ትውልዷ እና ዕድገቷ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ነው። መደበኛ ትምህርቷን በገብረ ጉራቻ ከተማ እስከ 12ኛ ክፍል ተምራለች፤ በአዲስ አበባ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲም በአካውንቲንግ ዲግሪ ተመርቃለች። እማወራና የአራት ልጆች እናት ነች፤ ወይዘሮ ሣራ ታዬ ተሰማ።
የእናትነት ጫና በዝቶ ልጆችዋን ለማሳደግና ለመንከባከብ ብላ ሥራውን እስከ አቆመችበት ጊዜ ድረስ ወይዘሮ ሣራ በተለያየ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሰርታለች፤ በኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን (አሁን ኮርፖሬሽን) ለስምንት ዓመታት እና በኦሮሚያ መንገዶች ባለሥልጣን ለአንድ ዓመት ያህል ሠርታለች ።
ወደ ሥዕሉ ሙያ ለመግባቷ መነሻዋ ታላቅ ወንድሟ ነበር፤ ወንድሟ ለሆቴል፣ ግሮሠሪዎችና ለጤና ጣቢያዎች ለተለያዩ ንግድ ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ የማስታወቂያ ጽሁፎችን በእጁ እየጻፈ፣ ምስሎችንም እየሳለ ይጠቀም ነበር፤ ዲጂታል ማስታወቂያ ሳይመጣ በፊት።
የሥዕል ፍላጎቱ ነበራት፤ በቤቷም መጠነኛ ሥዕሎች ትሥል ነበር፤ ለሰዎች ግን ብዙም የማሳየት ልምድ አልነበራትም። ሥዕሎችን መሳል ያስደስታት፤ ውስጣዊ እርካታ ይጭርባት እንደነበር ትገልጻለች። ለሰዎች ማሳየት ስትጀምር ሥዕሎቿ በጣም ተወዳጅ መሆናቸውን መረዳት ጀመረች፤ እሷም በስእሎቿ ይበልጥ ደስተኛ እየሆነች መጣች። በዛም ተነሳስታ የበለጠ መሣል እንደጀመረች ትናገራለች።
ሣራ በአንድ ወቅት በኦሮሚያ ባህል ማዕከል የባህል ልብስ ለመግዛት ሄዳ በአጋጣሚ ብርቱካን ጂማ ከምትባል ሠዓሊና ዲዛይነር ጋር ተዋወቀች። እግረ መንገዷን የሳለቻቸውን በኪስ ስልክ ፎቶ ያነሳቸውን ሥዕሎች አሳየቻት፤ እሷም ወደደችውና ለምን እኛ ማኅበር አትገቢም ብላ ከማኅበሩ እንድትቀላቀል አደረገች። በእሷ አማካኝነት የኦሮሚያ ሠዓሊያን ማኅበርን ተቀላቀለች።
ማኅበሩ የሥዕል ሙያዬን እንዳዳብር አደረገኝ፤ የተወሰነ ሥልጠናም ሰጠኝ ትላለች የምትለው ወይዘሮ ሣራ፣ በማኅበሩም አማካኝነት በአቢሲኒያ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት ያህል የሥዕል ትምህርት ሥልጠናም አግኝታ እንደነበር ትናገራለች። ትምህርቱን ግን አልቀጠለችበትም። ለአምስት ወራት ያህል እንደተማረች በወሊድ ምክንያት አቋረጠችው። በአምስቱ ወራት ግን የሥዕል ሙያዬን እንዳዳብር የሚያስችል ጥበብና ዕውቀት ገብይቼበታለሁ በማለት ትገልጻለች። ያቋረጠችውን ትምህርት በመቀጠል ለማጠናቀቅም ሀሳቡ አላት።
ልጆችዋን እያሳደገች ባለቻት ትርፍ ሰዓት ሥዕል ትስላለች። እናትነትንና ሠዓሊነት አጣምራ መጓዝ ጀመረች፤ ሥዕል ለመሳል የሚረዳት መጠነኛ ስቱዲዮ አዘጋጅታም መሳሉን ቀጠለችበት። የቤተሰብ ኃላፊነቱና ልጆች ማሳደጉ እንዳለ ሆኖ የተወሰነ የሚሰማት ነገርና መግለፅና ማሳየት የምትፈልገው ባህል፣ ዕይታና እሳቤ ካለ በሸራና በቀለም በመሳል የውስጧን የልብ ትርታ ታሰፍረዋለች።
“የሥዕሉ ፍቅር ስላለኝ ይመስለኛል መሳል ያስደስተኛል፤ የተሰማኝን ሊሆን ይችላል የሚያስደስተኝን ወይንም ሰው ቢያውቀው የምለው ባህል ስመለከት በመሳል መግለጽ ያስደስተኛል።”ትላለች
ከሥዕሎቿ መካከል ለመከላከያ ሚኒስቴር እውነተኛ ነገር ላይ ያተኮረ ሥዕል በስጦታ ያበረከተች ሲሆን፤ ይህን ጽሁፍ ለማጠናከር በምናነጋግራት ወቅት ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሥዕል ለማበርከት እየሄደች ነበር። ሥዕሉን ለማበርከት ሄዳ ስትመለስ በሰጠችን መረጃ ማኅበሩ ባጋጣሚ 81ኛ ዓመቱን ለማክበር እየተዘጋጀ በመሆኑ ሥዕሉን ወደው እንደተቀበልዋት ገልጻለች።
ለሰላም ሚኒስቴርም ከሀገር ሰላምና ባህል ጋር የተያያዘ ሥዕል ለመስጠት ማዘጋጀቷንም ጠቁማለች።
የቤተሰብ ሃላፊነቱና የልጆች እናት መሆኗ ሥዕሎቿን በተለያዩ ቦታዎች ማቅረብ አላስቻላትም፤ ነገር ግን የኦሮሚያ ሠዓሊያን ማኅበር ዐውደ ርዕይ ሲያዘጋጅ በሁለት ቦታዎች ሥዕሎቿን አቅርባለች። ለአውደ ርዕዩ ያዘጋጀሁዋቸውን ሥዕሎች ሀሳባቸው መወደዱን ጠቅሳ፣ መርጠው ለዐውደ ርዕይ እንዲቀርብ አድርገውታል ትላለች።
በርካታ ሰዎች ሳትማሪ እንደዚህ ዓይነት ሥዕል ስታቀርቢ ማየታችን ጥሩ ነው ብለው ያበረታቱኛል። ይህ ደግሞ ሞራል ይሰጣል፤ የበለጠ እንድሠራ ይረዳኛል፤ እኔም ሠርቼ ሰዎች በሚሰጡት አስተያየት ሳየው እወደዋለሁ። በዐውደ ርዕዩ ከሚቀርቡት ሥዕሎችም ልምድና ተሞክሮ በማየት እወስዳለሁ።ሥራህን ሰው ሲወድልህ ደስ ይልሀል እንድታሻሽለውም ይረዳሃል።” ስትል ታብራራለች።
“በሥዕል ሙያ ረገድ እንደ ችግር የማየው የሥዕል ዐውደ ርዕይ ሲከፈት መገናኛ ብዙሃን ብዙም ትኩረት ሰጥተው አይዘግቡትም፤ ዜናና ፕሮግራም አይሰሩበትም›› በማለት ሰአሊዋ ትገልጻለች።
እንደ ሰአሊዋ ገለጻ፤ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎቻቸውን አምጥተው ሥዕል ቢያሳዩ ከሚያስተምሩት የቀለም ትምህርት በተጨማሪ ወደ ሥዕል ስነጥበብ ለሚገባ ተማሪ ጥርጊያ መንገዱን ሊያመቻቹለት ወይም ጥቂት ፍላጎት ሊጭሩበትና ፍላጎቱ ተፋፍሞ ጥሩ ሠዓሊ ሊሆን የሚችልበት አልያም የሥዕል አድናቂ የሚሆንበትን ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሥዕል የማየት ፍላጎቱ ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች ቢኖሩም የሥዕል ዐውደ ርዕይ ሲከፈት መረጃ እንደማይኖራቸው ትጠቁማለች። የሥዕል ዐውደ ርዕዩ ሲጠናቀቅ በሰማን ኖሮ ብለው የሚቆጩ ሰዎች ጥቂት እንዳልሆኑም ትናገራለች።
ከሩቅ ቦታ ያለውን ትምህርት ቤት ትተነው የሥዕል ዐውደ ርዕዩ በተከፈተበት በአቅራቢያው የሚገኝ ትምህርት ቤትና መምህራኑ የስእል አውደ ርእይ የመመልከት ልምድን ሊያዳብሩ ይገባል ስትል ትመክራለች። ማስተማር ማለት ቀለም ማስቆጠር ብቻ አይደለም፤ ሁሉንም ተማሪ በአንድ ጊዜ ማምጣት ባይቻልም የተወሰነውን እያመጡ ቢያሳዩ የሥዕል አፍቃሪያንና ሠዓሊያንን ይፈጥራሉ።” በማለት ትመክራለች።
ሠዓሊነትንና እናትነት ሣራ “የልጅ እናት ሆኖ ሥዕል መሥራት ይከብዳል፤ ለመሣል ፈልጌ ልጅ ማጥባት መመገብ ወይም ማስተኛት የመሳሰሉ የእናትነት ግዴታዎች ይመጣሉ፤ ሥዕሉን እጀምርና ልጄን ካስተኛሁ በኋላ ከቆምኩበት በመቀጠል አጠናቅቀዋለሁ። አይመችም፤ መሳል ስጀምር ልጁ ይፈልገኛል፤ አንቺ ጋ ካልሆንኩ ይላል፤ ልጁን አጠገብህ አድርገህ መሳል አስቸጋሪ ነው›› ስትል እናትና ሥዕል ፈታኝ መሆናቸውን ታብራራለች።
ሥዕል ስትስል ልጅ አጠገብህ ካለ ቀለሙን ሊደፋብህ አልያም አንዱን ከአንዱ ሊደባልቅብህ ይችላል፤ የሚታዘል ከሆነ በጀርባዬ አዝዬ አስተኝቼ ተረጋግቼ እስላለሁ። ይሁ ሁሉ ችግር ግን ፍላጎትን ሊገድበው እንደማይችል ትናገራለች።
ሥዕል የምሠራው ጥበቡ ፍላጎቱ የሕይወት ጥሪው ውስጤ ስላለ ነው፤ ሰዎች በጥበቡ ረገድ የሚያስቡትን ለማድረግ የሚፈልጉት ነገር ካለ መጣርና መስዋትነት መክፈልን ሊያስቡበት ይገባል። ልጅ የማሳደግ የእናትነት ኃላፊነትና ጫና ቢኖርብኝም ሥዕል ከመሳል አላገደኝም። ወጣቶች ኮረዶች መስዋዕትነትን ከከፈሉ የአሰቡበት የስነ ጥበብ ደረጃ መድረስ ይችላሉ ስትል ትመክራለች።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013