አንጋፋ ስፖርተኛ ናቸው። ለተሳተፉበት የስፖርት ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ኦሎምፒክ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሄ ግነት ሳይሆን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ በገፆቹ የከተበው እውነት ነው። እኚህ ሰው ለአገር ባለውለታ ናቸው። ስፖርቱ አሁን ካለበት አንፃር ከተመለከትነው የእርሳቸው ሚና የእውነትም ገኖ ሊታየን ይችላል። ለመሆኑ እኚህ ስፖርተኛ ማን ናቸው? በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አለም አቀፍ የሳይክል ተወዳዳሪ፣ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ፈር ቀዳጅ፣ አሰልጣኝ እንዲሁም የጠንካራ ስብእና ባለቤት ጋሽ ገረመው ደንቦባ።
ተነግሮ ከማያልቀው የስፖርቱ ዓለም ትዝታ አላቸው፤ የህይወት ጉዟቸውን እንዴት እንዳሰመሩት እንዲያጫውቱን፤ ለሚወዱት ስፖርት እድገት ያላቸውን ልምድ እንዲያጋሩን ከመኖሪያ ቤታቸው ተገኘን። ለጥያቄያችንም ሳይሰስቱ ከታሪክ ባህራቸው ጨለፍ አድርገው አወጉን። የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን ናቸው።
እኚህ ባለታሪክ ከቤት ውለዋል። በእርሳቸው ዘመን ባላቸው ጥንካሬ ለአገር በብስክሌት ስፖርት ፈር ቀዳጅ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። እነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ይድነቃቸው ተሰማ ለዚህች አገር ከሰሩት ውለታ በማይተናነስ በብስክሌት ስፖርት ላይ ተጠቃሽ ስራ ሰርተዋል። ለዚህ ደግሞ የታሪክ ዶሴዎችን በቀላሉ መግለጥ በቂ ነው። ስለዚህ እኚህን ጀግና ማወደስ፤ ከዚያም ባለፈ በህመማቸው ሰዓት ከጎናቸው መሆን ይኖርብናል። ጀግናን በህይወት እያለ የማወደስ ልምድ ሊኖረን ይገባል። እንደ እድል ሆኖ ብዙ ጀግኖቻችንን ሳናሞግስ ካጠገባችን ተለይተውናል። ይህን ስህተት ሁሌም መድገም ሊበቃን ይገባል። ሁሉም ባለው አቅም ባለውለታ የሆኑ ስፖርተኞችን እውቅና ሊሰጥ ይገባል የሚል እምነት አለን።
የብስክሌት ጅማሮ
ጋሽ ገረመው ብስክሌትን የተዋወቁት ገና በጨቅላ እድሜያቸው ውድድሮችን በመመልከት ነው። በአምስት እና ስድስት አመታቸው እነ ካሳ ፈዲር፣ ኤርትራዊው ካሳ ርእሶም፣ ሙሉጌታ ካሳ፣ታዬ ክፍሌ የሚባሉ ብስክሌተኞች ከአንዋር መስኪድ ፊት ለፊት እነኡስማን ኪኪያ ሱቆች አካባቢ እነ ራስ ሃይሉን የመሳሰሉ ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንንቶች በክብር ቦታቸው ላይ ተቀምጠው ውድድር ሲያደርጉ በራፋቸው ላይ ሆነው በደረታቸው ተኝተው ይከታተሉ ነበር። ከስፖርቱ ጋር ወዳጅነት የጀመሩትም በዚያን ወቅት ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ብቃታቸውን በማሳየት የስፖርቱ ቁንጮ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ከ1945 እስከ 1955ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና በአለም የኦሎምፒክ ታሪክ ላይ ታሪክ የሰሩበት ዘመን ነው። በ1946 ከጠንካራ ኤርትራዊያን ጋር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆለታ ደርሶ መልስ 20 ዙር ውድድር ላይ 11 ዙር ታዋቂና ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን በመደረብ ጣፋጭ ድል አስመዘገቡ። ጃንሆይ በተገኙበት በዚህ ውድድር ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ለጋሽ ገረመው በልዩ ብቃታቸው ተማርከው የወርቅ ሰዓታቸውን ከእጃቸው በማውለቅ ሸልመዋቸዋል።
ሜልቦርን ኦሎምፒክ
ጋሽ ገረመው የሜልቦርን ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ደብዳቤ ለንጉሱ ለመፃፍ ተነሱ። «በአገሬ ለበርካታ ዓመታት የብስክሌት ሻምፒዮና ሆኛለሁ። በሜልቦርን በሚካሄደው ኦሎምፒክ ላይ በዚሁ ስፖርት ተሳታፊ ብሆን ለአገሬ ጥሩ ስም አስገኛለሁ» በማለት በራሳቸው የእጅ ፅሁፍ ጥያቄያቸውን ከተቡ።
ጃንሆይ እሁድ እሁድ ወደ ደብረዘይት ያቀናሉ። ጋሽ ገረመው ደብዳቤውን በአካል ለጃንሆይ ለማቅረብ ፈልገዋል። በአራተኛ ክፍለጦር መሿለኪያ በሚባል አካባቢ ነበር ንጉሱ ወደ ደብረዘይት የሚያልፉት። ሶስት እሁዶችን በዚህ አካባቢ ጥያቄውን ለማቅረብ መጠባበቅ ጀመሩ። በአራተኛው ተሳካላቸው። በብስክሌታቸው ላይ ሙሉ ትጥቃቸውን እንደለበሱ፤ ደብዳቤያቸውን ይዘው ወደጃንሆይ መኪና ተጠጉ። በንፋስ ስልክ አድርገው አቃቂ አብረዋቸው ብሰክሌት እየነዱ ተከተሏቸው። ደብዳቤያቸውን ከኪሳቸው በማውጣት ከጃንሆይ መኪና ትይዩ በመሆን ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ንጉሱ ትእዛዝ በመስጠት አስቆሙ። ጃንሆይ ጉዳያቸውን ተረድተውም ቤተመንግስት እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጡላቸው።
በቀጠሮ መሰረትም ተገኙ። የእልፍኝ አስከልካይ ፅህፈት ቤት ሹም የሆኑት ጄኔራል መኮንን ደነቀ ብርቱ ጉዳይ ይዘው ቤተመንግስት የተገኙትን ጋሽ ገረመውን ወደ ጃንሆይ ይዘዋቸው ቀረቡ። እሳቸውም «ከዓለም መወዳደር እፈልጋለሁ» ሲሉ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ኢትዮጵያ ተሳትፎ እንዲኖራት ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ።
ጃንሆይም «ከዓለም መወዳደር እንደምትችል በምን አወቅክ» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው በሰዓት 42 ኪሎ ሜትር እንደሚፈጥኑ መተማመኛ ሰጧቸው። በጊዜው የዓለም ፈጣን ብስክሌተኞች ሰዓትም ተመሳሳይ ነበር። ጃንሆይ ይህን ሲያውቁ «ማለፊያ» በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት ላይ እንድትሳተፍ አደረጉ።
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትሳተፍ ፈር የቀደደው የጋሽ ገረመው ቡድን ደግሞ መንግስቱ ንጉሴን፣ ፀሀይ ባህታን፣ መስፍን ተስፋዬን የያዘ ነበር። በውድድሩ ወቅት እንደ ቡድን ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ጋሽ ገረመውም በግል ከአገራቸው ቀዳሚ በመሆን የ24ተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።
ጋሽ ገረመው በብስክሌት ስፖርት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በ1962ቱ የሮም ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበሩ ፤ ሆኖም የመውደቅ አደጋ አጋጥሟቸው 9ኛው ዙር ላይ ከውድድር አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል። ያ ጉዳት ራሳቸውን ከውድድር እንዲያገሉ ቢያደርጋቸውም በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይም የብስክሌቱን ልኡካን ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት አገልግለዋል። ከዚያም በኋላ ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ለአገር ውለታ ሰርተዋል። አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ወኔ አላቸው፤ “መስራት እችላለሁ” በማለት ቢያንስ በማማከርና ልምድ በመስጠት አገር የማገልገል ፍቅራቸውን ዛሬም መወጣት ይፈልጋሉ።
የእረፍት ውሎ
አንጋፋው ብስክሌተኛ በውድድር ወቅት እግራቸው ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት ሰፊውን ጊዜ በቤት ውስጥ ነው የሚያሳልፉት። ይሁን እንጂ በአገኙት አጋጣሚ መንቀሳቀስ ይወዳሉ። ለአገራቸው ልዩ ፍቅር ስላላቸው ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ ስፖርት መድረክ ላይ የሚወክላትን አልባሳት በእረፍት ቀን ይለብሳሉ።
ታሪክ አዋቂ ናቸው። ይሄን ያዳበሩት ደግሞ ገና ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ነው። በማንኛውም አጋጣሚ መፅሃፍትን ማንበብ ስለአገር ጉዳይ መወያየት ይወዳሉ። በዘመናቸው ያሳለፉትን አስደሳችና አንዳንድ አጋጣሚዎችን ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው በማውጋት፣ ጓደኞቻቸው ጋር ትዝታን እየቀሰቀሱ በመጨዋወት ጊዜያቸን ያሳልፋሉ። ለሃይማኖታቸው ቀናኢ በመሆናቸውም እሁድና ቅዳሜ ቤተ ክርስቲያን ይስማሉ።
“ኢትዮጵያ የታሪክ ፈርጥ ነች” የሚሉት አንጋፋው ብስክሌተኛ ትውልዱ አገሩን መጠበቅ እንዳለበት ያሳስባሉ። ከሁሉም በላይ አንድነት፣ መተባበርና ፍቅርን ማስቀደም እንዳለበት በመናገር የነበረንን ቆይታ አጠናቀቅን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013