ርምጃ ባለመወሰዱ የዋና ኦዲተር ልፋት በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አላመጣም
አዲስ አበባ፦ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ የኦዲት መጓደልን ተከትሎ ተጠያቂ ባለማድረጉ ዋና ኦዲተር ላለፉት ዓመታት ቢጮህም በሚፈ ለገው ደረጃ ለውጥ አለመምጣቱን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታወቀ። ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ ለአዲስ ዘመን ብቻ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ቢጮህም ርምጃ በለመወሰዱ በኦዲቱ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በፋይናንስ ላይ በተሰራው ሥራ ስህተቶች ሙሉ ለሙሉ አይፈጠሩም ባይባልም አውቀው የሚሰሩ ጥፋቶች መቆም ነበረባቸው። ነገር ግን መቆም አልቻሉም።
በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም። በየዓመቱ ሪፖርት አቅርበን አንድ ጊዜ ጮህን ይቀራል። እንደዋና ኦዲተር ኃላፊነታችንን ተወጥተናል ያሉት አቶ ገመቹ ማድረግ ሲገባን ያላደረግነው አለ ለማለት በጣም እቸገራለሁ። ሁሉንም ጥረት ለማደረግ ሞከረናል። በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆንም ሰርተናል ነገር ግን በየጊዜው ማስተካካያ ባለመደረጉ የዋና ኦዲተር ሪፖርት የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣም። “ሪፖርት አይቼ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ሳስተያየው ለውጥ ካላመጣሁ እዚህ ምን እሰራለሁ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ” ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ አስፈፃሚው ትኩረት እያደረገ ቢመጣም ለውጥ ግን በሚፈለገው ደረጃ አልመጣም። ለምሳሌ፤ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጥናት እና ዲዛይን የላቸውም።
የመንግሥትን ገንዘብ እያስወጡ በተባለው ጊዜም እየተጠናቀቁ አይደለም። ተጠናቅቀውም የሚገባቸውን አግልግሎት እየሰጡ አይደለም በማለት መጮህ የጀመርነው ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ነው። በወቅቱ ርምጃ አልተወሰደም በማለት ሀዘናቸውን ይገልፃሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ