴ ወረዳ ውስጥ ነው። እርሳቸው አስቀድመው ነው ማሳቸውን ማዘጋጀት የጀመሩት። እስከ ስድስት ጊዜ ደጋግመው በማረስ አለስልሰው የዘር ጊዜውን እየተጠባበቁ ነው። በእርግጥ ይሄን ሥራ ያከናወኑት ብቻቸውን አይደለም።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በክላስተር ማምረት ጀምረዋል። በወቅቱ ያገኙትን ምርት እና የነበረባቸውን ድካም ሲያነፃፅሩት ድካምና ጊዜ ቀንሶላቸዋል። ምርታማም አድርጓቸዋል። በተለይ የበቆሎ፣ የጤፍና ስንዴ ዘርን ጨምሮ የዩሪያ ማዳበሪያ ቀድሞ የቀረበላቸውና የተጠቀሙ ከመሆኑ ጋር ሲደመር በጋራም በግልም ምርታማ እንደሚያደርጋቸው በእርግጠኝነት ነግረውናል።
በዚሁ ዞንና ወረዳ ሴት አርሶ አደር በላይነሽ ሙሉ ቀን እንደገለፁልን፤ ዩሪያ ማዳበሪያውን ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ከ30 እስከ 40 ቀን በማሳቸው ላይ መጠቀም የሚያስችላቸውን ዝግጅት አድርገዋል። ዳፕ ማዳበርያ ላይ እጥረት እንዳለ ግን አልሸሸጉም። ተባይን በተመለከተም በበቂ ሁኔታ መከላከል የሚያስችል ኬሚካል ግዢ መፈፀሙን ከወረዳው ግብርና መምሪያ በመስማታቸው ምርቴ ሲደርስም ሆነ በቡቃያው በተባይ ይጠቃል የሚል ስጋት እንደሌላቸው ነግረውናል። የማሳቸው አፈር አሲዳማ በመሆኑ በዘንድሮ መኸር ምርት ዘመን የአሲዳማ አፈር ማከሚያ ኖራ ግብዓት ተጠቃሚ መሆናቸውም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢሆን ተስፋ የግብዓት አቅርቦትን አስመልክተው እንደነገሩን፤ በወረዳው አርሶ አደር ዘንድ በዘንድሮ የመኸር ምርት የግብዓት አቅርቦት እጥረት የለም። አሁን ላይ በወረዳው በዕቅድ ከተያዘው 154 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ከ70 በመቶው በላይ ቀርቦ በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሆኗል። ከ20 በመቶ በላይ የሚገመተው ዳፕና ሌላው ቀሪ ግብዓትም ቢሆን በስርጭትና በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ። የግብአት አቅርቦቱ በጊዜ መቅረቡ እንደ ቀደሙት ዓመታቶች አርሶ አደሩ ግብዓት አገኝ፤ አላገኝ ይሆን በሚል ስጋት ሳይዘናጋ ትኩረቱን ስራው ላይ ብቻ እንዲያሳርፍ አስችሎታል። በተለይ በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች በአሁኑ ሰዓት ማሳቸውን በበቆሉ ዘር የሸፈኑበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጸውልናል። ግብዓት በተሟላ ሁኔታ ማግኘታቸው በቀጣይም ማሳቸውን በጤፍ ፣በገብስና በጥራጥሬዎች ለመሸፈን የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ከኦሮሚያ ቀጥሎ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ምርት አምራችና አቅራቢ የሆነው የአማራ ክልል በዘንድሮ መኸር ምርት በክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ለማልማት ታቅዶ አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል ።
የ2013/14 መኸር ምርት ዘመን ግብዓት አቅርቦትን አስመልክተን ያነጋገርናቸውና በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ የግብርና ግብአት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየሆነ መሆኑን ነው ያረጋገጡልን። የአርሶ አደሩ የግብዓት ፍላጎት ተሰባስቦ ግዢ የተፈፀመው በ2012 ዓ.ም ምርት ዘመን ወቅት መሆኑን ነግረውናል።
‹‹በምርት ዘመኑ 18 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈፀም እና ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በማቀድ ሙሉ በሙሉ ግዢ የተፈፀመበት ሁኔታ አለ›› ብለውናል። እንደ ዳይሬክተሩ ግዢው ከተፈፀመው አራት ዓይነት የአፈር ማዳበሪያ መካከል ጅቡቲ ወደብ ከደረሱት የአፈር ማዳበሪያዎች ውስጥ 2ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ኤምጂ ፣ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኤም ጂ ኤስ ፎረምና 689 ሺ ኩንታል ኤም ጂ ዚ ፎረም የተባለው ማዳበሪያ ነው። እንደ አቶ መንግስቱ ማብራሪያ፤ የዩሪያ ማዳበሪያ ፍላጎት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ነበር። ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 63 በመቶው ጅቡቲ ወደብ ደርሷል። ወደብ ላይ የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ድምር 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በዓመታዊ ፍላጎት ሲሰላ 85 በመቶ ነው። ከዚህ ውስጥ 15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 98 በመቶውን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሃገር ውስጥ ማጓጓዝ ተችሏል። ጅቡቲ የደረሰውን በማጓጓዝ በኩል 94 በመቶው ክንውን ተሳክቷል። ሀገር ውስጥ ከገባው ውስጥም 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታሉን ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጓጉዟል ። ይሄም ለማጓጓዝ ከታቀደው ዓመታዊ ዕቅድ 80 በመቶው መሆኑንም አመልክተዋል። 13 ነጥብ4 ሚሊዮን ኩንታሉን ለአርሶ አደሩ ካለበት ማሳ ለሚያደርሱት ሕብረት ስራ ማህበራት ማሰራጨት ተችሏል። አቶ መንግስቱ እንደገለፁት፤ ወደ ህብረት ስራ ማህበራት ከወረደው 9ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 69 በመቶውን አርሶ አደሩ በብድርም ፤በእጅ ለእጅ ክፍያም ገዝቶ እየተጠቀመ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል።
‹‹17 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ካለፈው ዓመት የከረመ የአፈር ማዳበሪያ የተሰራጨበት ሁኔታ አለ›› ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ ይሄም አዲስ ከገባውና ከከረመው ጋር የተሰራጨውን ወደ 78 በመቶ የሚያደርሰው እንደሆነም ተናግረዋል።
‹‹ግብርና ሚኒስቴር ዋና ዓላማው አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያው ደርሶት ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነቱን ሲያሳድግ ማየት ነው›› የሚሉት አቶ መንግስቱ የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ዓመታዊ ፍላጎት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 3ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል በዓይነትም በመጠንም የጨመረበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ሚኒስትሩ ከዚህ በመነሳት አቅርቦቱና ስርጭቱ በራሱ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ ያደረገበት ሁኔታ መፈጠሩንም ያብራራሉ። ከመቼውም ዓመት ይልቅ ዘንድሮ በወቅቱ በማቅረብ፣ በጥራት በማቅረብና ተቀናጅቶ ለአንድ ዓላማ በመስራት በኩል የተሻለ አፈፃፀም መኖሩንም ይጠቅሳሉ። ከዩሪያ በስተቀር በዕቅድ ከተያዘው ከምርት ዘመኑ ግብዓት አቅርቦት አብላጫውን መጠን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ የተቻለውም ለዚህ ነው ባይ ናቸው። የዩሪያ እጥረት መኖሩ እና እጥረቱን ለመቅረፍ በሁለት ወገን የተከፈለ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል። አንዱ ጎራ በፌዴራል ደረጃ የተዋቀረ ሁለተኛው ደግሞ ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው የተደራጀ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በፌዴራሉ መኪኖቹ ቁጥራቸው ጨምሮና በመርከብም ጅቡቲ ያለው ዩሪያ ቶሎ ቶሎ እንዲጓጓዝ የማድረግ ሥራ በቅንጅት መሥራት እንደሚጠቀስም ይናገራሉ። ሁለተኛውና በክልል ደረጃ እስከ ቀበሌ የሚሰራው ስራ በአግባቡ የመጠቀም ጉዳይን ያካተተ መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹ምርጥ ዘር ከአፈር ማዳበሪያ የሚለይበት ትልቁ ነገር በሀገር ውስጥ ተመርቶ በሀገር ውስጥ የሚቀርብ የግብርና ግብዓት መሆኑ ነው›› ይላሉ አቶ መንግስቱ። ይሄ ምርጥ ዘር ሀገር ቤት ውስጥ የማባዛት አቅም ነፀብራቅ እየሆነ ነው። በምርት ዘመኑም አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል አቅርቦ ለማሰራጨት መታቀዱን ይጠቁማሉ። ከተባዛው ውስጥ የተሰበሰበው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 71 በመቶ መሆኑንም ይናገራሉ ።
‹‹ዘሩ ይሰበሰባል፣ይበጠራል ጥራቱ ይረጋገጣል›› ሲሉም ይሄን የሚያረጋግጡ ገለልተኛ የጥራት ተቆጣጣሪዎች መኖራቸውንና ተበጥሮ ጥራቱ ተረጋግጦም 563 ሺህ ኩንታል ማቅረብ መቻሉን ነግረውናል። የተሰራጨው ከቀረበው 453 ሺ ኩንታል ወይም 80 በመቶው ነው ብለውናል። ከዚሁ ዘር አቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም ጥንካሬና ክፍተት ጋር ተያይዞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉት ምሁራን ራሱን ያቻለ ሰነድ የማዘጋጀት ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም ለምርት ዘመኑ በሊትርና በኪሎ ግራም የሚለኩና የተለያየ መጠን ያላቸው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ኬሚካሎች ግዢ መፈፀማቸውንና ጅቡቲ መድረሳቸውን እንዲሁም አንዳንዶች ቀድመው የሚፈለጉ በመሆናቸው በአውሮፕላን የተጓጓዙበት ሁኔታ መኖሩን አብራርተዋል።
እንደ አቶ መንግስቱ ገለፃ ፤ከምርት ግብዓት አቅርቦት አንዱ አሲዳማ አፈርን ማከሚያ የሚውለው ኖራ ነው።ቀደም ባሉት ዓመታት ኖራ እንደ ግብዓት ተቆጥሮ በዕቅድ ይያዝ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ለም መሬቶች በጎርፍና በተለያዩ ምክንያቶች በመጠረጋቸው አልፎ አልፎ አርሶ አደሩ የዘራውን የማያገኝበት ደረጃ እስኪደርስ የዘለቀ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ግብርና ሚኒስቴርም የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቷል። በ2013/14 ምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት ስርዓት ውስጥ አስገብቶታል። በጀት ተመድቦ 86 ሺህ ኩንታል ኖራ የቀረበበትና 13 ሺ ኩንታሉ ችግሩ ላለባቸው አራት ክልሎች የተሰራጨበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ። የሁሉም ዓይነት ግብዓት ስርጭትም ውጤታማና ተደራሽ እንደነበር ሳይገልጹ አላለፉም።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደ ሚጠቁመው በተያዘው የምርት ዘመን 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በዕቅድ የተያዘ በመሆኑ ለዚህ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው። አርሶ አደሩ የሚጠበቀውን ያህል ምርት ለማግኘትም የታቀደውን 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈን ግድ ይላል። ለዚህም ጠንካራ እንቅስቃሴ አርሶ አደሩ በአጭር ታጥቆ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊና የሚጠበቅ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013