በተንጋለልኩበት ከሩቅና ከሰፊ አዳራሽ የሚወጣ ድምፅ ወደጆሮዬ ደረሰ። ማን ስለምንና ስለማን እያወራ እንደሆነ መለየት ግን አልቻልኩም። በሰመመን ለትንሽ ጊዜ ቆየሁ። ቀጥሎ ወደ አፍንጫዬ ከተለመደው ውጪ የሆነ የመድኃኒትና የታፈነ ጠረን ደረሰ። ከቅድሙ ይበልጥ ከርቀት የምሰማቸው ድምፆች ደግሞ ተከታትለው ይሰማሉ።
“አዎ እሱ ጋ ጠበቅ አድርገህ ያዝው” ከአጠገቤ አይኔን ሳልገልጥ የሰማሁት ድምፅ ነበር። እጄን የሆነ ነገር ሲያጠብቀኝ ቀድሜ አይኔን ልገልጥ ሞከርኩ፤ ነገር ግን አልቻልኩም። አይኔ ላይ የሆነ ክምር የጫኑብኝ ያህል አንዳች ክብደት አይኔ ቆብ ላይ ሲያርፍ ተሰማኝ።
ራሴን ይበልጥ በማንቃት ላይ ነኝ። ለመነሳት ስሞክር “ቆይ ቆይ ፤ በልሁ ረጋ በል፤ ቆይ እረፍት አድርግ” የሚል ድምፅ አጠገቤ ካለ ሰው ሰማሁ። ማንነቱን አለየሁትም እጄ ተሳስሯል። ሰውነቴ ደቋል። ለመነሳት የሚሆን ምንም ጉልበት የለኝም። ምን ሆኜ ነው? ይሄ ነገር ህልም ነው ። ምን ሆኜ ነው መነሳት ያቃተኝ። አይኔንስ መግለጥ ያልቻልኩት ለምንድነው? ማንስ ነው አጠገቤ ያለው? ግራ የመጋባት ስሜቴ ይበልጥ በረታ። እንዴ ታዲያ እዚህ ቦታ ላይ እኔ ምን አደርጋለሁ?
የፊቴ ቆዳ ላይ የሆነ የሚለበልብ ስሜት ተሰማኝ። ቀስ እያለ ሙሉ የሆነ የቆሰለና የሚለበልብ ስሜት ሰውነቴን ሲሰማኝ እጄን ባለሁበት ለማንቀሳቀስ ሞከርኩ፤ ነገር ግን አልቻልኩም። የሆነ ሰው መዳፍ የጨበጠው እጄ የላኛው አይበሉባው ላይ አንዳች ነገር ተጠምጥሞበታል። ከቆይታ በኋላ ወደ ኋላ ተመልሼ የሆንኩትን ሁሉ ማሰብ ጀመርኩ።
ቤተልሄም ውድዋ ፍቅረኛዬ ትውስ አለችኝ። የተያየነው ከጓደኛዬ ኤርሚያስ ጋር ከሥራ ከወጣን በኋላ አንድ ሁለት እያልን ከምናመሽበት ቤት ነው። እስዋም ከጓደኞችዋ ጋር ሆና። በርቀት ተያየን። እኔ ለሥራዬ ትኩረት ከመስጠት ውጪ ለሴቶች ያለኝ ምልከታ ብዙም ነው። ከዚያ በፊት የፍቅር ቅርርብ ኖሮኝ አያውቅም። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኜ አንዲት ሰላም የምትባል ልጅ በአይን ከመውደድ ውጪ ትምህርቴን ጨርሼ ሥራ ተቀጥሬ የአሁኗን ፍቅሬን ቤተልሄምን እስክትዋወቅ ድረስ የፍቅር ግንኙነት ኖሮኝ አያውቅም። የዚያን ቀን ግን ቤቲን እንዳየኋት የሆነ የማላውቀው ስሜት እንዳተኩርባት አደረገኝ።
ብዙ በስርቆት ስንተያይ ቆይተን የሞት ሞቴን ቀና ብዬ ጠቀስ አደረኳት። ፈገግ ስትል አይቼ ልቤ ሞቀው። በአይን ጥቅሻ ደገምኳት፤ ተመቸኋት መሰለኝ አላሳፈረችኝም። ይበልጥ ተፍለቀለቀች። ይሄኔ ለጓደኛዬ ኤርሚያስ ነገርኩት። ወደስዋ ሳሳየው “እጅግ ውብ ናት፤ ከወደድካት አታምልጥህ “ ሲለኝ እኔም ደፋር ሆኜ ቀርቤ ልግባባት ወሰንኩ። ሄጄ ለዳንስ እጄን ዘረጋሁለት። አላሳፈረችኝም። እየደነስን አወራን።
ጊዜው እየመሸ ነበር፤ ቆየት ብሎ ቤቲና ጓደኞቿ እንሂድ ብለው ተነሱ፤ ስልክ ቁጥር ተለዋወጥን። ምሽት ላይ እቤት ገብቼ ልደውል ስልኬን አነሳሁ። በአንዴ የተቀየረው ስሜቴ ለኔው ገርሞኛል። በእርግጥ ቤቲ ውብ ናት። እኔም በዚህ መማረኬን አልክድም። ግን እንዴት ሳላውቃትና ብዙም ቀረቤታ ሳይኖረን ስለስዋ በዚህ መጠን ላስብ ቻልኩ። ስለኬን አንስቼ የሰጠችኝን ቁጥር ሞከርኩ፤ አንዴ እንደጠራ ተነሳ፤ በተስረቅራቂ ድምፅ” ሀሎ” የሚል ቃል ሰማሁ።
አፌ ተሳሰረብኝ፤ ደግማ “ሀሎ ማን ልበል” ስትል ከመዝጋትዋ በፊት የሞት ሞቴን “ሰላም መግባትሽን ለማረጋገጥ ነው የደወልኩት… ቅድም ሳባ ሆቴል አብሬሽ የነበርኩት ልጅ ነኝ” አልኳት።
“እ… እንዴት ነህ ሃሃሃሃሃሃ ስንት ዓመት በሰላም እየገባሁ ቆይቼ ዛሬ አንተን ስለተዋወቅሁ በሰላም ላልገባ እንዴት እችላለሁ… አረ ሰላም ነው፤ሰላም ገብቻለሁ” አለችኝ ። ከሁሉም በላይ ሳቅዋን ስሰማ ደስ ተሰኘሁ። ብችልና የሆነ ቀልድ ችዬ ባወራትና ብዙ ብትስቅልኝ ብዬ ተመኘሁ። ትንሽ አወራንና ተሰናበትኳት።
አልፎ አልፎ መገናኘትና ብዙ ጊዜ መደዋወላችን በረታ። ደጋግሜ እደውልላት የነበረው እኔ ነበርኩ፤አሁን አሁን ደግሞ እስዋ ይበልጥ መደወል ጀምራለች። እንደ ወደድኳት ስነግራት አላንገራገረችም። አብረን መሆናችን በዛ። በእረፍት ቀን እቤቴ መጥታ አብረን እንውላለን። ልክ የውበቷን ያህል የሚወደድ ባህሪ አላት። ይበልጥ ወደድኳት። እስዋም ወደጄሀለሁ፤ አብረኸኝ ሳትሆን ሲቀር ይጨንቀኛል ማለትን ደጋገመች።
በዚህ ሁሉ መሀል ግን ጓደኛዬ ኤርሚያስ የቤቲን ሁኔታ በጥርጣሬ በማየት አንዳንድ ነገሮች ላይ እንዳልቸኩል ይነግረኝ ጀመር። “ይህቺ ልጅ ሁኔታዋ አላማረኝም። በጣም ቸኮላችሁ። ለማኝኛውም ረጋ እያልክ” ይለኛል።
እኔ በጣም ስለወደድኳት ለጓደኛዬ ጆሮም አልሰጠ ሁትም። በእርግጥ አንዳንዴ የማልጠብቀው ነገር ላይ ስትዋ ሸኝ አገኛታለሁ። ስለቤተሰብዋ ጠይቄ ሁለት የተለያየ መልስ ሰጥታኛለች። ኤርሚያስ ግን ሁሌም በሚሆነውና በምታደርገው መለዋወጥ ግራ እየተጋባ “ተው በልኩ የዚህ ችን ልጅ ነገር አታፋጥነው፤ ረጋ ብለህ ተጓዝ” ይለኛል።
ቀናት አልፈው ስድስት ወር እንደቀልድ ሞላን። ቤቲም ከኔ ጋር የነበራት ግንኙነት ጠነከረ። ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችዋ ግራ ያጋቡኝ ጀመር። ኤርሚያስም በጥያቄው በረታ። ቤቲ ኤርሚያስን ብዙም አታቀርበውም። እኔና እሱ ከሥራ ውጪ ምንገናኝባቸው ቀናት አነሱ።
እስዋ ከእሱ ጋር እንድሆን ብዙም አትፈልግም። ባለመፈለግዋና አብረን ሆነን የሚያነሳላት ጥያቄ ብዙ ጊዜ ፈተና ስለሚሆንባት አይመቻትም። ሥራ ቦታ ሆነን ግን ለኔ እባክህን ተጠንቀቅ ማለቱ አልቀረም። ከሥራ ውጪም የቅርብ ጓደኛዬም ስለሆነ እጅግ በጣም እወደዋለሁ። እሱ የሚለኝን ሁሉ እሰማለሁ፤ ከቤቲ ውጪ ያለኝን ሁሉ እተገብራለሁ። ቤቲን ስለምወዳት እሱ የሚለኝን የተለያየ ጉዳይ እኔ በጎውን ብቻ እያየሁ ቆይቻለሁ።
ይህ በሆነ በሳምንቱ ደግሞ እክስቴ ታመመች ብላ ሌላ ብር ጠየቀችኝ። አልነበረኝም እንደምንም ፈልጌ ያለችኝን ሰጠኋት። አንድ ቀን በእረፍት ቀኔ እቤት መጥታ አብረን ሆነን ገዝቼ ያደረኩላትን የአንገት ሀብል ከአንገትዋ ሳጣው የት ሄደ ብዬ ጠየኳት። “ሌባ ከአንገቴ ላይ ወሰደብኝ” አለችኝ። “እንዴት ሳትነግሪኝ” ስላት። “እንዳትጨነቅ ብዬ ነው ብላ መለሰችልኝ” ከዚያ ቀን አንስቶ ነገሮችን በጥርጣሬ ማየት ጀመርኩና እከታተላት ጀመር።
ከቀናት በኋላ ባየሁት ነገር እጅግ በጣም ደነገጥኩ። ከሥራ እንደ አጋጣሚ በጊዜ ወጥቼ ለቤቲ ደወልኩላት። የለሁም ከቤተሰብ ጋር ከከተማ ወጥቻለሁ አለችኝ፤ ስላልነገረችኝ ቅር ቢለኝም ሳገኛት አወራታለሁ ብዬ ስልኩን ዘጋሁትና ጓደኛዬ ኤርሚያስ ጋ ደውዬ አገኘሁትና ወትሮ ከምንዝናናበት ቤት ራቅ ብለን አንድ መዝናኛ ውስጥ ገብተን አንድ ሁለት እያልን ከደቂቃ በኋላ አንድ ነገር አይቼ ሁኔታዎች ተለወጡ።
ከርቀት በሩ ላይ የኔዋ ቤቲ አንዱ ጎረምሳ ወገብ ላይ ተጠምጥማ ስትገባ ተመለከትኩ። ጓደኛዬ ሁኔታዬን አይቶ ሲዞር ባየው ነገር እሱም ተደናገጠ። ሸሸግ ብለን ሁኔታውን ማየት ጀመርን። ቤቲና ልጁ አንድ ጥግ ተቀምጠው እየተሳሳሙ ናቸው፤ ቤቲ ትስቃለች።
ትዕግስት አጣሁ፤ ግራ ተጋባሁ። በትንሹ ያደርጉት የነበረው መጠጋጋታቸው ጨምሮ ልጥፍ ብላበት መሳሳም ሲጀምሩ እመር ብዬ ተነስቼ ወደስዋ ጋ ቀረብኩ። ጎትቼ ሳነሳት በድንጋጤ ጮኸች። አብሯት የነበረው ወንድ ቡጢ ሰነዘረብኝ፤ እኔም ቀጠልኩ። ጠርሙሶች ተወረወሩ፤ ጮኸት በረከተ። ሁሉም ነገር በተኛሁበት ታየኝ። ከዚያ ፀብ ያተረፍኩትን ሰውነቴን በዚህ መልክ አገኘሁት። ተፈፀመ::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013