ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ታላቁ የህልውና ጉዳይ ነው። ሌሎች የኢትዮጵያን እድገት ማየት የማይሹ አካላት የውሃ ሙሌቱን ለማስተጓጎል በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤እያደረጉም ይገኛሉ።ሆኖም ኢትዮጵያውያን ለየትኛውም ጎታች ኃይል ሳይንበረከኩ የግድቡን ሁለተኛ የውሃ ሙሌት ለማከናወን ጫፍ ላይ ደርሰዋል።
እኛ ሰርቶ ማሳየት እንጂ እጅ መስጠት አለመድንም አናውቅምም። በተለይም በማንነታችንና በክብራችን ለመጣ። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ማንንም ቆፍሩልኝ፣ አግዙኝ፣ ሙሉልኝ ሳንል ሁለተኛውን ዙር ለመሙላት ቀናትን ብቻ እየጠበቅን ነው። እናት ከመቀነቷ አባት ከኪሱ ተማሪ ከደብተሩ ቀንሶ ያዋጣበትን ፍሬ የምንቀምስበትም ጊዜ በጣት የሚቆጠር ነው። ለእኛ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚዋጣው ተፈጥሮም ነው። እኛ በጉልበትና በገንዘባችን ግድቡን ስናቆም ፈጣሪ ደግሞ ከሰማይ መና የሆነውን ዝናብ ያወርድልናል። ተፈጥሮ እንድታግዘን ይረዳናል። በዚህም ማንንም ሳንነካ ይልቁንም ከሞትና ከስደት እየታደግናቸው እኛም ቀና እያልን እንቀጥላለን።
ኢትዮጵያን እኔነት ብቻ አይመቻቸውም ባህላቸውም ኑሯቸውም እኛ ነው። የጋራ ሥራ በጋራ ያጸድቃል፤ ያሳድጋል፤ ባለ ሀብት ያደርጋል ብለው የሚያምኑ፤ በተግባር የሚያሳዩም ናቸው። ለዚህም ነው ግብጽንና ሱዳንን በጋራ እንጠቀም ነገር ግን እናንተ ወጪ አይኑርባችሁ ያልነው። እነርሱ ግን አይ አትሰሩም ፤አትበሉም፤አታድጉም ሲሉን ቆይተዋል። በራሳችን ሀብት መጠቀም አትችሉምም ይሉናል። እንቢ ካላችሁ ሃያላኑ ያስገድዷችኋል አሉን። እንደ አሜሪካ አይነቶችም ጣልቃ ለመግባት ሞከሩ። ግን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነንና ‹‹ እኛ የማንንም ድጋፍም ሆነ ጣልቃ ገብነትም አንፈልግም፤ ስራም ሆነ ጀግንነት በደማችን ያለ ነው›› አልናቸው። ስለድርጊታቸውም ተቃወምናቸው። ተቃውመን አንቀርም እውነታውን በስራና በስኬት ልናሳያቸውም ደፋ ቀና እያልን እንገኛለን።
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ህብረብሔራዊነት፣ ፍቅር፣ ክብር፣ ውበት፣ ባህልና እምነት፣ የኑሮ ፍልስፍና ነው። በዚህም ተስፋውን እውን ለማድረግ የማይቆፍረው ድንጋይ አይኖርም። ምክንያቱም ህዳሴው ታታሪነታቸውን፣ ትጋታቸውን፣ ሰላም ወዳድነታቸውን፣ ምህታታዊ የሆነ ቀለማቸውን በአንድነት የሚያሳዩበት ቀስተ ደመናቸው ነው። የላባቸው ፍሬ ማህተምም ነው። እናም ይህንን የህልውናቸው ኩራት ለማንም አሳልፈው አይሰጡትም። ደማቸውን ገብረውም ቢሆን ስኬቱን ያያሉ እንጂ።
ግዙፉ ፕሮጀክታችን ዓለምን፣ ፖለቲካን፣ ቱሪዝም፣ ኢኮኖሚን፣ ህልውናን፣ ታሪክን፣ የተፈጥሮ ማህበራዊ ገጽታንና ሌሎች ምጡቅ ጉዳዮችን የሚያሳየን እንደሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ያውቃል። ለዚህም ነው ሳይሰስት ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ህይወቱንም ለመስጠት ቁርጠኛ የሆነው። እኔ ባልደርስ ለልጄ በሚል ስሜት በመጀመር ዛሬ ላይ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት ላይ ተደርሷል። መጋቢት 24 /2003 የህዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ቀን ነው። እንደውም ያቺ ወርሀ መጋቢት 24ኛዋ ቀን 2003 ዓ.ም ልዩ ቀኑ እንደሆነች አስቦ እድገቱን በዓመታት እየለካ ተስፋውን እያለመለመ ነገን አሻግሮ የሚያይባት ቀን ሆኗል።
የህዳሴ ግድብ ህዝቡ በዛሬ ችግሮቹ በነገ መልካም እድሎቹ መካከል ሆኖ እንዲጓዝና ተስፋውን እንዲያገኝ፣ ቁጭቱን እንዲፈታ የተቸረችውም አድርጎ ይወስዳታል። ውበትን፣ ሰላምን፣ የጠነከረ ህብረብሔራዊነቱን የሚያይባት መልካም ምሳሌያዊ ንግግሮቹን የሚተገብርባት ልዩ የአምላክ ስጦታ አድርጎ ይመለከተዋል።በአጠቃላይ የክልከላው ደመና የተገፈፈበትና የጽናትና የቁርጠኝነት አርማ ያረፈበት የተስፋ ማህደር ነው።
ህዳሴው የስጋት አይነጥላን የገፈፈ፣ እንችላለንን ያሳየ፣ ወደፊት መገስገስን በቁርጠኝነት ያጎናጸፈ ነው። ኢትዮጵያንን በአንድነት ማማ ላይ የሚያስቀምጥም ነው። ከሁሉም በላይ ብዙ ገጸበረከቶች በተስፋ አሻግረን እንድናይ ያደረገም ነው። ለአብነት ትበታተናለች፣ አታደርገውም፣ እርስ በእርስ እየተባላች መልማት አትችልም፣ ችግር መቷታል ወዘተ የሚሉትን ድባቅ የሚመታ መሆኑ አንዱ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ፣ ህዝባዊነትን፣ ሉአላዊነትን፣ የእውቀት ገበያን፣ የልማት አርበኝነትን ማጎናጸፉም ሌላው ገጸ በረከቱ ነው።
የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማለት የህዝብ መዝሙር ነው። የኑሮ ከፍታን መለኪያና መሸጋገሪያ መልህቅ ነው። መሶባችን፣ ጤናችን፣ ጎተራ፣ ተግባቦት፣ የስልጣኔ ማሳለጫችን ልዩ ጥበብና ገንዘባችን ነው። ታዲያ ይህንን ሀብት ማን የማይጠብቀው ኢትዮጵያዊ አለ?ማንስ የማይንከባከበው አካል አለ? እንደ እኔ እምነት ህይወቱን ሁሉ ለመሰዋት ወደኋላ የሚል ይኖራል ብዬ አልገምትም። ወርቅ ተፈትኖ ሀይሉን እንደሚያሳይና ክብሩን እንደሚመልስ ሁሉ ማንም ጫና ቢያሳርፍም እኛ ከሳት ውስጥ እንደሚወጣና ክብሩን እንደሚያስመልሰው ወርቅ በመሆናችን ጠላትን አትልፋ ማለት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ስኬቱ የእኛ እንጂ የእርሱ መቼም አይሆንም።
ኢትዮጵያ ፍትሀዊ ተጠቃሚነቷን የምታረጋግጠው ማንንም ጠይቃ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ከ86 በመቶ በላይ ከጉያዋ የምታመነጭ፣ ሀብትነቱ የራሷ የሆነ አገር ነች። ከዚያም ውጪ ቢሆን ማንንም አግዙኝ አላለችም። ይሁን እንጂ በፍቅር ትረታለችና እዚህ ግባ የማይባል ድርሻ ያላቸውን የታችኛው ተፋሰስ አገራት እኔ ብሰራውም ፍትሀዊነት ያስፈልጋልና እናንተም እንድትጎዱ አልፈልግም በማለት ላይ ትገኛች። ስለዚህም አብረን እንጠቀመው አለቻቸው። እነርሱ ግን ልባችሁም፣ አፋችሁም፣ ጥቅማችሁም የእኛ ብቻ ይሁን ከማለት አልፈው የዓለም አቀፍ የድንበር ዘለል ወንዞች ማዕቀፍን በመጋፋት ይህንን አታድርጉ ማለታቸውን ቀጥለዋል። ለዚህ ደግሞ አገራቱ በምክንያታዊነት፣ በፍትሀዊነት መጠቀም የሚለውን ነገር ቢያውቁትም መተግበር አይፈልጉም።
ኢትዮጵያ እየሰራች፣ እየመራች፣ አዲስ ተስፋዋን እያለመለመች ትገኛለች። ይህንን በበረታ እጅ ደግሞ ዜጋው ካለው ቀንሶ እየደገፈ ነው። ምክንያታዊ መሆንንም በተግባር ለዓለም እያስረዳ ነው። የተፈጥሮ ሀብት እጅ ላይ ያለ ወርቅ እንደማለት እንደሆነም ዛሬ እያሳየ ነው፤ ነገም ይቀጥላል። ተስፋችን እውን ሆኖም ነገ ወደፊት እንራመዳለን።በዚህ ሀይላችን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነጋችንንም እንሰራለን። እንደቀደመው ታሪካችን ሌሎችንም እናስጠልላለን፤ ከወደቁበት እናነሳለን። ለዚህ ደግሞ ሀይላችን አንድነታችን ነውና ሁልጊዜም ለሀገራችን ክብር በጋራ እንቁም። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013