ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቋል፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሰጠ ሲሆን በተለይ ወጣቱ ክፍል የነቃ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ወጣቱ ከመራጭነት ባለፈ በመታዘብና በሌሎች ስራዎች ላይ ሳይቀር ተሳትፏል፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከየምርጫ ክልሎች ተሰብስበው የሚመጡ ድምፆችን በመደመር ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ስራ ይሰራል፡፡ የምርጫ ውጤት ከተገለፀ በኋላ በምርጫው የተወዳደሩ ፓርቲዎች ውጤቱን በጸጋ መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ የሚደግፈው ፓርቲ ድምፅ አገኘም አላገኘ በሰላማዊ ሁኔታ ስሜቱን ሊገልፅ እንደሚገባ የዝግጅት ክፍሉ ያነጋገራቸው ወጣቶች ይናገራሉ፡፡
ወጣት ደመላሽ ይሁነኝ አራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣቱን በመግለፅ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ይናገራል፡፡ ወጣቱ ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ ከመምረጥ ባለፈ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በመሳተፉ በመዲናዋ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር ምርጫው መካሄዱን ያመለክታል፡፡
እንደ ወጣት ደመላሽ አባባል ከሆነ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ለወጣቱ የተደረጉት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ወጣቱ በታዛቢነትና በተመራጭነት የተሳተፈባቸው ቦታዎች በመኖራቸው ለአገሪቱ ዴሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለምርጫው ወጣቱን ህብረተሰብ ማሳተፋቸው ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ የምርጫ ውጤት ከተነገረ በኋላ ሁሉም ወጣት በሰከነ መንገድ ውጤቱን ሊቀበል ይገባል፡፡
ወጣት ሰላማዊት አግዘው ደግሞ በምርጫው ከተወዳደሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአንዱ ታዛቢ ነበረች፡፡ እሷ እንደምትናገረው፤ በምርጫው ወቅት መዘግየቶች ከመፈጠራቸው ውጪ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡ በተለይ እሷ ታዛቢ በነበረችበት ምርጫ ጣቢያ ወጣቱ ያለመሰልቸት እስከ ማታ ድረስ ተራውን ጠብቆ ሲመርጥ ነበር፡፡ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ብዙ ነገሮች ተሰርተዋል፡፡ በተለይ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ ወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት በተደጋጋሚ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እያንዳንዱ ሰው ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ሰላም የሚፈጥሩ ነገሮች ላይ መወያየቱ ውጤት አምጥቷል፡፡
የምርጫው ውጤት ከተነገረ በኋላ ወጣቱ በሰከነ መንገድ ውጤቱን ሊቀበል እንደሚገባውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸው በሚሰጧቸው መግለጫዎች ወደ ግጭት እንዳይገቡ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ወጣት ሰላማዊት ትናገራለች፡፡ በምርጫውም ውጤት በአሸናፊነት ህዝብን የሚወክሉ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሽግግር እንዲሆን ሊሰሩ እንደሚገባም ታስረዳለች፡፡
ሌላኛዋ በአምስት ኪሎ አካባቢ ያገኘናት ወጣት ሄለን ዳምጠው እንደምትናገረው፤ በተለያዩ አገራት ውስጥ በተደረጉ ምርጫዎች ውጤትን ባለመቀበል በወጣቱ ሀይል ብጥብጥና ሁከቶች ይነሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምርጫ በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ አገር የሚያፈርሱትም የሚቀጥሉትም ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቱ እየጎለመሰ ሲሄድ አገር ወደ መምራት የሚሸጋገሩ በመሆናቸው ከማንም በላይ ስለ ሰላም ማውራት ያለባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ ግጭቶች በተነሱባቸው አካባቢዎች ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶች ምክንያታዊ ያልሆኑና በአግባቡ ማገናዘብ የማይችሉ ናቸው፡፡ ምክንያታዊ ለመሆንና የፖለቲካ ሀሳቦችን ለመረዳት የግንዛቤ ማስጨበጫዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ አብዛኛው ወጣት የፖለቲካ ሀሳቦችን ሳይረዳ የሚነዳበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ የፖለቲካ መሪዎች የሚከተሉትን ርዕዮተ አለም ማወቅ የግድ ይላል፡፡ ሁሉም ብሄሩን ሳይሆን አንድ ያደረገውን አገራዊ ማንነት ብቻ በመመልከት ከእርስ በርስ ግጭት መቆጠብ አለበት፡፡
እንደ ወጣት ሄለን ገለፃ፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ወጣቱም በመምረጥና በመመረጥ እንዲሁም በመታዘብ የላቀ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በቀጣይ ሰላማዊ ሀኔታ እንዲፈጠር ወጣቱ በተደራጀ መንገድ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድም በእጁ የሰበሰባቸውን ውጤቶች በተደራጀ መንገድ ለህብረተሰቡ በየወቅቱ ሊያሳውቅ ይገባል፡፡ ሰላማዊ አገርን ለመፍጠር ወጣቱን ያቀፈ ስራ ማከናወን ከፀጥታው ሀይል የሚጠበቅ ነው፡፡
ወጣት ከፈለኝ ተስፋ እንደሚናገረው ደግሞ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች ሲራዘም ቆይቶ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም
ተከናውኗል፡፡ ምርጫው ያለምንም ፀጥታ ችግር የተጠናቀቀ ሲሆን የምርጫ ውጤቶችም በየጣቢያው እየተለጠፉ ናቸው፡፡ በምርጫው ወጣቱ በነቃ መንገድ ተሳትፎ በማድረጉ በቀጣይ በአገሪቱ ላይ ለውጦች እንደሚመጡ አመላካች ነው፡፡ ነገር ግን በክፍለ አገራት አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚኖራቸውን ቅሬታ በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ግንዛቤ መሰጠት አለበት፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ ወጣት ይሁን መሀመድ እንደሚናገረው፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት ማህበሩ ያለው ሚና ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ የሚኖር ነው፡፡ በቅድመ ምርጫ ወቅት መራጮችን የመቀስቀስ፣ ስለምርጫ ስልጠና መስጠት፣ መራጮች ካርድ እንዲያወጡ ማድረግ፣ የክርክር መድረኮችን ማመቻቸት፣ መረጃዎችን መስጠት የተጓደሉ ክፍተቶች ሲታዩ ከምርጫ ቦርድና ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንዲስተካከሉ የማድረግ ስራ ተከናወናል፡፡
ወደ ወጣቱ ሲመጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቱ ላይ የያዙትን አላማና እቅድ ወጣቱ ተረድቶች በፍላጎትና የእኔ የሚለውን ሰው ሳይሆን መምረጥ የሚገባውን፤ በትክክል የወጣቱን ችግር ሊፈታ የሚችል አላማና እቅድ ያለውን ፓርቲ ወይም ተወካይ መምረጥ ይገባል፡፡
ይህን ለመረዳት ፓርቲዎች በራሳቸው መንገድ የሚያቀርቡት እንዳለ ሆኖ ማህበሩ በሚያመቻቸው መድረኮች ፓርቲዎቹ በሚያደርጉት ክርክር እንዲወሰን ይደረጋል፡፡ በክርክሩ አጀንዳዎችን በመስጠት በአጀንዳው ዙሪያ ተዘጋጅተው ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ከወጣቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ፓርቲዎቹ የሚመልሱትን በመመልከት ወጣቱ ይጠቅመኛል የሚለውን በነፃነት እንዲመርጥ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የመኪና ላይ ቅስቀሳ በማድረግ የመራጭነት ካርድ እንዲወጣ ወጣት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ዴሞክራሲዊ መብቱን ተጠቅሞ ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥ ለማድረግ ማህበሩ እየሰራ መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ያስረዳል፡፡
እንደ ወጣት ይሁን አባባል፤ በምርጫው እለት ከምርጫ ቦርድ ከሚሰጥ ፈቃድ ጋር በማያያዝ ማህበሩ የታዛቢነትን ስራ ይሰራል፡፡ ምርጫው በትክክል መራጮች በተገኙበት ሁኔታ መፈፀሙን፣ መራጮች በነፃነት እየመረጡ ነው ወይ፣ የምርጫ ስርዓቱ አልተስተጓጎለም ወይ፣ የመራጮች የምርጫ ወረቀት በትክክል ገብቷል ወይ? የሚለው ጉዳይ በአግባቡ ይታይና ምሽት ላይ ደግሞ የምርጫ ወረቀት ቆጠራ ሲካሄድ በአግባቡ መከናወኑን ይታዘባል፡፡ ይህን የሚያደርገው የአዲስ አበባን ወጣቶች ወክሎ ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች ችግሮች ካሉ ችግሮቹ እንዲታረሙ በሪፖርት ወይም በመገናኛ ብዙሀን በኩል የማሳወቅ ስራ ያከናውናል፡፡ ትክክለኛው ነገር ከተከናወነ ያለውን ሁኔታ ያሳውቃል፡፡ ይህን በማድረግ አገሪቱ ወደተሻለ ደረጃ እንድታድግ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
ሌላኛው ስራ ከምርጫ ውጤት መገለፅ በኋላ ወጣቱ እንደ ግለሰብ የመረጠው ፓርቲ ካላሸነፈ ምርጫው ተጭበርብሯል፣ ተስተጓጉሏል ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ የምርጫ መጭበርበር በሚል ችግር እንዳይፈጠር የማህበሩ ታዛቢዎች በምርጫው ወቅት የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ እንዲሁም ሌሎች ሲቪክ ተቋማት በታዛቢነት ስራቸው ላይ አትኩሮት ሊሰጡ ይገባል፡፡ እንደ ማህበር ግን በታዛቢነት ወቅት የታዩ ትክክለኛ ነገሮችን ለህዝቡ የማሳወቅ ስራ ያከናውናል፡፡ ከምርጫው ውጤት በኋላ በአግባቡ የታዩትን ነገሮች ለሚመለከተው አካልና ለህዝብ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ የምርጫውን ውጤት ተከትለው የሚመጡ አለመግባባቶችና ግርግሮች ካሉ ደግሞ እንደ ወጣት ተወካይነት ችግሮች የሚፈቱት በውይይት፣ በንግግርና በክርክር እንዲሆኑ ጫና የሚያደርግ መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ያስረዳል፡፡
ወጣቱ ይበጀኛል የሚለውን ሲመርጥ ብሄር፣ በአካባቢ ሰው እንዲሁም በሀይማኖት መመሳሰል በሚሉ ነገሮች ውስጥ ሆኖ እንዳይመርጥ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል፡፡ ወጣቱ እቅድን ወደ ተግባር የሚለውጡና የአገርን አንድነት ሊያስቀጥሉ የሚችሉትን እንዲመርጥ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ወጣት ይሁነኝ ይናገራል፡፡ ምርጫው በተካሄደበት ወቅት ማህበሩ ተዛቢዎች መሰማራታቸውን በመጥቀስ፤ በማንኛውም ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን በመመልመል ምርጫውን እንዲታዘቡ ተደርጓል፡፡
በምርጫው ወቅት ከለሊቱ 10 ሰዓት ጀምረው ወደ ተመደቡበት ምርጫ ጣቢያ እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለምንም እረፍት ግዴታቸውን እንዲወጡ መደረጉን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ብዛት ያላቸው ወጣቶች በአካባቢያቸው ምርጫውን ተከትሎ የሚፈጠሩ የሰላም መደፍረሶችን ቅድመ መከላከል ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበርም ይጠቅሳል፡፡ በእንያንዳንዱ አካባቢ የቴሌግራም ቡድኖችን በመመስረት ችግሮች ሲያጋጥሙ ሪፖርት እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ወጣት ይሁነኝ ይጠቅሳል፡፡
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የህብረተሰቡ ትብብር ተጨምሮበት ይህ ነው የሚባል ችግር አልተከሰተም፡፡ በምርጫው ወቅት አጠቃላይ የወጣቱን እንቅስቃሴ ሊመሰገን የሚገባ ተግባር ማከናወኑን ወጣት ይሁነኝ ያስረዳል፡፡ ይህ የምርጫ ውጤትና ሰላምና መረጋጋት የመጣው በወጣቱ ተሳትፎና ለአገራዊ ሰላምና ፀጥታ ያለውን ተባባሪነት በማሳየቱ ነው፡፡ አገሪቱ ወደ ተሻለ ሁኔታ እንድትሸጋገር ካለው ፍላጎት አንፃር ነው፡፡ የፀጥታው ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ሊጠናቀቅ የቻለው በወጣቱ የላቀ ተሳትፎ መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ያመለክታል፡፡ ወጣቱ ለምርጫ በወጣበት ወቅት ፍላጎቱን ሌሎች ላይ ሳይጭን የሚፈልገውንና ይጠቅመኛል የሚለውን ለመምረጥ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ለመታዘብ መቻሉን ወጣት ይሁነኝ ይጠቅሳል፡፡ በምርጫ ጣቢዎች የሚሰጡ ትምህርቶችን በአግባቡ በመስማት ለምርጫው ስኬት የድርሻውን ተወጥቷል፡፡
ከምርጫ በኋላ ያለው ስራ የሚለካው ቀድሞ በተሰራው ስራ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ቀደም ተብሎ የተሰራው ስራ በምርጫና ከምርጫ በኋላ በሚኖረው ላይ አሻራ አለው፡፡ ከምርጫው ቀናት በኋላ ምንም አይነት ችግሮች የሉም፡፡ በየምርጫ ጣቢያው ውጤቶች እየተለጠፉ ነው፡፡ በምርጫው ውጤቶች እስካሁንም ምንም አይነት ክርክርና ጭቅጭቆች
የሉም፡፡ ውጤቶችን ወጣቱ በአንድ ቦታ ተሰብስቦ በሰላማዊ መንገድ እየተመለከተ መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ይናገራል፡፡ በምርጫው ውጤት ቅሬታ ያላቸው ሰዎች የሚመለከተውን አካላል በሰላማዊ መንገድ ማናገር ይችላሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች መቀጠላቸው ለወጣቱ ሰላማዊነት አስተዋፅኦ እንዳለው ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሸናፊ ተብሎ የሚገለፀው ፓርቲ ቀድሞ ሀሳብና እቅዱን አቅርቦ መስራት የሚችለው ሰላም ሲኖር መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ይናገራል፡፡ ሰላም ሊመጣ የሚችለው የምርጫ ውጤትን ከመቀበልና ካለመቀበል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል ያለበት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የነሱም ደጋፊ መቀበል እንዳለበት ወጣት ይሁነኝ ያስረዳል፡፡ መንግስት፣ የፀጥታ አካላት፣ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ህብረተሰቦች በአንድ መስራት ሲችሉ ሰላምና ፀጥታ ሊመጣ እንደሚችል ያመለክታል፡፡ መራጩና ተወዳዳሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና የተወጡ ሲሆን አሁን የሚቀረው የምርጫ ቦርድና የታዛቢዎች ስራ ሲሆን ታዛቢዎች ያዩትንና ያስተዋሉትን ነገር በቀጣይ ሪፖርት
ያቀርባሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ እጁ ላይ ያሉ ውጤቶችን ይፋ ማድረግ አለበት፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫው ውጤት ላይ ቅሬታ ካላቸው በህግ አግባብ የሚጠይቁበትን ነገር ማመቻቸት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013