
በዓለም ላይ ለጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ኢንዱስትሪ ምቹ ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ዘርፉ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ በማጐልበት፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል በመያዝና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦዎቹ ብዙ ተስፋ የተጣለበትም ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዝቅተኛ ክፍያ የሚገኝ የሰው ኃይል፣ ጥሬ ዕቃዎች እና በዝቅተኛ ወጪ የሚገኝ ኃይል መኖሩ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያን ተመራጭ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገቷን ለማፋጠን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን በቀዳሚነት አስቀምጣ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡
ዘርፉ በመላው ዓለም መቼም የማይነጥፍ ገበያ ያለው በመሆኑና ኢትዮጵያም ለዚህ ኢንዱስትሪ ምቹ በመሆኗ ከሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የበለጠ ተስፋ ተጥሎበታል። ከዘርፉ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ወጭ ምንዛሪ ለማግኘትም ውጥን ተይዞ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተሠሩ በርካታ ሥራዎች የሚፈለገውን እና የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብሎ መናገር ባይቻልም ከዘርፉ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ከዓመት ዓመት መሻሻል እያሳየ መጥቷል፡፡ ሆኖም በ2013 በጀት ዓመት የተገኘው ውጤት በተለያዩ ምክንያቶች ካለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመላከተው፤ በ2013 በጀት ዓመት ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ 218 ነጥብ 17 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የዕቅዱን 69 ነጥብ 61 በመቶ (151.88 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) ገቢ ተገኝቷል፡፡ የበጀት ዓመቱ የኤክስፖርት ገቢ አፈፃፃም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 11 ነጥብ 53 በመቶ (19.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) ቅናሽ አሳይቷል፡፡
የኢንስትቲዩቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባንታየሁ ገሰሰ እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ያገኘችው የወጪ ንግድ ገቢ ከለው ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የተሻለ ነው፡፡ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ረገድ ግን ክፍተት አለ፡፡
‹‹ የ2013 በጀት ዓመት ለጨርቃጨርቅ ዘርፉ ጥሩ አልነበረም፡፡ በአንድ በኩል የኮሮና ወረርሽኝ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥላ አጥልቶበት የነበረበት ዓመት ነው፡፡ ሠራተኛው በሙሉ አቅሙ መሥራት አልቻለም ነበር፡፡ ሆኖም ኮቪድን እየተከላከሉ የተሠራው ሥራ የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይቀንስ ተከላክሏል። እንዲያውም ከአንዳንድ ሀገራት አንጻር ሲታይ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ፋብሪካዎቹ ኮቪድን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት እና ሠራተኞቹም ቫይረሱ እንደያጠቃቸው እየተከላከሉ ሥራ ላይ መቆየታቸው አሁን የተመዘገበው የኤክስፖርት አፈጻጸም እንዲመዘገብ አስችሏል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የገበያ ትስስር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና አምራቾች ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በማምረት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ባንታየሁ፤ የሠራተኛው የክህሎት፣ የእውቀትና የአመለካከት ችግሮች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የምርት እጥረት ተከስቷል፡፡ የምርት እጥረት መከሰት ደግሞ ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ የሚፈለገውን ያህል እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት የጥጥና ጨርቃጨርቅ ግብይትን አቅም ለማሳደግ የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ አምራቾችንና ምርቶቻቸውን በተለያዩ መንገዶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ፣ በዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚጠየቁ የአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ የመደገፍ፣ ባለሀብቶች የመንግሥት ማበረታቻዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዶ ሲሠራ እንደነበር አቶ ባንታየሁ ያብራራሉ። የዘርፉ አምራቾች የገበያ አቅም ግንባታና ትስስር በመፍጠር እንዲሁም የጉምሩክ፣ የፋይናንስና ሌሎች ገቢና ወጪን በማቀላጠፍ ረገድ በርካታ ተግዳሮት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ባንታየሁ ገለጻ፤ በጥጥ ልማት እና ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማኑፋክቸሪንግ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የምርት ጥራት ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት የተከናወነ ሲሆን፤ የጥጥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጥጥ አምራቾችን በመደገፍ ምርታማነትን ለማሻሻል ድጋፍና ክትትል ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን ምርታ ማነት እና የምርት ጥራትን ለማሻሻያ ችግርን መሠረት ያደረገ የቴክኒክ ድጋፍና የማማከር፣ በተለያዩ የስልጠና አርዕስት ላይ በተግባር የተደገፈ የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ የአሠራር ማሻሻያ ትግበራ፣ የምርት ፍተሻ እና የግሬዲንግ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል።
የኢንዱስትሪዎች የግብዓት አቅርቦትን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቆ ሙት አቶ ባንታየሁ፤ የሀገር ውስጥ ግብዓት አምራቾችና ግብዓት ፈላጊዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ መደገፍና መከታተል፣ የተዳመጠ ጥጥ አምራቾችን ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር የማስተሳሰር፣ የጥጥ የጥራት ደረጃ በማረጋገጥ ግብይቱ እንዲሳለጥ የመደገፍ፣ የዘርፉን ግብዓት አቅራቢዎችን ማስተሳሰር የሚያስችሉ የምርት ግብዓት ፍላጎት መጠን፣ የምርት ጥራት እና ወቅታዊ መገበያያ ዋጋ መረጃ የማጠናቀር ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ2012/13 ምርት ዘመን 780 ሺ ሊትር የፀረ-ተባይ ኬሚካል እንደሚያስፈልግ ቢታቀድም በአዳሚ ቱሉ 37ሺህ 300 ሊትር ኢትዮ ሰልፋን እና በኤፍ ኤስ ኃ.የተ.የግ. ማህበር 53 ሺህ ሊትር በድምሩ 90 ሺህ 300 ሊትር ኬሚካል ለ32 አልሚዎች እንዲከፋፈል መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡
የቢቲ ጥጥ ዝርያን በተመለከተ ውጤታማነቱን ለመከታተል በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካኝነት የ2013/14 ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት የተላከ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት በ2013/14 ምርት ዘመን 1000 ሄክታር መሬት በቢቲ ጥጥ ዘር እንዲሸፈን በማድረግ ያለውን የኬሚካል አቅርቦት እና በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንዲቻል የዘር ፍላጎቱ መረጃ ተሰብስቦ ለአቅራቢው JK seed company በመላክ አልሚዎች የሚገጥማቸውን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ለመፍታትም ከካምፓኒው ጋር በመነጋገር አዲስ አበባ ድረስ እንዲያመጣና ባለው ምንዛሬ መሰረት በብር ግዢው እንዲከናወን ስምምነት ተደርሷል፡፡
እንደ ኮሚንኬሽን ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በ2012/13 ምርት ዘመን ከወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በተመረጡ ዘር አባዢ ባለሀብቶች አማካኝነት (ናሳ እርሻ ልማት 54 ሄክታር፣ ወረር 50 እና ፍሪኤል እርሻ ልማት 25 ሄክታር) 2 ሺህ 500 ኩንታል ምርጥ ዘር ተወስዶ እንዲባዛ ተደርጓል። ለቀጣይ 2013/14 ምርት ዘመን ለአምራቾች ሊቀርብ እንደሚችል በመስክ ዳሰሳ ተለይቷል፡፡ ለ2013/14 ምርት ዘመን የሚውል ከቱርክ የመጣ 10 ኩንታል አዲስ የጥጥ ዘር ለእርሻዎች እየተዳረሰ ነው፡፡ በተጨማሪም 5 ሺህ ኩንታል የሚሆን ነባር ምርጥ ዘር እንዲዘጋጅ ተደርጎ ለጥጥ እርሻዎች ተሰራጭቷል፡፡ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በቀጣይም ይሄ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ዘርፉን ያጋጠሙ የተለያዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የጠቆሙት አቶ ባንታየሁ፤ ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ገበያ የመነቃቃት ሁኔታ ቢኖርም በኢትዮጵያ ውስጥ አምራቾች ከፀጥታ ስጋት አንፃር ተጨማሪ ትዕዛዝ መውሰድ አለመቻላቸው ዘርፉን ካጋጠሙት ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን ያነሳሉ። የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ለምርት ግብዓት እና መለዋወጫ አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ እና የሥራ ማስኬጃ ብድር ቅድሚያ በማድረግ ተግዳሮቱን ለመቋቋም ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘርፉን ከተፈታተኑት ችግሮች አንዱ ነበር፡፡ ለምርት ግብዓት የሚሆን ለዘጠኝ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች፣ ለሁለት ጋርመንት ፋብሪካዎች እና ለአራት ለጥጥ ፀረ ተባይ ኬሚካል አቅራቢ ድርጅቶች በአጠቃላይ 15 ድርጅቶች የ23 ሚሊየን ብር የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጣቸው ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ መፍትሔ እንዲገኝ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ወቅታዊ ችግሮች ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት አብዛኛው ሠራተኛ ሥራ ላይ ባለመኖሩ ሁሉንም የታቀዱ መደበኛ ሥራዎችን ማከናወን አለመቻል እና ከአዲስ አበባ ውጪ ላሉ ፋብሪካዎች ድጋፍ ለማድረግ አለመቻል ኢንስትቲዩቱን ካጋጠሙት ችግሮች አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠትም እስከ መስከረም ወር ድረስ የተወሰኑ ባለሙያዎች ቢሮ እንዲገቡ በማድረግ ለሚመጡ ደንበኞች በጣም አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች እንዲሰጡ ሁኔታች ተመቻችተዋል፡፡
በጥጥ አቅርቦት እጥረት እና በዋጋ መናር አንድ ኪሎ ግራም በአማካይ ከ95 ብር በላይ መሆኑ ሌላኛው ዘርፉን የተፈታተነ ተግዳሮት እንደነበር የሚያብራሩት አቶ ባንቲ፤ ጥጥ በተፋጠነ መንገድ በኢግልድ እና በተመረጡ ስድስት ፋብሪካዎች አማካኝነት ፈጥኖ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እንዲችል ክትትል በማድረግ ችግሩ እንዲፈታ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
አቶ ባንታየሁ እንደሚሉት፤ የውጭ ንግድ ማበረታቻ ሥርዓት አጠቃቀም ዘመናዊ አለመሆን ከዘርፉ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት የአሠራር ሥርዓትን አውቶማይዝድ በማድረግ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ተችሏል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በሱዳን ድንበር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት አልሚዎች ወደ ምርት ሂደት አለመግባት እንዲሁም አልሚዎች በፀጥታ ችግር አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው የእርሻ መሳሪያዎቻቸውና ሌሎች ንብረቶች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ሌላኛው የዘርፉ ሳንካ መሆኑን ያብራሩት አቶ ባንታየሁ፤ ኢንስትቲዩቱ ከክልሉ ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት የእርሻ መሳሪያዎች ከጥፋት የሚድኑበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአፋር ክልል በተከሰተው ጐርፍ ከአገልግሎት ውጭ የሆነው ቦይ ባለመጠገኑ እና ሌሎች የጐርፍ መከላከያዎች ባለመሠራታቸው ጥጥ አልሚዎቹ ወደ ምርት ለመግባት ስጋት ላይ መሆናቸውን አልሸሸጉም። የአዋሽ ወንዝ በቀጣይ ጉዳት እንዳያደርስና በተወሰነ መጠን በጥጥ የተሸፈነው ሰብል የውኃ ዕጥረት እንዳይገጥም የመስኖ መሰረተ ልማቶች እንዲጠገኑ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013