የኢትዮጵያን የበፊት ገናናት እና አሁን ላይ ደግሞ ለወደፊት እድገት የምታደርገውን መምዘግዘግ አምነው መቀበል የማይፈልጉና እውነታውን በጥቁር ቀለም እንዳይታወቅ አደርገው ለማጥፋት እና ለማጠልሸት ለሚሹ ኃይሎች የኢትዮጵያ ህዝብ መልስ ሰጥቷል፡፡ በውስጥም በውጭም ያሉ ሃይላት ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሲያሟርቱት የነበረውን ሟርት ኢትዮጵያኖች በተለመደ ጨዋነት በዜሮ አባዝተው የክፋት ሟርታቸውን “የቀበሮ ደስታ” አድርገውታል ፡፡
ከምርጫው በፊት በነበሩ መድረኮች ሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎች ምርጫው ከሀገራቸው መብለጥ እንደማይችል አበክረው በከፍተኛ ወኔ ሰሩ፡፡ የምርጫውም ቀን
ደረሰ፡፡ በተግባርም የገቡትን ቃል ፈጸሙ፡፡ ስለኢትዮጰያ ክፉ ክፉን ሲያሟርቱ የነበሩ ሃሎች ያሰቡት ሳያሳኩ
ቀሩ፡፡ ቆሽታቸው አረረ፡፡ ኢትዮጵያኖችን ጠላትን እንዴት አድርገው ማሳፈር ያውቁበት ነበር ዛሬም ደገሙት፡፡
ኢትዮጵያኖች ሃገራቸው በጭንቅ ምጥ ስትያዝ ሃገራቸውን ምጥ አብረው ይጋሩታል፡፡ ምጡንም በጥበብ እና በጸሎት ከምጥነት ወደ ደስታነት ይቀይሩታል፡፡ ይህ ዝም ብሎ ወሬ አይደለም ሺህ ጊዜ በተግባር ተፈትኖ የታየ እንጂ፡፡ ለዚህ ማስረጃነት አንድ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ማየቱ በቂ ነው፡፡ አሸባሪው ህወሓት ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ መቀሌ መሸገ፡፡ ያጠፋውን አጥፈቶ በመሸገበት አሸሸ ገዳሜ እያለ ጥጋብ ነፍቶት ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ ሃገር የማየውቀው ምርጫ አደረገ፡፡ አጋፋሪዎቹም በየሚዲያዎቻቸው ዘገቡለት፡፡ መንግስትም በልበሰፊነት ታገሰው፡፡ ይህም አልበቃው ብሎ መከላከያን ወጋ፡፡ ይህ ወቅት ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ምጥ ውስጥ ነበረች፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በጥበብ እና በመተባበር ምጡን በጋራ አማጡት፡፡ በጋራ እና በመተባበር ባማጡት ምጥ እናታቸውን ህወሓት ከተባለ መጥፎ አሸባሪና አጋንንት ማላቀቅ ቻሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጋራ አምጠው በሰሩት ጀብዱ በአለም ላይ የሚገኙ የአሸባሪው ህወሓት ፍርፋሪ ለቃሚ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ማመን አልቻሉም ፡፡ አይመኑ እኛ ግን አድርገነዋል፡፡
“በምጥ ሰዓት ጩኸት ከሌለ ምኑን ምጥ ሆነ” እንዲሉ በአፍሪካ እና በተለያዩ አለማት ምርጫ ሲካሄድ መደባደብ ፣መጯጯህ ፣ መተራመስ የተለመደ ነገር ነው፡፡ በእኛ ሃገርም ከዚህ በፊት የነበሩ ምርጫዎች ላይ የተስተዋለ ነበር፡፡ ላያውም ለውጥ ለማያመጣ ምርጫጫ፡፡ አሁን ላይ ግን ነበር ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአለም ሃገራት ምሳሌ የሆነች ሃገር እንደነበረች ይታወቃል፡፡ አሁንም በምርጫው ስልጣንን በሃይል ጠምዝዘው መውሰድ ለሚፈልጉ፤ በጉልበት የህዝብን ድምጽ መውሰድ የሚያስከትለውን ችግር ከአሸባሪው ህወሓት እንዲማሩ ፣ የህዝብን ድምጽ ማክበር ደግሞ አሁን ያለው ገዥው መንግስት እና ተፎካካሪ ፓሪቲዎች በህዝብ የተሰጣቸውን ክብር በማየት ሌሎች ተሞክሮ እንዲወስዱ የሚያስችል ነው ፡፡
አንድ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይ ለመምረጥ በምርጫ መስጫ ቦታ ላይ ተገኝተው በነበረበት ሰዓት ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት “ከዚህ በፊት የተካሄዱ ምርጫዎች ቀድሞ ውጤቱ ይታወቅ ስለነበር አንደ ምርጫ አይቆጠሩም ፡፡ አሁን ግን ማንኛውም ፓርቲ የምርጫው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መተንበይ ስለማይችል እኛም የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ፍጹም በሆነ ጨዋነት የህዝቡን ድምጽ አክብረው መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምርጫው በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቅ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችል በጉልበቱ የማይችል ደግሞ በጾለቱ ሀገሩን ይጠብቅ ፡፡ “ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ጨዋነት የተሞላበት አስተያየት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ለዚያውም በምርጫ ቀን የሚገርም ነው ፡፡
ሌኛዋ ተወዳዳሪ አክለውም የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የህዝብን ድምጽ ለመቀበል ዝጉጁ መሆናቸውን እና የህዝብ ድምጽ ከተከበረ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት የምታሸንፈው ሲሉ ተሰሙ ፡፡ በምርጫ ቀን !!
አሁን ሙት ወቃሽ አያድርገኝ እና ማን ነው በወያኔ ዘመን ይህን የሚያደርግ ተፎካካሪ ፓርቲ? በፍጹም የማታይሰብ ነው ፡፡
ሌላው በ2013 ዓ.ም ምርጫ የታየው ክስተት እና የኢትዮጵያኖችን የጨዋነት ጥግ ያሳው የመራጮች ትዕግስት እና እስከ ሌሊት ድረስ ጠብቆ መምረጡ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች እንኳንስ ሌሊት ተመርጦ ይቅር እና ቀንም ተመርጦ ስርቆቱ እና ማጭበርበሩ ስንት እና ስንት ችግር ይዞብን መጥቶ ነበር፡፡ በ2013 ዓ.ም ግን ይህ ክስተት ሊፈጠር አልቻለም ፡፡ ነበር ሆኖ ቀረ ፡፡ ይህ ሁነት ደግሞ ይበልጡኑ ፣ሟርተኞችን ያበሳጨ ሆነ ፡፡
ሌላኛው በትናንትናው ዕለት የሟርተኞችን ብስጭት ያየሁበት ደግሞ ሟርተኞች በሚዲያዎቻቸው ትንሽም ስለኢትዮጵያ ምርጫ ሰላም እና ፍትሃዊነት ለመዘገብ አለመፈለጋቸውን ነው ፡፡ ምን መሰላችሁ ሟርተኞች በኢትዮጵያ ትንሽ ኮሽ ስትል ቀጥለው ቀጣጥለው ፤ጨምረው ጨማምረው በፕሮፖጋንዳ መፍጫ ወፍጮዎቻቸው እየሸረከቱ አለም ጉድ በል እያሉ እራሳቸውን ይዘው እዬዬ ሲሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አሁን በምርጫው ግን እንደዚ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሟርተኞችን አሳፍሯቸዋል፡፡
የሚገርመው የአሸባሪውን ህወሓትን የጨረቃ ምርጫ እንኳን እንደምርጫ ቆጥረው ነፋስ እንደቀላቀለ እና ወዠቡ እንደበዛበት ዝናብ ከዚ እና ከዚያ እንደሚማታ ዛፍ ስለጨረቃ ምርጫው ዘገባ ለመስራት ሲሞክሩ ነበር፡፡ በ2013ቱ ምርጫ በኢትዮጵያ ችግር ይፈጠራል ብለው ካሜራቸውን ተክለው ፤ የድምጽ ማጉያቸውን ከአፋቸው አስጠግተው፣ የጸብ ፊሽካ እስኪነፋ ቋምጠው እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ያሰቡት ሳይሆን ቀረ፡፡ እነሱም ከጥፋት ውጭ ስለኢትዮጵያ አንዘግብም ብለው የድምጽ ማጉያቸውን አፋቸው ላይ ካሜራቸው አይናቸው ላይ እንደደቀኑ ደንዝዘው ያዩትን ማመን አቅቷቸው በዚያው አሸለቡ ፡፡
ስለምን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ይህን ያህል መላላጥ አስፈለገ፡፡ ኢትዮጵያን ማጥፋት መጣር ባንዳዎችም ከአባቶቻችሁ የባንድነት ታሪክ ስለምን መማራ አቃታችሁ?፡፡ የውጮችም ደግሞ ከጣሊያን ሃፍረት ያልተማሩትስ ለምንድን ነው?፡፡
ይህን የኢትዮጵን ጠላቶች ክፋት ያየው አዝማሪ ያለው እውነት ነው ፡፡
“ እነኚህ በልገኞች እዩ ሲቀናጡ ፣
ኢትዮጵያን እናጥፋት ብለው ትዛዝ ሰጡ ፡፡ “
ይህንን ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚደረግ ዘመቻ የኢትዮጵያ ህዝብ በድምጹ ድባቅ እንደ መታ ሁሉ በቀጣይ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ለማከናወን በጋራ በመቆም ድጋሚ ታሪክ ሊሰራ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም
አሸብር ኃይሉ