ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሃላባ ዞን ዌራ ድጆ ወረዳ ከበንዶ ቀበሌ 16 የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ወክለናል ያሉ ሶስት ግለሰቦች ወደ ዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ይዘው መምጣታቸውን ባለፈው ሳምንት አስነብበናል። ‹‹መሬታችንን ተነጥቀናል፤ ያለአግባብ እኛ ብቻ ሳንሆን ቤተሰባችንም ለአደጋ እና ለጉዳት ተጋልጠዋል።›› ሲሉ በደላቸውን በመግለፅ መፍትሔ የሚሰጥ አካል ካለም መፍትሔ ይስጠን ብለዋል።
ፍረዱኝ ባዮቹ እንደተናገሩት፤ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ለይዞታቸው ግብር እየከፈሉ የቆዩበት መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኢንደስትሪ ልማት ስም ተወስዶባቸዋል። በገጠር መሬት የመጠቀም ህገመንግስታዊ መብታቸው የተጣሰ ሲሆን፤ የሚመለከተውን አካል በማነጋገር ችግራቸው እንዲፈታ በማለት አቤት ለማለት ተገድደዋል።
ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሃላባ ዞን ዌራ ድጆ ወረዳ ከበንዶ ቀበሌ በመምጣት አቤቱታ ካቀረቡት መካከል አንዱ አቶ ሃሰን አጌቦ ናቸው። አቶ ሃሰን እንደሚገልፁት፤ መሬታቸውን ያለአግባብ ተነጥቀዋል። ‹‹ለምን መሬታችን ያለአግባብ ይወሰዳል›› በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ካለማግኘቱም ሌላ ለበርካታ እንግልት ተዳርገዋል።
‹‹ሄርጳ የተሰኘ ኢንቨስተር በመቆፈሪያ ማሽን በመሬቱ የነበረውን ቡቃያ ሳያስቀር ገልብጦ መሬቱን ለሁለት ሰንጥቆታል። ለአርሶ አደሮቹ በሚል አርሰን የምንበላበትን መሬታችንን ለመኖሪያ ቤት እና ለጓሮ አትክልት የሚሆን ሁለት ሁለት ጥማድ መሬት ብቻ ትቶልን ‹ለኢንደስትሪ ልማት ይፈለጋል› በሚል ከእያንዳንዳችን ስድስት ስድስት ጥማድ መሬት ወስዶብናል።›› በማለት ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።
እንደ አቶ ሃሰን ገለፃ፤ ለክልሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ለአላባ ዞን እና ለወረዳውም ጥያቄ በማቅረባቸው ኢንቨስተሩ መሬታቸው አካባቢ እንዳይገባ፤ እንዳይነካ ተባለ። ይህን ያሉት የቀድሞዎቹ አመራሮች ሲሆኑ፤ በአርሶ አደሮቹ አቤቱታ ምክንያት መሬቱን የተከለከለው ኢንቨስተር ተነጥቆ ለአርሶ አደሮቹ መሬቱን ከመመለስ ይልቅ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮቹ ለራሳቸው መሬቱን ተከፋፈሉት። መሬት የተነጠቁት አርሶ አደሮች በገዛ መሬታቸው በፍራቻ ለቀበሌ አራት ለወረዳ ሁለት አመራሮች በመሬቱ እያረሱ ምርት ለማካፈል ተገደዱ። በኋላም ጉዳዩ የተደረሰባቸው አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደረገ። በመሃል ከአርሶ አደሩም ከባለሃብቱም ሳይሆን የቀረው መሬት ከአርሶ አደሮቹ ከብቶች መዋያነት ያለፈ ልማት ሳይከናወንበት ሳይታረስ ጦሙን ማደር ጀመረ።
ለዝግጅት ክፍላችን ይዘው በመጡት የስም ዝርዝር መሰረት 16ቱም አባወራ እያንዳንዳቸው ስድስት ጥማድ መሬት ተቆርጦባቸዋል። መሬቱ እንዲመለስ ችግሩ ይፈታ በማለት ከአርሶ አደሮች እንደተወሰደ ሁሉም ያውቃል በሚል ‹‹የመሬታችን ይመለስልን›› ጥያቄያቸውን በየደረጃው አቅርበዋል። ቀበሌ፣ ወረዳ እና ዞን ቢመላለሱም ፍትህ የሰጣቸው የለም። በክልሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን አቶ ሃሰን ተናግረዋል። በ16ቱ አርሶ አደር አባወራ ስር ከአራት መቶ ያላነሱ ሰዎች በዚህ መሬት ላይ ኑሯቸው የተመሰረተ ቢሆንም፤ ሲጠራ አቤት ብሎ መሬቱን ይገባችኋል የሚላቸው አካል ማጣታቸውን ገልፀው ነበር።
በሌላ በኩል ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደተናገሩት፤ ኢንቨስተሩ ማለትም አቶ ሄርጳ ፈይሳም ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን ለመሬቱም ካርታ የተሰጣቸው በመሆኑ፤ ‹‹ለአርሶ አደሮቹ ካልተሰጠ እኔ ካርታ ስላለኝ መሬቱ የሚገባው ለእኔ ነው›› ብለው በመጠየቅ ላይ ናቸው። ነገር ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለፁት፤ ባለሃብቱ መሬቱን በወሰዱበት ጊዜም ቢሆን ካሳ አልተሰጣቸውም። ለእዚህ እና ሌሎችም ተያያዥ መረጃዎች የቀበሌ እና የወረዳ እንዲሁም የዞን እና የክልል መስተዳድሮችን እንዲሁም ባለሃብቱን እና ሌሎች ምስክሮችን መጠየቅ እንደሚቻል ጠቁመው ነበር።
በዚህ በኩል የወረዳ እና የዞን እንዲሁም የክልል አመራሮችን በስልክ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ሳይሳካልን መቅረቱን ባለፈው ሳምንት እትማችን አስነብበናል። እነዚህ አካላት ምላሻቸውን ሲሰጡን የምናስተናግድ መሆኑን በጠቆምነው መሰረት የዞኑ እና የክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎች ሁኔታውን አስመልክቶ የሚያውቁትን እና የደረሱበትን ተናግረዋል። ይህንኑ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
በቅድሚያ መሬቱ ከአርሶ አደሮቹ ላይ ተነጥቆ ተሰጥቷቸዋል የተባሉት ባለሃብቱ ማለትም አቶ ሔርጳ ፈይሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአካባቢው በ1997 ዓ.ም መሬቱን ለማልማት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ አግኝተው ነበር። ጥያቄውን ሲያቀርቡ አሁን አቤቱታ እያቀረቡ ያሉት አርሶ አደሮች በቦታው አልነበሩም። ይዞታው የማንም አልነበረም። አካባቢው ላይ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ችግር ስለነበር በጊዜው ልማቱን አቁመውታል። በኋላ በ2000 ዓ.ም ውላቸውን አድሰው አካባቢውን መንጥረው ለልማት ምቹ ካደረጉት በኋላ፤ አንዳንድ ሰዎች በህገወጥ መንገድ አካባቢው ላይ ቤት መስራት እና ማረስ ጀምረዋል።
በጊዜው ድርጊቱን የቀበሌ አመራር ከማስቆም ይልቅ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ድርጊቱ ማስቀጠሉን ያስታውሳሉ። እስከ 2005 ዓ.ም ህገወጥ ሰፋሪ የበዛባቸው መሆኑን አመልክተው፤ በውላቸው መሰረት በየዓመቱ 25 በመቶ ማልማት ይጠበቅባቸው እንደነበር፤ ሆኖም ግን በአካባቢው ሰላም እንዳልነበረ እና መንግስትም ተገቢውን ጥበቃ ሳያደርግላቸው በመዘግየቱ መሬቱ በህገወጦች ሊከበብ መቻሉን ያስረዳሉ።
በጊዜው አርሶ አደሮቹ ቦታውን በህገወጥ መንገድ የያዙት በመሆኑ በ2000 ዓ.ም የነበረው ውል ተቀየረ። በ2005 ዓ.ም እንደገና ከዞኑ ጋር ህገወጥ ሰፋሪዎቹን ማስነሳት ከባድ ነው በሚል 152 ሔክታር የነበረው መሬት 39 ሔክታር መሬት ባለሃብቱ ከተሰጣቸው መሬት ላይ ተቀንሶ ውላቸውን አደሱ። የተቀነሰው መሬት አርሶ አደሮቹ ቤታቸው እንዳይነካ እና ጓሯቸውን እንዲያለሙ እና እንዳይጎዱ ታስቦ ብቻ እንደነበር አቶ ሔርጳ ያስታውሳሉ።
ሆኖም ግን የቀበሌ እና የወረዳ አመራሮች ከእርሳቸውም ሆነ ከአርሶ አደሮቹ ላይ ነጥቀው መሬቱን እራሳቸው ወስደውት እንደነበር ጠቁመው፤ ሆኖም ግን መሬቱ ለራሳቸው ቀድሞ እንደተሰጠ ዞኑም ሆነ ክልሉ እንደሚያውቁ ተናግረዋል። መሬቱ የእርሳቸው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸው መሆኑን እና ግብርም እየከፈሉበት እንደሚገኙ ገልፀዋል። በኋላ የመጡት ‹‹መሬቱ ለእኛ ይገባል›› ያሉት አርሶ አደሮች እና እርሳቸው ይገባናል በሚሉት መሬት ላይ፤ አሁን ደግሞ በመሃል ሌሎች ሰዎች እየሰፈሩበት እንደሚገኙ አብራርተዋል። አቶ ሄርጳ ለክልል የኢንቨስትመንት ቢሮ ጉዳዩን ቢገልፁም ከቀጠሮ ውጪ ምላሽ አልተሰጣቸውም። ቦታው ድረስ በአካል ሄዶ ያየ እና መፍትሔ ያስገኘ ሰውም የለም ብለዋል።
በቆሎ እና በርበሬን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን የሚያለሙት አቶ ሔርጳ፤ በእርግጥ መሬቱ ላይ አሁን ደግሞ ከቀበሌ ጋር በመመሳጠር በድጋሚ ሌሎች ሰዎች እየሰፈሩ ነው ብለዋል። በዚህ ላይ የወረዳዎች እጅም የሚኖርበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት አቶ ሔርጳ፤ ይህንን አቤቱታ ለወረዳ እና ለዞን ማቅረባቸውን እና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እንዲሁ ‹‹ቆዩ›› እያሏቸው በመንገላታት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ቦታው ላይ ነበርን በሚል ለቀረበው አቤቱታ አቶ ሔርጳ፤ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ። እርሳቸው ቦታው ምድረ በዳ ጫካ እንደነበር እና ቦታውን ለልማት ምቹ ሲያደርጉት ከአጎራባች ስልጤ ዞን ሳንቁራ ከሚባል አካባቢ የመጡ ሰዎች በተለያየ መልኩ ገብተው መሬቱን መያዛቸውን እና አያያዛቸውም በመደበኛ መልክ አለመሆኑን ይናገራሉ። አሁንም አቤቱታ አቅራቢዎቹ በቂ መንደር እንዳላቸው አቶ ሔርጳ ያመለክታሉ።
አመራሩ ጊዜ ስጡን እያለ እርሳቸውም ጊዜ ለመስጠት ቢሞክሩም አሁንም ህገወጥ ግንባታ መቀጠሉን አመላክተው፤ ግብር እየገበሩበት ቢሆንም ነገር ግን አሁንም ለሌላ እየተሰጠ መሆኑ እንዳማረራቸው ያመለክታሉ። ቀድሞም ቢሆን የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች የኢንቨስትመንት መሬቱን በሙስና መውሰዳቸው ከተረጋገጠ በኋላ፤ ለባለቤቱ እንደመመለስ መሬት ባንክ ገባ ተብሏል የሚሉት አቶ ሔርጳ፤ ነገር ግን በህጋዊ መንገድ የተከራዩትን እና ግብር እየከፈሉበት ያለውን መሬት ባንክ ገብቷል ማለት ተገቢ አይደለም በማለት አቤት ቢሉም የሚሰማ ጠፍቷል ይላሉ። አሁን ላይ ስራ ማቆማቸውን እና ተስፋ ወደ መቁረጥ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
የሃላባ ዞን የኢንቨስትመንት ቢሮ ማስፋፊያ ሃላፊ አቶ ጀማል ጉንቴ በበኩላቸው ለአቶ ሔርጳ የተሰጠው መሬት ፋይሉ የሚያሳየው 138 ሔክታር ነው። ለእዚህ መሬት ግብር እየከፈልኩ ቢሆንም ከቀበሌ አመራር ጋር ተመሳጥረው የገቡ ሰርጎ ገቦች መሬቱን እያባከኑብኝ ነው በሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያውቁ መሆኑን ይናገራሉ። በማመልከቻቸው መሰረት ከወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ እና ከወረዳው የግብርና ሃላፊ ጋር አብረው ቦታው ድረስ ተገኝተው ሁኔታውን ማየታቸውን ገልፀዋል።
በእርግጥም ለግለሰቡ በተሰጠ መሬት ላይ ሌሎች ሰዎች ሲያርሱ እና ቤት ሲገነቡ ማየታቸውን ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ ስለዚህ እዛው ከወረዳው ግብርና ሃላፊ ጋር ተነጋግረው ‹‹ግንባታው ትክክል አይደለም። መሬቱ የአቶ ሔርጳ ነው›› በሚል ቃለ ጉባኤ የተያዘ ሲሆን፤ በማረስ ላይ የነበረ አንድ ግለሰብ ከወረዳው አልፎ በፖሊስ እንዳታርስ ቢባልም፤ ፈቃኛ አልሆን ብሎ እንደነበር በመግለፅ ሆኖም ግንባታውም ሆነ የእርሻ ስራው ባለበት እንዲቆም መነጋገራቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ በአቶ ሔርጳ ሥም የተመዘገበ ያልታረሰ መሬት አለ። አቶ ሔርጳ ‹‹ለምን አላረስክም›› ተብለው ሲጠየቁ መሬቱ ላይ ውሃ ተኝቶበት ነበር የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ግን መሬቱ ላይ ሌሎች ሰዎች ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑ አይካድም። ስለዚህ ድርጊቱን ለማስቆም እና መሬቱ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ አስተዳደራዊ ውሳኔ ስለሚፈልግ የወረዳው አመራር እና የቀበሌ አመራር ባለለበት ጉዳዩ ታይቶ መሬቱ አሁንም ለባለሃብቱ የሚገባ ከሆነም፤ ተረጋግጦ መሬቱን የሚይዝበት ሁኔታ ይመቻቻል መባባላቸውንም ጠቁመዋል።
16ቱን አርሶ አደሮች በሚመለከት አቶ ጀማል የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ገልፀው፤ እነዚህኞቹ የመሬቱ ይገባኛል ጥያቄ አቅራቢዎች አዲስ ሶስተኛ ወገኖች ናቸው ይላሉ። በሌላ በኩል የቀበሌ መዋቅር እና የወረዳ መዋቅር መሬቱን ለሌላ አካል እያከፋፈሉ ነው በሚል የተገለፀውን ጉዳይ ግን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። መሬቱ እየተሸነሸነ መሆኑን መስማታቸውን ይህን ተከትሎ ላቀረቡት ጥያቄ ለችግኝ ጣቢያ መሬታቸው የተወሰደባቸው ሰዎች እና የውሃ ኩሬ የሚቆፈርበት ቦታ ላይ ለነበሩ ሰዎች ካሳ መሬቱ እየተሰጣቸው ነው የሚል ምላሽ የቀበሌ መዋቅር እና የወረዳ መዋቅር የነገሯቸው መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም ይህን ማድረጉ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ይህ ድርጊት ሲፈፀም ዞን ማወቅ ነበረበት በሚል ወቀሳ መሰንዘራቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ቀደም ብሎ በምን ምክንያት እንዳላረሰ ባይታወቅም ኢንቨስተር ተብሎ ፍቃድ የተሰጠው አካል ለማረስ እፈልጋለሁ መሬቱ የኔ ነው እያለ፤ ሰውየው የይገባኛል ጥያቄ እያቀረበ መሬቱን ማከፋፈል፤ በመሬቱ ላይ የቤት ግንባታ ማካሄድም ሆነ ማረስ ተገቢ አይደለም›› በማለት ቃለ ጉባኤ ይዘው መለያየታቸውን ተናግረዋል።
አሁን በቦታው ላይ ማንም የለም። መሬቱ አልታረሰም የሚሉት አቶ ጀማል፤ በዞን እና በወረዳው መካከል ያለው ልዩነት ኢንቨስተሩ 138 ሔክታር የራሴ ነው ብሎ የሚከራከረውን ግለሰብ የአንተ አይደለም ብሎ መመለስ ወይም የእርሱ ከሆነም እንዲያለማ ማመቻቸት ሲገባ ለሌላ ሶስተኛ ወገን መሰጠት የለበትም የሚል ክርክር መሆኑን ገልፀዋል። ለጊዜው መሬቱ ባለበት እንዲቆይ ወረዳዎች አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲወስዱ፤ በቀጣይ ዞኑ አስተዳደር ካዋቀረ በኋላ ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩ ይፈታል ማለታቸውን ገልፀዋል።
ከ16ቱ አርሶ አደር ይልቅ እስከ ክልል ድረስ ሔደው ጥያቄ ያቀረቡት ‹‹ለመስራት የቀበሌ መዋቅር ከልክሎኛል›› ያሉት አቶ ሔርጳ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ጀማል፤ በእርግጥ ወደ ዝግጅት ክፍሉ የመጡ አቤቱታ አቅራቢዎች እንዳሉት ሁሉ አቶ ጀማልም የአቶ ሔርጳ መሬት ላይ አመራር ይጠቀምበት እንደነበር እና ከአመራሮቹ ላይ የተነጠቁ መሆኑን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ ወደ ፊት በኮሚቴ ደረጃ ውሳኔ የሚተላለፍ ሲሆን፤ መሬቱ ማን ይጠቀምበት ይሆናል የሚለውን ለማወቅ አሁን ላይ መናገር አይቻልም ብለዋል። ባለሃብቱ ‹‹138 ሔክታር ተለክቶ ሊሰጠኝ፤ ይገባል።›› ሲሉ፤ በሌላ በኩል ወደ መሬት ባንክ ገብቷል ለአንተ አይገባም በሚል ወረዳ እና ቀበሌ ክርክር ይዟል ይላሉ። ከዚህ ውጪ ከአርሶ አደሮቹ የመሬት ባለቤትነት ጋር ተያይዞ እንደማያውቁ ጠቁመው፤ ወደ ፊት ቀደም ያሉ ሰዎችን ያካተተ ኮሚቴ በማዋቀር ውሳኔ የሚተላለፍ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ አቶ ሔርጳ በአካባቢው ለማልማት ሲመጡ ሌሎችም ባለሃብቶች ነበሩ በጊዜው መሬቱን ለክተን ሰጥተናል።›› የሚሉት ደግሞ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የኢንቨስትመንት ቢሮ የመሬት አቅርቦት ባለሞያ አቶ አበራ አዴቦ ናቸው። አቶ አበራ እንደሚናገሩት፤ ቦታውን ለአቶ ሔርጳ ሲሰጡ በስፍራው ማንም አልነበረም። ሰው ያለበትን መሬት ለኢንቨስተር መስጠትም ስለማይቻል ቀድሞም ሰው ነበር ማለት አይቻልም። በጊዜው ሃላባ ዞን ሳይሆን ወረዳ ነበር። ከቀበሌም ከልዩ ወረዳም የተወጣጣ ኮሚቴ ቦታውን ለአቶ ሔርጳ ሰጥተዋል።
አቶ ሔርጳ አሁን ላይ ለእነርሱ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልፀዋል፤ በእርሳቸው በኩል የሚያውቁት ባለሃብቱ
በመሬቱ እያለማ እንደሆነ እና የክልሉ ኢንቨስተር ነው የሚል እንጂ መሬቱ ተነጥቆ መሬት ባንክ ገብቷል የሚል መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል። ባለሃብቱ የተሰረዘም ሆነ መሬቱ ባንክ የገባ ከሆነ እነርሱ የሚያቁበት ነገር
ሊኖር ይገባ እንደነበር ተናግረው፤ አቤቱታ አቅራቢ አርሶ አደሮችን በሚመለከት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትል እና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት አቶ ዋሴ ዓለሙ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ አቶ ሔርጳ ህጋዊ ፈቃድ እና የመሬት ውል አለው። አፈፃፀሙ ግን ደካማ ነው። ነገር ግን አንዳንዴ የቀድሞ አመራሮች ከባለሃብት ላይ መሬት ይቀሙ እና ገበሬዎችን አስፍረው እንዲሰሩ እያደረጉ ሲጠቀሙ ሲያስቸግሩ ነበር። አሁን እነዚያ አመራሮች ተነስተዋል። ስለዚህ አርሶ አደሮቹ መጀመሪያ ሲያገኙ የነበረው ጥቅም ስለቀረባቸው እንደዚያ እንዲጠይቁ እና እንዲያመለክቱ አመራሩ ገፋፍቷቸው እንጂ ሶስተኛ ወገን ያለበት መሬት ለባለሃብት የሚሰጥበት ሁኔታ የለም ብለዋል።
በ2010 ዓ.ም ይህ ታይቶ እንደነበር በማመልከት፤ ገበሬዎቹ ለምን አይወጡም ሲባል የአመራር እጅ ስለነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። እንደ አቶ ዋሴ ገለፃ ምናልባት አሰጣጡ ላይ ከሶስተኛ ወገን ነፃ ሳይሆን መሬት ተረክቦ ውል ፈፅሞ ከሆነ የሚጣራ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ግለሰቡ ነፃ መሬት ተሰጥቶት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ መሬቱን ሌሎች እየወሰዱበት ከሆነ የሚጣራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዋናነት አመራር ሆን ብሎ የሚፈጥረው ነገር መኖሩን ማወቅ ይገባል የሚሉት አቶ ዋሴ፤ አመራር እንዲሁ ቁጭ ብሎ በኢንቨስተር መሬት ላይ አርሶ አደሮችን እያሰሩ የሚጠቀሙ መኖራቸው መዘንጋት የለበትም ብለዋል። ቦታውን ቀድሞም ቢሆን የሚያውቁት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዋሴ፤ በፊትም ከፍተኛ ችግር እንደነበር ባለሃብቶቹ ለአመራሮቹ ማሳረሻ ቦታ ካልሰጡ መሥራት ስለማይችሉ ያንን የሚያደርጉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ገልፀዋል። በኋላ ግን ተገምግሞ አመራሩ ሲወርድ አርሶ አደሮቹም በመሬቱ ላይ መጠቀም የሚችሉበት ዕድል ስለሚዘጋ አርሶ አደሮቹ የሚጮሁበት ሁኔታ ይኖራል ካሉ በኋላ፤ ይህን የሚገፋው የቀድሞ ተጠቃሚው አካል ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።
በቅርቡ የክልል ባለሞያ ቦታውን ሔዶ አይቷዋል። አፈፃፀሙ ደካማ ነው ብለዋል። ለዞን አስተዳደርም ግብረ መልስ ተሰጥቷል። በሌላ በኩል አቶ ዋሴ እንደሚናገሩት የሶስተኛ ወገን ጣልቃገብነትን እና የፀጥታ ችግርን መንግስት የማስተካከል ግዴታ አለበት። እንደዚህ አይነት ነገር ሲኖር ለዞን መረጃ ይሰጣል። ክልል በየጊዜው ሔዶ ኢንቨስትመንቱ ያለበትን ሁኔታ አረጋግጦ ባለሃብቶቹ ያለባቸው ችግር እንዲቀረፍ ያላቸውን ጥንካሬ እንዲያስቀጥሉ ክፍተታቸውን እንዲሞሉ መንግስትም ያለባቸውን ችግር እንዲፈታ ለዞኑ መረጃ ይልካል። አሁንም ክልሉ ጉብኝቱን የጨረሰ ሲሆን፤ በተመሳሳይ መልኩ ይህ አሁንም ይደረጋል። ነገር ግን እዚህ ላይ ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ግለሰቡ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ደግሞ በግብርና ልማት ኢንቨስትመንት ላይ 50 በመቶ ሊባል በሚችል መልኩ የፀጥታ ችግር ያጋጥማል። ሩቅ አካባቢዎች እንደ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ማጂ እና ሌሎችም አርብቶ አደሮች ባሉባቸው አካባቢዎችም በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ሰፊ ችግር አለ። ነገር ግን ይህ ችግር ቢቻል በወረዳ ካልሆነም በዞን ደረጃ መፈታት እንዳለበት ይታመናል። ከዚህ ውጪ ያለው ወደ ፊት የሚታይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ መሬቱን አስመልክቶ የቀረበው የአርሶ አደሮቹ አቤቱታ መሬቱን እየገበርንበት አርሰን ስንጠቀም ብንቆይም፤ ለኢንቨስተር በሚል ተነጥቀን መልሰን በገዛ መሬታችን እያረስን ለአመራር ምርት ስናካፍል ኖረን አሁን መሬቱን ተነጠቅን የሚል ነው። ባለሀብቱ በበኩሉ እንዳለማ የተሰጠኝ መሬት ላይ ህገወጦች ከወረዳ እና ከቀበሌ አመራር ጋር የጥቅም ትስስር ፈጥረው ወደ ተሰጠኝ መሬት እየገቡ እንዳልሰራ እየከለከሉኝ ፤ግንባታም እያከናወኑ ነው ብለዋል። የዞን እና የክልል የኢንቨስትመንት ቢሮዎች ደግሞ መሬቱ ለባለሃብቱ ሲሰጥ ማንም እንዳልነበረበት ህጋዊ መሆኑን ነገር ግን የኢንቨስትመንት አፈፃፀሙ ደካማ መሆኑን ገልፀዋል። ከክልሉም ሆነ ከዞኑ ያገኘነው ምላሽ እንደሚያመለክተው መሬቱ በኮሚቴ ደረጃ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል ከማለት ውጪ ቁርጥ ያ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። በቦታው ከባለሃብቱ ውጪ አቤቱታ አቅራቢ አርሶ አደሮችንም ሆነ አሁን በካሳ ስም እየሰፈሩ ስላሉት ሰዎች ህጋዊነት የተሰጠ ምላሽ የለም። አበቃን።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013