አዲስ አበባ:- ፋሽስቶች ኢትዮጵያዊያንን በግፍ የጨፈጨፉበት የሰማዕታት ቀን ትላንት ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሀውልት ተከበረ። የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ በክብር እንግድነት ተገኝተው የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል። ለበዓሉ ድምቀትና ክብር ሲባል የፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ኦኬስትራዎች ተገኝተው ወታደራዊ ማርሽ ትርዒት ያቀረቡ ሲሆን፤ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች እና ወጣቶችም ስነስርዓቱን ከመከታተል አንስቶ እስከ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥ ድረስ ተሳታፊ ሆነዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ትውውቅ የፈጠሩትና ከዓድዋ 120ኛው ዓመት በዓል ጀምረው ቡድን መስርተው ለ4ኛ ጊዜ በዓሉን በማክበር ላይ የሚገኙት ወጣቶች የታዳሚው አካል ሲሆኑ ለበዓሉ ድምቀት ከሰጡት ክፍሎች አንዱ ሆነዋል። “የተዋወቅነው በአብዛኛው በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ነው። አንድ አይነት ፍላጎትና አላማ ያለን ወጣቶች ነን።” የሚለው የ“ዓድዋ 120” ቡድን አስተባባሪና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወጣት መኮንን መንገሻ ቡድኑ በዚህ እንደማያቆም ያስረዳል። ይህንን የሰማእታት በዓል ማከበር የግድ ነው። ያለዚህ ሀውልት እኛ ምንም ነን። በርግጥ እዚህ ሰማእታት ሀውልት ስር ቆሞ ማክበር በአባቶቻችን ደም ላይ ነውና የቆምነው ያማል። ይሁን እንጂ ያኮራል፣ ያስደስታልም። ይህ ያባቶቻችንና እናቶቻችን መስዋእትነት መክፍል ነው ለዛሬ እኛነታችን መሰረት የሆነው የሚለው ወጣት መኮንን፤ “ሌሎችም ይህንን ሊገነዘቡት ይገባል። እኛ ወጣቶች አኩሪ ታሪክ ያለን በመሆኑ ልንኮራና ወደራሳችን ልንመለስ ይገባል።” ሲል ያሳስባል።
የዓርበኞች 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዓሉን ለማክበር በስፍራው የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ህዝባዊና አገራዊ የጀግንነት ዜማዎችን በማዜም በዓሉን አድምቀውታል። የተማሪዎቹን ቡድን በመምራት ወደ ስፍራው የመጡት መምህር ታደለ ገብረ ስላሴ እንደሚሉት፤ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የዚህ በዓል ታዳሚዎች ሊሆኑ ይገባል። ይህ በዓል በቀላሉ የሚታይ አይደለም የሚሉት መምህር ታደለ ገብረስላሴ፤ ይህ የቀድሞው ትውልድ ሰማእትነት ባይኖር ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይኖር ነበር ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ተተኪው ትውልድ የአባቶቹን ታሪክና ውለታ ሊያውቅ ይገባል። የአሁኑ ወጣትም አገሪቱ በፈለገችው ቦታ ሁሉ ተገኝቶ ይህንን ያባቶቻችንን ጀግንነት ሊደግመውና የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ ሊወጣ ይገባል፤ ብለዋል።
የቀድሞው ክቡር ዘበኛ ሰራዊት አባል ሃምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ የበዓሉ የክብር እንግዳ ሲሆኑ፤ በዓሉን እና ሰማእታቱን አስመልክተው “የዛሬዋ እለት ስንትና ስንት ደም የፈሰሰባት እለት ናት። በዛሬዋ ቀን ያለቀው ህዝብ ነው የዛሬው ነፃነታችን። እነሱን ማሰብ፣ ማስታወስና ማመስገን ይገባል። እለቱ የነሱ ደም ውጤት ነው። በተለይ ወጣቱ ይህን ልብ ሊለው ይገባል። ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቀው ቅኝ ባለመገዛቷ መሆኑን ሊያውቅና ለሰማእታቱ ክብር ሊሰጥ ይገባል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዓሉ ፋሺስቱ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ እንዲጨፈጨፉ ያደረገበት 82ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ግርማ መንግሥቴ