በአገራችን የምርጫ ታሪክ እንደዚህ ምርጫ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ከሌሊቱ 11 እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ቁር፣ ሀሩርና ዝናብ ሳይበግረው የተሳተፈበት ነጻ ፣ ሰላማዊ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲዊ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም ቢባል እውነት ነው ። ይህ ተስፋ ሰጭ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የለውጥ ኃይሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት ያሳየው ቁርጠኝነት እና የቅድመ ምርጫ ሒደቱ ነጻና ፍትሐዊ መሆኑ የላቀ አስተዋፅዖ አለው ። ድህረ ምርጫውን ሰላማዊ አድርጎታል ።
ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ ተቋማዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በአብነት እናንሳ ። የምርጫና የፖለቲካ ድርጅቶች አዋጅ ፣ የጸረ ሽብር ማሻሻያ አዋጅ ፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ ማሻሻያ አዋጅ፣ ወዘተረፈ መውጣትና መሻሻል ፖለቲካዊ ምህዳሩን በማስፋቱ ቅድመና ድህረ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የማይተካ ሚና ተጫውቷል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛነት መቋቋሙና ሰብሳቢዋን ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ ወገንተኝነት በሌላቸው ቋሚ የቦርድ አባላትና የሥራ መሪዎች መደራጀቱና መመራቱ ምርጫው ተአማኒ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ። ገዥው ፓርቲ የቦርዱን ነጻነትና ገለልተኝነት ከማክበር አልፎ ለቀደሙት አምስት ምርጫዎች ተመድቦ ከነበረ አጠቃላይ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ በጀት በመመደብ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲደራጅ ከማድረጉ ባሻገር ለክትትልና ቁጥጥር አመች በሆኑ የምርጫ ቁሳቁሶች እንዲታገዝ አስችሏል ። በዳኝነት ፣ በሰብዓዊ መብት ፣ በእንባ ጠባቂ ፣ በደህንነትና በጸጥታ ተቋማት የተከናወኑ የአሰራርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች አስተዋፅዖም እጅግ ከፍ ያለ ነው ።በዚህም ወደ 38 ሚሊዮን የሚጠጉ መራጮች የተመዘገቡበት እና ለዚህ የተጠጋ መራጭ ድምጽ የሰጠበት ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ተችሏል ። የአገር ውስጥና የውጭ ሟርተኞችን አንገት ያስደፋ ምርጫ ለዛውም በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከችግኝ ተከላ ጋር ተከናውኗል ። ለኢትዮጵያ ተደግሶላት የነበረ ቀውስና ግጭት መክኖ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ወጥታለች ። ለዚህ አንጸባራቂ ድል ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትውልድም ሆነ ታሪክ ሲያወሳቸውና ሲዘክራቸው ይኖራል ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከፍታውን አስመስክሯል ።
ምርጫው ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ስለመሆኑ የዓለማቀፍ ሚዲያዎችና የምዕራባውያን ምርጫ ታዛቢዎች ቡራኬና ይሁንታ አያስፈልገውም ። ሆኖም ምዕራባውያን እውነት ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መረጋገጥ የቆሙ ቢሆን ኖሮ ለዚህ ምርጫ ቆመው ባጨበጨቡ ነበር ። እማውና አበው ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ እንዳሉት ለነጩ የአደባባይ እውነት እንኳ እውቅና መስጠት አልፈለጉም ። እውነታውን ሳይበርዙና ሳይከልሱ ለመናገር አንደበታቸው ተሳስሯል ። በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ ዓላማ አቀፉ ሚዲያው ምርጫውን ከተንሸዋረረና ከራሱ እይታ አንጻር እንጂ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሀቅ አኳያ አልዘገበውም። ለሁሉም ሚዲያዎች ተመሳሳይ የዜና ቅጅ/script/ተጽፎ የተሰጣቸው እስኪመስል አልጀዚራ ፣ ቢቢሲ ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ ፣ አሶሼትድ ፕሬስ ፣ ኒውዮርክ ታይምስ ፣ ዋሽንግተን ፖስት ፣ ወዘተረፈ ያለ ልዩነት ቃል በቃል ምርጫው አወዛጋቢ እንደሆነ ዘግበዋል ። 20 በመቶ የሆነው መራጭ እንዳልተሳተፈበት ፣ የትግራይ ክልል እንደተገለለ ፣ አብላጫውን የኦሮሞ ሕዝብ የሚወክሉ የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ/ኦፌኮ/እና የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር/ኦነግ/አለመሳተፋቸውን ፣ በትግራይ ከ350ሺህ በላይ ሕዝብ ለከፋ ረሀብ መጋለጡን ፣ ከ2ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ መኖሩን ፣ ወዘተረፈ በመዘገብ የራሱን አማራጭ እውነት/alternative fact/ ፣ የተዛባና ሀሰተኛ መረጃ ሲሰልቅ ውሏል። ምንም እንኳ እውነት አንድ እውነት እንጅ አማራጭ እውነት ባይኖረውም ። ኦነግ በምርጫ ያልተሳተፈው በውስጡ የተፈጠረውን ውዝግብ ሳይፈታ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ ስላለፈው መሆኑን ኦፌኮም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በምርጫው እንዲሳተፍ ቢለምኑት በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ አባሎቼ ካልተፈቱ አልሳተፍም ማለቱን ግን አንዳቸውም መዘገብ አልፈለጉም ።
ሆኖም የለውጡን ፣ የሕልውናና የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ትርክት እንደነጠቁት ወይም እንደጠለፉት ሁሉ የምርጫውን ተረክ ለመቀልበስ ያደረጉት ጥረት አልሳካ ቢላቸው ምርጫው ላይ ጥላ ለመጣል በትግራይ ክልል በገበያ ቦታ ላይ በተፈጸመ የአውሮፕላን ጥቃት በርካታ ንጹሐን ተጎዱ የሚል መረጃ ካለፈው እሮብ ጀምሮ ማራገብ ጀምረዋል ። በተለይ አልጀዚራ በሰበር ዜና ከመዘገብ ባሻገር የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ጠላት የሆነውንና የአሸባሪው ህወሓትን ጦፈኛ ማርቲን ፕላውት ሀሰተኛ መረጃ በማጃመል የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡን ትኩረቱ ለማስቀየስ ጥረት አድርጓል ። በነገራችን ላይ ይሄን ዜና አልጀዚራም ሆነ ቢቢሲና ሌሎች ሚዲያዎች ከመቀባበላቸው በፊት ቀድሞ በቲዊተር ገጹ የለጠፈው ይኸው የአሸባሪው ህወሓት ምንደኛና ቤተኛ ማርቲን ፕላውት ነው ። ይህ አስቀድሞ የተቀነባበረ ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣል ። የመከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበነጋው ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓም በሰጡት መግለጫ መንግስት ጥቃቱን የፈጸመው ምግበ የሚባል ጀኔራል የሚመራው የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ የ1980 ዓም የ”ሀውዜን ጭፍጨፋ” ሊዘክር መሰባሰቡን አረጋግጦና የአሸባሪው ህወሓትን ጭፍራ ነጥሎ ዒላማ በማድረግ ነው ።
ከዛሬ 33 ዓመታት በፊት ታጋዩ ትግራይ ነጻ ከወጣች አሰናብቱን የሚል ጥያቄ ያነሳና አልዋጋም ይላል ። በሰማዕታት አጥንት በአደይ ትግራይ ቢለመን አሻፈረኝ ይላል ። በዚህ የታጋዩ ውሳኔ የተደናገጠው አመራር በዝግ ይዶልትና አረመኔያዊ እቅድ ይነድፋል ። ህወሓት ጥርሱን በነቀለበት ሴራ ፤ በሀውዜን የገበያ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጋይ በስፍራው እየተንቀሳቀሰ ነው የሚል የተሳሳተ መረጃ ለደርግ እንዲደርሰው ያደርጋል ። የተወሰኑ የታጠቁ ታጋዮች በገበያተኛው መሀል ውርውር እንዲሉም ይተውናል ። ህወሓት ይህን አሳሳች መልዕክት ይልክና ካሜራውን ደቅኖ የአውሮፕላን ድብደባውን ይጠባበቃል ። ደርግም የደረሰውን አሳሳች መረጃ መሠረት አድርጎ የአየር ድብደባ አደረገ ። በዚህም በርካታ ንጹሐን ተገደሉ ። ህወሓትም እንደለመደው የአየር ድብደባውን ቀርጾ ለዓለም አሰራጨ ። ትግራይ ነጻ ከወጣ ለምን እንዋጋለን ላሉ ታጋዮቹም ይሄን የተቀነባበረ ፊልም እያሳየ ትግራይ ነጻ ብትወጣም ደርግ ሙሉ በሙሉ ካልተደመሰሰ ሌላ ጊዜም እንዲህ ሕዝባችንን ይጨፈጭፋል በማለት አሳመናቸው ። እነሱም እስከ ደርግ ውድቀት ለመዋጋት ተስማሙ ። በዚህ ድራማ ተጨማሪ 30ሺህ አዲስ ምልምሎችን ለማሰባሰብ ቻለ ። ባለፈው እሮብ የደገመው ይሄንኑ የጨረተ ድራማውን ነው ። የትግራዋይን ልብ ለማሸፈትና የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡና ሚዲያው ትኩረቱን በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ እንዳያደርግ የተሸረበ ሴራ ። በዚህ ቀሽምና አረመኔያዊ ድራማ የእነ አልጀዚራን ሽፋን እና የእነ አሜሪካን መግለጫ አግኝቷል ። ህወሓት ለፖለቲካዊ ጥቅሙ ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ ዛሬም አረጋግጦልናል ።
እውነት በአሜሪካ የሚዘወረው ምዕራባዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የሕግ የበላይነት እሴቶቹ ቢሆን ኖሮ ለ30 ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩን ጠርቅሞ ፣ ዴሞክራሲን አመንምኖ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሲያፍን ፣ ጋዜጠኞችን ሲያስርና ሲያሳድድ ለኖረ ፣ ከ200 በላይ ጦማሮችንና ሌሎች ሚዲያዎችን ላገደ ፣ እንደ ቪኦኤና ኢሳት ያሉ ሚዲያዎችን ከድሀ ጉሮሮ የተቀማ በርካታ ሚሊዮን ዶላር አፍስሶ ከአየር ላይ የማውረጃ መሳሪያ/jammers /አስገብቶ ከስርጭት ለማውረድ ጥረት ያደረገ፣ ሒውማን ራይትስ ዋች በአንድ ወቅት እንደገለጸው ከ45ሺህ በላይ የፖለቲካ እስረኞችን ላማቀቀና ላጎረ ፣ አምስት የይስሙላ መረጣዎችን ላደረገ ፣ በከፋ ሙስና ለተዘፈቀ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ መከታና አለኝታ ባልሆነ ። በብድርና በእርዳታ የፈላጭ ቆራጩን ህወሓት ክንድ በማፈርጠም ኢትዮጵያውያን ለሶስት አስርተ ዓመታት በአፈና እንዲማቅቁ ባላደረገ ። በአደባባይ ከሚዘምሩላቸው እሴቶችና ዴሞክራሲ ይልቅ ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙት ምዕራባውያን በቀጣናው ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ውክልና ሰጥተውት ለነበረው ህወሓት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍና ሽፋን ይሰጡት ነበር ። ብቻውን ሩጦ መቶ በመቶ አሸነፍሁ ያለውን ምርጫ 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ነበር ሲሉ ትንሽ እንኳ አልቀፈፋቸውም ነበር ። የሚያሳዝነው አሜሪካ ይህን የምታደርገው እውነታው ሌላ መሆኑን እያወቀች ነበር ። የጁሊያን አሳንጁ ዊኪሊክስ በአደባባይ ባሰጣው ሚስጥራዊ የሲአይኤ መረጃ ህወሓት መሩ አገዛዝ ግፈኛና ዘራፊ እንደነበር የሚገልጹ መረጃዎች ከአዲስ አበባው ኤምባሲው በየቀኑ ይላክለት ነበር ። ሆኖም አይኔን ግንባር ያርገው ብላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ከግፈኛው ህወሓት ጎን መቆምን ነበር የመረጠው ። ከኦባማ አስተዳደር እንደ ሱዛን ራይስ ያሉት ደግሞ እፉኝቱን መለስ እስከማምለክ ደርሰው ነበር። ይች ሴቲዮ ነች ዛሬም በባይደን አስተዳደር በያዘችው ከፍተኛ ስልጣን ለህወሓት እርዝራዥ ጠበቃ በመሆን አሜሪካ ዛሬ በሀገራችን ላይ ለምታራምደው የተሳሳተ አቋም የዳረገችን። ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች እንደ ወገባቸው ቅማል ጠምደው ይዘውናል። ሰሞነኛው ጠንጋራ የምርጫ ዘገባቸው የዚህ ቅርሻቸው አካል ነው ። የህወሓት ርዝራዥ ይህን እድል በአግባቡ ተጠቅሞበታል። በተለይ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ታላቅ ክህደት ሲከሽፍ ዕቅድ “ለ”ን/plan B/ይዞ ብቅ ብሏል ። እሱም በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ እስከአፍንጫው በታጠቀ ጭፍራው የተከፈተው አጠልሽ አውደ ግንባር ነው ። ለዚህ እኩይ ዓላማው የምዕራባውያንን ቀልብ በቀላሉ የሚስቡ እንደ አስገድዶ መድፈር ፣ ረሀብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም፣ የንጹሐንን ግድያ ፣ የአናሳ ተጠቂ ስነልቦናንና ሌሎችን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ተጠቅሟል።
እንደ መውጫ ለጊዜውም ቢሆን አመነስቲ ኢንተርናሽናልን ፣ ሒውማን ራይትስ ዋችን ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ አገናኝን/ዩኤንኦቻ/ ፣ የባይደንን አስተዳደር ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያውን ፣ ወዘተረፈ በማሳሳት ግዳይ ጥለዋል ። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን እንድንቀር አድርገዋል ። ውሸት እውነትን ፣ ጨለማ ብርሃንን ረቷል ። ደካማው የኮሙኒኬሽንና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራችን ውድ ዋጋ አስከፍሎናል ። ሉዓላዊነታችን ተደፍሯል ። በፈተና ላይ የነበረው ለውጥ ጠልሽቷል ። ዙሪያችንን ከበው አሰፍስፈው ለውጡን ደጅ ቆመው ለሚጠብቁን እንደ ግብጽ ላሉ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል ። እውነት ለመናገር እንደ አገር ወዳድ ዜጋ ያበግናል ።
ሆኖም ይህን ሁሉ አሚከላና ኩርችት ፤ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ፈተናና ጫና ተቋቁመን በአገሪቱ ታሪክ ፋና ወጊ የሆነ ነጻ ፣ ሰላማዊ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ማካሄድ ችለናል ። የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ሕብረት ለምርጫ ፤ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እና ሌሎች ታዛቢዎች የመሠከሩለት ምርጫ በማካሄድ አሰፍስፈው ሲጠብቁ የነበሩ ጠላቶቻችን አሳፍረናል ። ሆኖም ደካማው የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራችን ዛሬም እጀ ሰባራ እንዳያደርገን አበክረን መስራት አለብን በመሸነፍ ማሸነፍ ፣ በማሸነፍ መሸነፍ አለ ! ከወጭ ቀሪ ኢትዮጵያ አትርፋለች ! አሸንፍለች !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም