
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2015 በሶስቱ ሀገራት መካከል በተደረሰው የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ግብፅና ሱዳን ለዝግጅት እንዲያመቻቸው የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሯን በይፋዊ ደብዳቤ እንዳስታወቀች የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ ገለጹ።
ፕሮፌሰር ይልማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ መሰረታዊ መረጃ የመለዋወጥ፣ በአካል ግንባታው ስፍራ ተገኝቶ የመመልከት፣ የመወያየትና ከባለሙያዎቹ ጋር እንዲነጋገሩ የማድረግ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፤ ይህ ተግባር ባለፉት አስርት አመታት ከውሃ ባለሙያዎች፣ ከፖለቲከኞችና ከዲፕሎማቶች ጋር ሲደረግ የቆየ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ በይፋዊ ደብዳቤ የሰጠችው መረጃም በዚህ መርህ የተመረኮዘ እንደሆነና ይህም የመረጃ ልውውጥ አንዱ አካል መሆኑን አስታውቀዋል። ሀገራዊ እንደነበርም አስታውቀዋል።
ሀገራቱ በስምምነታቸው መሰረት ግድቡ ቀስ በቀስ ሀምሌና ነሐሴ ላይ እንደሚሞላ ያውቃሉ ፣ ማረጋገጫ እንዲሆናቸውም ተነግሯቸዋል። ሀገራቱ ሀምሌና ነሐሴ ይሞላል የሚለውን መረጃ አስቀድመው በተጨባጭ አውቀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በኩል ሙሌቱ አይጎዳንም፤ ለዚህም እየተዘጋጀን ነው ሲሉ መደመጣቸውን አስታውሰዋል።
የውሃ ሙሌቱ የማይካሄድ ቢሆን ኖሮ የቅድሚያ ዝግጅቱ ለወጪና ለኪሳራ ስለሚዳርጋቸው ዝግጅት ማድረግ አያስፈልጋቸውም ነበር። ስለዚህ አሁን በቴክኒክ ደረጃ ለዝግጅት እንዲያመቻቸው ለሁለቱ ሀገራት መረጃ ማሳወቁ ለማረጋገጫነት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
እንድናሳውቅ የሚያስገድደን ህግ ባይኖርም የላይኛው ተፋሰስ ሀገር እንደመሆናችን ተባባሪነትና ወንድማማችነት መንፈስ አጠቃላይ ሁኔታውን ሪፖርት እያደረግን ነው። በዚህም እስካሁን ድረስ በመረጃ ልውውጥ ከ135 በላይ ሪፖርቶች ተሰጥተዋል። ምንም አይነት ጉዳት ሳናደርስ ምክንያታዊ አጠቃቀም እንደምንተገብር እያሳየናቸው እንቀጥላለን ብለዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ትልቁ ነገር የውሃ ሙሌት ሳይሆን ግንባታውን መጨረስ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፤ ሙሌቱ የውሃ ማስተላለፊያ መስመር ሳይዘጋ ራሱን በራሱ እንዲሞላ ይደረጋል። እንደዝናብ መጠን ሙሌቱ እንደሚወሰን አስታውቀዋል።
የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትን መጀመር አስመልክቶ ግብጽና ሱዳን በመርሁ መሰረት እንዲያውቁት ተደርጓል። ሀገራቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ሞልታ ብትጨርስ እንኳን መቃወማቸውን ይቀጥላሉ፤ ማመንም አይፈልጉም በአቋማቸውም ምንም ለውጥ እንደማያመጡ ጠቁመዋል።
አሁን በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉት ችግሮች ወይም ብዥታዎች ከህዳሴ ግድብ ጋር የተቀናጀ አሰራር ነው። ኢትዮጵያውያን በሁሉም ግንባር ጠንክረን ነጻነታችንንና መብታችንን አስከብረን መቀጠል አለብን። ይህም በቅንጅት እየተደረገብን ያለውን ጫና እንድናልፍ ይረዳናል፤ ፈተናውም የሚታለፍ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም የሉዓላዊነት መብቷ ነው። መብቷንም የሚነፍግ ከየትኛውም አካል ከመጣ በፅኑ እንቃወማለን። እውነትም ከኛ ጋር ነው ብለዋል።
በጸጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም