እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ሲማር የቆየ ቢሆንም፤ የሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባት ሠላም ነስቶት ኖረ፡፡ በተለይ ደግሞ በ1991 ዓ.ም የነበረው አስከፊ ጦርነት ጭራሹን ከሚወዳት ኢትዮጵያ ለይቶት አስመራ ሆኖ አዲስ አበባን ይናፍቅ ጀመር፡፡ እናም ዛሬ ሁኔታዎች ተቀይረው የናፈቃትን አዲስ አበባ መልሶ ሲመለከት፤ “የህዝብ ሠላም ሲመለስ ደስታዬ ወደር የለውም” ይላል፡፡ እንደ ጥበብ ሰው ይህን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚስችል ሥራ ላይ እንደሚያተኩር ይናገራል፡፡ ከእንግዲህ ጥበብ ስትፈውስ እንጂ ስትገድል የማየት ፍላጎት የለኝም የሚለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የባህል ቡድን ልዑካን የተካተተው አርቲስት- እስጢፋኖስ አብርሃም ነው፡፡
‹‹ጥበብ ትገድላለች፤ ወይም ትፈውሳለች፡፡›› በመሆኑም ጥበብ እንደ አጠቃቀማችን ትወሰናለች፡ ፡ በተለይ ጥበብን ለሠላም እና ለፍቅር መቀስቀሻ ስንጠቀምባት ዋጋዋ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሃሴትም ትሰጣለች፤ በተቃራኒው ስንጠቀም ደግሞ ጥፋቷ እንዲሁ የከፋ ነው ይላል፡፡ ሁለቱ አገራት ለዘመናት ተራርቀው፤ ለዚያውም ደም ተፋስሰው መኖራቸው ከስቃይ ውጭ ማናቸውንም አትራፊ አላደረግም፡ ፡ በተለይ ደግሞ በአንድ ማዕድ ቆርሰው በአንድ ትምህርት ቤት ተምረው በአንድ ላይ ደስታና መከራ ለዘመናት ተካፍለው የነበሩ ሰዎችን መከፋፈሉ ምንኛ ክፉ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በሁለቱ ህዝቦች መካከል እጅግ ጥላሸት የተቀባ ታሪክ ሲሆን፤ መሆን አልነበረበትም ይላል፡፡
ታዲያ ያለፈውን ቁጭትና ፀፀት ትተን ነገ አብረን ለመትመም ዛሬ በሩ ተከፍቷልና በጥበብ የሠላም አሻራችንን ልናኖር አንድ ብለን ጀመርን ይላል-አርቲስት እስጢፋኖስ፡፡ አርቲስት አደም ፋይድ አሚር በበኩሉ፤ ሁለቱ አገራት በጦርነት ውስጥ ገብተው እንደማየት በሕይወቴ የከፋ ጊዜ አልነበረም፡፡ ወንድም ወንድሙን ጎድቷል፣ ደም ፈሷል፡፡ ሆኖም ያ! መጥፎ ታሪክ ተረስቶ ወደ ሠላም መሸጋገሩ ከምንም በላይ በታሪክ ጎልቶ የሚፃፍ ክስተት እንደሆነ ነው የሚናገረው፤ በተለይ ደግሞ የሁለቱ አገራት መሪዎች ለሠላምና ለአንድነት የከፈሉት መስዋዕትነትና የህዝቡ ፍላጎት እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላል፡፡ አቶ ሚካኤል ተፈሪ የልዑኩ መሪ ሲሆኑ፤ ይህ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበርን፤ ለዚህም ከፍተኛ ትግል አድርገናል። ሁለት ወንድማማች ህዝቦች በታሪክ አጋጣሚ ቁርሾ ውስጥ ይግቡ እንጂ፤ መቼውንም ቢሆን ተራርቀው መኖር አይችሉም፡፡ እናም ታሪክ ተፈጠረ፤ ማርሽ ተቀየረ፤ ሠላም ወረደ እሰየው ይላሉ፡፡ አሁን የተጀመረው ለውጥም ወደፊት ስለመቀጠሉ አንዳችም አይጠራጠሩም፡፡
ይሁንና የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ጥላቻዎችንና አተካራዎችን ሳይሆን የሁለቱን አገራት ህዝብ በበለጠ የሚያቀራርብና አንድነቱን በሚያጠናከሩ መረጃዎች ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ ይጠይቃሉ፡፡ ስለሆነም ‹‹ከአሁን በኋላ ዜማችን ሠላም፣ መንዙማችን ሠላም፤ ቅዳሴያችንም ሠላም ነው›› ይላሉ፡፡ በአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኤርትራ ተወካይ አምባሳደር አርአያ ደስታ በአማርኛ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ንፋስ ገብቶት የነበረው የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ለዘመናት ተቋርጦ በአሁኑ ወቅት በአዲስ መልክ መታደሱ የሁለቱም አገራት ጥረትና ፍላጎት መሆኑን ጠቁመው፤ ከአሁን በኋላ በጠንካራ መሰረት ላይ የተጣለ ወዳጅነት ስለመፈጠሩ ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል ሠላም እንዲወርድ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ አይታይም፡፡ ከአሁን በኋላም ሠላም እንደሚቀጥል እና በሁለቱ አገራት ህዝቦች ልብ ውስጥም ለዘመናት ቤት ሠርቶ እንደሚኖር ተስፋ ይገልጻሉ፡፡ የደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሁለቱ አገራት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ግንኙነታቸው ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፤ አንድ ቀን እንደሚገናኙ ተስፋ አድርገው በፀሎት ላይ እንደነበሩ ይገልፃሉ፡፡ ታዲያ ዘመን አልፎ ዛሬ ስለ ሠላም እና አንድነት ተዘመረ፡፡ ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አመራርና ቁርጠኝነት ታላቅ እንደነበርና ይህም ፍሬ እንዳፈራ ይናገራሉ፡፡ ጥበብም ሠላምን በመስበክ ረገድ ሚናዋ የጎላ እንደሆነ የተናገሩት አፈጉባኤዋ ከአሁን በኋላ ሁለቱ ህዝቦች ወዳጅነታቸው ተጠናክሮ የሚቀጥልበት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ክልሉም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ክፍለ ዮሐንስ አንበርብር